Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ አገራዊ ምክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ሥርዓት በመዘርጋት ለአገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር በተቋቋመው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተሾሙት 11 ኮሚሽነር መካከል አንዱ አቶ ዘገየ አስፋው ናቸው። በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውን በሕግ በአሜሪካ ከሚገኘው ከዊስኮንሲ ሜዲሲን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ አቶ ዘገየ በሙያቸው ጠበቃ ሲሆኑ፣ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አንስቶ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች አገልግለዋል። በቀድሞው የመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሠሩባቸው መሥሪያ ቤቶች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በተቋቋመበት ወቅትም በሕዝብ ድምፅ ተመርጠው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚሽነር ሆነው እንዲያገለግሉ ተሹመዋል። ባለፈው ሳምንት የአገራዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ የተጀመረ ሲሆን ኮሚሽኑ ተሳታፊዎች ሰላስመረጠበት ሒደት፣ የአጠቃላይ ሕዝቡና የዳያስፖራው ተሳትፎ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ ስለሚነሱበት የገለልተኝነት ጥያቄዎች፣ ስለአጀንዳ መረጣ፣ እስካሁን በምክክሩ መካተት ስላልቻሉ ክልሎች፣ በማረሚያ ቤት ስለሚገኙ የሕዝቡ ድምፅ አለን ስለሚሉ የፖለቲካ ሰዎች ተሳትፎ፣ በተደጋጋሚ ቅሬታ ስለሚነሳበት የገዥው ፓርቲ ተፅዕኖና ሌሎችንም ጉዳዮችን በተመለከተ ናርዶስ ዮሴፍ ከኮሚሽነሩ ጋር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል።

ሪፖርተር፡- አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ምን ዓይነት ሥራዎችን አሳክቷል?

አቶ ዘገየ፡- አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ሁለት ዓመቱ ነው። በእነዚህ ሁለት ዓመታት መጀመሪያ ሥራውን በሚጀምርበት ጊዜ ይብዛም ይነስም ከሕንፃው በቀር ብዙም ዝግጅት አልነበረውም። ስለዚህ የመጀመሪያውን ዓመት በዝግጅት ነበር ያሳለፍነው። ዝግጅታችን እንግዲህ አንደኛ የዚህ የብሔራዊ ምክክር ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ምን እንደሆነ እሱን መቅረፅ ነበረብን። እንዲሁም ደግሞ የሠራተኞች አስተዳደርን በተመሳሳይ ማዘጋጀት ነበረብን። ከዚያ በኋላ ሠራተኞች መቅጠር ተጀመረ። አሁን ብዙ ሠራተኞች ቀጥረናል። ምክንያቱም በጀታችን የሚሸፈነው በከፊል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ድርጅት (ዩኤንዲፒ) ድጋፍ ነው፡፡ በከፊል የመንግሥት በጀት ነው። ሠራተኞችን፣ ሎጂስቲክስና ሁሉንም ካሟላን በኋላ ነው ወደ ሥራ የተሰማራነው። ከዚህ በኋላ የመጀመሪያ ሥራችን፣ እንደምታውቁት ይህ አካታችና አሳታፊ ምክክር እንዲሆን ስለተፈለገ፣ አካታች ከተባለ ደግሞ ጥቂቶቹን ብቻ ለይተን የምናደርግበት ምንም ዓይነት አካሄድ ስለሌለ፣ በአዋጁም የተሰጠን ሥልጣን ስለነበረ፣ አካታች የሚለው እኛ እንደገመትነው ከወረዳ በመነሳት ነው።

ሪፖርተር፡- ተሳታፊዎች የተመረጡበት ሒደት አካታች እንደነበር ምን ማስረጃ ማቅረብ ይችላሉ?

አቶ ዘገየ፡- ሁሉንም አካታች ለማድረግ ከወረዳ ነው ሥራ የጀመርነው። ከወረዳ በሚነሳበት ጊዜ እንዲሁ ለምክክሩ ሰዎች ስጡን ብለን ከመጠየቅ ይልቅ በእያንዳንዱ ወረዳ ሄደን በምንጠይቅበት ጊዜ በልዩ ልዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ማኅበራት አሉ። የሴቶችና የወጣቶች ማኅበራትን የመሳሰሉ አሉ። የመንግሥት ሠራተኞች አሉ። እንዲሁም ደግሞ የሃይማኖት መሪዎች። ከእነዚህም ባለፈ ሌሎችም ኑሯቸውን መሠረት በማድረግ በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተፈጠሩ ማኅበራት አሉ። ምክክሩን አካታች ለማድረግ መጀመሪያ ያገኘናቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች እነዚህ ናቸው። ከእነሱ ጋር ተነጋግረን የኮሚሽኑ ዓላማው ምን እንደሆነ ካስረዳናቸው በኋላ፣ ለአገራዊው ምክክር ተሳታፊዎችን ምርጫ የምንጀምረው ከእናንተ አካባቢ ነው ብለን ነግረናቸው ከእነሱ ጋር ጀመርን። ለምሳሌ በእያንዳንዱ ወረዳ እነዚህን የመሳሰሉ አሥር ማኅበራት አሉ። በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከመኖሪያ ሥፍራቸው የተፈናቀሉትን ጭምር እንዲሁ ቀርበናቸው ተነጋግረናል። ሌሎችም በሥራቸው ወይም ደግሞ በባህል ተፅዕኖ የተነሳ ህዳጣን (Minority) ሆነው የሚኖሩትንም ጨምረን፣ ከእያንዳንዱ ማኅበር ወደ መቶ መቶ ሰዎች በየወረዳው እንዲሰባሰቡ አደረግን። በየወረዳው የምንሰበስባቸው ከመካከላቸው ተነጋግረው፣ ተገማግመው፣ ማነው የእኛን ችግር የሚያቀርብልን? ትክክለኛ ሰዎችን እንዴት እንመርጣለን? የሚለውን እነሱ ራሳቸው ነው የሚመርጡት። ኮሚሽኑ ያደረገው በየወረዳው ከፖለቲካ ፓርቲ፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመንግሥት የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ ከፍትሕ ኃላፊዎች፣ ከዳኞች፣ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ከፌዴራል አንስቶ ከተዘረጉ ዕድሮች ውስጥ ወደ ሰባት የሚሆኑ ሰዎች ከለየን በኋላ ምርጫው መካሄድ ያለበት በእኛ ሳይሆን በእነዚህ ሰዎች ነው በሚለው መርህ ሥር ነው የተንቀሳቀስነው።

እነዚህ ሰዎች በተቻለ መጠን ለማንም አድሏዊነት የማያሳዩ ተብለው ነው በጥንቃቄ የተመረጡት። ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ ድጋፍ የሚያደርጉትን ወደ ቢሯችን ጠርተን የመግባቢያ ሰነዶችን ተፈራርመናል። እነዚህ ሰባት ሰዎች ናቸው እንግዲህ በየወረዳው ሄደው፣ አንደኛ ለተሰባሰቡት ሰዎች ዓላማው ምን እንደሆነ፣ የሚመርጡት ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ አስረድተዋል። ምክንያቱም ተመርጦ የሚመጣው ማንኛውም የሕዝቡን አደራ ለመሸከም የሚችል ሰፊ ትከሻ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ሁለተኛ ደግሞ የአካባቢውን ሁኔታ በሚገባ የሚያውቅ፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የተከበረ ነዋሪ የሆነ ሰው እንዲመርጡልን አስደርገናል። ይህን ካጠናቀቅን በኋላ በእያንዳንዱ ወረዳ ከሚገኝ እያንዳንዱ ማኅበር ሁለት ሁለት ሰው፣ ከአንድ ወረዳ ከ18 እስከ 20 የሚሆኑ ሰዎች ይመረጣሉ። ምርጫው የተደረገው እርስ በርሳቸው ተወያይተውና በምርጫ ቦርድ እንደሚደረገው በሚስጥር ነው። ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነበር።

ሪፖርተር፡- ከዚህ የምርጫ ሒደት በኋላ ምን ሠርታችኋል? ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተጀመረው ምክክር የሚቀጥልበት ሁኔታስ እንዴት ነው የሚሆነው?

አቶ ዘገየ፡- በአገራችንን ውስጥ ወደ 3,700 ወረዳዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች ተዘዋውረን እነዚህ ሰዎች መምረጥ ስለነበረብን በአሁኑ ጊዜ ከአማራና ከትግራይ ክልሎች በስተቀር በሁሉም ቦታ ምርጫ አካሂደናል። ይህንኑ ሥራ ለመሥራት የመረጥናቸውን ሰዎች ጎንደር ላይ አሠልጥነናል፣ አሁን ደግሞ ደብረ ብርሃን ላይም እየሠለጠኑ ነው። ይህ ካለቀ በኋላ ሥራው ይቀጥላል። ይህንን ሰሞን አዲስ አበባ የመጡት ከእነዚህ አካባቢዎች ሁሉ የተመረጡ ሰዎች ናቸው። ይህ ከገጠር የመጡ፣ ከክልል ከተሞች የመጡትን ብቻ ሳይሆን ከሁለቱ አስተዳደር ከተሞች አዲስ አበባና ድሬ ደዋ የተመረጡትንም ያካትታል።

ሰዎቹ ከየወረዳቸው ሲመረጡ አጀንዳ እንዲሰጡ ነው። ከሰዎቻቸው ጋር ተመካክረው መጥተው እዚህ አጀንዳቸውን ሰጥተውናል። አጀንዳቸውን በሚሰጡበት ጊዜ ችግር እንዳይገጥማቸው ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ፕሮፌሰሮች ተመርጠው በእነሱ ታግዘን ነው የምንሄደው። በአዲስ አበባ የተደረገው አጀንዳ የመስጠት ነው መነጋገር አይደለም። እነዚህ ሰዎች አጀንዳቸውን ከሰጡ በኋላ ከመጡት ውስጥ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ ለሚደረገው ምክክር የራሳቸውን ተወካዮች ይመርጣሉ። ከአምስት እስከ አሥር የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ። የአዲስ አበባውን ስናጠናቅቅ፣ ከአዲስ አበባ ከአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች፣ ከየቀበሌው የተውጣጡ ሰዎች፣ የመንግሥት አካላት፣ የፓርቲና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አባላት፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች የተካተቱበት ተሰባስበው አጀንዳቸውን ይሰጣሉ። አጀንዳ በሚሰጥበት ጊዜ ታሳቢ መሆን ያለበት አብዛኛው ሰው የትምህርት ደረጃቸው እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ ግንዛቤያቸውም የተለያየ ስለሆነ ለየብቻቸው አድርገን ነው ማንም ጣልቃ ሳይገባ ተመካክረው እነሱ ለሦስት ወይም ለአራት ቀናት ቁጭ ብለው አጀንዳችን ይኼ ነው ይላሉ። አጀንዳቸውን ይዘው ወደፊት የሚሄዱት ደግሞ እነዚህ ናቸው ብለው መርጠው ይነግሩናል። አሁን የደረስንበት ደረጃ ይህ ነው። የአዲስ አበባውን ስንጨርስ ወደ ሌሎች ክልሎች ሄደን ተመሳሳይ ጉባዔዎችን እናካሂዳለን። በዚህ መካከል ባለው ጊዜ የአማራ ክልልንና የትግራይ ክልልንም ሥራ እንሠራለን ብለን እንገምታለን።

ሪፖርተር፡- በምክክር ሒደቱ የተሳታፊዎች መለያና የአጀንዳ አሰባሰብ ሥርዓትን በተመለከተ የክልል፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የፌዴራልና የዳያስፖራ በሚል በተለዩ አራት የትኩረት አቅጣጫዎች እኩል የአፈጻጸም ሥርዓት ይከተላል የሚል ነገር ከኮሚሽኑ ሲነገር ቆይቷል። በተግባር ይህ ምን ማለት ነው? ‹‹እኩል›› ተፈጻሚ የሚሆነውስ እንዴት ነው?

አቶ ዘገየ፡- እኩል ተፈጻሚ የሚሆነው ለሚለው አሁን የለየናቸው አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሰዎች አካታች የሚባለው ነገር፣ ያለ አድልኦ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን ነው የተመረጠው። ለዚህም ነው በመዋቅሩ ታች ወርደን የጀመርነው። ሌላው በተለያዩ አኅጉሮች ውስጥ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ኢትዮጵያውያን አሉ። እስካሁን ድረስ በአውሮፓ የሚገኙትን አነጋግረናል። ምክክሩ ምን እንደሆነ፣ በምክክሩ ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው ተነጋግረናል። በአሜሪካም፣ በካናዳም፣ በአውስትራሊያም በሁሉም ቦታ ይህ ነገር ተካሂዷል። እነሱም አጀንዳቸውን ይዘው በፌዴራል ደረጃ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መጥተው አጀንዳችን ይህ ነው ብለው ያቀርባሉ። አጀንዳ ማቅረብ ማለት ያ አጀንዳ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አገኘ ማለት አይደለም። እዚህ ላይ ኢትዮጵያን ሊያሻግር የሚችል፣ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በተመለከተ አጀንዳዎች ላይ ምክክር ተደርጎ አገራዊ ስምምነት ላይ ቢደረስ ኢትዮጵያን ሊያሻግር የሚችል ነው የሚሉትን ሁሉም የመረጡትን አጀንዳቸውን ያመጣሉ። በሚወጡት መመዘኛዎች እነዚህ ከተመረጡ በኋላ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ይኼ ነው ተብሎ ይታወጃል። በሚታወጅበት ጊዜ ሁሉም በያሉበት አካባቢ በእነዚያ አጀንዳዎች ላይ ሐሳብ ይሰጣሉ። ማንንም ወደኋላ አላስቀረንም። አሁን ትንሽ የሚያስቸግረው ሁሉም አጀንዳቸውን ይዘው ወኪሎቻቸው አድርገው የሚከራከሩላቸውን ሊልኩ ይችላሉ። አንዳንዱ የሚያስቸግረው ዳያስፖራው በአብዛኛው በአሁኑ ጊዜ በግለሰብ ደረጃ እንጂ በማኅበር ተደራጅተው አልመጡም። በማኅበር ቢመጡ ኖሮ የሚያቀርቡትን አጀንዳ ራሳቸው ተነጋግረው በፌዴራል ደረጃ በሚደረገው ምክክር ላይ እንዲቀርቡ ለማድረግ ይቻላል። እሱንም አልጨረስንም፣ እየሠራንበት ነው።

ሪፖርተር፡- ከአጀንዳ መረጣና ማሳወቅ በኋላ የኮሚሽኑ ሚና ምንድነው የሚሆነው?

አቶ ዘገየ፡- እነዚህ ሁሉ አጀንዳዎች በሚገባ ከተጠኑ በኋላ በመጨረሻ ከብዙ አጀንዳዎች ጋር ተወዳድረው አንኳር አንኳር የሚባሉት ይለያሉ። የምምክር ውጤት አንድ ነጥብ ላይ መድረስ እንደ መሆኑ አጀንዳዎች ከተለዩ በኋላ የደረስንባቸው ጉዳዮች ደግሞ ወደ ሕግ ተለውጠው ለፓርላማው፣ ለአስፈጻሚው አካል ይቀርባሉ። ያ ፖሊሲ ሥራ ላይ መዋሉንም የሚቆጣጠረው ይኸው ኮሚሽን ነው፡፡ ሕዝቡ ተነጋግሮ እነዚህ ናቸው የአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ችግሮች ናቸው ብሎ ያቀረባቸው ጉዳዮች በሕግና በፖሊሲ ተቀርጸው ለመንግሥት ከገቡ በኋላ፣ መንግሥት እነዚያን አጀንዳዎች ማስፈጸሙን እንቆጣጠራለን። ለሕዝቡ ደግሞ ይህን ያህል ወራት የለፋችሁባቸው አገሪቱ የሚያሻግሩ አጀንዳዎች እነዚህ ናቸው ብለን እናሳውቃለን።

ሪፖርተር– በምክክሩ የአገሪቱን ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች ያካተቱ ማኅበራት አባላቶቻቸው በምርጫቸው መወከላቸው ተነግሯል። ነገር ግን ለምክክሩ ውጤታማነት ወሳኝ የሆኑ ቁልፍ የሚባሉ ባለድርሻ አካላት ከተሳታፊዎቹ መካከል ተካተዋል ወይ?

አቶ ዘገየ፡- እኛ ለዚህ ጉዳይ ከታች ጀምረናል። ለምሳሌ በኅብረተሰቡ ዘንድ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች (Prominent Personalities) የሚባል አንድ ዘርፍ አለ። በዚህ ዘርፍ ማለትም ታዋቂ ግለሰቦች በሚባሉት ከዚህ በፊት ባለፉት መንግሥታት ውስጥ የሠሩ ሰዎች፣ ለአገሪቱ በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎች እነሱም ተለይተው ልክ እንደ አንድ ቡድን ወደ ምክክሩ ይመጣሉ ማለት ነው። ይህ በዝግጅት ሒደት ላይ ያለ ነው።

ይህ ሁለት ሲደመር ሁለት አራት የሚባል ነገር አይደለም። አንዳንድ ቦታ ግድፈት ይታይ እንደሆነ ነው እንጂ የኮሚሽኑ ፖሊሲ ሁሉንም የሚያካትት ነው። አካታች ያልንበት ዋነኛው ምክንያት ኢትዮጵያ የአንድ ብሔረሰብ አገር አይደለችም። የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ስለሆነች ሁሉም በየጓዳው አጀንዳ አለው። ሁሉም መጥቶ መላ ሕዝቡ ከተወያየበት በኋላ ይህ ነው የምክክር አጀንዳው ብለን ለማውጣት ስለምንፈልግ ነው።

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ሕግ መሠረት ዕውቅና ተሰጥቷቸው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ይህ ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ ባሳለፋቸው ዓመታት ውስጥ አንድም ተጨባጭ ሥራ አላሳካም፣ መንግሥት ጊዜ ሊገዛበት ብቻ ያቋቋመው ነው በማለት ሲተቹት ይደመጣል። እዚህ ላይ የኮሚሽኑ ዕይታ ምንድነው?

አቶ ዘገየ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ በምንጀምርበት ጊዜ አንዳንድ ቅሬታ አሳይተው ነበር። ምክንያቱም ሌላ አገር የተደረገውን ምክክር ያውቃሉ። ለምሳሌ በቱኒዚያ በተደረገው ምክክር አብዛኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አባላትና ፓርቲዎች ናቸው። እዚህ አገር ግን እነዚህ አሁን ያሉት በሕግ ተመዝግበው ያሉ ወደ 60 የሚሆኑ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ላይ ችግር አለ ተብሎ የማጉረምረም ነገር ነበር፣ ችግር አለ ብለውም ይናገራሉ። ግን ቀርበን ከእነሱ ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ አሁን ወደ 40 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእኛ ጋር ይሠራሉ። ከእኛ ጋር ለማይሠሩት እስካሁንም ድረስ ብዙ ጥረት ሲደረግ ወደ ምክክሩ የለም አንገባም ያሉ አሉ። የራሳቸው ምክንያት አላቸው፣ ለማሳመን ግን ጥረት ተደርጓል። ይህ በጣም ግልጽ የሆነ ሒደት ነውና መጥታችሁ ብትሳተፉ መልካም ነው የምንለው። ለምሳሌ ዋናው ወሳኞቹ አጀንዳ ለመስጠት የሚመረጡት ሰዎች ናቸው። በየወረዳው የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በእዚያ በመራጩ ኮሚቴ (አጋር አካላት ነው የምንላቸው) እነሱ ውስጥ ተወክለዋል። ከእዚያም በላይ ለምሳሌ አዲስ አበባን በምንወስድበት ጊዜ ዋና ከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በፓርቲያቸው አማካይነት ለውይይቱ ቀርበዋል። እስካሁን ድረስ ምንም የሚጨበጥ ነገር አልተሠራም የሚባለውን ነገር ማንም ሰው ዓይቶ መገመት ይችላል፣ 3,700 ወረዳዎች ነው የምናካትተው። አሁንም አብረውን ነው የሚሠሩት። በዚህ ኮሚሽን ላይ አመኔታ የለንም የሚሉት ጥቂቶች የራሳቸውን ሐሳብ መያዝ መብታቸው ነው። በግድ አስገድደን ለማስገባት አይቻልም። አንፈልግም ካሉ ምክንያት አላቸው። በምክንያታቸው ሊቀሩ ይችላሉ። ግን እነሱ ቀሩ ተብሎ ሥራው አልቆመም። ሌሎቹ ፓርቲዎች ጉባዔ አላቸው፣ ጉባዔያቸውም ላይ እየሄድን እንሳተፋለን። እነሱም በብዙ የእኛ ሥራዎች ውስጥ አብረውን እየተሳተፉ ነው፣ ስለዚህ ቅሬታ ማቅረብ አይቻልም አይደለም፣ ቅሬታ ሊቀርብ ይችላል። ነገር ግን እውነቱ ይኼ ነው። ያላንዳች ማጋነን በአሁኑ ጊዜ ከብዙ ፓርቲዎች ጋር አብረን ነው የምንሠራው፡፡ ከዚያ በኋላም ደግሞ ነገሩ ወደ ላይ ወጥቶ ፌዴራልም በሚደርስበት ጊዜ ፓርቲዎች እርስ በርስ ተነጋግረው የቀረበውን አጀንዳ ከፈለጉ ሊሰባብሩት አልያም ሊደግፉት ይችላሉ። እዚህ ላይ ምንድነው መደረግ ያለበት? ሕጉም ፖሊሲውም በሚቀረፅበት ጊዜ የእነሱ ዕርዳታ አያስፈልግም አይባልም። ከእነዚህ ውጪ ወደ 30 የሚሆኑ አባላት ያላት አማካሪ ኮሚቴ አለ፡፡ እነዚህ የአማካሪ ኮሚቴ አባላት ከዩኒቨርሲቲዎች አንቱ የተባሉ ፕሮፌሰሮች ያሉበት፣ ትልልቅ ጠበቆች የነበሩ፣ በቀደመው መንግሥት ውስጥ የሠሩ ሰዎችም አሉበት፡፡ እነሱም የምንሠራውን ነገር በየጊዜው እየገመገሙ ዕርዳታ የሚያስፈልግ ከሆነ እንዲደግፉን እናደርጋለን። በመጨረሻም ምናልባት የአገሪቱ አጀንዳ ይህ ነው በሚባልበትም ጊዜ አሥራ አንዳችንም ኮሚሽነሮች ቁጭ ብለን ያንን ሁሉ እንሠራለን ማለት አይቻልም። ስለዚህ በእነዚህ አማካሪዎች እንደገፋለን። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች በስተቀር ሌሎቹ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች አጋሮቻችንን በማሠልጠን፣ ሁለተኛ ደግሞ አሁን ሰው አጀንዳ ለመስጠት በመጣበትና በሚመጣበት ጊዜ ለሕዝቡ ገለጻ የሚሰጡትም እነሱ ናቸው፡፡ በተቻለ መጠን ሁሉንም አሳታፊ አድርገናል፣ እውነታው ይኼው ነው።

ሪፖርተር– አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ተፅዕኖ ነፃ የሆነና ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው አካል ሆኖ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በግልጽ ሠፍሯል። ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ በአብዛኛው በገዥው ፓርቲ አባላት የተያዘ ነው የሚል ነገር አለ። ለምሳሌ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የአገራዊ ምክክሩ ከመንግሥት ወገን ብቻ የተቋቋመ በመሆኑ ኮሚሽኑ ችግሮችን ይፈታል የሚል እምነት እንደሌለው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ስለዚህ የመጀመሪያው ጥያቄ የገለልተኝነት ጥያቄ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ራሱ በገዥው ፓርቲ አብዛኛው ድምፅ የተቋቋመ እንደ መሆኑ የገዥውን ፓርቲ ፍላጎቶች የሚያስፈጽም አይሆንም ወይ? ሁለተኛው ጥያቄ በየክልሉ በየወረዳው እርስዎ በገለጿቸው መዋቅሮች በውይይት አጀንዳ ለማስቀመጥ ለመምረጥ በብልፅግና ፓርቲ ሰዎች መሪነት እየተካሄደ መሆኑን፣ በፓርቲው ሰዎች በኩል ነው አጀንዳ አቅራቢዎች የተመረጡትም የሚል ነገር አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች አሉ ሲባል ኮሚሽኑ ምን ዓይነት አሠራሮችን ነው የሚከተለው? በእነዚህ ቅሬታዎች ላይስ የኮሚሽኑ ምላሽ ምንድነው?

አቶ ዘገየ፡- እኛን አንደኛ ነገር ተዓማኒ አይደሉም፣ የመንግሥት ቅጥረኞች ናቸው፣ ለመንግሥት ያደላሉ ለሚባለው ለእዚህ ቦታ እኛ የተመረጥነው በሕዝብ ጥቆማ መሠረት ነው። ሕዝብ ጠቁሞን ነው እዚህ ቦታ የተቀመጥነው። ፓርላማው አይደለም የመረጠን። ኮሚሽኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ነው አልተባለም፣ ለፓርላማው ነው ተጠሪነቱ። ኮሚሽኑ ለፓርላማው ተጠሪ በሚሆንበት ጊዜ መጀመርያ በጀት የሚያገኘው ከመንግሥት ነው። ያለ መንግሥት በጀት ለመንቀሳቀስ አንችልም። ሁለተኛ በጀት የምናገኘው ከውጭ አገር ዕርዳታ ነው። ከውጭ የሚገኘው ገንዘብ እኛ ዘንድ መግባት የለበትም ተብሎ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (ዩኤንዲፒ) አማካይነት ነው ያ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ ሕዝቡ የሚያየውን ሎጂስቲክስ ሁሉ የሚያሟሉልን። ግን እስካሁን ድረስ (የደረሰብኝን የደረሰብንን፣ ነው የምናገረው) አንድም ጊዜ በዘረጋነው ሒደትና ሥልት ላይ ይህ ይቀየር ይህ ይነሳ ተብሎ ከመንግሥት በኩል አንድም ጊዜ ተፅዕኖ አልተደረገብንም፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ይህ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ አንድ ሰው የራሱን የግል ሐሳብ ሊናገር ይችላል። የመንግሥትን ፍላጎት ነው የሚያሟሉት የሚለው ነገር ምናልባት ትንሽ ቆየት አድርገው መጨረሻ ላይ ውይይቱ በሚደረግበት ጊዜ ሊያዩት ይችላሉ። አሥራ አንዳችንም ኮሚሽነሮች የምንተዋወቅ ሰዎች አይደለንም። ከተለያየ ቦታ ነው የመጣነው። መደረግ ያለበት ይህ ነው፡፡ በእነሱ ላይ ቅሬታ አለን ብለው የሚናገሩ ከሆነ በጅምላ መናገር ሳይሆን፣ እከሌ እንደዚህ ነው ተብሎ መጠቆም አስፈላጊ ነው። በመንግሥት አዋጅ በመውጣቱና እዚያ የሚያገለግሉትም ሠራተኞች በፓርላማ አማካይነት በሕዝብ ስለተመረጡ አመኔታ የላቸውም በማለት ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እኛ የምንለው ማስረጃ አቅርባችሁ አረጋግጡ ነው። ማስረጃ አለህ ወይ? እኔ እዚህ ከገባሁ ሁለት ዓመት አልፎኛል፣ አንድም ጊዜ አጀንዳችንንና ሥልታችንን በምንቀርፅበት ጊዜ የመንግሥት እጅ አልገባበትም። የሚቀጠሩት ሠራተኞች ዩኤንዲፒ ለይቶ ባስቀመጣቸው መንገዶች እዚያ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ነው፡፡ ያለፉት ሠራተኞች እኛ ዘንድ በሚላኩበት ጊዜ እንደገና ቃለ ምልልስ አድርገን እንወስዳቸዋለን እንጂ፣ በሠራተኛ አመራረጥ እንኳን የመንግሥት እጅ የለበትም። እንግዲህ ባለሙያ ብቻ አይደለም ብዙ ዓይነት የመንግሥት ሠራተኞች ነበሩ። ይህ ኮሚሽን የተወረሰው ከዚህ በፊት የወሰን ኮሚሽን ከሚባለው ነው። እዚያ ውስጥ የነበሩ ሲያገለግሉ የቆዩ የመንግሥት ሠራተኞች አሉ። ሾፌሮች፣ የዕቃ ግዥ ሠራተኞች፣ ኦዲተሮችና የመሳሰሉ ሠራተኞች ማለት ነው። እነሱን ለማባረር አልቻልንም።

እኛ ግን የቀጠርናቸው ባለሙያዎቹን ነው። እነዚህን ባለሙያዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ከቀጠርን በኋላ ደግሞ እንዲሁ አልለቀቅናቸውም። ጥልቅና ጠንካራ የሆነ ሥልጠና ተሰጥቷቸው የሚሠሩትን ነገር እንዲያውቁ፣ ሁላችንም በምናየውና በምንከታተለው ምንም ዓይነት ወገንተኝነት በሥራቸው ላይ እንዳያንፀባርቁ ነው ያደረግነው። ከዚህ ባለፈ በቀረበው ቅሬታ ላይ ለምን ተባልን አንልም። ሰዎች ሊሉን ይችላሉ፣ ነገር ግን ማስረጃ ካላቸው አቅርበው ያረጋግጡት ነው። ገና ለገና ይሆናል ተብሎ ያለፉትን መንግሥታት ባለማመን፣ እነዚህም እንደዚያ ናቸው ብሎ ማስቀመጥ አይቻልም። በነገራችን ላይ ይህ ኮሚሽን ብቻ አይደለም የምርጫ ቦርድም እኮ በፓርላማው ሥር ሆኖ ነው ተጠያቂ የሚደረገው። በተለይ ከፓርላማ የሚነገረን ነገር ዘገያችሁ ነው፣ መዘግየታችንን ደግሞ በማስረጃ እያስረዳን ነው። ቀላል አይደለም ሥራው። አሁን ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ በሚሠራበት ጊዜ ብዙ ችግር ያለበት ነገር ገጥሞናል። ነገር ግን ሁላችንም እንዲሁም ባለሙያዎቻችንም ቆራጦች ስለሆኑ ሄደው ተሠርቷል። የአማራ ክልልም እንዲሁ ይሠራል ብዬ እገምታለሁ። ከትግራይም ጋር እንሠራለን። ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነው። ምክክር የለም ማለት አልችልም፡፡ በአገራችንን ብዙ ብሔረሰቦች ዛፍ ጥላ ሥር ቁጭ ብለው ምክክር እያደረጉ ብዙ ችግሮቻቸውን ፈተዋል። የድሮዎቹ አንተም ተው አንተም ተው ነው፡፡ አሁን ግን ጠረጴዛ ዙሪያ እናምጣና እኔም የራሴን ሐሳብ አቀርባለሁ፣ አንተም አንቺም የራሽን ሐሳብ ታቀርባለህ ታቀርቢያለሽ፡፡ እየተከራከርን ተሸናፊና አሸናፊ ሳይኖር እንዴት ነው እነዚህን የቀረቡትን ነገሮች አዋህደን አንድ ውጤት ላይ የምንደርሰው ነው ምክክሩ። ምክንያቱም ከሌሎች ዓይነት ችግር አፈታት የተለየ ነው። ይህ የፍርድ ቤት ጉዳይ አይደለም ረቺና ተረቺ ያለበት። ወይም ሽማግሌዎች ገብተው አንተም ተው አንቺም ተይ አይሉበትም። በምክክሩ እውነቱ ላይ እንደርሳለን። ምክንያቱም ባለመደማመጥ ነው እንጂ ብዙ ችግር ሊፈታ ይችላል። እምነታችን እንደዚያ ነው። እየተከተልን ያለነው ሒደት በጠቅላላ አካታች ነው፡፡ አካታች የማይሆነውን ነገር ደግሞ ልንጠቆም እንችላለን። ቅድም እንዳልኩት አንድ ሥራ በሚሠራበት ጊዜ መቶ በመቶ ልክ ነኝ ለማለት የማይቻል ነገር ነው። በየቀኑ ነው ሥራ ስንሠራ ጉድለት በምናይበት ጊዜ እያስተካከልን ነው የምንሄደው። ይህ ለእኛ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። በፍልጥ አገር ከማስተዳደር በምክክር እናስተዳድር ተብሎ ነው ኮሚሽኑ የተቋቋመው፡፡ እናም ተዓማኒ አይደሉም የሚባለውን ነገር ሰምተናል፣ ከየቦታው ነው ጥያቄ የሚቀርብብን፣ ነገር ግን መልሳችን አሁን ያልኩት ነው።

ሪፖርተር፡- እርስዎ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አንስቶ በአገሪቱ ትልልቅ ለውጥ የፈጠሩ የሕዝብ አስተዳደር ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ነበረዎት። የአገሪቱን ጉዞ በእጅጉ በቀየሩ እንደ መሬት ላራሹ ባሉ ረቂቅ ፖሊሲዎች ላይ፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ረቂቅም ላይ የድርሻዎን አሻራ አሳርፈዋል። ሌሎችም ብዙ ኃላፊነቶችን ተወጥተዋል። እናም በእነዚህ ሁሉ መንገዶች አልፈው እንደ መምጣትዎ ምክክሩ በአጠቃላይ በፌዴራል ደረጃ ሲጠናቀቅ ምን ነገሮች ተግባራዊ ሊደረጉ ይችላሉ? ምን ዓይነት ለውጦች ሊፈጠሩ ይችላሉ? ብለን እንጠብቅ ለሚሉ ምላሽዎ ምንድነው?

አቶ ዘገየ፡- ይህን መመለስ አጀንዳ መጠቆም ይሆንብኛል። እኔ አጀንዳ መጠቆም አልችልም። አጀንዳ የሚጠቁመው ሕዝቡ ነው። በአጠቃላይ ግን ሕዝብንና መንግሥትን ያለያየው ጉዳይ ምን እንደሆነ ትኩረት ተሰጥቶ አንድ መፍትሔ ይገኛል። መንግሥትና ፓርቲን በተመለከተም ውይይት የሚደረግበት ነገር ነው። በአጠቃላይ ሕገ መንግሥቱ ተበታትኖ ይፈተሻል፣ ልክ ነው የሚልም ልክ አይደለም የሚልም ሊኖር ይችላል። ግን ያንን በውውይት ብንፈታው የሚል ነገር አለ፡፡ አሁን ለምሳሌ ብዙ አጀንዳዎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ እዚያ ውስጥ መግባት አልችልም።

ሪፖርተር፡- ከተሳታፊዎች ጋር በተያያዘ ከሚነሱት ነገሮች አንዱ በተለያዩ ክልሎች በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሕዝቡን ድምፅ እንወክላለን፣ ያላግባብ ነው የታሰርነው የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይ ከፖለቲካ ጉዳዩች አንፃር ሲታይ። ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያሉና የሕዝብ ድምፅ አላቸው ተብሎ ውጭ ባለው ማኅበረሰብ ስማቸው የሚነሳ ሰዎችን እንዴት ነው በምክክር ውይይቶች ተሳታፊ የሚደረጉት? የሕዝቡን ድምፅ እንወክላለን የሚሉ አካላት እንደ መሆናቸው መጠን ምክክሩስ ያለ እነሱ ውጤታማ ይሆናል?

አቶ ዘገየ፡- እነሱ ብቻ አይደሉም። ምክንያቱም ትጥቅ አንስተው በየቦታው የሚታገሉ አሉ። ለምሳሌ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አሉ። እኛ የምንለው አቋማችን ማንም ሰው ወደ ውይይት ቢመጣ እናስተናግዳለን፡፡ እዚህ ላይ ለምሳሌ ያህል የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ አለ፣ አንስተን እየተነጋገርንበት ነው። አሁንም እየተነጋገርንበት ነው፣ ምን ቢደረግ ይሻላል ነው። በኮሚሽኑ አቅም የታሰረ ሰው ይፈታ ለማለት ምናልባት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ከዚያም መጥተው ይወያዩ ለማለትም እንዲሁ። እንደሚመስለኝ ግን የተነሳው ጥያቄ አግባብ ስለሆነ፣ አሁን ስለተነሳ ብቻም ሳይሆን እየተወያየንበት ነው፡፡ ወደ ውሳኔ በምደርስበት ጊዜ እናሳውቃለን። በሚገባ ለማስረዳት ያህል ኃላፊነት (mandate) የሚባል ነገር አለ፡፡ የዚህ ተቋም ኃላፊነት ይህ ነው፣ ከዚህ ያለፍክ እንደሆነ ወደ ያልተፈቀደልህን ድንበር ጥሰህ ሄደሃል የሚባል ነገር ሊኖር ይችላል። ኃላፊነት ባይኖረንም አንዳንድ ሥራችንን ሊያሰናክሉ ይችላሉ የምንላቸው የምንገምታቸው ጉዳዮች አሉ። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ እንነጋገራለን። አሁን የተባለው ጥያቄ በእዚያ ንግግር ውስጥ ሊፈታ የሚችል ይመስለኛል።

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ በምክክር ጉባዔው የሚሳተፉ የኦሮሚያ ክልል ማኅበረሰብ ተወካዮች የማጠቃለያ ልየታ መድረክ በሻሸመኔ ከተማ ባካሄደበት ወቅት፣ በመድረኩ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች የሥራ ሒደቱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹በሌላ መንገድ እየታገሉ ይገኛሉ›› ያሏቸው አካላት ወደ ምክክር መድረኩ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበው ነበር። የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በምክክሩ ለሚሳተፉት የታጠቁ አካላት ኮሚሽኑ ተገቢውን ‹‹የጥበቃ ዋስትና›› (Safe Space) እንደሚያመቻች ተገልጾም ነበር። የጥበቃ ዋስትና ማመቻቸት የሚለው ምን ያካትታል? ኮሚሽኑ ይህንንስ የሚያደርገው በምን ሥልጣን ነው? አሁን እርስዎ ካነሱት ኃላፊነት (ማንዴት) ካሉት ነገር ጋር አያይዘው ምላሽ ቢሰጡ?

አቶ ዘገየ፡- ሥልጣን የለንም፣ መጠየቅ እንችላለን። ማመቻቸት እንችላለን፣ ግን ይህንን እናደርጋለን ማለት ትንሽ ከሥልጣናችን ወጣ ያለ ነገር ነው። ማመቻቸት የሚባለው ለምሳሌ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በሚረቀቅበት ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ ከአገር ተሰደው፣ የሄዱት ሁሉ ተመልሰው ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ተደርጎ ነበር። የ40 ቀናት የዕፎይታ ጊዜ ነበር የተሰጠው። ምንም ሠራህ ምን በ40 ቀናት ውስጥ ለሕገ መንግሥቱ ክርክር በምትመጣበት ጊዜ አትታሰርም ተብሎ ጊዜ ተሰጥቷል። ይህ ነው እንግዲህ ማረጋገጫው፣ የዕፎይታ ጊዜ የሚባለው ነገር። ይህንን የዕፎይታ ጊዜ እኔ በማውቀው ልክ ኮሚሽኑ ገና የጠየቀ አይመስለኝም። ይህንን ብንጠይቅም ጠይቀን ከተፈቀደልን የምንሠራው ነገር ነው እንጂ ተነስተን የምናደርገው አይደለም። ጥሪ የምናቀርብላቸውም ሰዎች እኮ እነዚህ ሰዎች ያሾፋሉ እንዴ ነው የሚሉት፡፡ ምን የደኅንነት ማስተማመኛ ኖሮን መጥተን እንነጋገራለን የሚል ጥያቄ ነው ሊነሳ የሚችለው። ስለዚህ ይህ በእዚህ መንገድ ነው መታየት ያለበት።

ሪፖርተር፡- አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ምክክር መድረኩን ለማካሄድ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ሥጋት ባለበት ሁኔታ ነው። የፀጥታ ችግሮች ባሉባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የምክክር ሒደቱ ተሳታፊዎችን ለመለየት ምን ያህል አስቻይ ሁኔታዎች አሉ? ምክክሩን ማድረግ መቻል አለመቻሉንስ በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

አቶ ዘገየ፡- እንዳልኩት የአማራ ክልልን እየሠራን ነው። የአማራ ክልልን በምንሠራበት ጊዜ አሁን ባለንበት ደረጃ እየሠራን ያለው እነዚያ አጀንዳ ለመስጠት የሚመረጡትን ሰዎች ለመለየት ነው። በአንዳንድ ቦታ እንደሚታየው እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ነው። አሁን እነዚህን ሰዎች ሄደን ለይተናቸው ኑ በሚባልበት ጊዜ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ይህንን በፀጥታ አካባቢ የሚፈጠረውን ችግር የአስተዳዳሪዎቹ፣ የፖሊሲ ኃይሉ፣ በየቦታው ያሉ የፀጥታ አስከባሪዎች ካልተጨመሩበት በስተቀር አስቸጋሪ ነው። ኦሮሚያ አካባቢ ስንወስድ መጀመሪያ አካባቢ ችግር ነበረብን፣ ግን እንደ ምንም ተደርጎ ታግዘን የሚመጡትንም ሰዎች በማደፋፈርና ሎጂስቲክስም በማዘጋጀት ሁሉም ተሰባስቦ እንደተባለው በሻሸመኔ የመጨረሻው የማጠቃለያ ልየታ ጉባዔ ነበር የተካሄደው። ብዙ ችግር አጋጥሞን ነበር ማለት ግን ይቻላል። ኦሮሚያ ውስጥ ያለው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ አንድ ሁለት ቦታ ችግር ቢያጋጥም ነው እንጂ ሌላው በሰላም ነው። አሁንም ተስፋችን አማራ ክልልም እንደዚሁ ዓይነት ነገር ይገጥመናል ብለን ነው። ግን እዚህም የምንከራከረው ለጥሩ ነገር ጠርተናቸው በሕዝቡ ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይደርስ እንፈልጋለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ችግር ካለ ከባድ ነው። ደግሞም አማራን የሚያህል ክልል ትተን፣ ትግራይን ትተን ይህንን ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ አካሄድኩ ለማለት በጣም ያዳግታል። ስለዚህ በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው፡፡ በዚህ እንሄዳለን ስንል አንድ ጉዳይ፣ በዚያ ስንል ሌላ አለ። እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ አለ፣ ግን መቅረት የለበትም፡፡ ከክልል መንግሥታት ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ አንዳንድ ነገሮች እየሠራን ነው፡፡ እንዳልኩት ጎንደር አካሂደናል። ደሴና እንዲሁም ሌሎች አንዳንድ ቦታዎች አሉ። ስለዚህ የፀጥታው ችግር መሰናክል እንደሆነ በሚገባ ተገንዝበናል፡፡ ያንን ደግሞ ዝም ብለን ጭልጥ ብለን የምንገባበት ሳይሆን፣ ለእዚህ የተመደቡ አካላት ካሉ አካባቢው ሰላም እንዲያደርጉልን የምናደርገው ጥረት አለ።

ሪፖርተር፡- በፀጥታው በኩል ያነሷቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው በትግራይ ክልል በምክክር ኮሚሽኑ ላይ እምነት የለንም የሚሉ ጥያቄዎች አሉ። ከዚያም ባሻገር በኮሚሽኑ በኩል ከዚህ ቀደም ይፋ በተደረጉ መረጃዎች መሠረት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ስላሉ ያንን አገባዶ ጥሪውን ሲያደርግልን ሥራችንን እንጀምራለን የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተባሉት ምን ዓይነት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው? ምክንያቱም በኦሮሚያ እርስዎ እንዳሉት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ሠርታችኋል? በአማራ ክልልም ችግሮችን አልፋችሁ ምክክሩን ለማካሄድ እየሞከራችሁ ነው፡፡ በተነፃፃሪ ሲታይ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎች ካሉ ሥጋቶች አንፃር የትግራይ ክልል የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የምክክር ኮሚሽኑ ትግራይ ውስጥ ሥራ የሚጀምርበት ሁኔታ የለም ወይ?

አቶ ዘገየ፡- አሁንም ወደ ማንዴታችን ልመለስ። ማንዴታችን እንደሚለው ማንንም ለምክክሩ ማስገደድ አንችልም። መጀመሪያ ኮሚሽኑ ወደ መቀሌ በሚሄድበት ጊዜ አብሬ ሄጄ ነበር። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን አነጋገርናቸው። አዎ አልተካተትንም የሚል ነገር አለ፡፡ ነገር ግን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት የሰማነው ባንካተትም ይህንን ሒደት እንደግፋለንና እንቀጥልበታለን ነው የተባለው። ግን በተከታታይ ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ እንደተባለው ማስተካከል ያለብን ጉዳዮች ስላሉ ነው የተሰጠው ምላሽ። እኔ እንደሚገባኝ በጦርነቱ ብዙ ሰዎች ከመንደራቸው ተፈናቅለዋል። ምናልባት የምናስተካክለው የሚባለው ነገር እሱ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ። ሌላው በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት እየተጠናቀቀ ይመስላል። ስለዚህ አሁንም ይህ ስላለ የሚቆም አይደለም፣ አሳውቀናል ይህ ችግር እንዳለብን። በሌሎችም አካላትም ይህ ምክክር እዚያም እንዲካሄድ ጥረት እየተደረገ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ እስከ መጨረሻው ድረስ ዕንቢታ ያለ አይመስለኝም። ምክንያቱም አቶ ጌታቸውም ሲናገሩ ካለማድረግ ዘግይቶም ማድረግ ይጠቅማል ነው ያሉት፡፡ በኮሚሽኑ ምሥረታ ጊዜ ክልሉ ጦርነት ላይ ነበረ። በምርጫና በሌላውም ላይካተቱ ይችላሉ። ግን አነጋግረናቸው በጎ ዕይታ ነው ያላቸው። ምናልባት ችግሩን የሚታውቀው ከሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ ነው። እኔ ግን በመላምት የምለው ከየቦታው የተፈናቀሉ ሰዎች ቦታ እስከሚይዙ የመጠበቅ ነገር ነው። በዚህ ላይ ሌላው ጉዳይ በአካባቢው ትልቅ ረሃብ መኖሩ ነው። ስለዚህ እነዚህ ችግሮች ናቸው እንጂ በትግራይም አካባቢ ምክክር እንደምናካሂድ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።

ሪፖርተር፡- አወያዮችና አመቻቾችን የመመልመል መሥፈርቶች ምን ነበሩ? በምክክሩስ ሚናቸውና ኃላፊነታቸው ምንድነው? ከኃላፊነታቸው ሊነሱ የሚችሉባቸው የተቀመጡ ዝርዝር ሁኔታዎችስ አሉ?

አቶ ዘገየ፡- ትልቁ ስብሰባ በሚጠራበት ጊዜ ዋነኛው ጥያቄ ማነው ስብሰባውን የሚመራው የሚለው ጉዳይ ነው። በዚህ በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የሚለውን ሰው ነው አመቻች የምንለው። አወያዮች የሚባሉት ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ነው መሠልጠን ያለባቸው። ምክንያቱም ሦስት ሰዎች ቁጭ ብለው እንኳ ሐሳብ አቅርቡ በሚባልበት ጊዜ አንዱ ከዚህ ይተኩሳል፣ ሁለተኛውም ሌላኛውም እንዲሁ፣ በጣም የሚጣረሱ ሐሳቦች ይመጣሉ። እነዚያን የሚጣረሱ ሐሳቦች በሚገባ ተረድቶ ወደ አንድ የጋራ ወደ ሆነ ነገር ለማምጣት ትልቅ የሆነ ችሎታ ነው የሚጠይቀው። ከዚህ በፊትም በምክክሩ ላይ በሁለት ውጭ አገሮች ሥልጠና ወስደናል። ምክክር ምን እንደሆነ፣ ሒደቱ ምን መምሰል እንዳለበት፣ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን። እንደሚባለው ማወያየትና አንድ ምጥ የያዛትን ሴት ማዋለድ አንድ ነው ነው የሚባለው። እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ከየቦታው ነው ሐሳብ የሚተኮሰው፡፡ ያንን የተተኮሰውን ሐሳብ ሁሉ አጠቃሎ በዚህ ትስማማላችሁ ወይ ብሎ አንድ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል። በዚያ ምክረ ሐሳብ ላይ እንስማማለን ከተባለ የጋራ መግባባት ተገኘ እሰየው። የለም እኔ እቃወማለሁ የሚባል ከሆነ ደግሞ ይህንን የሚቃወሙትን ነገር የሚያነጋግር እንደ ክሊኒክ ጎኑ ላይ የሽምግልና አቅም ያላቸው የማስተባበር ችሎታ ያላቸውን አወያዮች ማቋቋም ነው። ምንም ነገር ድብብቅ የለበትም። ይህ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ሰዎች የሚመለመሉበት፣ ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው፣ ሰዎች የሚመጡበት ስለሆነ እስካሁን ሥልጠናችንን እየጠበቅን ነው። እሱ ደግሞ የሚሆነው በአሁኑ ደረጃ ሳይሆን በፌዴራል ደረጃ ላይ በሚደረገው ምክክር ላይ ነው። አጀንዳ ወጥቶ ሕዝብ ወጥቶ በሚወያይበት ጊዜ እንዴት እናቀራርባቸዋለን የሚለውን ነገር አወያዩ ነው ወሳኝ ሰው። በዚህ በኮሚሽኑ ውስጥ ወሳኝ ሰው አወያዩ ነው። እሱን በጥንቃቄ ነው የምንይዘው። የአንተ ሐሳብ ደካማ ነው የእሷ ጠንካራ ነው ሳይባል ሁሉም ሐሳብ ከተሰበሰበ በኋላ ነው የጋራ አካፋዩን ዓይቶ በዚህ ትስማማላችሁ ወይ ብሎ ምክረ ሐሳብ የሚያቀርበው፣ አወያዩ ስለሆነ ማለት ነው። የአወያይ ሥራ ደንቡን የሚደነግግ የሕግ ክፍል አለን። አሁን ድንጋጌዎች እየረቀቁ ነው። ግን ችግሩ እነዚያን ሰዎች ማግኘት እጅግ ከሚባለው በላይ በጣም ወሳኝ ነው፣ ያለ በቂ ሥልጠናም አንገባበትም። ሥልጠናውንም በዚያው እየጠበቅን ነው።

ሪፖርተር– ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ ለውይይት መርጦ ከከተማ ከተማ የሚወስዳቸው ሰዎችን አበል ከፍሎ እንደሚያንቀሳቅሳቸው ይታወቃል። ከእነዚህ ተሳታፊዎች መካከል በቂ አበል እየተከፈለን አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ይደመጣሉ። በቂ በጀት የላችሁም ወይ?

አቶ ዘገየ፡- በቂ በጀት አለን። ለምንጋብዛቸው ሰዎች ለምግብ የሚበቃ አበል እንሰጣለን። ከቦታ ቦታ በሚጓዙበት ጊዜ የሚከፈላቸው የቀን አበል አለ። ይህንን አበል በሁለት ዓይነት መንገድ ነው የምንከፍለው። አንደኛ ኮሜርሻል ኖሚኒ በሚባሉት በኩል እዚያው ቁጭ ብለው በጥሬ ገንዘብ የሚከፍሉበት አሠራር አለ። አሁን ባሳለፍነው ሳምንት ከተደረገው ጉባዔ በፊት በአዲስ አበባ ተደርጎ በነበረ ሌላ ስብሰባ ባደረግንበት ወቅት፣ በዚህ መንገድ ነበር የተከፈለው ምንም ቅሬታ የለም። አንዳንድ ቦታ ደግሞ በባንክ አካውንት ለመክፈል የባንክ ደብተር ቁጥራችሁን ስጡ ስንል የራሳቸውን ትተው የሌላ የዘመዳቸውን አካውንት ቁጥር ይሰጣሉ (ይህንን በዓይኔ አይቻለሁ)። ሄደው ከባንክ አካውንታቸው ለማውጣት ሲሞክሩ ችግር ተፈጥሯል። ስለዚህ አሁን ለማድረግ እየሠራን ያለነው በአሁኑ የአዲስ አበባ ስብሰባ ላይ ከንግድ ባንክ ጋር ተነጋግረናል። ኮሜርሻል ኖሚኒ የግል ድርጅት ነው። አሁን ግን ክፍያው እዚያው ሲመጣ እንዲከፈለው በባንክ አካውንት ይከፈል የሚለውን ነገር እየተውነው ነው። ይህም ሆኖ ግን ለምሳሌ ደቡብ ምዕራብ ክልል በምንሠራበት ጊዜ በዚህ ምክንያት አልተከፈለንም የሚል ከፍተኛ ቅሬታ ተነስቶ ነበር። ከዚህ ልዑካን ተልከው እያንዳንዱ ያልተከፈለውን ዓይተው እየከፈሉ ይገኛሉ። መጨረስ አለመጨረሳቸውን እርግጠኛ ባልሆንም፡፡ አንዳንድ ግጭት ይኖራል። ለምሳሌ ለአምስት ቀናት ጠራናቸው ማለት የአምስት ቀናት ብቻ አይደለም የምንከፍለው፣ መምጫና መመለሻውንም ይጨምራል። አንዳንዶቹ በየቦታው ስለምናድር ተጨማሪ ክፍያ አድርጉልን የሚል ጥያቄ አላቸው። እሱንም ተጨማሪ ክፍያ እያደረግን ነው፣ ምክንያቱም እንግዶቻችን ናቸው። እኛን ለመርዳት ነው የመጡት።

ሪፖርተር፡- ምክክሩን ከአንድ ዓመት ባላነሰና ባልበዛ ጊዜ ውስጥ እንጨርሳለን የሚል የድርጊት መርሐ ግብር እንደነበር ሲነገር ቆይቷል። በእርግጥ በአንድ ዓመት ውስጥ መጨረስ ይቻላል?

አቶ ዘገየ፡- አይቻልም። አንደኛ ትንሽ የሥራው ስፋት ውስጥ ተገብቶ ካልታየ በስተቀር በከፍተኛ ተነሳሽነት ብድግ ብለን የሚከናወን አይደለም። አንዳንድ ጊዜ መጋቢት ላይ፣  ሚያዚያ ላይ ሊባል ይችላል፡፡ ግን ዝግጅቱን በምናይበት ጊዜ አይሆንም። አሁን ሁለት ዓመታችንን እየጨረስን ነው። በዚህ በሦስተኛ ዓመት ውስጥ ቢያንስ አሁን የቀረን እንደ ተናገርኩት ሁለት ክልሎች ነው። ሌላ ሌላ ደግሞ የቀረውን አሟልተን አገራዊ ምክክሩ በዚህ ዓመት በሦስተኛው ዓመት ለማድረግ የሚቻል ይመስለኛል። እንደተፈለገ ሊደረግም አይቻልም። አርሶ አደሩም እኮ ከሥራው ተነስቶ ነው ለምክክር የሚመጣው። የትራንስፖርት ችግር፣ የሎጂስቲክ ችግር ብዙ ነው። እንዲያውም በዚህ በአጭር ጊዜ ከ120,000 በላይ ነው የተሳተፉትና ለአጀንዳው የተዘጋጁት። የተባለው ሦስት ዓመት ካልበቃም እናራዝማለን፡፡ እኛ ግን ያንን ማራዘም ይደረጋል ብለን አንጠብቅም። በዚሁ ለማጠናቀቅ ነው እየሠራን ያለነው። ሁሉም ከተባበረንና ከረዳን መጨረስ እንችላለን ብለን ግን እናምናለን።  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...