Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮንስትራክሽን ጥሬ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለመደገፍ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ሊያዘጋጅ መሆኑን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ‹‹ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ›› የተሰኘ ድርጅት፣ ከግንቦት 22 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚቆይ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዓውደ ርዕይና ሲምፖዚየም ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያን እንገንባ!›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ዓውደ ርዕይ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ፈጠራን በማጎልበት የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑንና በአገር ውስጥ ያለው ጥቅል ምርት 21 በመቶ ድርሻ መያዙን የገለጹት አቶ ተመስገን፣ በ2014 ዓ.ም. ዘርፉ የሚያንቀሳቅሰው 54.8 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች ያለች አገር እንደሆነችና በ2009 ዓ.ም. ለግሉ ዘርፍ ከነበረው የብድር አቅርቦት 41.5 በመቶ ድርሻ፣ በአሁኑ ጊዜ 62 በመቶ መድረሱን አክለው ገልጸዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ በቀጣይ አራት ዓመታት በየዓመቱ ስምንት በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ መንግሥት ዘርፉን በማዘመን ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለመሳብ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመንገድ መሠረተ ልማት ባለፉት ዓመታት ከነበረበት 166 ሺሕ ኪሎ ሜትር ወደ 256 ሺሕ ኪሎ ሜትር ማደጉን ጠቅሰው፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተወሰዱ የማሻሻያ ዕርምጃዎች አማካይነት የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡ 

በተለይ በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ መሠረት የመንገድ፣ የባቡር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፣ መንግሥት ለአገር ውስጥ የዘርፉ ተዋናዮች ዕድሎችን በመፍጠር አመርቂ ውጤት ማምጣት ተችሏል ብለዋል፡፡

መንግሥት ዘርፉን ለመደገፍ ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ የኢንቨስትመንት ሕጎችን ለማውጣት በሒደት ላይ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቢግ 5 ኮንስትራክት ሲምፖዚየም ከሚካሄድባቸው የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ ትልቅ ዕመርታ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ ከ24 አገሮች የተውጣጡ 115 የዓለም አቀፍና ከ41 በላይ የአገር ውስጥ የዘርፉ ተዋናዮች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ብልፅግና ላይ ለመድረስ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሀብት የሚንቀሳቀስበትና በርካታ ባለድርሻ አካላት በአንድ ጊዜ በማሳተፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሳደግ የሚቻልበት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ሲምፖዚየሙም በዋናነት የተዘጋጀበት ምክንያት የዘርፉ ተዋናዮችን እርስ በርስ በማስተዋወቅ አብሮ የመሥራት ባህል ለማዳር ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በግንባታው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታትና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ፣ እንዲሁም የዘርፉ ተዋናዮች ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ለማግኘት እንዲረዳቸው ሲምፖዚየሙ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ አስረድተዋል፡፡

ዓለም የደረሰበትን የግንባታ ቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር በዘርፉ የአቅም ግንባታን ማሳደግ ይቻላል ያሉት ሚኒስትሯ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለኢንዱስትሪ ቱሪዝም መስፋፋት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ 80 በመቶ የግንባታ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ማቅረብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ጠቅሰው፣ በዘንድሮ የቢግ 5 ኮንስትራክት ባዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተዋንያን እንደተሳተፉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች