Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከንብ ባንክ በተሰናበቱ የማኔጅመንት አባላት ምትክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገለግሉ የነበሩ ኃላፊዎች ተመደቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ሰሞኑን ባሰናበታቸው አሥር ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ምትክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የቆዩ ስድስት የሥራ ኃላፊዎችን መደበ፡፡ ባንኩ እየወሰደ ባለው የሪፎርም እስካሁን ባሰናበታቸው አሥር የሥራ ኃላፊዎች ምትክ አዲስ የሾማቸው የማኔጅመንት አባላት ከቀሪዎቹ የማኔጅመንት አባላት ጋር ትውውቅ በማድረግ ሥራ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ 

ባንኩ ቀድም ሲል የነበሩትን የሥራ መደቦች በማሻሻል በሰጠው የሥራ ኃላፊነት ምደባ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ግርማ ፈቃደ፣ አቶ ሳምሶን አምዲሳ፣ አቶ በላይ ጎርፉ፣ ወ/ሮ ሐረገ ወይን አምሳለ፣ አቶ ዘውዱ ሐኪሙና አቶ ነፃነት ይርጋን መድቧል፡፡ 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ቺፍ የደንበኞችና ቅርንጫፍ ባንኪንግ ዋና ኦፊሰር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ግርማ ፈቃደ፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የደንበኞችና ቅርንጫፍ ባንኪንግ ኦፊሰር በመሆን መሾማቸውን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል። 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስትራቴጂና የትራንስፎርሜሽን ምክትል ዋና ኦፊሰር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ በላይ ጎንፋም በተመሳሳይ የንብ ባንክ ስትራቴጂና ትራንስፎርሜሽን ምክትል ዋና ኦፊሰር ሆነው ተሹመዋል። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በምክትል ክሬዲት ኦፊሰርነት ሲያገለግሉ የቆዩት ነፃነት ይርጋም እንዲሁ የንብ ባንክ ምክትል ቺፍ ክሬዲት ኦፊሰርነት ሆነው መሾማቸው ታውቋል፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰው ሀብት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦፊሰር በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ዘውዱ ሐኪሙም፣ የንብ ባንክ የሰው ሀብት ምክትል ዋና ኦፊሰር ሆነው ተመድበዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የባንክ አግልግሎት ምክትል ዋና ኦፊሰር ሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ ሐረገወይን አምሳለም በተመሳሳይ ኃላፊነት ንብ ኢንተርናሽናል ባንክን ተቀላቅለዋል።

ከንግድ ባንክ ከመጡት ከእነዚህ አምስት ተሿሚዎች ሌላ በንብ ባንክ የፋይናንስ ፋሲሊቲ ኦፊሰር በመሆን የተሰየሙት አቶ ሳምሶን አምደሳ ናቸው፡፡ እሳቸው አሁን ከፀሐይ ባንክ የወጡ ቢሆንም ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ ስለመሆናቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡  

የንብ ባንክ የማኔጅመንት አባላት ኃላፊነት ላይ የነበሩ ግለሰቦች እስካሁን በተደረገው ምደባ አለመካተታቸው ታውቋል። በቀሪዎቹ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ቀጣይ ምደባዎች እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ ባንኩ ገጥሞት ከነበረው ችግር ጋር ተያይዞ መጀመሪያ የቀድሞ የቦርድ አባላትን ከዚያም የቀድሞውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በማሰናበት በምትካቸው አዳዲስ ሹመቶችንና ምደባዎችን ማድረጉ አይዘነጋም፡፡  

በአሁኑ ወቅት ባንኩን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ የተሰየሙት እመቤት መለሰ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፍተኛ አመራር ደረጃ እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ናቸው፡፡ 

ባንኩ አዲስ በሾማቸው አመራሮች ውስጥ ከውስጥ ለቦታው የተመረጡ ያለመኖራቸው እያነጋገረ ሲሆን፣ ምናልባት ሹመት ባልተሰጣቸው ቦታዎች ላይ ሊመደቡ ይችላሉ የሚል ግምት አሳድሯል፡፡ እስካሁን ባለው ምድብ ግን ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላትን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጡ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡ 

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይም የባንኩን ከፍተኛ አመራሮች ባንኩ ገጥሞት ለነበረው ችግር ተጠያቂ መሆናቸውን በመጥቀስ ከሥራ ያሰናበታቸው አሥሩ ከፍተኛ አመራሮች አቶ ሰለሞን ጎሽሜ (ቺፍ ኮርፖሬት ሰርቪስ ኦፊሰር የነበሩ)፣ አቶ ሰይፉ አገንዳ (ቺፍ ከስተመርና ኦፕሬሽን ኦፊሰር የነበሩ)፣ አቶ መልካሙ ሰለሞን (ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩ)፣ አቶ አማኒ ታደሰ (የኢንተርናሽናል ባንኪንግ ፕሬዚዳንት የነበሩ)፣ አቶ አብርሃም ተስፋዬ (የስትራቴጂና ማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ)፣ አቶ ዓለሙ ሰማዩ (ምክትል ቺፍ ባንኪንግ ኦፕሬሽን ኦፊሰር የነበሩ)፣ አቶ ሽፈራው አርጋው (ምክትል ቺፍ የቅርንጫፍ ጉዳዮች ኦፊሰር የነበሩ)፣ አቶ ኤፍሬም ተሾመ (ምክትል ቺፍ ከስተመር ሬሌሽን ኦፊሰር የነበሩ)፣ አቶ ሙሉጌታ ድልነሳው የሪስክና ኮምፕሊያንስ ማኔጅመንት ዲፓርትመንት ዳይሬክተር የነበሩ) እና አቶ ሲራክ ይፍሩ (የውስጥ ኦዲት ዲፓርትመንት ዳይሬክተር የነበሩ) ናቸው፡፡

እየወሰደ ባለው ሰሞናዊ ዕርምጃዎችን በተመለከተ ከተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ነው፡፡ የተወሰደው ዕርምጃ በተለይም የምርምራ ሪፖርትን መነሻ እንዳደረገ ቢገለጽም፣ ይህንን ሪፖርት አስመልክቶ የደረሰ ምንም ነገር እንዳልነበር የሚገልጹ አሉ፡፡ 

የማኔጅመንት አባላት የስንብት ደብዳቤ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ የነበረው የርክክብ ሥርዓት ፍፁም ሙያዊ ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ እንዲካሄድ የተሞከረ ሲሆን፣ የመኪና ቁልፍ ወዲያው እንዲያስረክቡ፣ መኪና ይዘው እንዳይወጡ ብሎም የስልክ መስመር ወዲያው እንዲቋረጥ መደረጉ ከምን መነሻ እንደሆነ ለመረዳት አዳጋች ነው ሲሉ ሒደቱን የተቹም አሉ፡፡ 

በአሠራር ሒደት የሚፈጠሩ ክፍተቶች ቢኖሩ እንኳን ተሰናበቱ የተባሉት የማኔጅመንት አባላት በተለይም ከነበራቸው ቆይታና አስተዋጽኦ አንፃር እንዲህ ባለ መንገድ ለማሰናበት መወሰን የባንኩን ታሪክ የሚያውቁና ለማስቀጠልም ታሪክ ነጋሪ ለማሳጣት ተብሎ የሚመስል ነው ብለው የሚናገሩ አልጠፉም፨

በርካቶች እንደሚናገሩት ጥፋትም አለ ከተባለ የጥፋቱን መጠንና ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ እንዲህ ያለው የጅምላ ዕርምጃ፣ በተለይም የግል ስሜቶች ተንፀባርቀውበት እንዳይሆን ሥጋት እንዳላቸው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

በተለያዩ ስብሰባዎችም ከቦርዱ ጋር በነበሩ ስብሰባዎች የተለያዩ ሐሳቦች ሲነሱ የነበሩ ቢሆንም፣ የማኔጅመንት አባላትን እስካሁን ላበረከቱት አስተዋጽኦ በተለይም ባንኩ በችግር ውስጥ በነበረበት ወቅት ለማስቀጠል የተደረገውን ርብርብ ምንም ከግምት ያላስገባ እንደሚያስመስለው አንዳንዶች ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ዛሬ ላይ የባንኩ ቦርድ እንደ ስኬት የሚገልጻቸው ነገሮች በሙሉ በነበረው ማኔጅመንት የተከናወኑ መሆናቸውን መዘንጋት እንደሌለባቸው የገለጹት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ዕርምጃው እንዳስደነገጣቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

በሌላ በኩል ግን አሁን የተወሰደው ዕርምጃ ተጠባቂና አስፈላጊ ነበር የሚሉ ወገኖች ደግሞ እንዲህ ባለው መንገድ ዕርምጃው መወሰዱ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ 

በተለይ አዲስ የተሰጠው ሹመት ከባንኩ የውስጥ ሠራተኞች ያለመወሰዱ ቅሬታ የሚፈጥር ቢሆንም፣ በነበረው ማኔጅመንት የለውጥ ጉዞውን ማስኬድ የማይችል መሆኑ ስለታመነበት አዳዲስ ሰዎችን ከውጭ ማምጣቱ ተገቢ ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች