Saturday, June 22, 2024

አዲሱ የሃይማኖት ተቋማት ረቂቅ አዋጅና አሻሚ ጉዳዮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከአንድ ሺሕ ያላነሱ መስጊዶችና ቁቢዎችን የያዘችው ትንሿ ሐረር ከተማ በርካታ የእምነት ተቋማት በተቀራረበ አሠፋፈር ችምችም ብለው ይኖሩባታል፡፡ ከአንድ ሺሕ ዓመታት በላይ በኖረችው ዕድሜ ጠገቧ ሐረር በታሪካዊው ጀጎል ግንብ ውስጥ የሦስት ሃይማኖቶች ቤተ ዕምነቶች በ100 ሜትር ርቀት ተገንብተው ለዘመናት ኖረዋል የኦርቶዶክስ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ካለበት 100 ሜትር እልፍ ብሎ፣ የሙስሊሞች ታላቁ የጁምዓ መስጊድ ይታያል፡፡ ከእሱ 100 ሜትር አለፍ ሲባል የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጉልላቱን ከፍ አድርጎ ይገኛል፡፡ ይህ የሐረር ገጽታ ደግሞ በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚታይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማትን ተጎራብቶ በሰላም የመኖር የረዥም ዘመን ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡ ድምፃዊው “ራጉኤል አይደለም ወይ የአንዋር ጎረቤት” ብሎ እንደገጠመው ሁሉ በእምነት ተቋማት መካከል በተቀራረበ ቦታ ሠፍሮም ቢሆን፣ ፍፁም ሰላም በሆነ ሁኔታ መኖር የነበረ ባህል መሆኑን የሚያሳይ ተደርጎ ይወሳል፡፡ ይህ የረዥም ጊዜ የእምነት ተቋማት መስተጋብር ደግሞ የመንግሥት ሥራን ያቀለለ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቦችን አንድነትና የአገርን ህልውና ጠብቆ ያቆየ ትልቅ እሴት መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ይህ ነባር ዕሴት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ማከናወን አለበት በማለት ብዙዎች የሚያሳስቡት፡፡

በቅርቡ በፍትሕ ሚኒስቴር የተዘጋጀው አዲሱ “የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ” ከዚህ አንፃር በብዙ አቅጣጫዎች አስተያየቶችን የሚጋብዝ ነው፡፡ በስድስት ክፍሎችና በ32 አንቀጾች የቀረበው ረቂቅ አዋጁ ከሃይማኖት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ ጀምሮ፣ እስከ የኦዲት አሠራር ድረስ ብዙ ጉዳዮችን የሚመለከት ጭብጦችን የያዘ ነው፡፡ አዋጁ የእምነት ተቋማትን የመሬት ጥያቄ፣ የቀብር ቦታ፣ የአምልኮ አከዋወን፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ ከመንግሥት አካላት ሊሰጣቸው ስለሚገባ አገልግሎት፣ በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ስለሚሳተፉበት ሁኔታ እንዲሁም የውጭ አገር ዜጎችን ቀጥረው ስለሚያሠሩበት አግባብ ብዙ ዓይነት ድንጋጌዎችን ያቀፈ ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት መንፈሳዊ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ሊከተሏቸው ስለሚገቡ ሕጎች ሲዘረዝርም፣ ከድምፅ ብክለት ጀምሮ በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የወጡ ሕጎችን ስለመከተል አዋጁ ይጠቅሳል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት የእርስ በእርስ ግንኙነት ሰላማዊና መከባበር የሞላበት እንዲሆን የሚደነግገው አዋጁ፣ በውስጣቸው በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ሊከተሏቸው ስለሚገቡ የግልግል ሒደቶችም ያስቀምጣል፡፡ የእምነት ተቋማቱ ለሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ኦዲት ሪፖርታቸውን ከማቅረብ በተጨማሪ፣ ከውጭ አገሮች ስለሚያገኙት ገንዘብና ዕርዳታም በግልጽ ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው በረቂቁ ሠፍሯል፡፡

በእምነት ተቋማት መካከል 500 ሜትር ርቀት ሊኖር እንደሚገባ የሚያዘው አዋጁ፣ የእምነት ተቋማት አገልግሎት በመደበኛ ትምህርት፣ በመንግሥት ወይም ሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ እንዲሁም ባልተፈቀዱ ሕዝባዊ መገልገያ ቦታዎች ሊሰጥ እንደማይችል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት የተነጣጠሉ ናቸው የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መርህ ደጋግሞ የሚያነሳው ረቂቅ አዋጁ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት አማኝ ሆነው ካልሆነ በስተቀር መንግሥትን ወክለው በሃይማኖት በዓላት ላይ እንደማይገኙ ይደነግጋል፡፡ በሃይማኖት በዓላት ወቅት ከሚሰጡ የመንግሥት ኃላፊዎች መግለጫ ጀምሮ በሃይማኖትና በመንግሥት መካከል ጥርት ያለ ልዩነት መኖሩን በሚያንፀባርቅ ሁኔታ መስተናገድ እንዳለባቸው የሚጠቅሰው አዋጁ፣ ለተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮች ጭምር ትኩረት በመስጠት የቀረበ ነው፡፡

የሕግ ባለሙያውና ‹‹ወንጀልና ፍትሕ›› የተባለ መጽሐፍ በቅርቡ ያስመረቁት አቶ አበባው አበበ፣ ረቂቅ አዋጁ ከመነሻ መግቢያው ጀምሮ በጥንቃቄ ሊተነተኑ የሚችሉ ነጥቦች ያሉት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

“የሃይማኖት ተቋማት ለዘመናት ያዳበሩትን አብሮ በሰላም የመኖር፣የመከባበርና የመተማመን ባህል ለማዳበር ሲባል ነው ሕጉ ያስፈለገው ብሎ መንደርደሩ ግራ ያጋባል፡፡ ይህ አዋጅ ለእነዚህ ዓላማዎች መውጣት አለበት ወይ? በኢትዮጵያ ለሺሕ ዓመታት የቆዩ ተቋማት ይጠቀሱ ቢባል ከኦርቶዶክስና ከሙስሊም ቤተ እምነቶች ውጪ አሉን ወይ? ተቋማትን ከመገንባት የምናፈርስ አገር አይደለንም ወይ? ለ200 ዓመታት እንኳን የዘለቀ ተቋም አለን ወይ? እነዚህ ነባር የእምነት ተቋማት ለዘመናት የኖሩበት ይህ ባህል የሚታወቅ ነው፡፡ ቀድሞ ከነበረው ነገር ምን ጎድሎ ምንን ለማስተካከል ነው አዋጁ ያስፈለገው? እንዲያውም ፖለቲካው አይደለም ወይ የእምነት ተቋማትን እየተጫናቸው ያለው? አንዱ ሃይማኖት በሌላው ሃይማኖት ላይ የመነሳት፣ ስለሃይማኖት በድፍረት የመናገርም ሆነ በተቋማቱና በተከታዮቻቸው ላይ ጥቃት የማድረሱ ክስተት የቅርብ ጊዜ ሁነት አይደለም ወይ? ሃይማኖትን የፖለቲካ መገልገያ ለማድረግ የተነሱ ሰዎች አይደሉም ወይ ችግር እየፈጠሩ ያሉት?” በማለት ጥያቄዎች ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ አንፃርም የአዋጁ መነሻ ሐሳብ የቀደመው የእምነት ተቋማትን ችግር ወይም ጉድለት ለማረም የወጣ ነው ወይ የሚለው ጥያቄ እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ክፍል ሦስት የሃይማኖት በዓላት አከባበር፣ የሕዝባዊ ሀብቶች አጠቃቀምና የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ሠፍረዋል፡፡ በዚሁ ክፍል አንቀጽ 14 ላይም የሃይማኖት በዓላት በአደባባይ ስለሚከበሩበት ሁኔታ ተደንግጓል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ሥር በንዑስ አንቀጽ አምስት ላይ፣ “በመንግሥት ኃላፊዎች በሃይማኖታዊ በዓላት ሊተላለፍ የሚችል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የሃይማኖት እኩልነትና የመንግሥትና ሃይማኖትን መለያየት መርህን ያከበረ መሆን አለበት፤” ተብሎ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በንዑስ አንቀጽ ስድስት ላይ ደግሞ፣ “የመንግሥት ኃላፊዎች መንግሥትን ወክለው በሃይማኖት በዓላት ላይ መገኘት አይችሉም፤” ተብሎ ተደንግጓል፡፡

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 15 የአምልኮና አስተምህሮ አተገባበር ነው የሠፈረው፡፡ በዚሁ ሥር 15/2 ላይ ደግሞ በመኖሪያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶችና በሕክምና ማዕከላት አካባቢ የሚደረግ አምልኮ በአካባቢ ጥበቃ ሕግ የተቀመጠውን የድምፅ መጠን ያከበረ መሆን አለበት የሚል ድንጋጌ ሠፍሯል፡፡ ከዚህ ወረድ ብሎ አንቀጽ 15/3 ላይ በየትኛውም መንገድ የሚሰጡ ወይም የሚተላለፉ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች የሌሎችን ሃይማኖት ወይም እምነት የማያንቋሽሹ፣ በሕዝቦች መካከል መቃቃቀር የማይፈጥሩ፣ ጥላቻ የማያጭሩ፣ የሌሎችን ሃይማኖት የማያንቋሽሹ ወይም የሌላውን ሰው መብት የማይነኩ መሆን አለባቸው የሚል ድንጋጌ አለ፡፡

ቀጣዩ አንቀጽ 15/4 ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ለማከናወን ካልተፈቀደ በስተቀር ማስተማርን ጨምሮ ሃይማኖታዊ ተግባራትን በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ በሌላ ሃይማኖታዊ ተቋም አካባቢ፣ መኖሪያ አካባቢዎች፣ ማጓጓዣዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የአየር መንገድ ተርሚናሎች፣ ወታደራዊ ካምፕ፣ ሕክምና ቦታዎች ወይም በሌሎች የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች መፈጸም የተከለከለ ነው ይላል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 16 ላይ የአምልኮ ወይም የመቃብር ቦታ አሰጣጥን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ሠፍረዋል፡፡ አንቀጽ 16/1 የሃይማኖት ተቋማት መሬት አቅርቦት በመሬት አጠቃቀምና የሊዝ ሕጎች መሠረት የሚወሰን ይሆናል ብሎ ሲደነግግ፣ 16/2 ደግሞ በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል የሚኖረው ርቀት ቢያንስ 500 ሜትር መሆን አለበት ይላል፡፡

በዚህ አንቀጽ ሥር የእምነት ተቋማት የወሰዱትን ቦታ ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋል እንዳለባቸው ከማስቀመጥ ባለፈ፣ አጠቃቀሙ ከከተሞች ዕድገት ጋር ታሳቢ ሊሆን እንደሚገባና አስፈላጊ ሲሆንም ሊነጠቁ እንደሚችሉ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 17 ላይ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ተዘርዝሯል፡፡ በዚሁ ሥር 17/4 ላይ በመንግሥት ተቋማት ቅጥር ግቢ ወይም ቢሮ ውስጥ በመሆን ሃይማኖታዊ ትምህርትን ማስተማር ወይም በቡድን የአምልኮ ተግባር ማከናወን ክልክል መሆኑ ተደንግጓል፡፡

ወረድ ብሎ 17/6 ላይ ግን የንዑስ አንቀጽ አራት ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተቋሙን ወይም ሌላውን የእምነት ተከታይ ሊያውክ በማይችል መልኩ በግል የሚደረግ አምልኮን ወይም ጸሎትን፣ ወይም በጋራ የሚደረግ የማዕድ ጸሎትን የሚከለክል አይደለም በማለት የክልከላው ወሰን ተቀምጧል፡፡

በአንቀጽ 18 ላይ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ወይም ሕዝባዊ ድርጅቶች ስለሚሰጡ አገልግሎቶች ነው የተደነገገው፡፡ በዚሁ ሥር 18/2 ላይ ደግሞ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ከየትኛውም ሃይማኖት ወይም እምነት ዓላማና ግብ ነፃ ሆኖ መቋቋምና መሥራት አለበት በማለት፣ የሃይማኖት ፖለቲካ ድርጅት በኢትዮጵያ የተከለከለ ስለመሆኑ አስፍሯል፡፡

በአንቀጽ 19 ትምህርትና ሃይማኖታዊ ተግባራትን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኛሉ፡፡ መደበኛ ትምህርት በማንኛውም ሁኔታ ሃይማኖታዊ ይዘት የሌለው መሆን እንዳለበት በዚህ አንቀጽ ሥር ተደንግጓል፡፡ በ19/5 ላይ በማንኛውም የትምህርት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርትን ማስተማር ወይም በቡድን ማምለክ የተከለከለ ነው በማለት ነው ይህን ድንጋጌ የሚያፀናው፡፡ ወረድ ብሎ በ19/6 ደግሞ ሃይማኖታዊ አለባበሶች ማንነትን ለመለየት በሚያስችል መልኩ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይገባል ሲል እንደ ሂጃብ ያሉ አልባሳት አጠቃቀምን የተመለከተ ድንጋጌ ያስቀምጣል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው አበበ ግን ስለረቂቅ አዋጁ ዋና መንፈስና ዕሳቤ ለመረዳት የአዋጁን ዓላማዎች በጥልቀት መመርመር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡  “በአንቀጽ አራት የአዋጁ ዓላማን ሲዘረዝር የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት ጥበቃና አተገባበር የሚመራበት ግልጽ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የዜጎችን የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት ማረጋገጥ የሚል ነጥብ ያስቀምጣል፡፡ ይሁን እንጂ የእምነት ተቋማቱ የሚመሩበት ዶግማና ቀኖና ወይም ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚያዘው ጉዳይ ምን ሊሆን ነው የሚለውን ጥያቄ ያጭራል፡፡ የሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት ማረጋገጥም ዓላማው እንደሆነም አዋጁ ያወሳል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ሃይማኖት እኩል አይደለም ወይ? ነፃ አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ አይደለም አሁን ባለንበት ወቅት በቀደመው አድልኦ ነበር በሚባልበት ዘመንም፣ በኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ሁሉም ቤተ እምነቶች የመስፋፋትና ቤተ እምነት የመገንባት ነፃነት አልነበራቸውም ወይ የሚል ተጠየቅ ይነሳል፡፡ በጣም አጥባቂ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ባለባቸው አካባቢዎች ሳይቀር እስልምና ተስፋፍቷል፡፡ በተቃራኒው እስልምና በጣም በሰፋባቸው አካባቢዎች የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኞችን ማግኘት ይቻላል፡፡ በወለጋና በሌሎችም የደቡብ አገሪቱ ክፍሎች የፕሮቴስታንት ሚሽነሪዎች ትምህርትና ሃይማኖትን እንዳስፋፉ መረሳት የለበትም፡፡ ያኔ መንግሥታዊ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ነበር በሚባልባቸው ወቅቶች ሳይቀር ብዙ ዓይነት ቤተ ዕምነቶች በኢትዮጵያ መስፋፋታቸው ይታወቃል፡፡ አሁን እኩልነት በሕገ መንግሥቱ ታውጆ ሳለ አዋጁ ይህን ለማረጋገጥ የተረቀቀ ነው ማለቱ ትንሽ ዓላማውን ገርገጭ ያለ ያደርገዋል፤” በማለት ያብራራሉ፡፡

ጠበቃው ትንተናቸውን በዚሁ ዙሪያ ሲቀጥሉም ሌላኛው የአዋጁ ዓላማ የሃይማኖት ተቋማት የሚመዘገቡበትና ዕውቅና የሚያገኙበትን ሥርዓት መፍጠር መሆኑን እንደሚያስረዳ ይገልጻሉ፡፡ ቀድሞም ቢሆን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተብሎ የሃይማኖት ተቋማት ሲመዘገቡ ነበር የሚሉት ባለሙያው፣ ቀጥሎ ደግሞ በሰላም ሚኒስቴር ሥር እንደሆነ አውስተዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት መንግሥት አወቃቸው አላወቃቸው ተጠሪነታቸው ለተከታዮቻቸው አይደለም ወይ? መሬት ስጠን የማምለኪያ ቦታ የምንገነባበት ብለው መንግሥትን ከመጠየቅ ውጪ መንቀሳቀስ የሚከለክላቸው ምንድነው? የመሬት አሰጣጡም ቢሆን የሊዝ አዋጁ ለሃይማኖት ተቋማት መሬት በድርድር እንደሚሰጥ ነው የሚደነግገው፡፡ የእምነት ተቋማት ማኅበራዊ ፋይዳቸው ብዙ በመሆኑና ብዙ ሰው ስለሚከተላቸው ተብሎ ለውለታቸው በድልድል ነው ቦታ ሲሰጣቸው የኖረው፡፡ መንግሥት መሬት ቢሰጠውም ባይሰጠውም ተከታዮቹ ለሚከተሉት ቤተ እምነት የራሳቸውን ይዞታ መሬት ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ሕጋዊነቱን እስከተከተሉ ድረስ በዚህ ቦታ ለመጠቀም ተቋማቱ ምን ይከለክላቸዋል? አንድ የእምነት ተቋም ተከታይ እስካፈራ ድረስ ለመመዝገብ የሚከለክለውስ ምንድነው? ፍቅርሲዝም ነኝ የሚለው ሰውዬ ነገ ብዙ ሺሕ ተከታዮች ቢያፈራ አትመዘገብም ሊባል ነው ወይ? ከማኅበረሰቡ ግብረ ገብና ሥነ ምግባር በተቃረነ መንገድ አምልኮ አይከውን እንጂ አንድ የእምነት ተቋም ፈቃድና ምዝገባ ለማግኘት የሚገድብ ሕግ የለም፡፡ የማኅበረሰቡ እሴት ወይም ‹‹ኖርም›› የራሱን ብይን የሚሰጥ ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ጨዋነት የጎደለው አምልኮ ላድርግ የሚል ተቋም ከመጣ ሕጉ ሳይሆን ማኅበረሰቡ የራሱ ‹‹ኖርም›› ስላለው በዚያ የተነሳ ያገለዋል ወይም ዕውቅና ይነፍገዋል፡፡ አንዳንዴ እምነት በሕግ ብቻ አትዳኘውም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ሲያክሉም፣ ‹‹ሌላኛው የሕጉ ዓላማ የሃይማኖት መቻቻልን መፍጠር እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ በሌላ በኩልም የመንግሥትና የሃይማኖትን መለያየት ለማስከበር ነው ተብሏል፡፡ ሃይማኖቶች እዚህ አገር እንዳይቻቻሉ ፈተና እየሆነ ያለው ግን ፖለቲካው እንጂ፣ ከእምነት ተቋማቱ የመነጨ ምክንያት አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ መንግሥታት በኖሩም ነገር ግን የሃይማኖትና መንግሥት መለያየት ዓለም አቀፍ መርህ ነው፡፡ ሴኪዩላሪዝም (ዓለማዊነት) አንዱ ትልቁ የዴሞክራሲ መርህ ነው፡፡ በእኛ አገርም ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ነው፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም ተብሏል፡፡ የመንግሥት የሚባል ሃይማኖትም እንደሌለ ተቀምጧል፡፡ ይህ መርህ እንዲከበር የሚያደርገው ግን በመንግሥት የሚታወጅ አዋጅ ነው ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በአብዛኛው በእኛ አገር ሴኪዩላሪዝም እየተጣሰ ነው የሚያስብለው፣ ሲኖዶስ እንዲሁም መጅሊስ በጠቅላይ ሚኒስትር ሲታረቅ ስታይ ነው፡፡ ለምን የአገር ሽማግሌዎች አያስታርቁም? የተከበሩ ቀሳውስትና ሼኮች ከየእምነቱ አሉ፡፡ የበቁ የሚባሉና ሰው የሚያደምጣቸው ከሁሉም አሉ፡፡ እነሱ አስታራቂ ለምን አይሆኑም? በመንግሥት አካላት በዚህ ደረጃ የአስታራቂነት ሚና መወሰዱ ከሴኪዩላሪዝም መርህ ጋር ትንሽ አይጋጭም ወይ? ሲሉ በጥያቄ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ሌላው ፍርድ ቤት ሄዶ ስለመዳኘትም ተቀምጧል፡፡ ይህስ ቢሆን የሴኪዩላሪዝም መርህን የተከተለ ነው ወይ? ፍርድ ቤትም ቢሆን እኮ ይመዝናል፣ ማስረጃ ይሰበስባል፣ አቤቱታ ይሰማል፣ ሌላም፣ ሌላም፡፡ ይህስ ከጣልቃ ገብነት አይታይም ወይ? ፍርድ ቤት ገለልተኛ ነው ቢባልም ዞሮ ዞሮ የመንግሥት ተቋም እኮ ነው፡፡ አንተና መንግሥት ብትካሰሱ ፍርድ ቤት ለመንግሥት ያጋደለ ብይን መስጠቱ አብላጫ ዕድል አለው፡፡ ፍርድ ቤት ለመንግሥት ባያጋድል ኖሮማ በአሥር ሺሕ ብር ደመወዝ ፎቅ የሚሠሩ በርካታ ባለሥልጣናት ባሉበት አገር ብዙ ሰዎች በተፈረደባቸው ነበር፤›› በማለትም የሕጉን ዓላማዎች በጥልቀት ፈትሸዋቸዋል፡፡

የአዋጁ አንቀጽ 23 የሃይማኖት ተቋም የገቢ ምንጭና ሒሳብ አያያዝ ሥርዓትን የሚመለከት ነው፡፡ በዚሁ ሥርም 23/1 ላይ የእምነት ተቋማት በገቢ ማስገኛ ሥራዎች መሰማራት ይችላሉ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ በአዋጁ መግቢያ ለሃይማኖት ተቋማት ትርጓሜ ሲሰጥ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች መሆናቸውን ያስቀመጠ በመሆኑ፣ ይህ አተረጓጎምም ከዚህ ድንጋጌ ጋር ሊቃረን እንደሚችል ይገመታል፡፡

በአንቀጽ 24 ደግሞ ከውጭ አገር ስለሚሰጥ ድጋፍ የተዘረዘረ ሲሆን፣ በዚህ ሥርም ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ከውጪ አገር የሚመጣ የገንዘብ ዕርዳታ ስጦታ ወይም የገንዘብ ድጋፎችን በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ እንዳለበትና ይህን ሲከውንም የለጋሹ ድርጅት ወይም ግለሰብ ስምና አድራሻ፣ የተለገሰው የገንዘብ ስጦታ ወይም ድጋፍ ዓይነትና መጠን፣ ስጦታው ድጋፉ የተሰጠበት ልዩ ዓላማ፣ እንዲሁም ሌሎች ከስጦታው ወይም ከድጋፉ ጋር የተቀመጡ ሁኔታዎች በዝርዝር መቅረብ እንደሚኖርባቸው ያዛል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ግዴታዎችና የተከለከሉ ጉዳዮችን በሚመለከቱ አንቀጾች ላይ ያተኮሩ ማብራሪያዎችን የሰጡት አቶ አበባው በበኩላቸው፣ በዚህ ግርጌ ሲያሰፍር የተቋማቱን የገቢ አሰባሰብና የወጪ አስተዳደር በሕግ እንዲተዳደር ማድረግ ተብሎ መቀመጡን ጠቁመዋል፡፡ “ቀድሞውንም ቢሆን የእምነት ተቋማት መንፈሳዊ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ብቻ ሳይሆንኑ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ሥራዎችን ፋይናንስን ጨምሮ የሚሠሩ አደረጃጀቶች አሏቸው፡፡ ስለዚህ ሕጉ ቀድሞውንም የነበረን አካል ይኑር እያለ ነው፡፡ ሌላው በሃይማኖት ሽፋን ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች የማሳወቅ ግዴታ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ተራ ሆቴሎችና ትንንሽ ተቋማት ጭምር የሚያደርጉት ግዴታ ነው፡፡ የኦርቶዶክስም ሆነ የሙስሊም ተቋማት በሥራቸው ብዙ ሕዝብ የሚመሩ ግዙፍ ተቋማት ናቸው፡፡ ሕጉ ብቻ ሳይሆን ራሱ ምዕመኑም ጭምር ተቋማቱን ይጠብቃል፡፡ በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ ለእምነት መሞት በኢትዮጵያ ባህል እንደ ፅድቅ ነው የሚቆጠረው፡፡ ወደድንም ጠላንም ይህ ሃይማኖት ከሕይወት በላይ የሆነበት አገር ነው፡፡ አንድ ቦታ ተቋማቱ የሆነ ነገር ቢፈጠርባቸው በየአካባቢው ሆ ብሎ ይነሳል፡፡ የእምነት ተቋማቱን ጠባቂ መንግሥት ብቻ ሆኖ መቅረቡና ወንጀል ሲፈጸም አጋልጡ መባሉ፣ ከዚህ አንፃር ክብደት የሚሰጠው ጉዳይ አይመስለኝም፤” በማለት ነው ጠበቃው ምልከታቸውን ያጋሩት፡፡

‹‹ከዚሁ ጋር በማያያዝ በሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ተሳታፊ መሆንና መተላለፊያ መሆን የተከለከለ ነው ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የእምነት ተቋማት መሠረታዊ የገቢ ምንጭ ምዕመናን ናቸው፡፡ የሃይማኖት ኦዲት አቀራረብን በሚመለከትም ቢሆን የሴኪዩላሪዝም መርሁን ለማስከበር ፈተና አይሆንም ወይ? አንድ ምዕመን በግሉ አንድ ቤተ ክርስቲያን ሊያሠራ ይችላል፡፡ ይህን ከየት የመጣ ገቢ ብለው ተቋማቱ ሊያቀርቡ ነው? በምፅዋት የተሰበሰበ ገንዘብን ምን ሊሉት ነው? የእምነቱ ተከታዮች በገንዘብ ብቻ አይደለም በዓይነትና በሙያም ለሃይማኖታቸው ይሰጣሉ፡፡ ብሎኬት፣ አሸዋ፣ ሲሚንቶ፣ ወርቅ፣ ዣንጥላ፣ ሻማ፣ እጣን፣ ወዘተ አዋጥተው ነው ተቋሞቻቸውን ያቀኑት፡፡ የኦዲት ሪፖርት ለዚህ ሁሉ ይቅረብ ከተባለ የሚፈጠረው ችግር ውስብስብ ነው፤›› የሚል ይዘት ያለው ሐሳብም ሰንዝረዋል፡፡

በአንቀጽ 25 ላይ የሃይማኖት ተቋማት የኦዲት ሥርዓት የተጠቀሰ ሲሆን፣ በሦስት ወራት ጊዜ በገለልተኛ ኦዲተር አሠርቶ ማቅረብ እንዳለበት የሚመለከተው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ይህን ሪፖርት እንደሚያጣራና አስፈላጊ ከሆነ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ተቀምጧል፡፡

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች በተቀመጡበት በአዋጁ ክፍል ስድስት ሥር አንቀጽ 29 የውጭ አገር ዜጋን ቀጥሮ ስለማሠራት ሠፍሯል፡፡ በ29/1 አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ያልተሰጠውን የውጭ ዜጋ ማሠራት አይቻልም ይላል፡፡ በ29/2 ተቀጣሪው የውጭ ሠራተኛ በምን አግባብ የሥራና መኖሪያ ፈቃድ እንደሚያገኝ የተቀመጠ ሲሆን፣ የውጭ ዜጋን ተቀብሎ ለማሠራት ለሚመለከተው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በማሳወቅ የሥራ ፈቃድ ከሚመለከተው አካል ለማግኘት የሚያስችለውን የድጋፍ ደብዳቤ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማግኘት አለበት ሲል ነው የደነገገው፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው በሰጡት ማብራሪያ፣ የማኅበረሰቡ ሥነ ምግባራዊ ዕሴቶች አንዳንዴ ከሕግም ከፍ ያለ ቦታ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና የእምነት አባቶች ትግራይ በሄዱ ጊዜ እንደዚያ በፀጥታ አካላት በር ላይ ሲፈተሹ መታየቱ ኅብረተሰቡን ክፉኛ አስቆጥቶት እንደነበር ለዚህ በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ “ታላቅን ማክበር በተለይም የእምነት አባትን ማክበር በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ ነው ይህ የሆነው፡፡ የእምነት አባቶችን እንደ ወንጀለኛ ቆጥሮ በአደባባይ መዝለፉ፣ አክብሮት የጎደለው አያያዝ መስጠቱና ማውገዙ ለደኅንነትና ለሰላም ማስከበር ሲባል የተደረገ ነው ቢባልም ዞሮ ዞሮ ተቃውሞ መፍጠሩ መታወቅ አለበት፤” የሚል ሙግትም አቅርበዋል፡፡

‹‹የተከለከሉ ቦታዎች ላይ ሃይማኖታዊ ቅስቀሳ ማድረግ የሚለውም ቢሆን ያልተብራራ አንቀጽ ነው፡፡ የምርጫ ሕጉ ለምሳሌ ምን ይላል የሚለውን ማዛመድ ለዚህ አስፈላጊ ነው፡፡ የመቃወምና የመሠለፍ ዴሞክራሲያዊ መብት ምን ይላል የሚለውም ማመሳከሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ የመሬት አሰጣጡን ስናይ የሊዝ አዋጁን አንስተን እንዳዛመድን ሁሉ ባልተፈቀደ ቦታ ሃይማኖታዊ ቅስቀሳ ማድረግ የሚለው ጉዳይም ከሌሎች ሕጎች ጋር ተዛምዶ ሊታይ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አንድ ቀን በተከለከለ ቦታ ሃይማኖታዊ ቅስቀሳ አደረገ በሚል አሻሚ ሁኔታ፣ ሰዎች በሕግ የመጠቃት ዕጣ ሊገጥማቸው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

“የእምነት ተቋማት የውጭ አገር ሠራተኛን ቀጥረው ስለሚያሠሩበት ሁኔታ በሕጉ ተቀምጧል፡፡ ይህ ፍፁም አሻሚ ድንጋጌ ነው፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ መሠረት ለትርፍ የሚሠራና ለትርፍ የማይሠራ ሠራተኛ ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በእኛ አገር ነባራዊ ሀቅ የዜጎችን የሥራ ዕድል እንዳይሻሙ ተብሎ ብዙ የውጭ ሠራተኞች በተወሰኑ ሥራዎች እንዳይገቡ የሚል ሕግ ቢበጅም፣ ነገር ግን ይህን በሚቃረን መንገድ ጀብሎ እስከመሸጥ የሚሠሩ ቻይኖችና ህንዶች እናያለን፡፡ ይህ ተጨባጭ ሁኔታ ባለበት ያውም ለፅድቅ የሚደረግ የሃይማኖታዊ አገልግሎትን የውጭ ሠራተኛ በሚል መዳኘት ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሚመለከተው አካል የድጋፍ ደብዳቤ ካላገኙ በስተቀር የውጭ ሠራተኞች የሥራ ፈቃድ አያገኙም የሚለው ንዑስ አንቀጽ ደግሞ፣ ጉዳዩን የበለጠ ያወሳስበዋል፤” የሚል ሥጋት እንዳላቸው በመጥቀስ ነው ጠበቃው ማብራሪያቸውን የደመደሙት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -