Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሒደት ለአገራዊ ምክክር ስኬታማነት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተባለ

የምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሒደት ለአገራዊ ምክክር ስኬታማነት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተባለ

ቀን:

በአዲስ አበባ የተጀመረው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት፣ ወደፊት ለሚከናወነው አገራዊ ምክክር ስኬታማነት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ የከተማ አስተዳደርና ክልላዊ የምክክር ምዕራፉን ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በጀመረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ዋና ኮሚሽነሩ መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ በመመካከር ወደ መግባባት መድረስ አማራጭ የሌለው ብቸኛ አገራዊ መፍትሔ መሆኑን፣ ወደፊት ለሚከናወነው አገራዊ የምክክር ጉባዔ ስኬታማነትም ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

‹‹በሚገባ የሚተዋወቁ ሕዝቦች ይከባበራሉ፣ ይተሳሰባሉ፣ እርስ በርሳቸው በእኩልነት ይተያያሉ። ማንኛውም ችግር የሚፈታው በሐሳብ ልዕልና መሆኑን ተረድተው የጉልበት ወይም የማስገደድ መፍትሔ ጊዜያዊ መሆኑን በመገንዘብ፣ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን ምክክር በመርህ ደረጃ ይይዛሉ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የምክክር ምዕራፉ እሑድ ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. አምስተኛ ቀኑን ሲያስቆጥር፣ በመድረኩ የሚሳተፉ ሰዎች የተመረጡበት መንገድ ከወረዳ ጀምሮ በክልል በሚገኙ ተቋማትና ማኅበራት በተላከ ደብዳቤ መሠረት የተወከሉ ናቸው ሲሉ ኮሚሽነር አምባዬ ኦርጋቶ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የተመረጡት ሰዎች በኮሚሽኑ የተመረጡ ሳይሆን፣ በየክልሉና በከተማ ውስጥ በተካሄደ የኅብረተሰብ ውይይት ወቅት ከአሥር የተለያዩ መደቦች (Categories) ውስጥ የተካተቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ሴቶች፣ መምህራን፣ የዕድር፣ የንግድ ማኅበረሰብ፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የግል ተቋማት፣ የተገለሉ የማኅበረሰብ ተቋማትና ሌሎችም ናቸው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ 22 የተለያዩ መደቦች ያሏቸው ባለድርሻ አካላት ማለትም የሃይማኖት ተቋማት፣ የክልልና አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ይገኙበታል በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹እነዚህ አካላት በቡድን ውይይት በማድረግ የየራሳቸውን ጥያቄ በአጀንዳ በማሰባሰብ እንደ አገር የማንግባባቸው ጉዳዮች የሚባሉትን በመለየት፣ ለመፍትሔ የሚረዱ ጥያቄዎችን በመያዝ በሚስጥር በተመረጡ ተወካዮች በሚካሄደው ምክክር ያቀርባሉ፤›› በማለት ኮሚሽነር አምባዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም ሁሉም ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት፣ መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳዎቻቸውን ከተው እንደሚወያዩ፣ በሚቀርቡት አጀንዳ ሐሳቦች መመሳሰል ቢኖርም የሚዘለል ወይም የሚደፈጠጥ አጀንዳ አይኖርም ብለዋል፡፡

አንድ ላይ መሰብሰብ የማይችል ልዩነት ያለው አጀንዳ ካለ አንዱ ቡድን የሌላውን ቡድን አጀንዳ ማሳነስ ሳይኖር በልዩነት ይቀመጣል ተብሏል፡፡

በውይይቱ ማብቂያ ቡድኑን በመወከል የአጀንዳ ግብዓቶችን ከሌሎች ግቦች ጋር አብረው የሚያደራጁ ከሁሉም ቡድን የተውጣጡ 25 ሰዎች በመምረጥ፣ የተመረጡትም የጋራ ጉባዔ በመሰየም የተጠቃለለ አጀንዳ ለማደራጀት አስቸኳይ፣ አስፈላጊ፣ ከፍተኛ ውክልና ያላቸው የሚሉትን ለመለየት ይሠራሉ ብለዋል፡፡

‹‹ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወክለው የተገኙ ተስፋዎችንና ሥጋትን በመደማመጥ ተመካክረው የጋራ ዓውድ በሚያደርግ ሒደት የጋራ እውነቶች ምን እንደሆኑና መፍትሔዎች ይለያሉ፤›› ሲሉ ኮሚሽነር አምባዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ማንም ሰው ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ፣ እርስ በርስ መከባበር፣ ሰብዓዊ ክብርን አለመጣስ፣ ከጥላቻና ከንግግር መቆጠብ፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም የምክክር መርሆች መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ አጎ ናቸው፡፡

በሰነዱ ላይ ቅር የተሰኘ ወገን ቅሬታውን አሟልቶ በሚያቀርብበት ጊዜ ከፈለገ ማንነቱን ባይገልጽ ችግር እንደማይኖረው አስረድተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ከ2,500 በላይ ተሳታፊዎች በመክፈቻ መድረኩ ተካፋይ ሆነዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...