Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኢኮኖሚው ከሰሜኑ ጦርነት በፊት የነበረውን ቁመና እንዲያገኝ አራት ዓመታት እንደሚያስፈልጉ በጥናት ተመላከተ

ኢኮኖሚው ከሰሜኑ ጦርነት በፊት የነበረውን ቁመና እንዲያገኝ አራት ዓመታት እንደሚያስፈልጉ በጥናት ተመላከተ

ቀን:

እ.ኤ.አ. በ2020 በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት በፊት ወደ ነበረው የኢኮኖሚ ቁመና ለመመለስ መጠነኛ ጥረቶች ከተደረጉ፣ ቢያንስ አራት ዓመታት እንደሚያስፈልጉ በአንድ ጥናት ተመላከተ።

‹‹በግጭት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን ኑሮ መልሶ መገንባታ›› በሚል ርዕስ ሐሙስ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደ የጥናትና ፖሊሲ ኮንፈረንስ፣ ዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት (International Food Policy Institute) ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ግጭቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያስከተሉት ተፅዕኖ (Economic Impact of Recent Conflict in Ethiopian) በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን ጥናት አቅርቧል።

ኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት ካስከተለው የኢኮኖሚ ችግር ለመውጣት መጠነኛ እንቅስቃሴዎችን የምታደርግ ከሆነ፣ አራት ዓመታትን እንደሚፈጅባት በጥናቱ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን የተፋጠኑ የማገገሚያ መንገዶችን የምትጠቀም ከሆነ ኢኮኖሚው በቀጣዩ ዓመት መሻሻሎችን ሊያሳይ እንደሚችል ጥናቱ ጠቁሟል።

- Advertisement -

በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ክልሎች ተፈጥረው የነበሩና አሁንም ድረስ የቀጠሉት ግጭቶች፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ ተፅዕኗቸውን እንዳሳደሩ ጥናቱ ገልጾ፣ ለዚህ ማሳያም በፋብሪካዎች፣ በመንገዶችና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የደረሰውን ውድመት በማሳያነት ያቀርባል። ግጭቶች በመንግሥት ወጪዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየታቸውንና የሰሜኑ ጦርነት በተጀመረበት ዓመት ጭማሪው 31 በመቶ መድረሱን አመላክቷል። 

ጥናቱ የደረሰውን ውድመት ለመለካት፣ ‹‹ግጭቶቹ ያስከተሉት ቀጥተኛ ውድመትና ከውድመቱ ጋር የተገናኙ ተያያዥ ኪሳራዎች›› በማለት በሁለት ሁኔታዎች አስቀምጧል። በዚህም የአገሪቱ ጠቅላላ ምርት የሰሜኑ ጦርነት ባስከተለው ቀጥተኛ ውድመት ምክንያት ወደ 7.5 በመቶ ዝቅ ማለቱን፣ በቀጥታ ያስከተለው ውድመትና ከውድመቱ ጋር በተገናኙ ተያያዥ ኪሳራዎች ምክንያት ጠቅላላ ምርቱ ወደ 12 በመቶ ዝቅ እንዳለ ይገልጻል።

በተመሳሳይ የግለሰቦች የመግዛት አቅም ጦርነቱ ተከስቶ በነበረበት ዓመት ወደ 8.3 በመቶ ዝቅ ማለቱን ያስረዳል፡፡ ከችግሮቹ ለመውጣትም የኢኮኖሚውን ሁኔታ ያገናዘበ ኢንቨስትመንት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ያብራራል፡፡ የተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠርና ለግጭቶች መከሰት ዋነኛ ምክንያቶችን በመለየት ለጥናቶችና ለፖሊሲዎች ግብረ መልሶች ቀዳሚ አጀንዳዎች ሊሆኑ እንደሚገባ በጥናቱ ተጠቁሟል። 

ከዚህ ጋር ተያይዞ የትጥቅ ግጭት፣ የመሬት ይዞታ ዋስትናና ከመሬት ጋር የተያያዙ ኢንቨስትመንቶች (Armed Conflict, Tenure Security and Land Related Investments) በሚል ርዕስ በመድረኩ በቀረበው ሌላው ጥናት ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በመሬት ይዞታቸው ላይ ደኅንነት እንደማይሰማቸው ተገልጿል።

ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ያለው የመሬት ይዞታ ባለቤትነትና ዘለቄታ ባለው ከመሬት ጋር የተያያዘ ኢንቨስትመንት ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገው ጥናቱ፣ በግጭት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ከመሬት ጋር ለተያያዙ አለመግባባቶች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑንና የስርቆት ዕድሉም ከፍ ያለ መሆኑን አመላክቷል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ያሉትን የመሬት ማረጋገጫ ፕሮግራሞች ማጠናከር፣ የአርሶ አደሮችን እምነት መጨመርና ከመሬት ነክ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩትን ግጭቶች መፍታት የሚሉ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል።

በመድረኩ ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮችና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ተገኝተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ  በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች በግብርናው ዘርፍ ውድመት እያስከተሉ መሆናቸውንና እነሱም የአገር ውስጥ ፍልሰትና የምግብ ዋስትና አለመኖር እንደሆኑ ገልጸው፣ ኢኮኖሚውን ወደ አለመረጋጋት እየመራው ነው ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታትም ዘላቂነት ያላቸው አስቸኳይ ድጋፎችንና የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንትን ጎን ለጎን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...