Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ የመጨረሻ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የሃይማኖት ተቋማት ቅሬታ...

በሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ የመጨረሻ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የሃይማኖት ተቋማት ቅሬታ አቀረቡ

ቀን:

  • ከውጭ አገር የሚገኝን የገንዘብ ዕርዳታ ማሳወቅአዋጁ እንዲወጣ ተደረገ

የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት በተካሄደ የመጨረሻ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የተገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡

ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሃይማኖት መሪዎች፣ ጉዳዩን የሚመለከት ቡድን ማቋቋማቸውን ገልጸው፣ የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ቀድሞ ስላልተሰጣቸው በዝርዝር ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት መብትና ክብር የሚጠብቅ መሆኑ ማረጋገጥ እንደሚገባ ያስታወቁት የሃይማኖት መሪዎቹ፣ በአብዛኛው ተከብሮ የቆየው የሃይማኖቶች ነፃነት ላይ ገደቦችን እንዳይጥል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ከዚህ በፊት ለውይይት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ይነሱ የነበሩ መሠረታዊ ጥያቄዎች በመጨረሻው የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይም ተንፀባርቀዋል፡፡ ሃይማኖታዊ ተግባራትን በሚከለክለው የረቂቅ አዋጁ ክፍል ላይ፣ በአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናሎች መፈጸም የተከለከለ ነው በሚል የቀረበው ሊስተካከል እንደሚገባ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን በመወከል የተገኙ ተሳታፊዎች ገልጸው፣ ሦላት የደረሰበት ሙስሊም በአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናሎች እንዳይሰግድ መከልከል እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

አክለውም በከተሞች ለአምልኮና መቃብር የሚሰጥ ቦታ የከተማውን የዕድገትና የልማት ዕቅድ ወይም ማስተር ፕላን የማይቃረን መሆን እንዳለበት በረቂቁ ቢገለጽም፣ ይህ ወደ ተግባራዊነቱ ሲገባ አስቸጋሪ እንደሚሆንና መጀመሪያ የተገነባ ቤተ እምነት ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር የሚቃረን ነው በሚል እንዳይፈርስ ዋስትና የማይሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመንግሥት ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞች ሁሉ እምነት እንዳላቸው፣ ለአብነትም አንድ ሙስሊም በመንግሥት ተቋም ተቀጥሮ ሲሠራ ሶላቱን በሚሰግድበት ወቅት፣ በተቋሙ ውስጥ ሃይማኖታዊ ክንውን አድርጓል ሊባል መሆኑንና ረቂቅ አዋጁ ይህን እንዴት ማስታረቅ እንደሚችል ጥያቄ አስነስቷል፡፡

በግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ ላይ የተገኙ የወንጌል አማኞች ካውንስል ተወካይ በበኩላቸው፣ ረቂቅ አዋጁ በወንጌላውያን ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹በተለይም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ የሚከለክሉ የረቂቁ ክፍሎች፣ ወንጌል መስበክ መሠረታዊ አስተምሯችን ለሆነው ለወንጌላውያን ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህም መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም በሚል የተቀመጠውን መርህ የጣሰ እንዳይሆን ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በረቂቁ ላይ የተቀመጡ የቃላት ትርጉሞች ላይ ጥያቄያቸውን ያነሱት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተወክለው በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ በተለይም የአደባባይ በዓላትን በሚመለከት ‹‹የአደባባይ ኩነት›› ተብሎ የተቀመጠው ትክክለኛ ትርጉም አይደለም ብለዋል፡፡

ለዚህ በማሳያነት ያስቀመጡት ‹‹የአደባባይ ኩነት በተፈቀደው ቦታ ብቻ መደረግ አለበት›› በሚል በረቂቁ ላይ የተቀመጠውን ሲሆን፣ ለአብነትም የጥምቀት በዓል የአደባባይ ሃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም፣ ከተፈቀደለት አደባባይ ውጪ መንገዶች ላይ  መካሄድ አይፈቀድም የሚል ትርጓሜ እንዳይሰጠው ያሠጋል ብለዋል፡፡ 

በተጨማሪም ‹‹የሃይማኖት ተቋም የሚይዘው ስያሜ፣ ዓርማ ወይም ምልክት ቀድሞ ከተቋቋመ ተቋም ስም፣ ዓርማ ወይም ምልክት ጋር ተመሳሳይ መሆን የለበትም›› በሚል በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው፣ ‹‹በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ መሆን የለበትም›› በሚል ሊስተካከል እንደሚገባና ለዚህ ምክንያታቸውም፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ስያሜ የኢትዮጵያ የሚለውን ብቻ በማውጣትና የራሳቸውን በመተካት አገልግሎት ላይ ሲያውሉ የሚታዩ አካላትን ስለተመለከትን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

አክለውም በሃይማኖት ተቋማት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሃይማኖት ሕጎች እንደ አስገዳጅ ሕግ ሆነው በመደበኛ ፍርድ ቤት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንደሚገባ፣ ምክንያቱም ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የሚዳኙት በሃይማኖታዊ ሕግ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተውና ተሻሽሎ ለውይይት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ መጠነኛ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ በመጀመሪያው ረቂቅ ላይ ያልነበረና የመንግሥትንና የክልሎችን ግዴታና ኃላፊነት በመዘርዘር የተቀመጠው ክፍል አንዱ ሲሆን፣ በዚህ የረቂቁ ክፍል መንግሥት በሃይማኖት አስተምህሮና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይችል ተደንግጓል፡፡

በተጨማሪም ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ከውጭ አገር የሚላክለትን የገንዘብ ዕርዳታ፣ ስጦታ ወይም ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችን በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ እንደሚኖርበት ተደንግጎ የነበረው የረቂቅ አዋጁ ክፍል ከተሻሻለው ረቂቅ ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የሃይማኖት ተቋሙን ኦዲት ሪፖርት ለሰላም ሚኒስቴር እንዲያቀርብ፣ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በሦስት ወራት ውስጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በገለልተኛ ኦዲተር ማስመርመር እንደሚኖርበት የተቀመጠው የረቂቁ ክፍል በተሻሻለው ላይ ተካቷል፡፡

ለውይይት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የተሻሻለው ሌላኛው የረቂቁ ክፍል፣ አለባበስንና የተማሪዎች አመጋገብን ጨምሮ በማንኛውም የትምህርት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚደረግ ሃይማኖታዊ ተግባር፣ የመንግሥትና ሃይማኖት መለያየት መርህንና የሃይማኖት ነፃነትን በጠበቀ መንገድ መከናወን አለበት የሚለው ነው፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው ረቂቅ አዋጅ ላይ ይህ ክፍል ሃይማታዊ አለባበሶች ማንነትን ለመለየት በሚያስችል መንገድ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይገባል በሚል ተመላክቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙ የሰላም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ የመጨረሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል ያለው ልዩነት ምን ድረስ እንደሆነ ሳይታወቅ ቆይቷል ያሉት ኃላፊዎቹ፣ አዋጁን ማዘጋጀት ያስፈለገውም ይህን በግልጽ ለማስቀመጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አክለውም መንግሥት በሃይማኖት ተቋማት ነፃነት ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው፣ ነገር ግን አብረው በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ በሕግ የተቀመጠ አሠራር ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በመድረኩ የተነሱ ሐሳቦችን በግብዓትነት ወስዶ ለሚመለከተው አካል የሚቀርበውን ረቂቅ አዋጅ እንደሚያዘጋጅ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...