Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናሕወሓት በቀጣዩ ድርጅታዊ ጉባዔው የገጠሙትን ችግሮች መርምሮ የሕዝብን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ አስታወቀ

ሕወሓት በቀጣዩ ድርጅታዊ ጉባዔው የገጠሙትን ችግሮች መርምሮ የሕዝብን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ አስታወቀ

ቀን:

በአብርሃም ተክሌ

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ‹‹ቀጣዩ 14ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ሕወሓት እንደ ድርጅት የገጠሙትን ችግሮች መርምሮ፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት የምናረጋግጥበት ይሆናል፤›› አሉ፡፡

ሊቀመንበሩ ይህንን የተናገሩት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ እንደ ድርጅት አጋጥሞናል ያሉትን ስትራቴጂካዊ የአመራር ክፍተትና የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያጎላ አመራርን እንድንፈጥር ያስችለናል ያሉበትን ቀጣዩን 14ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ከማድረጋቸው በፊት፣ የጉባዔውን ዓላማና ከጉባዔው ምን እንደሚጠበቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

- Advertisement -

ጉባዔው ከሚካሄድባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች ውስጥ አንዱ ብዙ የማጣራት ሥራ እንደሚሆን ገልጸው፣ ይህም ተግባር አሁን መሬት ላይ አሉ ካሏቸው እውነታዎች በመነሳትና እነሱንም ለመቀየር የሚያስችል መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጉባዔው ብዙ መጣራት የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች የሚፈታ ሲሆን፣ አሁን መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ከግንዛቤ በመክተት፣ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችልም ነው፤›› ብለዋል፡፡                

ቀጣዩ ጉባዔ ሕወሓት እንደ ድርጅት ያጋጠሙትን ችግሮች የሚያጣራበት እንደሆነ ገልጸው፣ ከዚህ በፊት በተደረገ ድርጅታዊ ግምገማ የተደረሰበትን ስትራቴጂካዊ የአመራር ክፍተት ጨምሮ፣ የብቃትና የቅንነት ችግር፣ የሕዝብ ተጠቃሚነት ችግር በቀናነት ይስተካከሉበታል በማለት አስረድተዋል፡፡

ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ ብዙ የተቀየሩ ነገሮች እንዳሉ የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ሆኖም አሁንም ብዙ ያላለቁ ችግሮች አሉ፡፡ ከተቻለ ለውጡ ካለው አካሄድና በሚመጥነው ፍጥነት አብሮ መጓዝ፣ ካልሆነ ግን ከለውጡ ጋር አብሮ መለወጥ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ቀጣዩ ጉባዔ የአሠራርና የአተያይ ፍተሻ በማድረግ በተቀናጀ መንገድ መታረም ያለባቸውን ሥራዎች ማከናወን እንዲያስችል ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

ሊቀመንበሩ በመቀጠል ጉባዔው ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች በሟሟላት መንገድ መካሄድ እንደሚጠበቅበት ገልጸው፣ መለወጥ ያለበትን ነገር እየለወጡ አብሮ መቀጠል የሚያስችል ጉባዔ መሆን እንዳለበትም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ከድርጅቱ ዋና ችግሮች ውስጥ አንዱ የአመራር ችግር ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት ግምገማና ውይይት አስፈላጊ ነው ብለው፣ ቀጣዩ ጉባዔ ይህንን በሚመጥን ደረጃ እንደሚካሄድና ለትግራይ ሕዝብ ቀና ሆኖ ለማገልገል እንዲያስችል ያደርጋል ብለዋል፡፡ ‹‹የጉባዔው መድረክ ሕወሓትን በሚመጥን ደረጃ የሚዘጋጅና ከዚህ በፊት ካደረግናቸው ጉባዔዎች ትምህርት የወሰደ ሲሆን፣ ያሉብንን ችግሮች ማለትም አጠቃላይ ድርጅታዊና የአመራር ችግሮችን የሚፈታ ሆኖ መውጣት አለበት የሚል እምነት አለን፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና በሕወሓት መካከል አለ ስለተባለው ልዩነት እንዲያብራሩ የተጠየቁት ሊቀመንበሩ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩና በሕወሓት መካከል መሠረታዊ ልዩነት የለም ብለዋል፡፡ ሆኖም በሁለቱ ወገኖች መካከል ግን የፖለቲካ ልዩነት እንዳለ የገለጹት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ የፖለቲካ ልዩነታቸው እንደ ሕወሓት አመራር ያለ ልዩነት እንጂ፣ እንደ ጊዜያዊ አስተዳደርና እንደ ሕወሓት የተፈጠረ አይደለም ሲሉ ገልጸውታል፡፡

‹‹ልዩነቱ በሁለቱ የሕወሓት አመራሮች መካከል ያለ ልዩነት እንጂ፣ የጊዜያዊ አስተዳደርና የሕወሓት ልዩነት አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ለሕዝብ ቅድሚያ በመስጠት የሚፈታ ነገር ነው፤›› ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ሕወሓት ተመሳሳይ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ የመፍታት ልምድ ስላለውና አሁን ያለውንም ፖለቲካዊ ልዩነት በተመሳሳይ እንደሚፈታው ገልጸው፣ ቀጣዩ ጉባዔ ለልዩነቱ ዓይነተኛ መፍትሔ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ከቀናት በፊት የሕወሓት ቃል አቀባይ ኮሎኔል አማኑኤል አሰፋ ስለቀጣዩ የሕወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ ዝግጅትን በተመለከተ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቀጣዩ 14ኛው ጉባዔ ለክልሉ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረው ነበር፡፡ ጉባዔው የሚካሄደው በጣም ውስብስብ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ፣ ሕወሓት ካለበት የውስጥ ተግዳሮት ወጥቶ በትግራይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የመሪነት ሚናውን ለመወጣት ወሳኝ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ሕወሓት የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ስትራቴጂካዊ የአመራር ክፍተት አጋጥሞኛል ባለበት ድርጅታዊ ግምገማ ወቅት፣ ጠላት እጅ ወድቀዋል ባላቸው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሌሎች የድርጅቱ አባላቶችን ጨምሮ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምንና ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔርን ከማዕከላዊ ኮሚቴና ከሕወሓት አባልነት ማሰናበቱ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...