Saturday, June 22, 2024

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መታረቅ ታላቅ የዜና ርዕስ በነበረበት በዚያ ወቅት ዛሬ የተፈጠረውን ማሰብ ለብዙዎች ከባድ ይመስል ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በአስመራ ጎዳናዎች “ኢሱ… ኢሱ…” “ዓብይ… ዓብይ…” እያሉ የሁለቱ አገር ሕዝቦች ዕንባ እየተራጩ መሪዎቻቸውን በዕልልታና በደስታ ሲያጅቡ የታየበት የለውጥ ወቅት፣ ትዝታ ሆኖ እንደሚቀር ብዙዎች አልገመቱም፡፡ በኢትዮጵያ ከመጣው የፖለቲካ ለውጥ ጋር አብሮ የመጣው የኢትዮጵያና የኤርትራ የ20 ዓመታት ጠብና ቁርሾ ረግቦ የመታረቅ ዜና፣ ከሁሉም በገዘፈ ሁኔታ በቀጣናውም በዓለም አቀፍ ደረጃም ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
‹‹ብርጌድ ንሓመዱ›› በመባል የሚታወቀው የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ ሰሞኑን በሚሊኒየም አዳራሽ ያደረገው ስብሰባ
ተሳታፊዎች

ይሁን እንጂ ያ የሁለቱ አገሮች ዕርቅ የፈጠረው ደስታና ሀሴት የትግራይ ጦርነት ሲጀምር ጣዕሙና ለዛው መቀየር ጀመረ፡፡ ጦርነቱን ተከትሎ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ግንኙነት ሲቀንስ ታየ፡፡ ዓብይና ኢሳያስ አብረው መታየት ተው፡፡ በሒደት በሁለቱ መንግሥታት መካከል አለመተማመን ስለመፈጠሩ በሰፊው ይዘገብ ጀመር፡፡ የጦርነቱ ይዘትና አካሄድ ተለዋዋጭነት ብዙ ነገሮችን በሁለቱ ግንኙነት መካከል ስለመለወጡ ግምቶች ይወጡ ጀመር፡፡ ከሁለት ዓመታት የሦስት ዙር ጦርነት በኋላ የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቋጨበት መንገድ ደግሞ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በሌላ መንገድ እንደሚፈትነው ሲገመት ነበር፡፡

እንደተገመተውም ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ወዲህ በነበረው አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት መሻከሩን የሚጠቁሙ ብዙ ምልክቶች መታየት ቀጥለዋል፡፡ በአማራ ክልል ከፋኖ ኃይሎች ጋር የሚካሄደው አንድ ዓመት ያስቆጠረው ውጊያ የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት የኃይል አሠላለፍ የለወጠ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ያልተገመተ የባህር በር ፍላጎትና ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት፣ ሌላው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት መላላት ማሳያ ተደርጎ ይታያል፡፡ ኤርትራ በኢትዮጵያ የባህር በር ፖሊሲ ምክንያት ሥጋት አድሮባታል መባሉ ይህንኑ ይጠቁማል፡፡

ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸው መሻከሩን ቀርቶ መቀዛቀዙንም የሚያሳዩ ፍንጮችን በይፋ ለማሳየት ሲቸኩሉ አልታየም፡፡ በአሽሙርና አጋጠሚን ተገን በማድረግ የፖለቲከኞች የቃላት ውርወራ እዚህም እዚያም ሲደረግ ቢቆይም፣ ነገር ግን ሲገመት የቆየውን ነገር ተጨባጭ የሚያደርጉ ይፋዊ ዕርምጃዎች ሲወስዱ ብዙም አልተስተዋለም፡፡ ይህ ግን ብዙም አልዘለቀም፡፡ በዕርቁ ሰሞን ኢሱ (ወዲ አፎም) ከዓብይ ጎን ቆመው ከረዥም ጊዜ በኋላ በአማርኛ ለመጀመሪያ ጊዜ በተናገሩበት በሚሊኒየም አዳራሽ ‹‹ብርጌድ ንሓመዱ›› የተባለው የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይል የኤርትራን መንግሥት የመታገያ ስብሰባ ከሰሞኑ ሲያደርግ ግን ብዙ ነገር ግልጽ ሆኖ መታየት ጀመረ፡፡ ከሰሞኑ ኢሳያስ አፈወርቂ በ33ኛው የኤርትራ ነፃነት በዓል ላይ ያሰሙት ዲስኩርም ቢሆን ያነጣጠረው በኢትዮጵያ ላይ እንደሆነ ብዙዎችን ያግባባ ጉዳይ ነበር የሆነው፡፡

ለ20 ዓመታት ተጣልተው ለስድስት ዓመታት መልሰው የታረቁት ኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታቱ በግልጽ ይፋ ባያደርጉትም፣ እያንፀባረቋቸው ካሉ አቋሞች አንፃር ዳግም ወደ አለመግባባት ማምራታቸው እየታየ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ተባብሶ ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚለው በርካቶችን አሥግቷል፡፡ ወደ ጦርነት ካመሩ በቀጣናው ምን ዓይነት ቀውስ ይፈጠራል የሚለውና ተያያዥ ጥያቄዎች አሁን መልስ የማፈላለጊያ ጊዜያቸው የደረሰ ነው የሚመስለው፡፡

ከሰሞኑ የኤርትራ ባለሥልጣናት የሳይበር ጥቃት በአገራቸው ላይ መፈጸሙን ሲናገሩ ነበር፡፡ የሳይበር ጥቃቱ በኤርትራ መረጃ መረብ ሥርዓት ላይ ስለመሞከሩና በባለሙያዎች ስለመምከኑ ተናግረዋል፡፡ የሳይበር ጥቃቱ የነፃነት ቀን በተከበረበት ዕለት መሞከሩን ያመኑት ባለሥልጣናቱ፣ ‹‹ከየት ሊመጣ እንደሚችል የኤርትራ ሕዝብ ያውቀዋል›› ሲሉ ነበር በሆድ ይፍጀው ስሜት ያለፉት፡፡

ስለሳይበር ጥቃቱ መነሻ እንዲህ ነው አይደለም ለማለት እንደሚቸገር የገለጸው ኤርትራዊው ጋዜጠኛ ሰናይ ገብረ መድኅን፣ ነገር ግን ኤርትራዊያን ወጣቶችና ምሁራን በኤርትራ ለውጥ ለማምጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክረው የተዘጋጁበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻል፡፡ እነዚህ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኤርትራዊያን ደግሞ በማንኛውም የትግል መንገድ በኤርትራ ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ተጠናክረው የተደራጁበት ወቅት መሆኑን ይገልጻል፡፡ ‹‹ብርጌድ ንሓመዱ›› ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የተበተነው ኤርትራዊ ለውጥ ፈላጊ ኃይል በሳይበር ጥቃት ጨምሮ በትጥቅ ትግል ለውጥ ለማምጣት መታገል መጀመሩን የሚናገረው ጋዜጠኛው፣ የሰሞኑ ጥቃትም የዚያ አካል ሊሆን እንደሚችል ይገምታል፡፡

ዲፕሎማሲና ፖለቲካዊ ሥልቶችን የተከተለ ግንኙነትን የማቋረጥ ዕርምጃ ሁለቱ አገሮች ሲወስዱ አለማየቱንና አሁንም ቢሆን የአየር በረራና የስልክ ግንኙነቱ መቀጠሉን የሚናገረው ጋዜጠኛው፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያ የተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ አሠላለፍ ለግንኙነቱ መላላት መነሻ ሆኗል ብሎ እንደሚያምን ያስረዳል፡፡

‹‹የኢሳያስ አገዛዝ በየጊዜው ከሚፈጠር ሁኔታ ጋር ራስን በመለዋወጥ የፖለቲካ ፍላጎትን የማስጠበቅ አካሄድ የኖረበት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለኳታር፣ ለሳዑዲ ዓረቢያ፣ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እያለ ከጊዜው ጋር እየተገለባበጠ ነው የመጣው፡፡ ከዚህ ቀደም በኤርትራ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ይይዝ የነበረበት ሁኔታ ይታወቃል፡፡ በሒደት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ፍቅር ካልሆንኩ አለ፡፡ ከባድመ ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚታገሉ የነፍጥ ኃይሎችን ሲደግፍና ሲያስጠልል ቆየ፡፡ ዕርቁን ተከትሎ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ልዩ ግንኙነት ፈጠረ፡፡ አሁንም ደግሞ ተመልሶ የኢትዮጵያ መንግሥት በሥጋትነት የሚያነሳቸው ኃይሎችን ሲያስጠጋ ነው የሚታየው፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት አለ ለማለት ቢያስቸግረኝም፣ ነገር ግን በኤርትራ ሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራጅቶ የሚታገለውን ‹‹ብርጌድ ንሓመዱ›› ቡድንን የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያስተናግድ ዓይተናል፡፡ የ‹‹ብርጌድ ንሓመዱ›› ኃይሎች የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንደሚቀጥል፣ የእነሱም ትግል እንደሚቀጥል አሳውቀዋል፡፡ ይህ ምን ድረስ ይቀጥላል የሚለውን በሒደት እናያለን፤›› ነው ያለው፡፡

በኢትዮጵያ የመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ከኤርትራ ጋር ለመታረቅ ዝግጁ የሆነ አዲስ አስተዳደር ለሥልጣን መብቃቱ፣ ለሁለቱ አገሮች መታረቅ ታላቅ ዕድል እንደነበር በርካቶች ያወሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ሁለቱን አገሮች ለረዥም ዓመታት ያቃቃረውንና በዓለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ቤት በሄግ የተሰጠውን ይግባኝ የለሽ የድንበር ብይን ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃደኛ መሆኑም፣ ለዕርቀ ሰላሙ መሠረት የጣለ ምክንያት ተደርጎ ይገለጻል፡፡ የሁለቱ አገሮች ዕርቀ ሰላም ማውረድ ብዙ ተስፋና ሀሴት በዜጎች መካከል ፈጠረ፡፡ ይህ አጋጣሚ የሁለቱን አገሮች መሪዎች ከማጨባበጥና ከማስተቃቀፍ በዘለለ የፈጠረው ነገር የለም ቢሉም አንዳንዶች፣ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላላቅ የሰላም ሽልማቶችን እስከማስገኘት የደረሰ ትልቅ ፖለቲካዊ ለውጥ እንደነበር ብዙዎች አይረሱትም፡፡

በኖቤልና በሄሰን የሰላም ሽልማቶች፣ እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ የክብር ሜዳሊያ ዓለም አቀፍ ጭብጨባን ያገኘው የኤርትራና የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ከመሪዎችና ከፖለቲከኞች የአቻ ለአቻ ግንኙነት በዘለለ ተቋማዊ መሠረት እንዲይዝ በርካቶች በጊዜው ወትውተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ በቂ ጥረት ባለመደረጉና ግንኙነቱ መርህን የተከተለ ሊሆን ባለመቻሉ፣ ዛሬ ተመልሶ ለመበላሸት መዳረጉን ነው ጋዜጠኛ ሰናይ የሚናገረው፡፡

‹‹የኢሳያስ መንግሥት በሒደት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጭምር እጁን በቀጥታ አስገብቶ በጦርነት መሳተፉና ወደ 70 ሺሕ የሚገመቱ ኤርትራዊያንን በጦርነት መማገዱ ኤርትራን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ በኢትዮጵያ ጦርነት ጦሩን ማሳተፉ ሳያንስ የኢሳያስ አገዛዝ ተጠያቂነቱን በጦር መኮንኖችና በአመራሮች ላይ ለመደፍደፍ መሞከሩ አስደናቂ ተለዋዋጭነት ነው፡፡ አሁን ደግሞ መልሶ ከኢትዮጵያ ጋር መላተሙ አገዛዙ ሥልጣኑን ለማስቀጠል ሲል ምንም ዓይነት አማራጭ ጦርነትን ጨምሮ ለመከተል አሁንም ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ነው፤›› በማለት ጋዜጠኛው ሐሳቡን ይገልጻል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላኛው አስተያየት ሰጪና የፖለቲካ ተንታኝ ግን፣ የዕርቀ ሰላሙ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆን በትግራይ ፖለቲከኞች ጭምር ሲፈለግ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

‹‹በትግራይና በኤርትራ ድንበሮች መካከል ግብይት ተጀምሮ ነበር፡፡ ራሳቸው በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነበር፣ አወዛጋቢውን የድንበር ውሳኔ ያለቅድመ ሁኔታ ለመቀበል በኢትዮጵያ በኩል የተወሰነው፡፡ ኤርትራ የሰሜኑ ጦርነት ሲጀመር ወደ ጦርነቱ ለመግባት የሚያስገድዳት በቂ ምክንያቶች ነበሯት፡፡ ትግራይ ተነጥላለች፣ ትግራይ ልትወረር ነው፣ ኢሳያስና ዓብይ ትግራይን ለመውረር ከጦርነቱ በፊት ሲያሴሩ ነበር የሚለው ክስ የተለመደ የፖለቲካ ቅጥፈታቸው ነው፡፡ ከሕወሓት ባህሪ አንዱ ከደደቢት በረሃ ጀምሮ ይዘውት የመጡት ሌሎች ያጠቁናል የሚል የሥጋት ፖለቲካ (ሲጅ ሜንታሊቲ) አንዱ ነው፤›› በማለትም ገልጸውታል፡፡

ግንኙነቱ መልሶ መጠውለግ የጀመረው ከመጀመሪያውኑ በራሱ በሕወሓት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደነበር የሚከራከሩት የፖለቲካ ተንታኙ፣ ድንበሩ እንደተከፈተ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን መደገፍ እንደጀመሩ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የ‘አክል’ እንቅስቃሴ በትግራይ ኃይሎች ሲደገፍ ነበር፡፡ ይህ በወያኔና በሻዕቢያ መካከል ከቆየው መጠራጠር ጋር ተዳምሮ ኤርትራና ኢትዮጵያ ትግራይን ሊወጉ ሲዘጋጁ ነበር የሚል የሴራ ፖለቲካን ወለደ፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ ሲቀጥሉም ምዕራቡ ዓለም የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካን የሚመለከትበት መነጽር የተዛባ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

‹‹እጅግ በተወሳሰበ ቀውስ የተዘፈቀውን የአፍሪካ ቀንድ ችግርን በአንድ መሪ ላይ የመደፍደፍ አባዜ ይታያል፡፡ ኢሳያስ ከተወገደ የአፍሪካ ቀንድ ችግሮች ይፈታሉ ከሚል ግምገማ የመነጨ ደካማ ፖሊሲ ሲሆን፣ ይህንን በማስረፅ ደግሞ ሕወሓቶች ለብዙ አሥርታት ተግተው ሠርተዋል፡፡ ኤርትራን በጫና አፈር አስግጦ የመደራደር (ስቴት ክራፍት ዲፕሎማሲ) ፖሊሲን ተቋቁማ መቀጠል የቻለች አገር ናት፡፡ የማዕቀብ ፖሊሲ ከበባ ውስጥ የኖረችው ኤርትራ እንጂ ሕወሓት አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ወያኔና ምዕራባዊያን አጋሮቹን እልህ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፤›› በማለት ከኤርትራ ጋር ተፈጥሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም የገጠመውን ፈተናና እንቅፋት አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል አሁን በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ለተፈጠረው ቁርሾ መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን እንዲያስረዱ የተጠየቁት የፖለቲካ ተንታኙ፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በተለይም መከላከያ መቀሌን ለትግራይ ኃይሎች ትቶ ከወጣበት አጋጣሚ እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡

‹‹ኤርትራዊያን መከላከያ ከመጀመሪያው ዘመቻ ስምንት ወራት በኋላ ትግራይን ለቆ ሲወጣ፣ እኛም እንድንወጣ ሳይነገረንና ዝግጅት ሳናደርግ ነው የወጣው የሚል ቅሬታ ያነሳሉ፡፡ በአንዳንድ ግንባሮች ጦራቸው ተጋላጭ ሆኖ መመታቱ አበሳጭቷቸዋል፡፡ ወደ ባድመ አፈግፍገው ራሳቸውን አጠናከሩ፡፡ ከሐምሌ ጀምሮ ወያኔ ወደ አማራ ክልል ዘመቻ በማድረግ ጋይንት ላይ ቢመታም፣ በወሎና በአፋር በኩል ጥቃቱን አስፋፋ፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት እያዩ ዝም አሏቸው ብሎ በኤርትራ ኃይሎች ላይ ቅሬታ ይዞ ነበር፡፡ ሆኖም በአፋር በኩል የድንበር መስመሩ እንዳይያዝ ዕገዛ አድርገው ነበር፡፡ ወያኔ ከሸዋ ሮቢትና ከከሚሴ ተመቶ ከተመለሰ በኋላ ጥር ላይ የኢትዮጵያ የጦር መኮንኖች ሲሸለሙ ለኤርትራዎችም ሊሰጥ ጥሪ ቢደረግም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ በዚሁ ወቅት ደግሞ ኤርትራ ለዳግም ወረራ መከላከል በሚል ለአማራ ኃይሎች ሥልጠና መስጠት ጀምራ ነበር፡፡ በአከር ላይ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ተሰጥቶ ሁለተኛ ዙር ሊሰጥ ሲል ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በመከልከሉ ቆመ፡፡ ሦስተኛውን ዙር ጦርነት ወያኔ በኤርትራና በወልቃይት መስመር ጠንከር ያለ ውጊያ በመክፈት ነበር የጀመረው፡፡ የኤርትራ ኃይሎች ጭምር መስዋዕትነት ከፍለው በጥምር ኃይሉ ድል ተደመደመ፡፡ ሆኖም የፕሪቶሪያው ስምምነት ወያኔን ከሞት የታደገ ሆነ፡፡ ስምምነቱ የጥይት ጩኸትን ከማስቆም ባለፈ ለሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች ችግር መፍትሔ ይዞ የመጣ አልነበረም፡፡ ከዚያ ወዲህ የኤርትራ የጦር መኮንኖች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበረ ቢሆንም፣ ከመሪዎች ወደ ወታደራዊ መኮንኖች ወርዶ የቆየውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያጠናክር ሥራ ሠርተው ሳይሆን የስንዴ ማሳ ጎብኝተው እንዲመለሱ ነበር የተደረጉት፤›› በማለት የተናገሩት ተንታኙ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ከፋኖ ጋር የተጀመረው ጦርነት ደግሞ ብዙ ለውጦችን ይዞ እንደመጣ ገልጸዋል፡፡ አሁን ኤርትራ የፋኖ ኃይሎችን ትረዳለች የሚል ቅሬታ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳለውም ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል በሕወሓት በኩል በቅርቡ ለ60 ቀናት ግምገማ ብሎ በተቀመጠበት ወቅት ሦስት የአጀንዳ ወረቀቶች ቀርበው እንደነበር የፖለቲካ ተንታኙ ይገልጻሉ፡፡

‹‹አንዱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ያበቃለት ነውና በደም፣ በቋንቋና በባህልም ከምንመስለው ኤርትራ ጋር ተጣምሮ ወደብ ያለው ነፃ አገር መፍጠር ይሻላል የሚል ሰነድ ሲሆን፣ የኤርትራ መንግሥትን ማስወገድና በምትኩ ተስማሚ አገዛዝን የመመሥረት ሐሳብ የያዘ ሰነድ ነው፡፡ ሁለተኛው ሰነድ አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይን ህልውና ማስጠበቅ የሚቻለው የኢትዮጵያ የደኅንነት መዋቅርን በመጠቀም ነው የሚል ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ጥብቅ አጋርነት መፍጠርን ያስቀደመ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የተዳከመ ነውና ከአማራና ከሌሎች የታጠቁ ኃይሎች ጋር ተሠልፎ መንግሥቱን መጣል ይቻላል የሚል ሐሳብ የያዘ ሰነድ ነው፡፡ የሕወሓት (የትግራይ) ኃይሎች እነዚህን ሦስት መሠረታዊ አጀንዳዎች እንደ አማራጭ በማቅረብ እንደ አስፈላጊነቱ ሁሉንም አማራጭ ለመጠቀም ተስማምተው ነው የተነሱት፡፡ በሦስቱም መንገዶች የአስመራ መንግሥትን ማዳከም እንደሚቻል የታመነበት ሲሆን፣ በብዙ መመዘኛዎች እነዚህ ሰነዶች ጨርሶ የሚጣሉ አይደሉም፤›› በማለት ከፕሪቶሪያ ስምምነት ወዲህ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የኃይል አሠላለፍና ከኤርትራ ጋር ስለሻከረው ግንኙነት ተንታኙ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኤርትራ ፕሬዘዳንት ከሰሞኑ የነፃነት በዓል ሲከበር ባሰሙት ዲስኩር፣ በኤርትራ ዙሪያ ያሉ ጎረቤቶች በጠቅላይነትና በመቆጣጠር ስሜት ጠብ ጫሪ እንቅስቃሴ እያደረጉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቀውስ እየፈጠሩና እየተጠቀሙ በመካከላችን መከፋፈል ለመፍጠር የሚጥሩ ጎረቤቶች ከበውናል፡፡ በቀጣናው የበላይነትና ጠቅላይነት እንጨብጣለን በሚል መንፈስ የጦርነትና ወረራ ትንኮሳ እያደረጉብን ይገኛሉ፡፡ ባለፉት 33 ዓመታት ነፃነታችንን አፅንተን በመኖራችንና የጠቅላይነት ስሜታቸው ባለመርካቱ ተቃጥለዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ዙር ጦርነት ሊከፍቱብን ድግስ ላይ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ንግግር በግጭት የምትታመሰዋን ሱዳንን በመሥጋት የተስተጋባ አይመስልም የሚሉ አሉ፡፡ ንግግሩ ደካሞቹን ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲም ሆነ ሶማሌላንድን በመሥጋት የመጣም አይመስልምም ይሉታል፡፡ የኢሳያስ ሥጋት መነሻው በቀጣናው በሰላም በመኖር የምትታወቀዋን ኬንያን ግምት ውስጥ ያስገባም አለመሆኑን ብዙዎች ይጋሩታል፡፡ ኢሳያስ ከዚህ ይልቅ በባህር በር ፖሊሲና በሰሜኑ ጦርነት አያያዝ ሒደት ጋር በተገናኘ አለመግባባት ለገጠማቸው ለኢትዮጵያ ያስተላለፉት መልዕክት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ለዚህ ሥጋት ደግሞ ኤርትራ ሙሉ ዝግጅቱና አቅሙ እንዳላት ተናግረዋል፡፡

ከሰሞኑ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሰሜኑ ጦርነት አያያዝና አፈታት ወይም በባህር በር አጀንዳዎች ሁለቱ ወገኖች ባለመስማማታቸው የመጣ ነው የሚለውን ብቻ የማይፈልጉ በርካታ ወገኖችም አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በቀጣናው የኃይል የበላይነት ለመጨበጥ የሚፈልጉ ልዕለ ኃያላን አገሮች የፈጠሩት ጫና እንደሚጎላባቸው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ኢትዮጵያንና የቀጣናውን አገሮች በውስጥ የፖለቲካ ችግሮች ከመበጥበጥ ባለፈ አንዱን አገር ከሌላው ጋር በማላተም፣ ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ የሚፈልጉ ከዓረቡ ዓለም እስከ ምዕራባዊያን የተሠለፉ ኃይሎች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡

ኤርትራ በቅርቡ የሩሲያ ባህር ኃይል መርከቦችና ወታደሮችን ስታስተናግድ መታየቷን ብቻ ሳይሆን፣ ኢሳያስ አፈወርቂ በሞስኮ ጉብኝታቸው የገጠማቸውን ታላቅ መስተንግዶ ያነሳሉ፡፡ በሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ላይ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ዘመቻ በመደገፍ ምዕራባዊያኑን ሲራገሙ መታየቱ፣ ሞስኮ በቀጣናው ልትከተል ስለምትችለው ፖለቲካዊ ፍላጎት እንደማሳያ ያቀርቡታል፡፡

ቻይና የተማሩት ኢሳያስ በቅርቡ በቤጂንግ ጉብኝታቸው የገጠማቸው ታላቅ አቀባበልና መስተንግዶ፣ አስመራ በቤጂንግ የአጋርነት ካምፕ ውስጥ ለመሆኗ ማስረጃ አድርገው አንዳንዶች ያቀርቡታል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በገቡበት ፉክክር መካከል ሪያድን ለመምረጥ ያላመነቱት ኢሳያስ፣ የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር የሆነችውን ዓረብ ኤምሬትስ ትተው ወደ ሳዑዲዎች ጎራ ማጋደላቸውንም ይጠቅሱታል፡፡ በሌላ በኩል በሱዳን የዕርስ በዕርስ ጦርነት የኤርትራም ሆነ የሳዑዲዎች የድጋፍ ምርጫ የሱዳን ብሔራዊ ጦርን ለሚመሩት ለጄኔራል አብዱልፈታ አል ቡርሃን ያዘመመ መሆኑን ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡ ይህን የአጋርነት አዛምድ እስከ ካይሮ የሚወስዱት ሌሎች ወገኖች ደግሞ ከሱዳኑ አልቡርሃን ጎን መቆም ግብፅን፣ ሳዑዲንና ኤርትራን እንደሚያስተሳስር ይገልጻሉ፡፡ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ጠላትነትም እግረ መንገድ ያስታውሱታል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟ በቀጣናው ይዞት የሚመጣው የኃይል አሠላለፍ ሽኩቻ እንዳለ ሆነ በዚህ አካባቢ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸው ቱርክ፣ ኳታርና ኢራን የመሳሰሉ ኃይሎች አሠላለፍም በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት በርካቶች ያሳስባሉ፡፡ አሜሪካን ጨምሮ በትንሿ ጂቡቲ ጦር ያሠፈሩ ከአሥር ያላነሱ ኃያላን አገሮች ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ውዝግብም ሆነ ዕርቅ ምን እንደሚፈልጉ በጥንቃቄ መገምገም እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ በሌላ በኩል የባብ ኤል መንደብን ጠባብ የባህር ወሽመጥ የዘጉት የየመን ሁቲ ኃይሎች ቀጣናዊ ችግር ለቀንዱ ተጨማሪ ራስ ምታት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ጋዜጠኛ ሰናይ ግን ለቀንዱ አካባቢ ትልቁ ራስ ምታት የኢሳያስ መንግሥት መሆኑን ነው አጠንክሮ የሚናገረው፡፡ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖና ፍላጎት የቀጣናውን ችግር ቢያወሳስበውም፣ ነገር ግን ኢሳያስ አፈወርቂ ቀጣናውን በሚመለከት የሚተነትኑበት መንገድና የሚያራምዱት ፖሊሲ ሁሌም ቢሆን አዋኪ ሆኖ መቆየቱን ያስረዳል፡፡

‹‹የኤርትራ ነፃነት በዓል ለእኔ ኢሳያስ የራሱን ፍላጎት የሚያራምድበት ነው፡፡ ኤርትራ ነፃ ሆነች ቢባልም ወደ ጨለማ ነው ያስገባት፡፡ ፓርላማ የለም፣ አገራዊ ዕቅድ የለም፣ አቦይ ተስፋው እስኪባል ድረስ ሁልጊዜ የማይተገበሩ ነገሮችን በመናገር ነው የሚገዛው፡፡ በቀጣናው ፖሊሲም ቢሆን ሁልጊዜ የጦርነት አማራጭን ከአጀንዳው ለይቶ አያውቅም፡፡ ለዚህ መፍትሔው ኤርትራዊያን የጀመሩትን ዓለም አቀፍ ተቃውሞ አጠናክረው በመቀጠል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኤርትራ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፤›› በማለት ነበር ሐሳቡን የደመደመው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -