Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድና መረጃ ማዕከል ለመፍጠር የተጀመረው የኢንዱስትሪዎች ቆጠራ በመስከረም ወር እንደሚጠናቀቅ ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር አቀፍ ደረጃ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ያሉ የኢንዱስትሪ ተቋማት፣ የራሳቸው የንግድ መረጃ ማዕከል ኖሯቸው በምርትና በግብዓት ትስስር እንዲፈጥሩ ለማድረግ የተጀመረው ቆጠራ፣ በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢንዱስትሪዎች ቆጠራ በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አማካይነት እየተደረገ መሆኑንና በ2016 ዓ.ም. ሚያዝያ ወር ውስጥ ለሙከራ ያህል በደብረ ብርሃን፣ በወላይታ ሶዶ፣ በአምቦና በአዳማ አካባቢዎች ቆጠራ መካሄዱን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ዓባይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር በመረጃ ከመያዝ ባለፈ መንግሥት ዘርፉ ላይ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ሲያወጣ፣ ተጨባጭ ውጤት ለማስገኘት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ እያንዳንዱ አምራች ኢንዱስትሪ በምን ዓይነት ዘርፍ ውስጥ እንደተሰማራ፣ እየተጠቀመ ያለው ቴክኖሎጂ ምን እንደሚመስልና ምን ዓይነት ምርቶችን ኤክስፖርት ያደደርጋል የሚለውን ጨምሮ ወደ አሥራ ስድስት የሚጠጉ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን በማጠናከር ቆጠራው የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ 22 ሺሕ ያህል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚታሰብ፣ አራት ሺሕ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በፕሮጀክት መያዙን ጠቁመዋል፡፡

ስለኢንዱስትሪዎቹ እስካሁን የጠራ መረጃ እንደሌለ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ የንግድ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ አማካይነት ከስታትስቲክስ አገልግሎት ጋር በመሆን እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ልማት ማቋቋሚያ ጋር አብሮ በወጣው ደንብ መሠረት በአገር ደረጃ የመካከለኛ፣ የአነስተኛና የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች አደረጃጀት በካፒታልና በሰው ኃይል ደረጃ ምን ማሟላት አለበት የሚለውን ለማጣራት ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አምራች ኢንተርፕራይዞች ቁጥራቸው በውል ካለመታወቁ ባሻገር የት ይገኛሉ? ምን ያመርታሉ? የማምረት አቅማቸው ምን ያህል ነው? የሚንቀሳቀሱበት የገንዘብ መጠንና የሠራተኞች ብዛት ምን ያህል ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ዝርዝር መረጃ አለመኖረን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዋና ዳሬክተር አለባቸው ንጉሤ (ዶ/ር) ተናግረው ነበር፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከስታትስቲክስ አገልግሎት ጋር እየተሠራ እንደነበር ገልጸው፣ የአምራች የኢንተርፕራይዞችን ዝርዝር መረጃ ለመለየት በስታትስቲክስ አገልግሎት አማካይነት ከ40 በላይ የሚሆኑ መጠይቆች መዘጋጀታቸውን ማስረዳታቸው አይዘነጋም፡፡

የኢንተርፕራይዞች ቆጠራ ሲጀመር የማሽነሪና የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅቶች፣ እንዲሁም በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማሩ አምራቾች የጥራት ደረጃና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ለመለየት የሚያስችል አሠራር እንደሚፈጠር ገልጸው ነበር፡፡       

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች