Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአገራዊ ምክክር ላይ መሳተፍ የማይችሉና የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት አጀንዳዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ...

በአገራዊ ምክክር ላይ መሳተፍ የማይችሉና የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት አጀንዳዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

በእስር ላይ በመሆናቸው ምክንያት በአገራዊ የምክክር ሒደቱ ላይ መሳተፍ የማይችሉ የተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በምክክሩ እንዲነሱ የሚፈልጓቸው አጀንዳዎች፣ አባል በሆኑባቸው ፓርቲዎች ሊቀርቡ እንደሚችሉ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አስታወቀ፡፡ 

በአገሪቱ ሕግ መሠረት ተመዝግበውና ፈቃድ አግኝተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክር ሒደቱ እንዲሳተፉ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ለሪፖርተር የገለጹት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ፣ ፓርቲዎቹ ያላቸውን አጀንዳ ይዘው ወደ ምክክር ሒደቱ በመቅረብ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ መድረስ እንዲችሉ በምክክሩ መሳተፋቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በምክክር ሒደቱ ሊሳተፉ የሚችሉበት መንገድ ይኖር እንደሆነ የተጠየቁት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት፣ ‹‹በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አቋም ነው ያላቸው፡፡ ይህ አቋማቸውም በማንኛውም የፓርቲያቸው አባል ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ኮሚሽኑ በሕግ በተያዙ ሒደቶች ውስጥ ጣልቃ የመግባት መብትና ኃላፊነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡ 

- Advertisement -

 ኮሚሽኑ የተሰጠው ኃላፊነት አካታች የሆነ የምክክር መድረክ ማካሄድ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ ይህም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል እያራመዱ የሚገኙ ኃይሎችን እንደሚጨምር አስረድተዋል።

ስለሆነም የትጥቅ ትግል እያራመዱ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች በምክክር ሒደቱ ለመሳተፍ ወስነው ሲመጡ የደኅንነት ችግር እንዳይገጥማቸው፣ የሚያስፈልጋቸውን ከለላ ለመስጠት ኮሚሽኑ ከመንግሥት አካላት ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

አባላቶቻቸው ከታሰሩባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፣ የአገራዊ ምክክር ሒደቱ ሲጀመር አንስቶ በርካታ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከጥያቄዎቻቸው መካከልም በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲ አባሎቻቸው እንዲፈቱ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ እንዳላቸውም ገልጸዋል። እነዚህ ጥያቄዎች ሊመለሱ ባለመቻላቸው ኦፌኮ ኮሚሽኑ እያዘጋጀ ባለው የምክክር ሒደት ላይ እየተሳተፈ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በበኩሉ በእስር ላይ የሚገኙ አባላቱ ካልተፈቱ፣ በአገራዊ ምክክሩ ላይ ለመሳተፍና አጀንዳዎችን ለመላክ እንደማይችል አስታውቋል። ኢሕአፓ ላቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘም፣ የፓርቲው ተቀዳሚ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የፓርቲውን ሊቀመንበር ጨምሮ በርካታ አባሎቻቸው በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ተቀዳሚ ሊቀመንበሩ፣ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በምክክር ሒደቱ ላይ እንዲነሱ የሚፈልጓቸው አጀንዳዎች ‹‹በተወከሉበት ፓርቲ ሊቀርብ ይችላል›› በማለት ኮሚሽኑ የሰጠውን ምላሽ ፓርቲያቸው ፈጽሞ እንደማይቀበለው አስታውቀዋል።

አሁንም ቢሆን ፓርቲያቸው ይህንን ጉዳይ በቅድመ ሁኔታነት ያስቀመጠው መሆኑን ያመለከቱት ተቀዳሚ ሊቀመንበሩ፣ ይህ ጥያቄ ካልተመለሰ ኢሕአፓ በምክክር በሒደቱ እንደማይሳተፍ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...