Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኮማንድ ፖስትና ብሔራዊ ደኅንነት ጣልቃ ቢገቡም የወርቅ ኮንትሮባንድ ሊቆም አልቻለም ተባለ

ኮማንድ ፖስትና ብሔራዊ ደኅንነት ጣልቃ ቢገቡም የወርቅ ኮንትሮባንድ ሊቆም አልቻለም ተባለ

ቀን:

  • በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የማዕድን ኮሚቴ አዲስ መርሐ ግብር እያዘጋጀ ነው

በመከላከያ ኮማንድ ፖስትና በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጭምር ክትትል ቢደረግም፣ በክልሎች እየጨመረ የመጣው የወርቅና የማዕድናት ኮንትሮባንድ ሊቆም እንዳልቻለ ተገለጸ፡፡

በማዕድናት ሕገወጥ ግብይት፣ ኮንትሮባንድና የፀጥታ ችግር ምክንያት በባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው ወርቅ ሦስት ቶን ብቻ እንደሆነ፣ ይህም ከዕቅዱ 50 በመቶ ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡ የወርቅ ገቢም ከታቀደው 363 ሚሊዮን ዶላር 67 በመቶ ብቻ መሳካቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመጋቢት ወር ብሔራዊ ባንክ የገባው ወርቅ 350 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ ይህም በ2014 ዓ.ም. መጋቢት ወር ከተገኘው 800 ኪሎ ግራም በእጅጉ ያነሰ ነው ተብሏል፡፡

- Advertisement -

በአገሪቱ ያሉ ወርቅ አምራቾች የባህላዊና የኩባንያ ተብለው ሲከፈሉ፣ በተለይ በባህላዊ አምራቾች የሚወጣው ወርቅ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባት ያቆመ መሆኑን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከታቀደው 2‚306 ኪሎ ግራም ውስጥ 609 ኪሎ ብቻ (26 በመቶ) መቅረቡን መረዳት ተችሏል፡፡

በተለይ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ካቀዱት አንፃር የቀረበው እጅግ አናሳ መሆኑን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የማዕድን ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ፈጽሞ ወርቅ ካላቀረቡት የትግራይ፣ የአፋር፣ የደቡብ ኢትዮጵያና የሶማሌ ክልል አንፃር የበፊቶቹ እንደሚሻል ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በኩባንያዎች ከቀረበው 2‚400 ኪሎ ግራም ወርቅ ውስጥ ሚድሮክ ጎልድ በከፍተኛ መጠን ያቀረበ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ገብተዋል የተባሉ ሌሎች ዘጠኝ የወርቅ ኩባንያዎች ሲደመሩ ያቀረቡት ከ100 ኪሎ ግራም በታች ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ስቴላ፣ ዙምባራ፣ ኦሮሚያ ማይኒንግ ኤልኔት፣ ኢዛናና ኢትኖ ማይኒንግ የሚባሉት ይገኙበታል፡፡ በተለይ ኢዛና 375 ኪሎ ግራም አቀርባለሁ ቢልም ምንም ዓይነት ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳላስገባ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ከወርቅ በተጨማሪም የታንታለም አፈጻጸም 40 በመቶ ብቻ የተሳካ ሲሆን፣ ኦፓል 49 በመቶ ነው፡፡ በአንፃሩ የሊትዬም፣ የጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናት የወጪ ንግድ የተሻለ አፈጻጸም ታይቶበታል፡፡

አብዛኛው የባህላዊ አምራቾች ወርቅ በሕገወጥ ግብይትና በኮንትሮባንድ ከአገር የሚወጣ መሆኑን፣ በአንፃሩ ኩባንያዎች ደግሞ በፀጥታ ምክንያት ወደ ሥራ ሊገቡ እንዳልቻሉ ሪፖርቱ ያትታል፡፡

በተለይ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያና በደቡብ አካባቢዎች በወርቅ ማውጫ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እንዲጠበቁና የክልል መንግሥታት ከኮማንድ ፖስትና ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በእነዚህ ክልሎች ፕሬዚዳንቶች፣ የቢሮ ኃላፊዎችና የማዕድን ማውጫ አካባቢዎች አስተዳዳሪዎች ከኮማንድ ፖስት ኃላፊዎችና ከፌዴራል ተወካዮች ጋር ርብርብ እያደረጉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በባህር ዳር የብልፅግና ፓርቲ ስብሰባ ላይ የወርቅና የማዕድናት ኮንትሮባንድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው፣ በተለይ አሶሳና ሽሬ ከፍተኛ የሕገወጥ ወርቅ ዝውውር መተላለፊያ መሆናቸውን አስረድተው ነበር፡፡

በተለይ ሕገወጥ ወርቅ በሱዳን፣ በኬንያና በሶማሊያ ድንበሮች ከአገር በመውጣት በዋናነት ዱባይና ህንድ እንደሚደርሱ፣ እንዲሁም እስከ ኡጋንዳ ድረስ ከዚያም ወደ ዱባይ የሚያመራ ሰንሰለት እንዳለ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በሕጋዊውና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ክፍተት ዋነኛው የችግሩ ምንጭ እንደሆነም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ብሔራዊ የማዕድን ልማት አስተባባሪ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮችና የክልል ፕሬዚዳንቶች የኮሚቴው አባል ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኮሚቴው በማዕድን አምራች አካባቢዎችና በማዕድን ኩባንያዎች ፕሮጀክቶች በመገኘት ምልከታና አሰሳ ካደረገ በኋላ፣ የማዕድናት ኮንትሮባንድን ለማስቀረት አዲስ የድርጊት መርሐ ግብር እያረቀቀ መሆኑን በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...