Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል በ1960ዎቹ የተመሠረተና በርካታ እህት ኩባንያዎችን ያፈራ ነው፡፡ ሼባ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ ሼባ ቪሌጅን (መንደርን) ገንብቶ ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡ ግንባታው ሰባት ዓመት የፈጀው መንደሩ የመዋኛ ገንዳን ጨምሮ ሃያ ለቤተሰብ የሚሆኑ ቪላዎች ያሉት ሲሆን ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን ከአልኮል መጠጥ በቀር ይሰጣል፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት  ለ132 ቋሚና ለ50 ወገኖች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡ የሼባ ቪሌጅ ስለሚሰጠው አገልግሎትና በአጠቃላይ የሼባ ግሩፕ በኢትዮጵያ እያከናወናቸው ስላለው ተግባራት የማነ ብርሃኑ የድርጅቱን ባለቤት አቶ ካሊድ መሐመድን አነጋግሯቸዋል፡፡

የሳባ መንደር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- ሼባ ቪሌጅን ለመገንባት ምን አነሳሳዎት?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- ሼባ ቪሌጅ ከቬባ ግሩፕ የወጣ ነው፡፡ በቬባ ግሩፕ ሥር ብዙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ትልቁና አንጋፋው ቬባ (ሳባ) የጉዞ ወኪል ነው፡፡ ሼባ በኢትዮጵያ የመጀመያው የጉዞ ወኪል ሲሆን፣ የተመሠረተው በ1965 ዓ.ም. ነው፡፡ ሼባ አቪዬሽን፣ ሼባ ዳቦ ቤትና አሁን ለምረቃ የበቃው ሼባ ቪሌጅ እህት ኩባንያ በመሆን የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ሼባ ቪሌጅን ለመመሥረት ዋና ምክንያት የሆነኝ የውጭ አገር ቆይታዬ ነው፡፡ ለ18 ዓመታት በጂቡቲ፣ በኬንያና በዑጋንዳ ተቀምጨያለሁ፡፡ በውጭ አገሮች የምናያቸውን ነገሮች በአገራችን ብዙም የምናያቸውና የምናገኛቸው አይደሉም፡፡ በኬንያ ሞምባሳ ከተማ በአንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ‹‹ሞምባሳ ቪሌጅ›› የሚባል አለ፡፡ እኔም ኬንያ በነበርኩበትና ከዚያም አገር ለቅቄ ለሥራ ወደ ኬንያ በምመላለስበት ወቅት የማርፈው እዚህ ሎጅ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ሎጅ በሚሰጠው አገልግሎት ስለምደሰት ይህን የመሰለ ሎጅ ኢትዮጵያ ላይ ለምን አልገነባም በሚል ሐሳብ የተጠነሰሰና ተግባራዊ ለማድረግ የተቻለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሼባ ቪሌጅን ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ ወሰደ? በምን ያህል ካፒታልስ ተገነባ?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ሰባት ዓመት ሆኖታል፡፡ ነገር ግን መሀል ላይ የኮቪድ ወረርሽኝ መጥቶ ለሦስት ዓመት ያህል ሥራችን ወደ ኋላ ሊጎትተው ችሏል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን አሁን ላይ ግን ሥራው ባማረ መልኩ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ ሼባ ቪሌጅን ለመገንባት 350 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን እስካሁን ለ132 ሰዎች ቋሚና ለ50 ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድልን መፍጠር ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የቪሌጁ አገልግሎት ምንድነው?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- ሼባ ቪሌጅ በ25,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በውስጡ ሃያ ቪላ የያዘ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቪላ ከሦስት እስከ አምስት መኝታ ቤቶች አሉት፡፡ በተጨማሪም በጀርባው ለእንግዶች (ለሾፌርና ሠራተኛ) የሚሆን ሰርቪስ ክፍሎች ያሟላ ነው፡፡ ለቤተሰብ መዝናኛ በሚሆን መልኩ ታቅዶ የተሠራ ነው፡፡ ከአንድ ቤተሰብ ጋር  አብሮ የሚመጣ ሾፌር፣ ሠራተኛ ወይም እንግዳ ርቆ ሌላ ቦታ መከራየት አይጠበቅበትም፡፡ እያንዳንዱ ቪላ ቤት በ500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ቤቶቹ ዘመናዊ ኪችን ያላቸው ናቸው፡፡ እንግዶች የራሳቸውን ምግብ እዚያው አብስለው መመገብ እንዲችሉ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ሌላው ቪሌጁን ከሌሎች መሰል ቪሌጆች ለየት የሚያደርገው የአልኮል መጠጥ የማይሸጥበት መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሼባ ግሩፕና እህት ኩባንያዎቹ የተሰማሩባቸውን የሥራ ዘርፎች ምንድን ናቸው?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- በሼባ ግሩፕ ሥር የሚገኘው ሼባ አቪዬሽን አምስት የተለያዩ የውጭ አገር አየር መንገዶችን ወክሎ ይሠራል፡፡ እነዚህ አየር መንገዶችም ገልፍ ኤይር (ከባህሬን)፣ ጀዚራ ኤርዌይስ (ከኩዌት)፣ ፍላይናንስ (ከሳዑድ ዓረቢያ) ኤር አልጄሪያ (ከአልጄሪያ) እና ሙካ ኤርላይንስ (ከመካከለኛው ምሥራቅ) ናቸው፡፡ ከእነዚህ አየር መንገዶች ጋር በጥምረት በመሥራታችን የአገራችንን ቱሪዝም ከማነቃቃት አንፃር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እያበረክትን እንገኛለን፡፡ ቪሌጁን ስንገነባ ዋና ዓላማችን የነበረው ትራቭልና ቱር ለማገናኘት ነበር፡፡ ይህም ተሳክቶልናል ብለን እናምናለን፡፡ ሌላው በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ዳቦ ቤት ነው፡፡ ለዳቦ ቤት 48 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን በሁለት ፈረቃ የሚሠራ ነው፡፡ እዚያው ቢሾፍቱ  ‹‹ማማ›› ሕንፃ ላይ ‹‹ሆት››፣ ‹‹ፒዛ›› እና ‹‹ኩችን ፍራንች ኪን›› የተባሉ ሁለት ሬስቶራንቶችም አሉን፡፡ በአጠቃላይ ሼባ ግሩፕ በሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች ውስጥ ከ350 በላይ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሼባ ቪሌጅ አሁን እየሰጣቸው ከሚገኙ አገልግሎቶች በተጨማሪ በቀጣይ ሊሰጣቸው ያቀደው አገልግሎቶች ይኖራሉ?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- በቪሌጁ ልንሠራቸው ያሰብናቸውና ያላጠናቀቅናቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ቴኒስ ኮርት (የቴኒስ መጫወቻ)፣ ቮሊቮል ኮርት (የመረብ ኳስ)፣ ባስኬት ቦል ኮርት (የቅርጫት ኳስ) እና ኢንዶር ስዊሚንግ ፑል (የቤት ውስጥ መዋኛ ገንዳ) በቅርብ ጊዜ ይኖረናል ብለን እናስባለን፡፡ ኢንዶር ስዊሚንግ ፑል ለሴቶች ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚደረግ ነው፡፡ ይኸውም አንዳንድ የሙስሊም ማኅበረሰብ ሴቶች ብዙውን ጊዜ ይህንን ዕድል አያገኙም፡፡ የመዋኛ ችግር አለባቸው፡፡ በመሆኑም ይህን ታሳቢ በማድረግ (የቤት ውስጥ መዋኛ ገንዳ) እየገነባን እንገኛለን፡፡ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃም ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በውጭ አገሮች በምን ሥራ ላይ ነበር የቆዩት?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- በጂቡቲ እያለሁ በኢምፖርት ሥራ ላይ ነበር ተሰማርቼ የቆየሁት፡፡ በኬንያና ዑጋንዳ ደግሞ በትራንስፖርትና ኤክስፖርት ዘርፍ ላይ ስሠራ ቆይቻለሁ፡፡ ፍራፍሬዎችንና አትክልትን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ኤክስፖርት አደርግ ነበር፡፡ ወደ አገር የተመለስኩት በለውጡ ማግሥት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሼቫ ቪሌጅን ለመገንባት የገጠማችሁ ተግዳሮት ካለ ቢነግሩን?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- ትልቁ የገጠመን ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከውጭ ለምናስገባቸው ዕቃዎች በተፈለገው ፍጥነት ፈቃድ ያለማግኘት ነው፡፡ ይህንን ፕሮጀክት 90 በመቶ የገነባነው በራሳችን ሀብት ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ መብት እንኳ አልተጠቀምንም፡፡ ይህንንም ያደረግነው ከቀረጥ ነፃ መብት ለማስፈቀድ የምንሄድበት መንገድ ረዥም በመሆኑና ይህንን ለማሳጠር ስንል ነው፡፡ ይህን ሥራችንን በመመልከትም በቀጣይ ለምናካሂዳቸው ግንባታዎችና ከውጭ አገሮች ለምናስገባቸው ቁሳቁሶች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና ዕገዛ እንደሚያደርግልን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሼባ ግሩፕ በቀጣይ ሊሠራቸው ያቀዳቸው ፕሮጀክቶች ካሉ ቢጠቅሱልን?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- ሼባ ግሩፕ በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በቢሾፍቱ ከተማ ላይ እየገነባነው የምንገኘውና በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠቀው ዘመናዊ የጂም ማዕከል አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ላይ ይህን መሰል ቪሌጅና ሪዞርት መገንባትም ሌላው የዕቅዳችን አካል ነው፡፡ በተጨማሪም በሌሎች ዘርፎች የምንሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ ከበጎ አድራጎት ወይም ለማኅበረሰብ ድጋፍ ከማድረግ አንፃር ምን ይመስላል?

አቶ ካሊድ መሐመድ፡- ሼባ ግሩፕና እህት ኩባንያዎቹ በበጎ አድራጎትና በሰብዓዊ ተግባራት ዙሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይህን፣ ይህን አድርገናል ብለን መግለጽ ተገቢ ባይሆንም በቅርቡ እንኳ በግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች በተለያዩ ጊዜያት የገንዘብ ድጋፍ አበርክተናል፡፡ በተጨማሪም ለአንድ ወር ያህል በቀን 500 ዳቦ ለተፈናቀሉ ወገኖች ስንለግስ ቆይተናል፡፡ ይህ በቅርብ ያደረግነውን ለማስታወስ ያህል እንጂ፣ አቅም በፈቀደ በማናቸውም ጊዜ ችግር ለገጠማቸው ወገኖች እጃችንን እየዘረጋን እንገኛለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...