Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፕሪሚየር ሊግ ጉዞው

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፕሪሚየር ሊግ ጉዞው

ቀን:

የዓመቱን የጨዋታ መርሐ ግብር ሊያጠናቅቅ አራት ጨዋታ የቀረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት መሰባሰቡን ተከትሎ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

ዘንድሮ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ በ56 ነጥብ የሊጉን ደረጃ ሲመራ፣ አብሮት ያደጉት ዱራሜ ከተማ ደግሞ በስምንት ነጥብ በወራጅ ቀጣናው ከግርጌ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት 16 ቡድኖችን ይዞ በአክሲዮን የተደራጀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ንግድ ባንክ የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

- Advertisement -

ከቀሪው የጨዋታ መርሐ ግብርና በቀጣይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚዎች አንፃር፣ ከወዲሁ አሸናፊውን ቡድን መገመት አዳጋች ቢሆንም፣ በሊጉ ተደጋጋሚ ድሎችን በማስመዝገብ የሚታወቁት ቅዱስ ጊዮርጊስና ሌሎችም ቡድኖች ጨምሮ ከሚያሳዩት እንቅስቃሴና ወቅታዊ ብቃት አኳያ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሸናፊነቱን ቅድሚያ ግምት የሚሰጡ በርካታ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ሰለሞን በበኩላቸው፣ ቡድናቸው አሁን ላይ ሊጉ አራት የጨዋታ መርሐ ግብር እየቀረው ውድድሩን በበላይነት ሊያጠናቅቅ ነው በሚለው አይስማሙም፡፡ ነገር ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አመራሩ ከስፖርት ማኅበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ ኤቤ ሳኖ ጀምሮ በተዋረድ ቡድኑን ለማጠናከር እያደረጉለት ካለው ድጋፍና ክትትል አንፃር ውጤቱና ደረጃው ቢያንስበት እንጂ እንደማይበዛበት ያምናሉ፡፡

የሊጉን ጉዞ መነሻ በማድረግ በሊጉ ደረጃና ጥራት ላይ ግን አሁንም ጥያቄ የሚያነሱ አልጠፉም፡፡ ብዙዎቹ ክለቦች በተለይም በአሁኑ ወቅት ከበጀት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ የሚናገሩ አሉ፡፡

 በቅርቡ ሁለት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ማለትም የአዳማ ከተማና የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ቡድኖች የሆቴል ዕዳ ‹‹አልከፈላችሁም›› በሚል የተጨዋቾቻቸው አውቶቡሶች ሳይቀር የታገቱበትን አጋጣሚ በመጥቀስ፣ አንዳንዶቹ መርሐ ግብር ለማሟላት ካልሆነ አሁን ላይ ለጥራት ብዙም ትኩረት እየሰጡ አለመሆኑ ጭምር ይነገራል፡፡

ከዚህ አንፃር በፋይናንስ ረገድ ብዙም ችግር እንደሌለበት የሚነገርለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድሩ አሸናፊ ቢሆን ምን ይደንቃል? ለሚለው ጥያቄ አቶ አስናቀ፣ ‹‹እግር ኳስ ምን እንደሚፈልግ በቅጡ መረዳት የሚችል አመራር ካለ በሚነገረው ነገር አልስማማም፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዚህ ውጤት የበቃው እንደሚነገረው የገንዘብ አቅም ስላለው ብቻ ሳይሆን፣ አመራሩ ከላይ እስከታች እግር ኳሱ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ በመቻሉ ብቻ ነው፤›› ብለው ሌሎችም በዚህ ልክ ማቀድና መሥራት ከቻሉ እንደ አገር የሚፈለገውን የእግር ኳስ ዕድገት ዕውን ማድረግ እንደሚቻል ጭምር ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በፊት የአሸናፊነት ዕድሉን አግኝተው በአኅጉራዊ መድረክ አገር መወከል የቻሉ ቡድኖች ቢኖሩም በአብዛኛው ከአንድ ዙር ያለፈ ተሳትፎ ሳይኖራቸው ሲሰናበቱ መመልከት የተለመደ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ በለስ ቀንቶት አሸናፊ ቢሆን፣ በአኅጉራዊ መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቀጠል ይችል ዘንድ ምንድነው ዕቅዱ ለሚለው አቶ አስናቀ ሲመልሱ፣ ቡድኑ በትልቅ የፋይናንስ ተቋም የሚተዳደር እንደመሆኑ መጠን ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን፣ የድጋፍና የክትትሉ ዋና መነሻም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የበላይ ጠባቂውን ጨምሮ በተዋረድ ያሉ አመራሮች ክለቡ የሚያደርጋቸውን እያንዳንዱ ጨዋታ በሱፐር ስፖርት አማካይነት ስለሚከታተሉ፣ በድክመቱና በጥንካሬው ዙሪያ ገንቢና ሙያዊ የሆኑ አስተያቶች የሚሰጡበት አሠራር  በመኖሩ ለክለቡ ጥንካሬ ጥሩ ነገር እያበረከተ መሆኑንም ሥራ አስከያጁ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሊጉ በዲኤስቲቪ አማካይነት ቀጥታ ሥርጭት ማግኘቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ክለቦች በእያዳንዱ ጨዋታ ላይ የነበራቸው ደካማና ጠንካራ ጎን ምን እንደሆነ ለመለየት ዕድል ከማስገኘቱ ባለፈ በዳኝነት የሚታዩና መሰል ችግሮች ቢያጋጥማቸው፣ አቤቱታ ለማቅረብ አመች መሆኑን አቶ አስናቀ ያስረዳሉ፡፡

በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ምክንያት ፕሪሚየር ሊጉ አንዲቋረጥ ሲደረግ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ26 ጨዋታዎች 56 ነጥብ ይዞ ሲመራ. መቻል በ51፣ ባህር ዳር ከተማ በ45፣ ኢትዮጵያ ቡና በ44፣ የዓምናና የሃቻምናው አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ43፣ አዳማ ከተማ በ41፣ ፋሲል ከነማ በ40፣ ድሬዳዋ ከተማ በ37፣ ሐዋሳ ከተማ በጎል ክፍያ በልጦ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በእኩል 36፣ ኢትዮጵያ መድን በ34፣ ሲዳማ ቡና በ31፣ ወላይታ ድቻ በ29፣ ወልቂጤ ከተማ በ16፣ ሻሸመኔ ከተማ በ14 እና ሀምበሪቾ ዱራሜ በስምንት ነጥብ ተከታትለው ይገኛሉ፡፡

መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከባህር ዳር ከተማ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ከሻሸመኔ ከተማና ከኢትዮጵያ መድን ጋር በቀጣይ የሚያርጋቸው ጨዋታዎች ውጤቱ የዋንጫ ባለቤት ከማድረግ ባሻገር፣ በሚቀጥለው ዓመት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስሊግ አልያም በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽ ዋንጫ ተሳትፎውን የሚወስን ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...