Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በሁሉም ሥፍራ በሁሉም የሕይወት መስክ በዚህ ዘመን በየዕለቱ የሚያጋጥሙን ነገሮች ብዛት እየጨመረ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕይወታችን በገጠመኞች የተሞላ እስከሚመስል ድረስ በድንገተኛ ጉዳዮች ስንደመም እንኖራለን፡፡ በቅርቡ የገጠመኝ ጉዳይ ከዓመታት በፊት የገጠመኝን አስገራሚ ክስተት ስለሚያስታውሰኝ ወደኋላ ልመልሳችሁ፡፡ ‹‹ወዴት መሄድ እንዳለብህ የምታውቀው ከየት እንደመጣህ ስትረዳ ነው…›› አይደል ብሂሉ? ለማንኛውም በአንድ ወቅት የገጠመኝ እንዲህ ይመስላል፡፡ ጊዜው ራቅ ቢልም ድርጊቱ ግን አይረሳኝም፡፡

ከበርካታ ዓመታት በፊት አንድ ወዳጄ ክፍለ ሀገር ውስጥ የገጠመው የፍርድ ቤት ውሎ ይህንን ይመስላል፡፡ ሰውየው በሰው አካል ላይ ጉዳት በማድረስ ተከሶ አውራጃ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ በተከሳሽ ላይ ሦስት ምስክሮች ተቆጥረው ስለነበር የዚያን ቀን ምስክርነት እየተሰማ ነው፡፡ ሁለቱ ምስክሮች ደርጊቱ መቼ እንደተፈጸመና ማን ማንን በመደብደብ ጉዳት እንዳደረሰ ከመሰከሩ በኋላ መስቀለኛ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ከሰጡ በኋላ ይሸኛሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ውስጥ የነበሩት ታዳሚዎች በምስክሮቹ ቃል ላይ የታዘቡት ሁለቱም ተመሳሳይ ነገሮችን ማስረዳታቸውን ነው፡፡

ሦስተኛው ምስክር ተጠርቶ የምስክርነት ቃሉን ሲሰጥ ግን ጉምጉምታ መሰማት ጀመረ፡፡ ዳኛው በመዶሻቸው ፀጥታ ካስከበሩ በኋላ መስቀለኛ ጥያቄዎች ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ዳኛው ምስክሩን፣ ‹‹ለመሆኑ ተከሳሽ ተጎጂውን እንዴትና በምንድነው የመታው?›› ብለው ሲጠይቁት፣ ተከሳሹ ያለ ምንም ማመንታት፣ ‹‹በሽጉጥ ግንባሩን ነው ያለው…›› ይላቸዋል፡፡ ልብ በሉ ሌሎቹ ምስክሮች የመሰከሩት ተከሳሽ ተጎጂውን በዱላ እንደ መታው ነው፡፡ ዳኛው የመገረም በሚመስል ስሜት፣ ‹‹ግንባሩን በሽጉጥ ከመታው እኮ ገድሎታል ማለት ነው፡፡ ተጎጂው ግን ይኼው በሕይወት አለ፡፡ ምን ዓይነት ምስክርነት እየሰጠህ ነው?›› ብለው ያፋጥጡታል፡፡ ምስክሩ ምንም እንዳልተፈጠረ ትከሻውን ከፍ ዝቅ አድርጎ፣ ‹‹ማለቴ ሽጉጡን ተኩሶ ሳይሆን ወርውሮ ነው ግንባሩን የበረቀሰው…›› ሲል ችሎቱ በሳቅ ተናጋ፡፡ ዳኛው ምስክሩ ተገዝቶ ነው የመጣው በሚል መንፈስ በፖሊስ ጥበቃ ሥር እንዲውል አዘው፣ ሌላ ቀጠሮ በመስጠት ሌሎች ባለጉዳዮችን ሲያስጠሩ ወዳጄ በምስክሩ ድርጊት በጣም ማዘኑን እንደነገረኝ አይረሳኝም፡፡

ይህንን የሚያስገርም የምስክርነት ቃል ለበርካታ ዓመታት እያስታወስኩ በመኖሬ፣ ስለምስክርነት ሲነገር ወይም ውይይት ሲኖር ትዝ ይለኛል፡፡ ይህ ነገር ይበልጥ ትዝ ያለኝ ግን በራሴ ላይ በደረሰው ነገር ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በምሠራበት መሥሪያ ቤት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሠረት ሁሉም የሥራ ክፍሎች ዝርዝር ዕቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ይታዘዛል፡፡ ይህ ዕቅድ የሁለተኛ መንፈቅ ዓመትን የሚመለከት ነው፡፡ በእኛ ዲፓርትመንት ደግሞ ዕቅዱን ሠርቼ እንዳቀርብ በቅርብ አለቃዬና በሥራ አስኪያጁ እታዘዛለሁ፡፡ በዚህ መሠረት በዲፓርትመንቱ ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች ጋር በመመካከር ሠርተን የጨረስነውን ዝርዝር ዕቅድ ለቅርብ አለቃዬ አቀርባለሁ፡፡

የቅርብ አለቃዬ ዝርዝር ጉዳዮችን ካየ በኋላ አፍንጫውን ነፍቶ፣ ‹‹የተሠራው ያልተሟላ ዕቅድ ነው…›› በማለት እሱ የሚፈልጋቸውን ነገሮች እንዳካትት መመርያ ቢጤ ሰጠኝ፡፡ ይህ በግል ጥቅም የታወረና ለሥራ ደንታ የሌለው አለቃዬ በእያንዳንዱ ዕቅድ መጨረሻ ላይ እንዲሰገሰጉ የፈለገው፣ ለእሱ ተጨማሪ ጥቅም የሚያስገኙ አልባሌ ነገሮችን ነው፡፡ አዕምሮው በሙስና የተተበተበ ስለሆነ ለድርጅቱ ውጤታማ ለሆኑ ተግባሮች ደንታም አይሰጠውም፡፡ በእሱ ድርጊት ሁሌም ውስጤ ስለሚበግን፣ ‹‹ከፈለግክ ራስህ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ዕቅዱን መሥራት ትችላለህ፡፡ አለበለዚያ ግን ሌብነትን የሚተባበር ርካሽ ተግባር ውስጥ አልገባም…›› አልኩት፡፡ ከመጠን በላይ ሲደነፋብኝ፣ ‹‹ሰውዬ ሥርዓት ይኑርህ፣ አሁንም የእንዳንተ ዓይነቱን ራስ ወዳድ ተልካሻ ዕቅድ አልሠራም…›› ብዬው ወደ ቤቴ ሄድኩ፡፡

በነጋታው ቢሮ ስገባ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢሮ ትፈለጋለህ ተባልኩ፡፡ እዚያ ስደርስ ዋና ሥራ አስኪያጁ ነብር ሆነው ጠበቁኝ፡፡ ‹‹ስማ አንተ እንዴት ብትጠግብ ነው አለቃህን የምትሳደበው?›› እያሉ ተውረገረጉብኝ፡፡ የሆነውን ሁሉ ዘርዝሬ ነገርኳቸው፡፡ እሳቸው ሙስናው ላይ ሳይሆን ትኩረታቸው፣ ‹‹አለቃህን ሰደብክ ነው የምልህ…›› እያሉ ፎከሩ፡፡ ውስጤ ተቆጥቶ ስለነበር፣ ‹‹ከዕቅዱ ጋር በተያያዘ ተጋጨን እንጂ አልተሳደብኩም፡፡ በዚህ ላይ ያጣላን ሥራ እንጂ የግል ጉዳይ አይደለም…›› አልኩኝ፡፡ አሁንም እየተንጎራደዱ፣ ‹‹ምስክር ተቆጥሮብሃል…›› አሉኝ፡፡ በጣም ገርሞኝ፣ ‹‹እነማን ናቸው?›› አልኩዋቸው፡፡ መጥሪያውን ተጭነው ጸሐፊዋን ‹‹አስገቢ…›› ሲሏት አለቃዬ ዘው ብሎ ገባ፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ሦስት ምስክሮች አሉ፡፡ አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ሁለተኛዋ ጸሐፊዬ ናት፡፡ ሦስተኛው ደግሞ እሱ አለቃህ ነው…›› ሲሉኝ በጣም ገረመኝ፡፡ ‹‹እርስዎና ጸሐፊዎ ባልነበራችሁበት ምን እንደምትመሰክሩ ይታያል፡፡ ነገር ግን እሱ እየከሰሰኝ ምስክር እንዴት ይሆናል?›› ስላቸው፣ ‹‹አይ ሞኞ ተበዳይ የመጀመሪያ ምስክር እንደሚሆን አታውቅም?›› እያሉ ሲፎክሩ፣ የአለቃዬና የሥራ አስኪያጁ ዝምድና ከአሁን በኋላ እንደማያስቀጥለኝ እያሰብኩ፣ ‹‹በሉ እንግዲህ መደበኛው ፍርድ ቤት እንገናኝ…›› ብያቸው ቢሮአቸውን ጥዬላቸው ወጣሁ፡፡ ወገኖቼ እኔ ይህንን ግላዊ ጉዳይ እንደ መነሻ ማሳያ እንዲሆን አቀረብኩ እንጂ፣ በየቦታው ብትሄዱ እንዲህ ዓይነቱ ነውር ነው የበዛው፡፡ አገራችን ከእንዲህ ዓይነቶቹ ነውረኞች ካልፀዳች በስተቀር ሀቀኞችና ትጉሃን እየተገፉ ሥርዓተ አልባነት እንደሚስፋፋ አልጠራጠርም፡፡ 

(ሳምሶን ሲርጋጋ፣ ከቦሌ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...