Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየፓርላማ አባላት ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዜጎችን የሚያስለቅስ ተቋም ሆኗል አሉ

የፓርላማ አባላት ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዜጎችን የሚያስለቅስ ተቋም ሆኗል አሉ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ዜጎች የሚያለቅሱበትና በደላላ ምክንያት የሚጉላሉበት ተቋም ሆኗል ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ፡፡

ምክር ቤቱ ሐሙስ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው 29ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የኤምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ፣ ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡ በውይይቱ የምክር ቤት አባል የሆኑት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተገኝተው ነበር፡፡

በሁለቱም አዋጆች ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ አባላት መካከል አቶ አበረ አዳሙ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ተቋሙ ሕዝብ የሚያለቅስበት ተቋም ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ተቋሙን ለዚህ ሁሉ ችግር ያጋለጠውና በሕዝቡ ዘንድ እሮሮ የበዛበት፣ በሕግ ክፍተት ምክንያት ከሆነ ቋሚ ኮሚቴው እንዲመለከተው ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

- Advertisement -

በተመሳሳይ ሌላው የምክር ቤት አባል፣ ‹‹የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተቋም በደላላ ምክንያት ተገልጋዩ የሚንገላታበትና ለከፍተኛ ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ነው፤‹‹ ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን ሊያስቀር የሚችል አሠራር በረቂቅ አዋጁ ተካቶ እንዲመጣ ታሳቢ እንዲሆን፣ እንግልት ሊያስቀር የሚያስችልና ተገልጋዮች በቀጥታ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡

ከሶማሌ ክልል ተመርጠው የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ካሚል ሀሽ በበኩላቸው፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ዜጎች አገልግሎት ፍለጋ ሲሄዱ ዜጋ በመሆናቸው የሚኮሩበት እንጂ የሚሸማቀቁበት መሆን የለበትም የሚል አስተያየት አቅርበዋል፡፡

የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ አገልግሎት ጠያቂ ዜጎች ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ተቋሙ ሲሄዱ፣ ምርመራ (interrogation) የሚመስል ድርጊት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ዜጎች አገልግሎቱን ተከብረው ሊያገኙ እንደሚገባና ለዚህም አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

‹‹ትናንት ከሰዓት በኋላ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እኔም ለአገልግሎት በሄድኩበት ወቅት አገልግሎት አንሰጥም ውጡ ተብለናል፡፡ ሕፃን ልጅ የያዙ እናቶች እንኳን ቅድሚያ እንደማይሰጣቸው ተመልክቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን ችግር በመረዳት ለተቋሙ የበላለይ ኃላፊዎች ስለተመለከቱት ‹‹ምግባረ ብልሹ›› አሠራር በስልክ መልዕክት መላካቸውን፣ ነገር ግን ከኃላፊዎች ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ ማንም ዜጋ የሚከበርበት እንጂ የሚያፍርበት መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

አቶ ካሚል አክለውም ከሶማሌ፣ ከትግራይ፣ ከአፋርና ከሌሎች ድንበር አካባቢ የሚመጡ ዜጎች ፓስፖርት ለመውሰድ ኢትዮጵዊነታቸውን ለማጣራት የሚደረገው ሒደት አካሄዱ ጫን ያለ ነው ብለዋል፡፡

ለውይይት የቀረበውና ወቅቱን ያገናዘቡ ለውጦች ተካትተውበታል የተባለለት የኢሚግሬሽና ዜግነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም ባወጣው አዋጅ ላይ እንደተብራራው፣ ተቋሙ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በሰዎች የመነገድ ወንጀል ድርጊት፣ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትንና የመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል እንደሚያስችለው ተገልጿል፡፡

በረቂቅ ማቋቋሚያ አዋጁ አገልግሎቱ ለሥራው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ሥልጣኑንና ተግባሩን አግባብነት ላላቸው ለፌዴራልና ለክልል አካላት በውክልና ሊሰጥ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

በረቂቅ ማቋቋሚያ አዋጁ እንደተገለጸው በርካታ ኢትየጵያውያን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓና ደቡብ አፍሪካ እየፈለሱ መሆናቸውንና አብዛኞቹ የጉዞ ሰነድ የሌላቸው ወይም በደላሎች በተጭበረበረ ሰነድ የሚወጡ ናቸው፡፡

ዜጎች የሚሰደዱበት አገር ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በውል የማያውቁ በመሆናቸውና የሚጠበቅባቸውን በውል ስለማይረዱ፣ በሕገወጥ ደላሎች ከአገር እንዳይወጡ ከሄዱም በኋላ በደል ሳይደርስባቸው የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ የማመቻቸት ኃላፊነት በረቂቅ አዋጁ ተሰጥቶታል፡፡

በተመሳሳይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 354/95 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ አንድ ግለሰብ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በሕግ መሠረት በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ቢሆንም፣ በተግባር ከፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ እስኪገኝ ድረስ በብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ወይም ሊያደርሱ የሚችሉ ሰዎች ከአገር እየወጡ ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም መሰል ተግባራት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ በመሆናቸው፣ ይህንን ችግር በመቅረፍ በተለየ ሁኔታ በብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ በሚኖርበት ወቅት፣ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ማንኛውም ሰው ከአገር እንዳይወጣ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡

ዳይሬክተሩ ከሚመለከታቸው የመረጃ አገልግሎትና የሕግ አስከባሪ ከአካላት ከሚያገኘው መረጃ ወይም አገልግሎቱ በራሱ ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት፣ ማንኛውም ሰው ከአገር እንዳይወጣ ማገድ እንዲቻል የተፈቀደለት ሲሆን፣ ያላግባብ የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት እንዳይገድብ በፍርድ ቤት እንዲፀድቅ የሚያስገድድ ድንጋጌ ስለመቀመጡ ተገልጿል፡፡

በረቂቁ ላይ አንድ መንገደኛ አጓጓዥ መንገደኛውን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ወይም ከአገር ለማስወጣት ከማጓጓዙ በፊት፣ የመንገደኛውን ቅድመ ጉዞ መረጃና ስም ዝርዝር ለአገልግሎቱ ከሦስት ሰዓት ቀድሞ እንዲያሳውቅ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች እየተበራከቱ በመሆናቸውና በሕገወጥ ድርጊቶች እየተሳተፉ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ስለሆነ፣ በአስተዳደራዊ ቅጣት ከሕገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ በረቂቁ ተገልጿል፡፡ ይህም በጥቁር መዝገብ በማሥፈር ከአገር እንዳይወጡና ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲገቡ ማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚወሰድ ተደንግጓል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...