Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ባንክ ከአሥር በላይ የማኔጅመንት አባላቱ እንዲሰናበቱ ወሰነ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክን በቺፍ ኦፊሰርነትና በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን ጨምሮ፣ ከአሥር በላይ የሚሆኑ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ከሥራ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ማስተላለፉ ታወቀ፡፡

ባንኩ ውስጥ ረዥም ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት ከፍተኛ አመራሮች ከተጀመረው ሪፎርም ጋር ተያይዞ በተሰጠ ውሳኔ ከሥራ መሰናበታቸውን የሚገልጸው ደብዳቤ፣ ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደደረሳቸው የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ለተሰናባቾቹ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የደረሳቸው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ከሥራ እንዲሰናበቱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በዚህ ስብሰባ ባንኩ አሁን ለደረሰበት ችግር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን አጣርቶ እንዲያቀርብ ቦርዱ አቋቁሞ በነበረው አጣሪ ቡድን ሪፖርት መሠረት ጥልቅ ውይይት በማድረግ፣ ሊወሰድ በሚገባው ዕርምጃ ላይ በቀረበ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በንብ ባንክ ላይ ባደረገውና እያደረገ ባለው ምርመራ አሁን ለደረሰበት ውድቀት የቀድሞ ቦርድና የባንኩ ማኔጅመንት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን፣ በባንኩ ላይ በውጭ ኦዲት ከተደረገው የምርመራ ግኝት አኳያ በባንኩ ከፍተኛ አመራርነት መቀጠላቸው ተገቢ ባለመሆኑ፣ ከግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከሥራ እንዲሰናበቱ እንደተወሰነ በዚሁ ደብዳቤ እንደተገለጸላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቦርዱ ተወስኖ በአዲሷ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እመቤት መለሰ (ዶ/ር) ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ ከሥራ መሰናበታቸው የተገለጹት አመራሮች፣ በእጃቸው ያለውን የባንኩን ንብረት እንዲያስረክቡ ታዟል፡፡ ከሥራ መሰናበታቸው ከተገለጸላቸው ከፍተኛ አመራሮች መካከል አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ቦርድ ኃላፊነቱን ከተረከበ በኋላ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ መልካሙ ሰለሞን አንዱ መሆናቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ አቶ መልካሙ ባንኩ አጋጥሞት ነበር ከተባለ ችግር ጋር ተያይዞ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ ገነነ ሩጋን ካሰናበተ በኋላ፣ አዲሷ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስከተሰየሙበት ጊዜ ድረስ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ቀደም ብሎም የሒዩማን ካፒታል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፡፡

ከአቶ መልካሙ በተጨማሪ ከሥራ መሰናበታቸው ከተገለጸላቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካከል አቶ ሰይፉ አገና (ቺፍ ከስተመርና ኦፕሬሽን ኦፊሰር)፣ አቶ አብርሃም ተስፋዬ (የስትራቴጂና ማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዚዳንት) እና አቶ አምኒ ታደሰ (የኢንተርናሽናል ባንኪንግ ኦፕሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት) ይገኙበታል፡፡ ከከፍተኛ ማኔጅመንት አባላት መካከልም አቶ ሙሉጌታ ድልነሳው (የሪስክና ኮምፕሊያንስ ማኔጅመንት ዳይሬክተር)፣ አቶ ሲራክ ይፍሩ (የኢንተርናሽናል ኦዲት ዳይሬክተር)፣ አቶ ኤፍሬም ተሾመ (የደንበኞች አገልግሎት ምክትል ኦፊሰር)፣ አቶ ሽፈራው አርጋው (የብራንችና ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ) እና አቶ ዓለሙ ሰማዬ (ምክትል የባንክ ኦፕሬሽን ኦፊሰር) ከግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የስንብት ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ ሪፖርተር ምንጮች ገለጻ ከሆነ ባንኩ በሚያሰናብታቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ምትክ በቀናት ውስጥ ምደባ ይደረጋል፡፡

ባንኩ የወሰደው ዕርምጃ ተጠባቂ እንደነበር የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ ዕርምጃው ባንኩ ያቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ በባንኩ ችግሮች ላይ አጥንቶ ያቀረበው ሪፖርት እንደ መነሻ መወሰዱንም አስረድተዋል፡፡ ባንኩ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መረጃ ከመስጠት ቢቆጠብም፣ ብሔራዊ ባንክ በንብ ባንክ ችግር ውስጥ መውደቁን ገልጾበት በነበረ ሪፖርቱ በሥራ ላይ በነበሩት የቦርድና የማኔጅመንት አባላት ላይ እምነት የለኝም በማለቱ፣ ዕርምጃው አይቀሬ እንደነበር ከተገኘው መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡  

አዲሱ ቦርድ ወደ ኃላፊነት ከመጣ ወዲህ የባንኩን አመራር በአዲስ የመተካትና ብሔራዊ ባንክ ባመላከተው አቅጣጫ ዕርምጃ ለምን አልተወሰደም የሚል ጥያቄ፣ በቅርቡ አካሂዶት በነበረ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከባለአክሲዮኖች መቅረቡ አይዘነጋም፡፡

በወቅቱም የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሺሰማ ሸዋነካ፣ ባንኩ ለገጠመው ችግር ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ አካላትን በሚመለከት በጥልቀት እየተሠራበት መሆኑንና ጉዳዩ የተዘነጋ እንዳልሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

አዲሷ ዋና ሥራ አስፈጻሚም ከሪፖርተር ጋር አድርገውት በነበረ ቃለ ምልልስ ባንኩ ሪፎርም እንደሚያደርግና እንደ አዲስ የሚቀርፁትን ስትራቴጂ ሊያስፈጽም የሚችል ብቁ የሆነ የሰው ኃይል በተገቢው ቦታ መመደብ እንዳለባቸው ተናግረው ነበር፡፡ ይህንንም ከ15 እስከ 30 ባሉት ቀናት ውስጥ የሚተገብሩት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ገጥሞት ነበር በተባለ ችግር ዙሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለባለአክሲዮኖች በግልጽ እንዳሳወቀው ችግሩን እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ለባንኩ አመራሮች ያቀረበው የአስተካክሉ ዕርምጃ ሊከናወን ባለመቻሉ፣ በወቅቱ በኃላፊነት ላይ የነበሩ የቦርድና ማኔጅመንት አባላት ባንኩን ያሻግራሉ የሚል እምነት እንደሌለው መግለጹም አይዘነጋም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የቀድሞዎቹ 12 የቦርድ አባላት ላይ እስከ ስድስት ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ በየትኛውም ፋይናንስ ተቋም ውስጥ እንዳይሠሩ መወሰኑ አይዘነጋም፡፡

አዲሷ ሥራ አስፈጻሚም አለ የተባለውን ችግር እንደሚቀርፉ በማሳወቅ፣ ለዚህም የሚወስዷቸው የተለያዩ ዕርምጃዎች እንደሚኖሩ ሰሞኑን ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡  

ቦርዱና አዲሷ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባንኩ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ምክንያት ናቸው ባሏቸው በአመራር ደረጃም ሆነ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች በሚገኙ ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች