Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ለሕዝብ ጥቅም›› በሚል የመሬት ይዞታን የሚያስለቅቀው የሕግ ድንጋጌ በግልጽ እንዲብራራ ተጠየቀ

‹‹ለሕዝብ ጥቅም›› በሚል የመሬት ይዞታን የሚያስለቅቀው የሕግ ድንጋጌ በግልጽ እንዲብራራ ተጠየቀ

ቀን:

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሳ የሚከፈልበትንና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን አዋጅ እንደገና ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ፣ ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› የሚለው በግልጽ ተብራርቶ እንዲቀመጥ ተጠየቀ፡፡

የፌዴራል መንግሥት ለሚያከናውናቸው መሠረተ ልማቶችና የማኅበራዊ አገልግሎት ማስፋፊያ ሥራዎች ንብረት የመገመት፣ ካሳ የመክፈልና የማስነሳት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ለክልል፣ ለወረዳና ለከተማ አስተዳደር ለመስጠት የሚያስችል በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 1161/2011 የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማሻሻያ ረቂቁ ላይ ከሁለት ወራት በፊት ውይይት አድርጎበት፣ ለዝርዝር ዕይታ ለከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮችና ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ነበር፡፡

- Advertisement -

ከሁለት ወራት በኋላ ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በረቂቅ ማሻሻያው ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በመድረኩ ከቤቶች ኮርፖሬሽን የመጡ አንድ ተሳታፊ ባነሱት ጥያቄ፣ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም›› መሬት ማስለቀቅ የሚለው ግልጽነት ይጎድለዋል ብለዋል፡፡ የበለጠ የሕዝብ ጥቅም ማለት ምንድነው? መለኪያዎቹ ምንድናቸው? የሚሉት በአፈጻጸም ወቅት ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሰፊ ጥናትና አመላካች ጉዳዮች እንደሚያስፈልጉት ጠቅሰው የሕዝብ ጥቅም የቱ ጋ ነው? የትኛውስ የሕዝብ ጥቅም አይደለም? ለሚለው ግልጽ መሥፈርት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ቡልቻ ለሬቻ በበኩላቸው፣ ለሕዝብ ጥቅም የሚለው ትርጉም በግልጽና በሚገባ ዳብሮና የማኅበረሰቡን ጥቅም ግምት ውስጥ አስገብቶ የተዳሰሰ አይመስልም ብለዋል፡፡

የሕዝብ ጥቅም የሚለው ዕሳቤ በበርካታ አገሮች በፍርድ ቤት ቀርቦ የሚታይ መሆኑን፣ መሬቱ የሚውለው ለሕዝብ ጥቅም ነው አይደለም የሚለውን ፍርድ ቤት እንደሚወስነው አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ባይቻል እንኳ የሕዝብ ጥቅም ምንድነው የሚለውን በግልጽ ለመለየት የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ዴኤታ እንድርያስ ጌታ (ዶ/ር) ግንባታ በሚያካሂዱ አካላት ለሕዝብ ጥቅም ተብለው የሚለቀቁ ቦታዎች የትኞቹ ናቸው የሚለው ታውቆ፣ በተለይም ከመሠረተ ልማትና ከማኅበራዊ አገልግሎት ማስፋፊያ ውጭ የሆኑት በተወሰነ ማሳያ ተለይተው ቢቀመጡ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

የሕዝብ ጥቅም በሚለው ጉዳይ ላይ በርካታ ተሳታፊዎች የትርጉም ችግር እንዳይፈጠርና የመሬት ባለቤቶችን እንዳይጎዳ ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ንዋይ በሰጡት አስተያየት፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መሬት በሚወሰድበት ወቅት ለሚታዩ ጉዳዮች ልዩ ችሎት ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በክልልም ሆነ በፌዴራል የዚህ ዓይነቱ ችሎት መደራጀት እንደሚኖርበት፣ በተለይ አሁን የሚቀርቡት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች አብዛኞቹ የመሬት ጉዳዮች በመሆናቸው አፋጣኝ ውሳኔ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡ እንዲህ መሰሉ ጉዳይ የተለየ ዕውቀት ባላቸውና ልምድ ባላቸው ዳኞች የሚስተናገድ ከሆነ ፍጥነትም ጥራትም እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ አክለውም የሕዝብ ጥቅም የሚባለው ነገር አመላካች ትርጉም ቢሰጥበት መልካም ነው ይላሉ፡፡ አንድን መሬት ለሕዝብ ጥቅም ያስፈልጋል ብለው በሚወስኑ አካላት ማናቸውም ተቋማትና የአስተዳደር ዕርከኖች እንደ መነሻ የሚሆናቸው መሥፈርት ያስፈልጋቸዋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ፣ የቀረበው ማሻሻያ አዋጅ መሆኑንና ዋነኛው ማሻሻያ ከካሳ አከፋፈል እንጂ፣ የሕዝብ ጥቅም የሚለው በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መብራራቱን ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ችግር ካለ ወደፊት ይታያል ብለዋል፡፡

የተጋነነ ካሳን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተወከሉት አቶ ደረጀ አየለ፣ ለጆሮ የሚከብዱ ውስብስብ ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ የሕዝብ ጥቅም የሚለው ጉዳይ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የተቀመጠ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ አዋጁን ለማሻሻል በዋነኝነት ያስፈለገበት ምክንያት የአካባቢ አስተዳደር መዋቅሮች ከዳኝነት አካሉ ጋር በአገናኝ ደላሎች በተጠናና በተቀናጀ መንገድ ዝርፊያ እየፈጸሙና የተጋነነ የካሳ ክፍያ እየጨመረ በመምጣቱ ነው ብለዋል፡፡

በተጋነነ የካሳ ጥያቄ መሠረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 11 ቢሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ስምንት ቢሊዮን ብር በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፣ የሕዝብ ጥቅም የሚለው ጉዳይ በተሟላ መንገድ መታየት አለበት ብለዋል፡፡ የሕዝብ ጥቅም ከካሳ አከፋፈልና ከቦታ ተነሽነት ብቻ ሳይሆን፣ የመሠረተ ልማትና አገልግሎቶችና ግንባታዎችም ለሕዝብ ጥቅም መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሕዝብ ጥቅም የሚለው ሐረግ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 1161/2019 እንደተብራራው የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማጎልበት የክልል ካቢኔ፣ የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋ ወይም አግባብ ባለው የፌዴራል አካል በመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ወይም በልማት ዕቅድ ወይም በመሠረተ ልማት መሪ ፕላን መሠረት ለሕዝብ የተሻለ የጋራ ጥቅምና ዕድገት ያመጣል ተብሎ የሚወሰን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ዓመት የመሬት ይዞታን ለልማትና ለሕዝብ ጥቅም ማስለቀቅን ከሰብዓዊ መብቶች መርሆች ጋር በማያያዝ በሰጠው መግለጫ በቅድመ ማስለቀቅ፣ በማስለቀቅ ወቅት፣ እንዲሁም በድኅረ ማስለቀቅ ጊዜ መንግሥት ሊያሟላ የሚገባቸው የሰብዓዊ መብቶች መርሆችን ያልተከተለ መሆኑንና በኃይል ማፈናቀል እንደተፈጸመ እንደሚቆጠር ጠቅሶ፣ ይዞታ የማስለቀቅ ተግባር በአጠቃላይ ሰዎችን ቤት አልባ እንዲሆኑና ለሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጋላጭ ማድረግ የለበትም በማለት ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...