Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርእኛ ኢትዮጵያውያን ከየት መጥተን ወዴት እየሄድን ነው?

እኛ ኢትዮጵያውያን ከየት መጥተን ወዴት እየሄድን ነው?

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

ኢትዮጵያውያን ከየትም እንምጣ ከየት እስከ 1445 ዓ.ም. እስላማዊና ክርስቲያናዊ ኃይሎች ግጭት እስከ ጀመሩ እስከ 1558 ዓ.ም. ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያን ሁኔታ በመመርመር፣ ‹‹ዛሬ የተለየን ነን›› ከሚሉት አካል ጋር ትክክለኛውን የወሰንም ሆነ አገር የማን ነች ብለን ከጠየቅንና ከተረዳን በኋላ፣ አተርፍ ባይ አጉዳይ እንዳንሆን አንድነታችንንና ኢትዮጵያዊነታችንን አክብረንና ተከባብረን ለመኖር መሞከሩ እጅግ የተሻለ ስለሚሆን ልብ እንግዛ። ኢትዮጵያ ከ1558 ዓ.ም. በፊት ምን ትመስል ነበር? የማንስ ነበረች? ብለን ወደ ጥያቄና ታሪክ ከገባን ዛሬ ለተነሳው ውዥንብር ትክክለኛውን መስመር ቢያስይዝም ጉዳዩን ለማሻሻል ሳይሆን፣ በከፋ ሁኔታ ታሪክን ሳያገናዝቡ ለሚከንፉ አካላት የባሰውን ችግር እንዳይፈጥር ይታሰብበት።

ሌሎች ሥልጣኔ ለማግኘት ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለቴክኖሎጂና ለሌሎች ተግባራት ሲሽቀዳደሙ የእኔ ከተማ ነው፣ የዚያኛው ነው በማለት ጊዜ ማጥፋት፣ ለአንዳንድ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሹመት ፍለጋ ጉዳዩ ያልገባውንና የታሪክ ተመክሮ ያልጎበኘውን ወጣት እያሳሳቱ በሐሰት ታሪክ ባያወናብዱ መልካም ይሆናል። የየአካባቢውም ሽማግሌዎች የታሪክ ምሁራን ባይሆኑም እንኳ የነበረውንና ያሳለፏቸውን ዘመን፣ በዕድሜ የተማሩትና የሚያውቁት ስለሆነ፣ ስለሰላም ቢሰብኩና እውነተኛውን ታሪክ ቢመሰክሩ መልካም ስለሚሆን ሽማግሌዎች በዝምታ ተቀምጣችሁ አገራችንን ለአደጋ አታጋልጡ ለማለት ነው።

- Advertisement -

የብሪታኒያ ዋና ከተማ ለንደን ሲሆን የአይሪሹ፣ የስኮቲሹ፣ የዌልሹና የእንግሊዝ የጋራ ከተማ ነው። እስከ 1970ቹ ድረስ ምናልባት ለጀርመንና ለግሪክ ተወላጆች ብቻ የእንግሊዝ የዜግነት ዕድል ሲሰጥ ለሌላ አይፈቀድ እንደነበረ ሁላችን የምናውቀው ጉዳይ ነው። ከተማዋም የመላው ብሪትሽ እንጂ የግል ወይም የእንግሊዝ ብቻ አይደለችም። በተመሳሳይ መንገድ አሜሪካ ገብቶ ማንም ሰው በሕግ ተፈላጊውን ሁሉ ከፈጸመ ያለበት ከተማ የዚያ የነዋሪው ሕዝብ እንጂ፣ የዛሬ 300 ዓመታት የነበሩት ነጮች ብቻ አይደለም። ለነገሩማ ይህንን ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ ፈረንሣይ፣ እንግሊዝና ደቾች በጠየቁ ነበር። የእኛ ዓይነት ሞኞች ስላልሆኑ በአገር ልማትና ብልፅግና በማመናቸው ከአውሮፓ ተሰዶ በመጣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየተገለገሉ አገራቸውን የጋራ አድርገው፣ እኛ ግን በሆነ ባልሆነው የምንፋለጠውን ዳር ቁጭ ብለው የሆነ ነገር ሲያርከፈክፉብን ማየት እንኳ አቅቶን እርስ በርሳችን እየተናጨን ነው።

የሠለጠኑት በሰማይ ላይ ሲበሩ ብስክሌት እንኳ ያልሠራን፣ ከስንዴ ልመና ያልወጣን፣ በተገቢው መንገድ መኖር ያልቻልን፣ ለም አፈር፣ በርካታ ወራጅ ወንዞች እያሉን ሠልጥነው መሥራት የሚችሉ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሥራ አጥተው በየጎዳናው ሲንቀዋለሉ፣ ታዳጊ ሕፃናት አባባ-እማማ ዳቦ መግዣ ስጡኝ ራበኝ እያሉ ሲለምኑ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም እንኳ አልቻልንም፡፡ አገር ለመበታተንና ለእነዚያ ቋምጠው ሲጠባበቁን ለነበሩ ጠላቶቻችን መንገድ እየከፈትን መሯሯጣችን እጅግ ያሳፍራል። እንዲያውም ከተቻለ አፍሪካን አንድ አድርጎ እንደ አሜሪካኖቹ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት ወደፊት በመራመድ ተንቆ የቀረውን የጥቁር ሕዝብን ታላቅነት ማስመስከርና ማሳመን ሲገባ፣ አገርን በጣጥሶ ወደ ትንሽነት ለመውረድ መሞከሩ እጅግ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አጥፊ እንቅስቃሴ የምትመሩ ፖለቲከኞች ልብ ግዙ ለማለት ነው።

ለምሳሌ የቀድሞዋን ዩጎዝላቪያን እንመልከት፡፡ ከታላቅነት ወርዳ ወደ አምስት ትንንሽ አገርነት ተከፋፍላ ያመጣችውን ውጤት ተመልከቱ። ግማሽ ያህሉን ሕዝባችንን ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም መልካችሁ በፀሐይ ጠቁሮ ነው እንጂ፣ አጥንታችሁ እኮ የእኛው ነው እያሉ ያስተምሩ እንደነበረ በወለጋ ያስተምሩ የነበሩ የጀርመን ሚሽነሪዎች የማይረሳ ታሪክ ነው። ሞኝ ወገኖቼም ያንን ተቀብለው መዝፈን ጀመሩ፣ መዝፈንም ብቻ አይደለም ሊሆኑም ፈለጉ፡፡ ጠቅላላ ጥቁርን ሊያጠፋ ወይም ባሪያ አድርጎ ሊገዛው የነበረውን አውሮፓዊ ፊደል ያለ ኃፍረት የእኛ ፊደል ነው ለማለትም ተሞከረ። ዋ አለማወቅ ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ነች›› እንዲሉ፣ በተዘዋዋሪ በቀላሉ አታልለው ሊገዟቸው ሲሞክሩ ሰተት ብለው እጅ መስጠት ኢትዮጵያዊ ወኔና ባህል ስላልሆነ፣ በኢትዮጵያዊነታችሁና በፊደላችሁ ኮርታችሁ ብትጠቀሙ መልካም በሆነ ነበር።

የሚገርመው ነገር አፍሪካውያን ነፃ ወጥተው የአፍሪካን አንድነት ድርጅትን ሲያቋቁሙ መጀመሪያ የቀረበው ሐሳብ የአፍሪካ ፊደል የኢትዮጵያ እንዲሆን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፊደል እንጠቀም የሚል ሐሳብ ተሰንዝሮም ነበር፡፡ ግን ሁሌም የማይተኙልን የአፍሪካ ጠላቶች ወዳጅ መስለውና አዘናግተው በዚያም ላይ ‹አዲስ ፊደል ስታስተምሩ ብዙ ነገር ያመልጣችኋል› በሚል ተልካሻ ምክንያት ተረሳስቶ እንዲቀር መደረጉን ነባሮቹ ያስታውሱታል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቋንቋውን ማንም ሊነሳው አይችልም፡፡ ነገር ግን ጥቅምና ጉዳቱን አመዛዝኑት። አማራው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ አፋሩ፣ ሶማሌው፣ ጉራጌው፣ ከፋውና ሌሎችም ይህ ፊደል የእኛ ነው ቢሉ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የአንተ ወይም የአንቺ አይደለም ብሎ ሊከራከር አይችልም፡፡ ሁላችንም የእኛ ነው ብለን ራሳችንን ከፍ አድርገን ብናየው መልካም ይሆናል።

ለምሳሌ አፍሪካዊ ወንድሞቻችንን እንመልከት፡፡ ለዘመናት በቅኝ ሲገዙ ኖረው በ1960 ዓ.ም. የነፃነት ጮራ ሲፈንጥቅላቸው ያሳለፉት ውሳኔ፣ ‹ወደ ገዛ ቋንቋችን እንመለስ ካልን ከልማት ጎዳና በጣም ብዙ ርቀን የዘለዓለም ተመፅዋች ሆነን ስለምንቀር፣ ቋንቋ መግባቢያ እንጂ ምንም ማለት አይደለምና በዚህ ልጆቻችን በሚገባቸው ከዓለምም ሊያገናኘን በሚችል ጠላት ቢሆኑም ቋንቋቸውን እንጠቀምበት…› ብለው በመወሰናቸው እነሆ ብዙኃኑ አፍሪካውያን በለመዱት በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሣይኛ፣ በስፓኒሽ፣ በፖርቺጊዝና በሌሎችም ቋንቋዎች ተግባብተውና አብረው ለመኖር ችለዋል፡፡ በእኛ ኢትዮጵያውያን መሀል በቋንቋ ካልተለያየን የሚለውን ሐሳብ ይዘው ላይ ታች የሚሉ ሰከን ብለው ቢያስቡ የተሻለ ይሆናል። ጊዜያዊ ሩጫ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ማናችንም ከማናችን የማንለይ አንድ ዓይነት ሰዎች ከልማት ይልቅ ለጥፋት መንገድ መክፈትና ወገንን ከወገን ማለያየት ተገቢ አይደለም፡፡

በ1930ዎቹ ገደማ የጀርመን ሚሽነሪዎች የበተኑብንን መርዝ ደፍሮ የሚናገርና የሚያስተምር በመጥፋቱ፣ አዲሱን ትውልድ ከመልካም ነገር ይልቅ ተንኮልን በማስተማር ሌት ከቀን ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ወገኖቻችን ከመጥፎ ተግባር ለመቆጠብ ቆም ብለው ያስቡ፡፡ ነገሮችን ሁሉ መርምረው ወደ ልማት ቢያመሩ ለሁላችንም የተሻለ ይሆናልና ይታሰብበት። አለበለዚያ ወደ 1455 ዓ.ም. ተመልሰን ታሪክን አገላብጠን ወደ የማያባራና ለማንም ወደ የማይጠቅምበት ሁኔታ እንዳንገባ ጥንቃቄ ያሻናል። ግራኝም ያን ያህል ጥረት አድርጎና አገርን አውድሞ በመጨረሻ ሳይጠቀም መና ሆኖ ቀርቶ የለምን? ታዲያ ከአጉል ምኞትና ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከመጣር ይልቅ እንደ ሌሎቹ ለልማት ብንሰማራ አይበጀን ይሆን? ይታሰብበት እላለሁ፡፡

የዛሬዋን ታላቋ አሜሪካን በአንክሮ መመልከት መልካም ነው፡፡ በቅጡ ተመልክተንም ግንዛቤ እንውሰድ። ማንኛውም ሰው አሜሪካ በሕግ ገብቶ የሥራ ፈቃድ አግኝቶ ለአምስት ዓመታት ከቆየ በኋላ፣ የአሜሪካ ዜጋ እሆናለሁ ካለ የመሆን መብት አለው። አሜሪካዊ ከሆነ በኋላ ደግሞ የማይችለው ነገር ቢኖር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን ብቻ ነው። የላይኛው ምክር ቤት አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል (Senate and Congress) መሆን ግን ይቻላል። ታዲያ ይህ ሁሉ ሰው በቋንቋ ቢለያይ የሚያመጣውን መከራና ችግር አስቡት። ይህም ማለት ሰው በየቋንቋው፣ በየቤቱ፣ በየማኅበረሰቡ አይነጋገርም ማለት ሳይሆን አንድ የጋራ ቋንቋ ብቻ ሕጋዊና መጠቀሚያ ይሆናል ማለት ነው (የሥራ ቋንቋ እንደሚባለው)። አለበለዚያ ጥቁር አፍሪካውያን የጥንት የአባትና የእናት ቋንቋቸውን ሲፈልጉ፣ ሜክሲኳውያን የየቀበሌ ቋንቋቸውን ሲሹ ስፓኒሽ፣ ፖርቹጊዝ፣ ፈረንሣይና ጣሊያን የራሳቸውን ሲያሳድዱ አገሪቱ ተከፋፍላ በየጎጡ ሲራኮቱ ተበታተነች ማለት ነው።

በኢትዮጵያ እውነተኛ ታሪክ ከተሸሸገ ወደ ሃምሳዎቹ ዓመታት ልንሸጋገር ነው። ባሪያ ፈንጋዮች ንጉሥ ሲባሉ፣ እውነተኛዎቹ ታሪክ አስታዋሽ አጥተው ሲቀሩ፣ ይህንን እንኳ የሚያስታውስና ለኅብረተሰቡ የሚተርክ የታሪክ ምሁር ሲጠፋ ‹‹ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ›› ሆነና ቀረ። ሰው በገዛ አገሩ ሠርቶ መኖር ሳይችል፣ ወጣት ኢትዮጵያዊት ሕፃን አዝላ በየጎዳናው ስትለምን፣ አዛውንት በየመንገዱ የምበላው አጣሁ ሲሉ፣ በተቃራኒው የበርካታ ሚሊዮን ብሮች ዘመናዊ መኪኖች እያሽከረከሩ፣ ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው ማመላለሻ ውድ አውቶሞቢሎች በከፍተኛ ወጪ መግዛት የሚችሉ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የሚሯሯጡ ኃይሎች ልብ እንዲገዙ እጠይቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ አብረንና ተባብረን አሁን ያለውን መከራ መቋቋም ይኖርብናል።                      

አገር የሁሉም እንጂ የአንድ ጎሳ ወይም የአንድ መሪ ቡድን አለመሆኗ ታውቆ ወደ ልቦናችን ብንመለስ የተሻለ ይሆናልና ይታሰብበት። ታላቅ አገር ይዘን በታሪኳ ብቻ መኖር አንችልም፡፡ ያለፉት ቅም አያቶቻችን፣ ቅድመ አያቶቻችን፣ አያቶቻችን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን በሠሩት ታላቅ ሥራ በየትኛውም ዓለም ብንዞር የነፃዪቱ ኢትዮጵያ ልጆች ነን ብለን አንገታችንን ቀና እናድርግ፡፡ ማንም ዝቅ ሊያደርገን ቢፈልግ በፍፁም ሳንሸማቀቅ ኮርተንና ተከብረን እንደኖርን ራሴ ምስክር ነኝ። አንድ የሚያስቅ ቀልድ መሳይ እውነተኛ ታሪክ ልንገራችሁ፡፡ በካሊፎርኒያ ስቴት በሳኖዜ ከተማ ሁለት ጓደኛሞች በአንድ መኪና አንደኛው እያሽከረከረ አንደኛው ጎኑ ተቀምጠው ይጓዛሉ፡፡ በፍጥነት ነዳህ ብሎ የትራፊክ ፖሊስ ያስቆመውና ከመኪና ውረዱ ብሏቸው ሁለቱም ይወርዳሉ፡፡

ፖሊሱ መኪናውን አስደግፎ በማንም ጥቁር ላይ እንደሚደረገው ሁሉ በእነዚህም ላይ ለማድረግ ‹ዩ ስቱፒድ ኒገር…› ይለዋል ወጣቱን አሽከርካሪ፡፡ ወጣቱም ‹ዋች ዩር ላንጉጅ፣ አይ አም ኖት ኤ ኒገር…› ይለዋል። በዚህን ጊዜ ፖሊሱ ተገርሞ ጓደኛውን ‹ዳዝንት ሂ ሉክ ላይክ ኤ ኒገር…› ይለዋል፡፡ ያኛው ደግሞ ‹ሂ አክትስ ዲፈረንትሊ፣ አይ ቲንክ ሂ ኢዝ ኖት ኖርማል ኒገር…› በማለት ይመልስለታል። በኋላ ፖሊስ ቢሮ ሄደው ጉዳዩ ሲጣራ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ታውቆ ይቅርታ የተጠየቀበትን ዘመን ሳስታውስ፣ ምን ያህል ራሳችንን ከፍ አድርገንና በሌላውም በኩል የተከበርን እንደነበር አይረሳኝም፡፡ እኛ ጥቁር አይደለንም ለማለት ሳይሆን፣ ከጥቁሩም ከነጩም የተለየንና ነፃነታችንን ጠብቀን የኖርን በመሆናችን ማንም የሚሰጠንን ተቀፅላ ስም የማንቀበል ኩሩ ሕዝብ እንደነበርን ለማስታወስ ነው።

ከጊዜ ጋር ጊዜውን መስለው ተራማጅ ነን ባዮች የኢትዮጵያን መልክ ለመለወጥ ቢሹም፣ አገራችን የማይለወጥና የማይሻር ባለታሪክ በመሆኗ እኛ በኢትዮጵያዊነታችን የምንኮራ ብዙኃኑ እናምናለን፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!›› እያልን በስሟ ኮርተን ስለምንኖር፣ ወጣት ኢትዮጵያውያንን በማያውቁትና ባልገባቸው ጉዳይ ግራ አናጋባቸው። ይልቁንስ ለልማትና ለአንድነት እናነሳሳቸው። ሌላ ምሳሌ ደግሞ ልስጣችሁ፡፡ አንድ የ12 ዓመት ኢትዮጵያዊ ልጅ አንድ ቀን ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ውሎ ቤቱ ሲገባ ‹አባቴ?› ብሎ አባቱን ተጣርቶ፣ ‹ለመሆኑ ማርቲን ሉተር ኪንግ ባይፈጠር ኑሮ ነፃነት የሚባል ነገር ለጥቁር ሕዝብ አይኖረንም ነበር…፤›› አለው፡፡ አባትየውም፣ ‹‹ልጄ እኛ እኮ ኢትዮጵያውያን ነን› ቢለው፣ ‹ኢትዮጵያስ ብትሆን ምን ነፃነት ይኖርህ ነበር?› ብሎ በማርቲን ሉተር ነፃ የወጣን መሆናችንን ሊያስረዳ ፈለገ፡፡ ልብ በሉ ማንነታችሁንም ዕወቁ ለማለት ነው። ይህ ልጅ ከእናትና ከአባቱ የኢትዮጵያን ታሪክ ከተረዳ በኋላ በማንነቱ ኮርቶ ሌሎችንም ማስተማር ጀመረ፡፡ ልጆቻችን በኢትዮጵያዊነት ለመኩራራት እንዲችሉ በጎ በጎውን እናስተምራቸው።                                                                           

ሌሎች የደረሱበት የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ዕድገት ለመረማመድ ወጣት ልጆቻችን ከልመና ይልቅ ሠርተው የሚኖርበትን መንገድ እናስተምራቸው፡፡ ሕፃን ተሸክማ በየመንገዱ የምትንከራተተዋን ወጣት እናት ከልመና እናውጣት፡፡ ወጣቱ በየመንገዱ ከሚለምን እንደ ዕድሜው ዕርከን በየትምህርት ቤቱ ገብቶ ዕውቀትን እንዲገበይና የነገ ሳይንቲስት፣ መሐንዲስ፣ የቀዶ ሕክምና ሐኪም፣ በተለያዩ ዘርፎች ምሁርና የታሪክ መዝጋቢ ኢትዮጵያውያንን ኮትኩተን እናሳድግ። ጊዜ በከንቱ አይለፍብን። እባካችሁ እንደማመጥ፣ ለመግባባት እንሞክር ነው መልዕክቴ። ሊያነጋግረኝ፣ ሊመክረኝም ሆነ ሊገስፀኝ የሚሻ ካለ በደስታ እቀበላለሁና በኢሜይል አድራሻዬ እንገናኝ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከዚህ ቀደም የሕይወት ታሪካቸውን የሚዘክር፣ ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተሙ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...