Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉአገር በቀል ዕውቀት ለማኅበራዊ ተግዳሮቶች መፍቻ

አገር በቀል ዕውቀት ለማኅበራዊ ተግዳሮቶች መፍቻ

ቀን:

በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሰባተኛውን ዓመታዊ አገር አቀፍ የቋንቋና ባህል ዓውደ ጥናት፣ ‹‹አገር በቀል ዕውቀት ለማኅበራዊ ተግዳሮቶች መፍቻ›› በሚል የኮንፈረንስ ጭብጥ አካሂዷል፡፡ በዓውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ የቀረበው ቁልፍ ንግግር ለጋዜጣው እንዲመጥን ሆኖ አንደሚከተለው ቀርቧል:: 

ቋንቋ፣ ባህልና አገር በቀል ዕውቀት በፅኑ የተቆራኙ ማኅበራዊ ዘርፎች ናቸው፡፡ በዚህ ዝግጅት ስለቋንቋ በመጠኑ የምገልጸው ከቋንቋ አገልግሎትና ፍቺያዊነት ብያኔዎች አንፃር ተነስቼ ነው፡፡ ከሳፒር የተባለ ምሁርን ጠቅሶ ጌታቸው እንዳለማው (2011) እንደገለጸው ቋንቋ በተወልዶ (በደም) የማይወረስ የሰው ብቻ የሆነ፣ ማኅበረሰባዊ ቡድኖች የሚተሳሰሩበት የተግባቦት መሣሪያ ነው ብሏል፡፡ ቋንቋ ባህል በሚገኝበት መንገድ የሚገኝ፣ የሚለምዱት ወይም የሚማሩት እንጂ ይዘውት የማይወለዱት፣ ሁልጊዜ ለውጣዊና በአንዳንድ አጋጣሚዎችም የሚጠፋ ወይም የሚሞት፣ በጽሑፋዊ መልዕክትም ሊወከል የሚችልና በቦታና በጊዜ በግድ የማይመደብ የሰው ልጅ ብቻ የሆነ የመግባቢያ መሣሪያ ነው፡፡ ይህ የአገልግሎትና ፍቺያዊ ብያኔ የብሔር ፖለቲከኞች ለቋንቋ ከሚሰጡት ‹‹የከፋፍሎ መግዛት ብያኔ›› ይለያል፡፡ የብሔር ፖለቲከኞች ቋንቋን በደማዊ ማንነት የሚገኝ ‹‹የእኛና እነሱ ፍረጃ›› የፖለቲካ ኪራይ መሰብሰቢያ መሣሪያ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ 

- Advertisement -

የአገር በቀል ዕውቀትና የቋንቋ ግንኙነት የሚመሠረተው የቋንቋ አንዱ ተግባር ሐሳብ/ነገር/መረጃ ማስተላለፍ በመሆኑ ላይ ነው ሲል ጌታቸው እንዳለማው (2011) ገልጿል፡፡ ያለቋንቋ የአገር በቀል ዕውቀት ለሌላው አካል በሚገባ አይተላለፍም፡፡ የአገር በቀል ዕውቀት ሲዳብር፣ ሲጎለብትና ሲሰርጽ ባህል ይሆናል፡፡ ባህል በማኅበር የተለመደ/የተወረሰ ዕውቀት ወይም  በጋራ የተገኘ ተሞክሮ ነው፡፡ ሊዮንስ የተባለ ምሁር ባህል አንድ ሰው የአንድ ማኅበረሰብ አባል በመሆኑ አጋጣሚ ብቻ የሚለምደው ወይም የሚያገኘው ዕውቀት ነው ሲል ገልጿል፡፡

የባህልና አገር በቀል ዕውቀት ምንጭ ብዝኃ ሕይወትና ብዝኃ ሕይወትን የሚጠቀም የማኅበረሰብ ክህሎትና ልምምድ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ባህል የተመሠረተበት የብዝኃ ሕይወት ገጽታ ከምድረ ገጽ ሲጠፋ  ተያያዥ የሆነው ባህል ቀስ በቀስ ይጠፋል፣ በሚጠፋው የባህል ክምችት መጠንም የማኅበረሰቡ ማንነት ቀስ በቀስ ደብዝዞ ይጠፋል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የብሔር ፖለቲከኞች ተዋናኝ በሚሆኑበት አገር ፖለቲከኞቹ በአንዱ ማኅበረሰብ ቋንቋና ባህል መዳከም ላይ የሌላው እንዲበለጽግ እርስ በርስ ይተናነቃሉ፡፡ 

ተያያዥነት ያላቸውን ቋንቋ፣ ባህልና አገር በቀል ዕውቀት ሁሉንም በዚህ ጽሑፍ ለመተንተን ስለሚያስቸግር በአገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የአገር በቀል ዕውቀት ምንነት፣ አመዳደብ፣ በውርስ ተላላፊነት፣ የዕውቀት ዘርፉን የትኩረት አጀንዳ የማድረግ አስፈላጊነት፣ የዘርፉ ማኅበራዊ ተግዳሮቶች፣ የዘርፉ መዳከም ጥቂት አስረጂዎች፣ ለሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ያለው ፋይዳና መዋቅራዊ ሽግግር አስፈላጊነት በቅደም ተከተል ይተነተናል፡፡

የአገር በቀል ዕውቀት ምንድነው?  

የአገር በቀል ዕውቀት (Indigenous Knowledge, Traditional Knowledge) በሁሉም ዘንድ በስፋት የሚናፈስ ቃል (Buzzword) ይሁን እንጂ መዋቅራዊ አደረጃጀቱ ላይ በሁሉም ዘንድ በቂ ግንዛቤ የተያዘ አይመስልም፡፡ የአገር በቀል ዕውቀት የአንድ ማኅበረሰብ መለያ የሆነ፣ የተካበተ የነገሮችና ሁኔታዎች ዕይታ፣ የአስተሳሰብና የግንዛቤ ችሎታ፣ ዘርፈ ብዙ የባህላዊ አሠራር ሥርዓትና ልማድ ተመጣጣኝ ቴክኖሎጂና ክህሎትን ሁሉ ይመለከታል፡፡ 

አንዳንድ አገሮች ለአገር በቀል ዕውቀት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የዕውቀት ዘርፉ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ሲሉ  የአገር በቀል ዕውቀትን የሚመለከት አንቀጽ በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ አካትተዋል፡፡ ነገር ግን በአገራችን ስለአገር በቀል ዕውቀት ጉዳይ በሕገ መንግሥታችን የተቀመጠ አንቀጽ ባይኖርም እንኳ በአዋጅ ቁጥር 482/2006 የተጠቀሰ ሐሳብ አለ፡፡ በተጨማሪም አገራችን የፈረመችውን  ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ስምምነት (Biodiversity Convention, 1992) መሠረት በማድረግ በተዘጋጀው ብሔራዊ የብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ላይ ስለአገር በቀል ዕውቀት ጉዳይ ተጠቅሷል፡፡  

የአገር በቀል ዕውቀት ምድቦች 

እንደ ዘርፉ ተመራማሪ ስሊከርቪር (2005) የአገር በቀል ዕውቀት በሁለት ምድቦች ይመደባል፡፡ አንደኛው ምድብ የአገር በቀል ዕውቀት ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት (Tacit) ይባላል፡፡ ይህ የአገር በቀል ዕውቀት ከማኅበረሰቡ ትዕይንተ ዓለም (World View) የሚመነጭ፣ በማኅበረሰቡ የእርስ በርስ ግንኙነትና ከተፈጥሮ ጋር ባለው መስተጋብር ውጤት ላይ የተመሠረተ፣ የማኅበረሰቡን የጋራ ማንነት ገላጭ የሆነና ማንኛውም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ሁሉ ያቀፈ ነው፡፡ ሃይማኖት፣ ሥነ ቃል፣ ወግ፣ ትውፊት፣ አፈ ታሪክ፣ ተረት፣ ተረትና ምሳሌ፣ ሞራል፣ ዘርፈ ብዙ የማይዳሰስ ባህል፣ የአሠራር ሥርዓታት (የማኅበረሰባዊ ቅራኔ አፈታት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ልማት፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ የአለባበስ፣ የዳኝነት፣ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር፣ ወዘተ) ሁሉ በዚህ የአገር በቀል ዕውቀት ምድብ ይካተታል፡፡ 

ይህ የአገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ ከማኅበረሰቡ የጋራ ሥነ ልቦናና ታሪክ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ የዕውቀቱ መጥፋት ወይም መዳከም የማኅበረሰቡ ማንነት መዳከም ወይም መጥፋት አመልካች ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ዕውቀቱ እንደ ማኅበረሰቡ የዕድገት ደረጃ በአፈ ታሪክ፣ በሥነ ቃል/ኪነ ቃል ወይም በሥነ ጽሑፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ የብሔር ፖለቲካ ሥር በሰደደበት የመንግሥት ሥርዓት መዋቅራዊ ለሆነ የብሔረሰብ ተኮር ጥቃት ተጋላጭ የሆነው የአገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ ይህ ምድብ ነው፡፡

ሁለተኛው ምድብ የአገር በቀል ዕውቀት በአካባቢ ባለሙያዎች የተያዘ ዕውቀት ወይም የጠበብት ዕውቀት (Explicit) ነው፡፡ የዕውቀቱ ባለቤቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ታቅፈው የሚኖሩ ጠበብት በመሆናቸው እነሱ በግል የያዙት ዕውቀት የማኅበረሰብ ዕውቀት አካል ነው፡፡ ይህ ዕውቀት የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ አያያዝና ጥበቃ ሥርዓት የሚጠቁም ሲሆን፣ ዕውቀቱ በብዙኃኑ ውስጥ በመሠራጨት በሚገባ ሲስፋፋና ሲሰርፅ ወደ ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት (Tacit) የመሸጋገር ዕድል አለው፡፡ ማኅበረሰቡ ዕውቀቱን ቀስ በቀስ የጋራ ዕውቀት (Common knowledge) ስለሚያደርገው በአንድ አካባቢ ጠበብት ብቻ የተያዘ ዕውቀት ሆኖ አይቀርም፡፡ የአገር በቀል ዕውቀት የይዞታ ባለቤትነት መብት (Patent Right) የሌለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የሥር ማሽ ሕክምና (Herbalism)፣ ሽመና፣ ሸክላ ሥራ፣ አናጢነት፣ ግንበኝነት፣ አንጥረኝነት፣ ፋቂነት፣ የአካባቢ ባህላዊ ግብርና ዘዴ (ጥምር ግብርና፣ ቅይጥ ግብርና) ወዘተ በዚህ የአገር በቀል ዕውቀት ምድበ ውስጥ ይካተታሉ፡፡  ይህ የአገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ ልዩ ዕውቀት ባካበቱ የማኅበረሰቡ አባላት መንጭቶና ጎልብቶ ቀስ በቀስ ወደ ሌላው የማኅበረሰቡ አባል በልምድ ቅስሞሽ ሲተላለፍና በስፋት ሲሠራጭ ተቋማዊ የአካባቢ ማኅበረሰብ ዕውቀት ይሆናል፡፡ የዕውቀት ዘርፍ ምድቡ የተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀትን ያህል መዋቅራዊ ጥቃት ባይፈጸምበትም የዕውቀቱ ጠበብቶች የመገለል ብሎም የሞራል ማላሸቅ ማኅበረሰባዊ ጥቃት ሲፈጸምባቸው ኖሯል፡፡

የአገር በቀል ዕውቀት በውርስ ተላላፊነት፣ ተስፋፊነትና ታዳጊነት

አገር በቀል ዕውቀት ከዕውቀቱ ባለቤት ወደ ቤተሰብ አባል፣ ወደ ማኅበረሰቡና ከማኅበረሰብ ወደ ማኅበረሰብ የሚተላለፍ ዕውቀት ነው፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት በመታገዝም ሊያድግና ሊዘምን ይችላል፡፡ በዕውቀቱ ባለቤቶች ብቻ በጥብቅ ሚስጥር ተቆልፈው የሚያዙ እንደ ባህላዊ ሕክምና ዕውቀት ያሉ ቢኖሩም፣ ሚስጥሩ ክፍት በሚሆነበት አጋጣሚ ሁሉ ማንኛውም አገር በቀል ዕውቀት በኅብረተሰብ ውስጥ የመስፋፋት፣ በኢንዱስትሪ ልማት የመሳለጥና መዋቅራዊ ሽግግር የማድረግ ዕድል አለው፡፡ 

የረዥም ዘመን የሕዝብ የእርስ በርስ መስተጋብርና አብሮነት ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የአገር በቀል ዕውቀት ተጋሪነት መሠረት ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊ መልክዓ ምድርና የአግሮኢኮሎጂ ቀጣና በመሠራጨት የሚኖሩ ከ80 በላይ ብሔረሰቦች አንዱ ከሌላው የሚለዩባቸው የአገር በቀል ዕውቀቶች ቢኖሩም፣ በባህል ውርርስና ልውውጥ የተነሳ የአገራችን ብሔረሰቦች የበርካታ አገር በቀል ዕውቀቶች የጋራ ባለቤቶች ሆነዋል፡፡ በመሆኑም የአገር በቀል ዕውቀት ተላላፊ፣ ተስፋፊና ታዳጊ ነው፡፡  

በአገራችን ይህ ዕውቀት የዚያኛው ብሔረሰብ ልዩ ዕውቀት ነው፣ ያኛው የዚያኛው ብሔረሰብ ነው ብሎ ድንበር ለማበጀት ያስቸግራል፡፡ ዳሩ ግን ኢትዮጵያውያን የጋራ አገር በቀል ዕውቀት ባለቤት ሆነዋል ማለት ቢቻልም፣ የሁሉም አገር በቀል ዕውቀት ልውውጥ ተካሂዶ ሥርጭቱ በሥነ ምኅዳርና ማኅበረሰብ አንፃር ተጠናቋል ማለት አይቻልም፡፡ በአንድ ምሳሌ ለማሳየት በደቡቡ የአገራችን ክፍል የሚታወቀውን የእንሰት የአገር በቀል የማኅበረሰብ ግብርና ምጣኔ ሀብት አጠቃቀም ዕውቀትን፣ ወደ ወሎ አካባቢ ለመሳብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ምርምር በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ 

የአገር በቀል ዕውቀት ለምን ዋና የትኩረት አጀንዳ ሊሆን ይገባዋል?

የአገር በቀል ዕውቀት በምዕራባዊያን የዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት መስፋፋት መነሻ ሲሆን የአገር በቀል ዕውቀት ባለቤት ለሆኑት በዕድገት ወደ ኋላ ለቀሩ አገሮች ደግሞ ሊበለፅግ የሚችል ጠቃሚ የዕውቀት ዘርፍ ነው፡፡ የአገር በቀል ዕውቀትን በኋላ ቀርነት የሚያጣጥሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የመኖራቸውን ያህል መጠበቅ፣ መበልጸግ፣ መጎልበትና ለትውልድ መተላለፍ ያለበት ዕውቀት መሆኑን የሚመሰክሩ አሉ፡፡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቀው የምዕራባውያን ዘመናዊ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ  በማደግ ላይ ላሉ አገሮች  ከውስጥ ለሚመነጭ ዘላቂ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብቻውን አስተማማኝ መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል፣ ታዳጊ  አገሮች በአገር በቀል ዕውቀት ክምችታቸው መበልፀግ ላይ ያተኮረ የልማት ዕድገት ፖሊሲ ሊነድፉ እንደሚገባ የሚመክሩ ጠበብቶች አሉ፡፡ የትምህርትና የምርት ትግበራ ሥርዓታቸውን ከአገር ባህል ዕውቀት አጠቃቀም ጥረት ጋር ሊያቀናጁ እንደሚገባቸው ይመክራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የደሃ አገሮች ፖለቲከኞች የአገራቸው የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ልማት ዕድገት ፍልስፍና ከአገር በቀል ዕውቀት ተፋትቶ፣ የምዕራባውያንን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤት በመኮረጅ ላይ ብቻ እንዲንጠለጠል ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ 

የአገር በቀል ዕውቀት ማኅበራዊ ተግዳሮቶች ምንድናቸው?

የአገር በቀል ዕውቀት የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች መፍቻ በመሆን የሚያገለግል ይሁን እንጂ፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ዕውቀት ለዘላቂ ማኅበረሰባዊ ልማት ለማዋል ተግዳሮቶች አሉ፡፡ በመሆኑም የዕውቀት ዘርፉ በዘላቂነት አድጎ መዋቅራዊ ሽግግር ለማድረግ የተጓዘው መንገድ ምቹ አልነበረም፡፡ ሁለቱም የአገር በቀል ዕውቀት ምድቦች (ተቋማዊና የጠበብት) ዕድገታቸውን ከሚያቀጭጭ እንቅፋት ነፃ ሆነው አያውቁም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ  የአገር በቀል ዕውቀቶች እንቅፋቶች በአገራችን በጊዜ ሒደት ሲተካኩ የመጡት ሥርዓተ መንግሥታትና በቅርቡ የተከሰተው የብሔር ፖለቲካ አስተሳሰብ ናቸው፡፡ ለአገር በቀል ዕውቀት ተገቢውን ዕውቅና አለመስጠት፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ማጣጣልና ማራከስ፣ መበረዝና ማደብዘዝ፣ የሌላውን ቋንቋ ጠልነት፣ የቱባ ባህል ሽሚያ፣ የጋራ ታሪክ ጠልነት፣ ቀኖና መጣስ የመሳሰሉት ችግሮች የተቋማዊ ማኅበረሰብ ዕውቀት ዕድገት እንቅፋቶች ወይም የህልውና ፀሮች ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜ የዚህን ችግር መገለጫ ብቻ ብንመለከት፣ የሥርዓቱ መሪዎችና ተከታዮቻቸው በመድረክ ሲያስተጋቡ የነበሩትን ብሔር ተኮር የአገር በቀል ዕውቀት ጥቃት ማስታወስ ይቻላል፡፡ 

‹‹ወሎ ንግርቱን ይጠብቅ››፣ ‹‹የአማራ ተረት››፣ ‹‹የአማራ ትምክህት››፣ ‹‹ነፍጠኛ  አማራ››፣ ‹‹ከአማራ ጋር አትጋቡ/የተጋባችሁም ተፋቱ»፣ ‹‹አትዋዋሉ/እሳት አትጫጫሩ››፣ ወዘተ የሚሉት ሁሉ የዚህ ተቋማዊ ዕውቀት ባለቤት የሆነውን አንዱን ማኅበረሰብ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጥሎ ዝቅ ለማድረግና ለማቆራረጥ የተፈጸመ መዋቅራዊ ጥቃት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ እንደ ተቋማዊ የአገር በቀል ዕውቀት ሁሉ ጠበብት-መራሹ የአገር በቀል ዕውቀትም ከገዥ መደብ ተፅዕኖ አላመለጠም፡፡ ጠበብትን ማሳደድ፣ ማደናገር፣ ሞራል ዝቅ ማድረግ፣ ተገቢውን ዕውቅና ከበሬታ መንፈግ፣ ጠበብት መራሽ የአገር በቀል ዕውቀት እንዳይጎለብት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተራክቦ በልፅጎ ለአገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ ዕድገት እመርታ በበኩሉ ድርሻውን እንዳያበረክት የመጣ የሄደው የገዥ መደብ ሥርዓት  በዘርፉ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደሩ በአስረጅነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ቢያንስ ለዕውቀት ዘርፉ ተገቢው ጥበቃ አልተደረገም ማለት ይቻላል፡፡ 

በጠበብት የተያዘ የማኅበረሰብ ዕውቀት ለመንግሥትና የፖለቲካ ድርጅቶች ጥቃት ተጋላጭ እንደነበር ከታሪካችን ስናስታውስ፣ በሌላ በኩል የልዩ ሙያ ባለቤት የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለዘመናት የከፈሉት ዋጋ ቀላል እንዳልነበረ እንረዳለን፡፡ ሥርዓቱ ሸማ ሠሪውን «ቁጢት በጣሽ»፣ ነጋዴውን «መጫኛ ነካሽ»፣ አንጥረኛውን «ቀጥቃጭ»፣ የቆዳ ባለሙያውን «ፋቂ»፣ ወዘተ በማለት የሙያውንና ሙያተኞችን ክብር ዝቅ በማድረግ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት በማሳጣት የጥበብ ሥራ ውጤታቸውን ያለ ይሉኝታና ወሮታ ሲጠቀም ኖሯል፡፡ የዚህ ችግር ሰንኮፍ ከሥሩ ገና ስላልተነቀለ ተፅዕኖው ዛሬም በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ማኅበረሰቦች ዘንድ መኖሩና የጥበቡ ባለቤቶች ቅሬታቸውንና ብሶታቸውን በተለያየ ግብረ መልስ፣ በአመፅ ጭምር ሲገልጹ ይታያል፡፡ ይህ ችግር በመንግሥትና ኅብረተሰቡ በኩል የአገር በቀል ዕውቀትን ዋና አጀንዳ አድርጎ ካለመሥራት የመጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአፍ የሚነገረውን ያህል ለአገር በቀል ዕውቀት መቀጠልና መዋቅራዊ የዕድገት ሽግግር ማድረግ አልተሠራም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጠበብት አገር በቀል ዕውቀት ለባህል ብረዛ (Acculturation) እና ለቴክኖሎጂ ተፅዕኖ (Technology Pressure) ተጋላጭ ተደርጓል፡፡ ቀስ በቀስ እየደበዘዘና እየጠፋ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ተቋማዊ የአገር በቀል ዕውቀት የገዥ መደቡን ፍላጎት እስካላሟላ ድረስ የቱንም ያህል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ፋይዳ ይኑረው፣ የሚደረግለት የሕግ ጥበቃና ድጋፍ እምብዛም ነው፡፡ የአጭር ጊዜ የቡድን ስትራቴጅካዊ ጥቅም የሚመለከተው ገዥ መደብ የረዥሙ ጊዜ የአገርና ማኅበረሰብ ህልውና፣ ዕድገትና ገጽታ ግንባታ አያስጨንቀውም፡፡

የአገር በቀል ዕውቀት በኢትዮጵያ እየተዳከመ መምጣት ጥቂት አስረጂዎች 

በአገራችን የአገር በቀል ዕውቀት በመዳከም ላይ ይገኛል የሚለውን ትችት ዕውነታነት መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር ለማገናዘብ ጥቂት መረጃዎችን በመምረጥ በአስረጅነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከላይ ለተጠቀሰው አባባል ድጋፍ የሚሆን ጉልህ ማስረጃ ከቻይና ጋር ከተፈጠረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ውጤት ብቻ እናገኛለን፡፡ ቻይና በአገራችን የሚካሄደው አብዛኛው የመንገድ ሥራና ሌሎችም የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ዋና ተቋራጭ እየሆነች ትገኛለች፡፡ አገሪቱ በሥራው ላይ የአገሯን ዜጎች ባህላዊ ልብሳቸውን አልብሳ ስታሰማራ፣ በአንፃሩ የአገራችን ወጣቶች የባህል ልብሳቸውን አውልቀው በመጣል ከመቀመጫ አካላቸው በታች ቻይና ሠራሽ የተቀዳደደ ሱሪ ከቡቲክ ገዝተው እንዲለብሱ ተፅዕኖ አድርጋለች፡፡ የአገር በቀል ዕውቀታችንንና ሥነ ልቦናችንን በዚህ መልኩ እያከሰመች መሆኗን ያልተገነዘበ ዜጋ  አለ አልልም፡፡ 

‹‹ሽፎን›› በሚል የብራንድ ስም የሚታወቅ ልጥፍ የጥልፍ ጥበብ ፍሬም የሚዘጋጅ የሴት ቀሚስና ነጠላ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከቱርክ ያለገደብ እንዲገባ በመፍቀድና በአገር ውስጥም እንዲመረት በማድረግ የአገራችንንና የብሔረሰቦቻችንን ቱባ የአለባበስ ባህል ለአደጋ አጋልጠናል፡፡ በረቀቀ ተፅዕኖ የአገራችን አገር በቀል  የጥበብ ሥራ ዕውቀት ቀስ በቀስ እንዲከስም፣ በዘርፉ የተሰማሩ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ምርት ገዥ እንዲያጣ፣ በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ዜጎች ሥራ አጥ እንዲሆኑ፣ የአገር ውስጥ ገበያው በአማራጭ ዋጋ ለአልባሌ ልብሶች ክፍት እንዲሆን እየተባበርን መሆኑን ቁብ ሳንል የምንቀር አይመስለኝም፡፡ 

ከልብስ የዕደ ጥበብ ዘርፍ ውጭ በሌሎች የዕደ ጥበብ ዘርፎች ጭምር (በሸክላ ሥራ፣ በእንጨት ሥራ፣ የቆዳ ሥራ ውጤቶች፣ ወዘተ) የሚታየው መዳከም ተመሳሳይ ነው፡፡ በአንፃሩ አገሮቹ ያደረሱብንን ተፅዕኖ ሳናገናዝብ የአገሮቹ ቅርብ ወዳጅ መሆናችንን ለማስመስከር፣ የቻይናና የቱርክ ቋንቋ ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካልተሰጠ እንሞታለን የሚሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰዎችን እንታዘባለን፡፡ በአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ለግዕዝ ቋንቋና ለቻይና ቋንቋ የተሰጠውን ትኩረት ክብደት በንፅፅር ማየት ይቻላል፡፡ በአገር አቀፍ ቋንቋነት የሁሉም ዜጋ የጋራ መግባቢያ ሆኖ የቆየውን የአማርኛ ቋንቋ በመጥላትና በማስጠላት አንዳንድ ክልሎች ቋንቋው በትምህርት ዓይነትነት እንዳይቀጥል ሲያደርጉ፣ በአማራ ክልል አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችም የአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራም እንዲቋረጥ የሚደረግ ተፅዕኖ አለ፡፡ ተቀባይነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አየጨመረ የመጣውን የአማርኛ ቋንቋ በተወለደበት አገርና ሕዝብ መሀል ለማክሰም የሚደረገው የፖለቲካ ሴራ እንቆቅልሽ በጣም ያስገርማል፡፡ ለአፍሪካ ብቸኛ አኅጉር በቀል ሆሄና ለአገራችን የኩራት ምንጭ የሆነውን የግዕዝ ሆሄያት የድምፅ ክፍተቶች በጥናትና ምርምር በመሙላትና የነበረውን መልካም ጅማሮ በማስቀጠል፣ የሁሉም ብሔረሰቦች ቋንቋ የጋራ መተግበሪያ ማድረግ ሲገባ መስተጋብራችንን፣ አብሮነታችንንና የጋራ ተግባቦታችንን ሐረግ በጣጥሶ ልዩነታችንን በማጉላት ጭራሽ መቀራረብ የማንችል ለማስመሰል የባህር ማዶ ሆሄን (Latin) ተውሰው የብሔረሰባቸው የሥነጽሁፍ ሆሄ ያደረጉ የብሔር ፖለቲካ መርከበኞች መኖራቸው ሌላው እንቆቅልሽ ነው፡፡  

የገዥ መደብ የአገር በቀል ዕውቀት እንቅፋትነትን የሚያስረዱ በርካታ መገለጫዎችን ማቅረብ ቢቻልም፣ ለአብነት ያህል «አራቢነት ወይም ፋቂነት» የተጋረጠበትን እንቅፋት ለማየት እንሞክር፡፡ ዘርፉ በአገራችን በበርካታ ማኅበረሰቦች መሠረት ያለው ቆዳና ሌጦን የሚጠቀም በጠበብት የተያዘ የአገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ ነው፡፡ ከማኅበረሰብ  ገበያ የሚሰበሰብ ቆዳና ሌጦን  ቦግ እልም በሚል ጥገኛ የቆዳ ኢንዱስትሪና ንግድ መዋቅር ውስጥ ዘላቂነት በሌለው ሁኔታ በማስገባት የግል ወይም የቡድን ጥቅም ለማፍራት ከሚደረግ መናኛ የኪራይ መሰብሰብ እንቅስቃሴ በስተቀር ለጥሬ ሀብቱ መታወቂያ ለሆነው የአገር በቀል ዕውቀት ዕድገት፣ እንዲሁም ለጥሬ ሀብቱ በዘላቂነት ጥቅም ላይ መዋል የሚደረግ ብርቱ ጥረት አይታይም፡፡   

ቀደም ሲል አባቶቻችን በፈጠሩት ጠንካራ የአገር በቀል የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት የተነሳ አገራችን ኢትዮጵያ የከፍተኛ የቀንድ ከብት ባለቤት ለመሆን በመቻሏ፣ የአፍሪካ አኅጉር የእንስሳት ሀብት ክምችት ቀጣና የመጠሪያ ስም (Ethiopian Zoogeographical Region) ሆናለች፡፡ በቀንድ ከብትና  በቆዳና ሌጦ ሀብት ላይ የተመሠረተውን የአገር በቀል ዕውቀት ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ሳናስችል፣ ዛሬ በአባቶቻችን ወቅት የነበረውን የቀንድ ከብት አኃዝ (ስታትስቲክስ) የከፍታ ጣራ እየጠቀስን እንኖራለን፡፡ አባቶቻችን የቀንድ ከብት ሀብት ክምችታችን በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሚያደርግ የዘረጉት ባህላዊ የአሠራር ሥርዓት ነበራቸው፡፡ ሴት ከብት (ካልመሰነች ላም በስተቀር)፣ ጥጆች፣ ወይፈንና ጊደር ለገበያ እንዳይቀርቡ የሚያግድ አገር በቀል የከብት ሀብት አጠቃቀምና ልማት ሥርዓት ነበራቸው፡፡ «የቆዳ ቴክኖሎጂ የላቀ ከፍታ ደረሰ» በሚባልበት አገር የከብት ቆዳ ዋጋ አጥቶ በከንቱ የትም ተጥሎ ወድቆ የሚቀርበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ የአገር በቀል ዕውቀት የሆነውን «ፋቂነት» አጎልብቶ በማስቀጠል ዘመናዊ የቆዳ እንዱስትሪው የሚያጋጥመውን መንገጫገጭ በመቋቋም የተፈጥሮ ሀብታችንን በዘላቂነት መጠቀም የሚያስችል አገር በቀል ሥልት ሊኖረን ሲገባ፣ ባሳየነው የአፈጻጸም ጉድለት የጥገኛ ኢንዱስትሪው ውድቀት ሰለባ በመሆን የተፈጥሮ ሀብታችንም፣ ተዛማጅ የአገር በቀል ዕውቀቱም ሁለቱም ተያይዘው እንዲጠፉ አደረግን፡፡ በመሆኑም ለጉዳይ ማውጫ በየመንደሩ የሚታረዱ የቀንድ ከብቶች ቆዳ የሚቀበርበትን ጉድጓድ ጎን ለጎን በመቆፈር የከብት ቆዳ ሀብት አጠቃቀማችን የት ደረጃ ላይ እንደደረሰ አሳይተናል፡፡ በተጨማሪም ለንግድ ሥራ አዋጭነት መርህ ብቻ በመታመን አባቶቻችን ያቆዩልንን የቁም ከብት ደህንነት ማስጠበቂያ ባህላዊ የክልከላ ደንቦች (Taboos) ቁብ አላልንም፡፡ 

አገር በቀል ዕውቀትን ሕገመንግሥታዊ ድጋፍ ሰጥቶ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ተገቢ በሆነ የአገር በቀል ዕውቀት ፖሊሲ ለማሳደግ የተሄደው ርቀት እምብዛም ነው፡፡ ይልቁንም የአገር በቀል ተቋማትን በማዳከም ወይም ቀስ በቀስ በማደብዘዝ አገር በቀል ዕውቀቶችንና በዕውቀቱ አማካይነት የተገነባውን የማኅበረሰብ ትስስርና አንድነት ለመፋቅ የተደረገው ጥረት ይበልጣል፡፡ በጠበብት ከተያዙ አገር በቀል ዕውቀቶች አንፃር በአገራችን ልዩ ሙያና ዕውቀት ያላቸው ዜጎች እነሱ እየተጎዱ ያለ ፍላጎታቸው ለገዥ መደቦች ህልውና መቀጠል የኅብረተሰብ አገልጋይ ሲሆኑ ኖረዋል፡፡ የገዥ መደቡ አባላት ግብረ በላዎች የዕውቀቱን ባለቤቶች በማግለል፣ ከውጤቱ ተጠቃሚ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር አጋጭቶ ሰላም በማናጋት፣ ዕውቀቱን በማቀጨጭ እንዳይጎለብት፣ ብሎም ወደ አገራዊ ኢንዱስትሪ ዕድገት እንዳይሸጋገር ማድረግን ስልታቸው አድርገው ኖረዋል፡፡ 

የአገር በቀል ዕውቀት ለሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ያለው ፋይዳ

በአገር በቀል ዕውቀት ፓኬጅ ውስጥ አገር በቀል የአገር አስተዳደር፣ የቤተሰብ አስተዳደር፣ የልጅ አስተዳደግና የማኅበረሰባዊ ግጭት አፈታት ባህልና ተቋማት ይገኝበታል፡፡ የአገር በቀል ዕውቀትን ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ማሳለጫ አማራጭ ሥልት አድርጎ መጠቀም ይገባል፡፡  አገራችንን የገጠማት የወቅቱ የሰላም ዕጦት ፈተና መንስዔው በአገራችን ዳብሮ የቆየው የአብሮ መኖር እሴት በብሔር ፖለቲካ ተፅዕኖ ምክንያት መሸርሸርና ተቋማቱን አዳክሞ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ላይ ለተመሠረተ ከፋፋይ ፖለቲካ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና መሰጠቱ ነው፡፡ የችግሩ መፍትሔ በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም «አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም» እንዲሉ፣ ለአገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓት ቀዳሚ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ከፖለቲካ የድብብቆሽ ጨዋታና ሸፍጥ የሚመነጭ መፍትሔ የመጠበቅ ዝንባሌ አይሏል፡፡ በፖለቲካ ቡድኖች መካከል የተፈጠረ የሐሳብ ልዩነትን በመመካከር ሳይሆን በድርድር ለመፍታት፣ እርስ በርስ ካለመተማመን የተነሳም የፈረንጅ ጣልቃ ገብነትና በሌላ አገር ከተማ መገናኘት  ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ሆኗል፡፡ ሁሉም ዓይነት የአገር በቀል ዕውቀትና ሥርዓታችን  ለብሔር ፖለቲካና ተፅዕኖው ልክፍት የተጋለጠ መሆኑን በመረዳት፣ ሁሉም ዜጋ ለመፍትሔው ካልተንቀሳቀሰ በስተቀር ወጣቱ ትውልድ አገሩን ከጥፋት ለማዳን አይቻለውም፡፡

ዴሞክራሲንና ልማትን ለማፋጠን ተቋማዊ የአገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር ማሳለጥና ሁለቱንም አመጣጥኖ መጓዝ ይገባል፡፡ የሕዝቡ አብሮነት የተመሠረተባቸው እሴቶች ማኅበራዊ መሠረት ምን እንደነበር በማጥናት ተገቢውን ዕውቅና መስጠት ለሚፈጠሩ ግጭቶች ማስወገጃ ይጠቅማል፡፡ ተፈጥሯዊ ላልሆኑ ሰው ሠራሽ የፖለቲካ ችግሮች በአገር በቀል ሥርዓቶቻችን ላይ በመመሥረት ፈጣን መፍትሔ እየሰጡ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡  

የአገር በቀል ዕውቀት መዋቅራዊ ሽግግር አስፈላጊነት 

አገር በቀል ዕውቀትን ለማኅበራዊ ተግዳሮቶች መፍቻ ለማዋል መወሰድ ያለባቸውን የአጭርና የረዥም ጊዜ ‹0ርምጃዎች ለይቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ የሚወሰደው ‹0ርምጃ አገር በቀል ዕውቀት ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናና የፖሊሲ ድጋፍ አግኝቶ ዋና የትኩረት አጀንዳ እንዲሆን ከማድረግ ይጀምራል፡፡ የየብሔረሰቡን ቱባ ባህል ከመጠበቅ ጀምሮ ኅብረተሰቡ ህልውናቸው በሕግ እንዲከበር ለሚፈልጋቸው ነባር እሴቶች ሁሉ የሕግ ከለላና ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከአገር በቀል ዕውቀት ጋር የሚዛመድ ዘርፍ የሚመሩ የመንግሥት አካላትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በፖሊሲ የተደገፈ አማራጭ የአገር በቀል ዕውቀት ልማት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በአገሪቱ የሥርዓተ ትምህርትና የኢኮኖሚ ልማት ዕድገት ፖሊሲና ስትራቴጅካዊ ዕቅድ ውስጥ እንዲካተት ግፊት በማድረግ፣ በአገራችን ላይ የሚካሄደውን የልማት ዕድገት እንቅስቃሴ ማፋጠን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአገራችን ሥርዓተ ትምህርት ከመነሻው ከአገር በቀል ዕውቀት የተፋታ መሆኑ ዋናው ችግራችን ነው፡፡ የአገር በቀል ዕውቀትን አጎልብቶ ወደ ዘመናዊ ትምህርት መዋቅር በቀላሉ ከማሸጋገር አንፃር የአብነትና መድረሳ ትምህርት ቤቶችን የሕፃናት ትምህርት አማራጭ መነሻ ተቋማት ማድረግ፣ በየደረጃው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የአገር በቀል ዕውቀት ፓኬጅ በአግባቡ እንዲካተት ቢደረግ ችግራችንን እያረምን ለመሄድ ያስችለናል፡፡ ለአብነትና መድረሳ ትምህርት ቤቶች ማበብ ተገቢውን የፖሊሲ ድጋፍ መስጠት፣ የተሰበረውን የአገር በቀል ዕውቀት ማሸጋገሪያ ድልድይ ለመጠገን ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ከባድ የኢንዱስትሪ ልማት ማስፋፋትን ከመሻት ጎን ለጎን  በጠበብት የተያዘ የአገር በቀል ዕውቀትን የሰፊውን ሕዝብ የዕለት ከዕለት የሥራ ክንዋኔ በሚያፋጥንና ኑሮውን በሚያሻሽል ደረጃ፣ በተመጣጣኝ ቴክኖሎጂ በማጎልበት የአገር በቀል ዕውቀት ሽግግር ቀስበቀስ እንዲፈጠርና ዘርፉ እንዲያብብ የሚያደርግ የኢንዱስትሪ ልማት ዕድገት አቅጣጫ መከተል ሊተኮርበት ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው adalhusm@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...