Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅበሬ እና ገበሬ

በሬ እና ገበሬ

ቀን:

የመጀመሪያ ፈር ያለው ትምህርት የተማርኩት ከላይ በተቀመጠው ርዕስ በ‹በሬና ገበሬ› ነው። እማማም የመጀመሪያ መምህሬ ናት። በሰነድ የተደገፈ ሰርቲፊኬት ባትሰጠኝም ዕድሜ ልኬን የማስታውሰው  ትልቅ መልእክት በሐሳቤ ውስጥ ስላብኝ አልፋለች።  ፊደል መቁጠር ምን ማለት እንደሆነ በውል ባትረዳም ፊደል መቁጠር ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን ያስተማረችኝ እርሷ ናት፡፡

በአንድ ወቅት እናቴ በሰፈራችን እንደ አድባር ከሚቆጠረው ትልቅ ባሕር ዛፍ ስር ቁጭ ብላ የአክርማ መሶብ እየሰፋች ነበር። እኔም ከአጠገቧ ሁኜ የባሕር ዛፍ ፍሬ እየለቀምኩ እንደ በሬ እያወጋሁ እጫወት ነበር።

ድንገት ከወደ ውስጥ አክስቴ የውኃ እንስራዋን አዝላ ወደ ምንጭ ልትሄድ ተነሳች።  እኔም ትንሿን ደንበጃን  ይዤ ወደ ካልሄድኩ ብዬ አቧራ አስነሳሁ። አክስቴም ዞር በል እንስራ ተሸክሜ አንተን አልጎትትም፤ አትሄድም ብላ ከለከለችኝ።

እኔም እማማ ደስ እንዲላት ውሃ መቅዳት እፈልጋለሁ  ብየ ማልቀስ ጀመርኩ። አክስቴም እማማ ደስ የሚላት ውሃ ስትቀዳላት ሳይሆን አጠገቧ ቁጭ ብለህ ስትጫወት ነው። ውሃ እሄዳለሁ  ካልክ ግን ከአሁን አሁን ውሃ ውስጥ ገባ ብላ ትጨነቃለች አለችኝ። እኔም እሺ እማማን እንጠይቃትና ደስ አይለኝም ካለች አልሄድም አልኳት። 

እርሷም እሺ ብላኝ ወደ እማማ አጠገብ ሄድንና ድንገት ተሽቀዳድሜ እማማ ውሃ ባልቀዳ ነው ወይስ ብቀዳ ደስ የሚልሽ አልኳት።  ልጄ አክስትህን አታስቸግራት  እኔ ደስ የሚለኝ አሁን አክስትህን እያስቸገርክ ወደ ወንዝ ስትሄድ ሳይሆን  ነገ ትልቅ ሰው ሁነህ ማየት ነው። አንተ አድገህ ቁምነገር ላይ ደርሰህ ለወግ ለማረግ በቅተህ ማየት ነው አለችኝ። እኔም ደንበጃኔን ጥየ ከአያቴ ጉያ ገብቼ ቁጭ አልኩ። 

 አክስቴም ወደ ውሃ ሄደች እኔም እማማ ጸጉሬን እየዳበሰችኝ ልጄ እየውልህ የእኔን የእናትህን  ምክር ስማ አንተ ትልቅ ሆነህ፣  ፊደል ቆጥረህ ፣ለሀገር ለወገን የምትጠቅም ሰው ስትሆን ከማየት በላይ የሚስደስተኝ ነገር  የለም። የኔ ደስታ ሰዎች የናቁትን ዋጋ የምትሰጥ ሰው ሁነህ ማየት ነው። ይህ እንዲሆን  በአንተ ላይ አደጋ በሚያደርስ ስፍራ ሁሉ እንዳትገኝ እሺ ልጄ ! አለቺ መልሴን በመጠባበቅ። እኔም ቀና ብየ ዓይን ዐይኗን እያየሁ ትልቅ ባልሆንስ ምን ችግር አለው ። ትንሽ ሁኜ እያለቀስኩ አስቸገርኩሽ ማለት ነው? ወይስ ትልቅ ስሆን ምን አገኛለሁ? ብየ ጠየቅኋት። 

 እርሷም ልጄ  አሁን ሁሉም ነገር ላንተ ከጫወታ የዘለለ አይደለም። ትልቅ ስትሆን ግን የአንድ ፊደልን ዋጋ ትረዳለህ ። አንድ ፊደል  መላ ታሪክህን ልትቀይር ትችላለች ። ብቻ አንተ ጠንክረህ ፊደል ቁጠር። እማማ እባክሽን ግልጽ አድርጊልኝ እንዴት አንድ ፊደል ታሪክ ይቀይራል? ብየ ጠይቄ መልሷን እጠባበቅ ጀመር። 

እየውልህ ልጄ ለምሳሌ “በሬ” የሚል ቃል አለ።  እዚህ ቃል ላይ አንድ ፊደል ወይም ሁለት ፊደል ብትጨምር ሌላ ታሪክ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል “#ገ” ፊደልን  ከፊት ለፊቱ ስትጨምር  “#ከበሬ” ወደ “#ገበሬ” ይቀያራል። ልብ በል በሬ ቀንበር የሚሸከም፣ በጅራፍ የሚገረፍ ፣ ምግቡን ከሌላ ሰው እጅ የሚጠብቅ፣ በባለቤቱ መልካም ፈቃድ የሚቆይ እና እድሜው ገፋ ሲል የሚታረድ ነው። ነገር ግን  “”#ገበሬ” ጠማጅ ፣ ገራፊ ፣ እረኛ፣ ለበሬ መኖ የሚሰጥ ፣ አዛዥ ፣ የሀገር ዋልታ ይሆናል። 

ከእነዚህ ሁለት ቃላት ውስጥ ልዩነት  የፈጠረችው አንድ “#ገ” ፊደል ብቻ ናት። አየ ልጄ አንድ ፊደል በጨመርክ ቁጥር አዛዥ ትቀንሳለህ፣ ምግብህን ከሰውጅ መጠበቅ ታቆማለህ፣ የመጣው ሁሉ አይጠምድህም፣ ጅራፍ ያለው ሁሉ አይገርፍህም፣ ስጋ ያማረው ሁሉ አያርድህም። ራስህ አዛዥ ናዛዥ ትሆናለህ። 

 ስለዚህ አድገህ ማየት እፈልጋለሁ ያልኩህ በልጠነዋል እንጥመደው ብለው የሚመጡትን ፊደል በመጨመር ብለጣቸው።  የበለጠህ ሁሉ እንዳይጠምድህ በልጠህ ጥመዳቸው ለማለት ነው። ነገር ግን ቀንበር እንዳታጸናባቸው ተጠንቀቅ። እንድትበልጥ የረዳህ ፊደልህ እንጂ በቀልህ አይደለምና በአግባቡ  እዘዛቸው በማለት መከረችኝ።  እኔም ከዚያን ቀን  ጀምሮ በአንድ ፊደል ታሪክ እንደሚለወጥ በማመን  ፊደል በመቁጠር ጊዜየን እየገፋሁ ነው። 

 እማማ ፊደል የመቁጠርን ጥቅም እና የፊደልን ገልበት ያወቅሁብሽ  ከተለያየን አራት ዓመታችንን  ያዝን አይደል? ምክርሽ ጠቅሞኝ ደረጃ በደረጃ ፊደል እየጨመርኩ አለቃ እየቀነስኩ ነው። አድጌ ማየት ህልምሽ ነው። መድረስ የምፈልግበት ደርሼ ልታይኝ ባትችይም ጅማሬየን ስላየሽልኝ እጅግ ደስተኛ ነኝ። እማ ትልቅ ሰው ሆኜ ሳላስመሰግንሽ ሞት እንዳይቀድመኝ በነፍስሽ ጸልይልኝ። አሁንም በአጸደ ነፍስ ሆነሽ ስኬቴን ለማየት እንደምትጓጒ አውቃለሁ ። እኔም ያኔ በጨቅላ አእምሮየ የተቀበልኩትን መመሪያ ለመፈጸም ደፋ ቀና እያልኩ ነው። ዛሬ ለአንድ ሰው ዋጋ በማይሰጥበት ዘመን ለፊደልና ለስርዓተ ነጥብ ዋጋ ሰጥቼ ቀጥ ብየ እንድቆም የረዳኝ ያኔ በጨቅላ አእምሮየ የመከርሽኝ ምክር ነው።  ዛሬ እውነት በመንጋ እየተፈረደባት ባለበት ዘመን አንድ ሰው ለውጥ ያመጣል  በሚል እምነት  ቀጥ ብየ እንድቆም ያደረገኝ የመከርሽኝ ምክር ነው። በዚህ መንገድ  ተልእኮዬን እንድጀምር ስለረዳሽኝ አመሰግናለሁ።  ያለ ሰርቲፊኬት በጉንፊሽ ሳለሁ የሰጠሽኝ ዲግሪ እያሳደግኩት እየኖርኩበት  ነው። 

– መምህር ጌታባለው አድማሱ  (ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም.)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...