Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጭምር እንዳረጋገጠው የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ገብቶ ቆይቷል፡፡ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሊያጋጥማቸው ቢችልም ንብ ባንክ ግን በተለየ ችግር ውስጥ እያስገባው በመሆኑ በብሔራዊ ባንክ የቅርብ ክትትል የሚደረግበት እስከመሆን ደርሷል፡፡ በዚሁ ምክንያት ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ባንኩ ለገጠመው ችግር ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የቀድሞ 12 የቦርድ አባላት ለስድስት ዓመታት በየትኞቹም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንዳይሠሩ አግዷል፡፡ አዲስ የቦርድ አባላት በማስመረጥም ወደ ሥራ እዲገቡ አድርጓል፡፡ አዲሱ ቦርድም የባንኩን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሰናብቶ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይሞ ነበር፡፡ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲያፈላልግ ቆይቶ የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት እመቤት መለሰ መለሰ (ዶ/ር)ን መርጧል፡፡ ሹመታቸውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፀድቆ ሥራ ጀምረዋል፡፡ አዲሷ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከ22 ዓመታት በላይ የሥራ ላምድ ያላቸው ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከማርች 2022 ጀምሮ የስትራቴጂ ፕላኒንግና ትራንስፎርሜሽን ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግና ፋይናንስ ያገኙት እመቤት (ዶ/ር)፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) በቢዝነስ ሊደርሺፕ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያ ሲሆኑ፣ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶችም አገልግለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሪፎርምና ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ቢሮን በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ ኮርፖሬት የሥራ ጥራት ማረጋገጥና ሪፖርቲንግ ምክትል ፕሬዚዳንትና የብድር ትንተና ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ቀደም ብለውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በመምርያ ኃላፊነት ሲያገለግሉ ነበር፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታቸው የነበራቸው አስተዋጽኦ ቀላል የማይባል እንደነበረ፣ ባንኩም ለደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉና የሚያውቋቸው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በእመቤት (ዶ/ር) የ22 ዓመታት የሥራ ልምድና ሒደት፣ እንዲሁም ከዚህ በኋላ በንብ ባንክ ሊሠሩ ያቀዱትን ሥራና የባንክ ኢንዱስትሪውን በአጠቃላይ በተመለከተ ዳዊት ታዬ ከእመቤት መለሰ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ 22 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ብዙዎች አዲሷ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት ማን ናቸው? ከየት ተነስተው ነው እዚህ የደረሱት ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይፈልጋሉ፡፡ በተለይ በንግድ ባንክ ውስጥ በርካታ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ስለሠሩ ትንሽ ማብራሪያ ቢሰጡ?

/ እመቤት፡- ለሃያ ሁለት ዓመታት የሠራሁት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ባንኩን የተቀላቀልኩት የማኔጅመንት ሠልጣኝ ሆኜ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቅጥር ሒደት እስኪያልቅ ድረስ ለአምስት ወራት ያህል በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሠርቻለሁ፡፡ በመሀሉ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመግባት ሙከራ አድርጌ ነበር፣ ሙከራዬ ግን አልተሳካም፡፡ ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተቀላቀልኩ፣ ከዚያ አልተንቀሳቀስኩም፡፡ ለአምስት ዓመታት ሠራሁና በቀኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ማስተርሴን ለመሥራት ሥራውን ለመልቀቅ አስቤ የነበረ ቢሆንም፣ ባንኩ ስፖንሰር አድርጎኝ ትምህርቴን እንድማር ደገፈኝ፡፡ የማስተርስ ትምህርቴን ከዓመት ከስድስት ወራት በኋላ እንደጨረስኩ ወደ ሥራዬ ተመለስኩ፡፡ ባንኩ ማስተርሴን ካስተማረኝ በኋላ ባንኩን ለመልቀቅ በጣም ተቸገርኩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ውስጤ መወሰን አልቻለም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቤቴን ያህል ነው የምወደው፡፡ በንግድ ባንክ ቆይታዬ ከማኔጅመንት ክፍል ጀምሮ በቅርንጫፎች ሳይቀር ሠርቻለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሠራሁት ግን በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ በብድር ክፍል ነው፡፡ ከብድር ኦፊሰርነት ጀምሬ የብድር ኤክስፐርት ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ ዶክትሬቴን ከወሰድኩ በኋላ ወደ ሪስክ ማኔጅመንት ዲፓርትመንት ተዘዋወርኩኝ፡፡ በዚህም ኃላፊነቴ ሥልጠና የምሰጥበት ጊዜ ይበዛ ነበር፡፡ ይህ ሥራ ለእኔ ሌላ ዕድል ነው የሰጠኝ፡፡ የማላውቀውን ክህሎት ነው ያገኘሁበት፡፡ በተለይ ማስተማር እንደምችል ነው ያሳየኝ፡፡ በዚያን ወቅት ኮሜርስ ኮሌጅ በትርፍ ጊዜዬ አስተምር ነበር፡፡ ከኮሜርስ መምህራን ጋር ሆኜ ‹‹Banking Practice and Principles›› የሚል መጽሐፍ ለመጻፍም አስችሎኛል፡፡ በዚህ የማስተማር ሥራዬ የባንክና የፋይናንሻል ኢንስቲትዩሽን ነክ የሆኑ ኮርሶችን እሰጥ ነበር፡፡ ከዚያም በቢዝነስ ሊደርሺፕ ላይ የዶክትሬት ትምህርቴን ጀመርኩ፡፡

በዚህ ወቅት ደግሞ በንግድ ባንክ ውስጥ የግዥ ሥራ አስኪያጅ ነበርኩና የነበረውን የግዥ ሲስተም ጥሩ እንዳልነበር ስለተረዳሁ፣ ቦታው ላይ በተመደብኩ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ሥራውን አስተካክዬ ማስኬድ እፈልጋለሁ ብዬ በወቅቱ የነበሩትን ምክትል ፕሬዚዳንት ፈቃድ ጠየቅሁ፡፡ ከዚያም የፋሲሊቲ ፕሮሰሱን በአዲስ መልክ እንዲስተካከል አደረግኩኝ፡፡ ይህ ለሥራዬ ደግሞ ሌላ ከፍተኛ ዕውቅና ሰጠኝ፡፡ የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆንኩ፡፡ ዶክትሬቴን እየተማርኩ ነበርና ትምህርቴን እስክጨርስ ልውጣ ብልም እዚያው ማሠልጠን እንደምችል ተነገረኝ፡፡ በቋሚነት አሠልጣኝ ሆኜ ከሊደርሺፕ [አመራር] ወደ አሠልጣኝነት ገባሁ፡፡ የባንኩን ሠራተኞች ለአንድ ዓመት አሠለጠንኩ፡፡ የዶክትሬት ትምህርቴን እንደጨረስኩ ጊዜ ካለሽ ወደ ሊደርሽፕ ተመለሺ የሚል ጥያቄ አሁንም ከማኔጅመንቱ ቀረበልኝ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 የክሬዲት ኳሊቲ አሹራንስ ዳይሬክተር ሆንኩኝ፡፡ ይህ አዲስ ኮንሰፕት (ዕሳቤ) ነው፡፡ ለባንኩም አዲስ ነገር ነው፡፡ ይህም የደንበኞችን የብድር ሒደት ጤናማነት መከታተልን ይመለከታል፡፡ በባንክ ሥራ ውስጥ ትልቁ ሥራ ብድር በመሆኑ እሱን የበለጠ አጠንክረን ለመሄድ የሚያስችለን አዳዲስ ፕሮሲጀሮችን በማውጣት፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ዲዛይን በማድረግ ሲስተም ማዘጋጀትን ይመለከታል፡፡ ለዚህ ሲስተም በአጭር ጊዜ ፕሮሲጀር ዲዛይን አድርገንና ፖሊሲ አውጥተን ሥራውን ጀመርን፡፡ በሚገርም ሁኔታ ውጤታማ ሥራ ሠራን፡፡ ከዚያ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የማስተዋወቅ ሥራ ውስጥ ገባን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተርበዚህ ወቅት ያስተዋወቃችኋቸው አዳዲስ አገልግሎቶች የትኞቹ ነበሩ?

/ እመቤት፡- የዳያስፖራና የኤንጂኦ ፕሮጀክቶችን የመሳሰሉትን ቀርፀን ማስተዋወቅ ችለናል፡፡ ሌሎች አገልግሎቶችም እንዲጀመሩ አድርገናል፡፡ በዚህ ውጤታማ በመሆኔ ይመስለኛል በስድስት ወራት ውስጥ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆንኩት፡፡ በዚህ አዲሱ የኃላፊነት ቦታ በዋናነት የተለያዩ የብድር ሥራዎችን ከኋላ ሆኖ መሥራት ነበር፡፡ የብድር ማፅደቅና የመሳሰሉ ሥራዎችን እንሠራ ነበር፡፡ የደንበኞችን ፍላጎት ከማየት፣  የብድር ጤናማነቱን ከመከታተል አንፃርና የመሳሰሉትን ሥራዎች ሠራን፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ባንኩ ሌላ አዲስ ነገር አሰበ፡፡ ኮርፖሬት ኳሊቲ አሹራንስ የሚባል ሰፋ ባለ ደረጃ ሰባት ዲፓርትመንቶች ያሉት ክፍል ተቋቋመ፡፡ በዚህ ክፍል የሚሠራው ሥራ ቀደም ብዬ ከነበርኩበት ሥራ ጋር ተያያዥ ስለነበር ማኔጅመንቱ ወደ እዚህ ክፍል አዛወረኝ፡፡ እዚህ ብዙ ጥሩ ጥሩ ሥራዎች ሠራን፡፡ በተለይ የባንኩን የጥራት ልህቀት (Quality Excellence) ሞዴል ዲዛይን አደረግን፡፡ ከዚያም የማኔጅመንት ለውጥ ሲመጣ በቦርድና በማኔጅመንቱ ታምኖበት ባንኩ ሪፎርም መደረግ አለበት ተብሎ ወደ ሥራ ሲገባ፣ ለዚሁ ሥራ የሪፎርምና ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ቢሮ ተቋቋመ፡፡ አሁንም በምክትል ፕሬዚዳንትነት ይህንን የሪፎርም ቢሮ እንድመራ ኃላፊነት ተሰጠኝ፡፡ ይህ ለእኔ ትልቅ ዕድል ነበር፡፡

በተለይ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ መልካም አጋጣሚን ነው የፈጠረልኝ፡፡ አጠቃላይ ግምገማ (Comprehensive Assessmnet) የስትራቴጂ ሥራ ነበረው፡፡ ይህንን እንድመራ ነው የተደረገው፡፡ ሪፎርሙ ሁሉን አቀፍ ነበር፡፡ ይህንን ሥራ በጣም ታዋቂ የሆነ አማካሪ ድርጅት ቀጥረን ነበር ያሠራነው፡፡ ከዚያ አማካሪ ድርጅቱ ጋር ከቅጥሩ ጀምሮ የባንኩን ችግሮች ለመፈተሽ (Diagnostics) አብረን ነው የሠራነው፡፡ ከቅጥሩ በኋላ በሰባት ወራት የሚሠራ ሥራ ነበርና ጨረስን፡፡ ይህንን እንደጨረስን በፊፎርሙ መሠረት ወደ ትግበራ ገባን፡፡ የድርጊት መርሐ ግብሩን ይዘን ለባንኩ አዲስ መዋቅር ሠራንለት፡፡ ባንኩን ደንበኛ ተኮር አደረግነው፡፡ በዚያ ስትራክቸር (መዋቅር) መሠረት ሠራተኞች ተመደቡ፡፡ ይህንንም ትግበራ የመምራቱ ኃላፊነት ተመልሶ ለእኔ ተሰጠ፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክት ቢሮው ሥራውን ጨርሶ አቆመ፡፡ ትግበራውን ከስትራቴጂው ጋር መጣመር ስላለበት ይህን ለማስተግበር፣ እ.ኤ.አ. መጋቢት 22 ቀን 2022 የስትራቴጂ ፕላኒንግና ትራንስፎርሜሸን ምክትል ፕሬዚዳንት ኃላፊነት ሊሰጠኝ ቻለ፡፡  

ሪፖርተርይህ የኃላፊነት ቦታ ምን ዓይነት ሥራ ነበረው?

/ እመቤት፡- ሲሰጠኝ የኃላፊነት ቦታው የነበረው እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 20 ቀን 2022 እስከ ዴሴምበር 31 ቀን 2023 ድረስ የሚተገበር የ24 ወራት ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ማዘጋጀት ነበር፡፡ ይህንን ማስፈጸም ዋነኛ ሥራችን ሆነ፡፡ በወቅቱ የአምስት ዓመታት ስትራቴጂ የነደፍን ቢሆንም፣ የሁለት ዓመታት ደግሞ የትግበራ ፍኖተ ካርታ (Implementation Roadmap) ነበረው፡፡ ይህንን ፍኖተ ካርታ እንደሚመራ ሰው ኃላፊነት ሲሰጠኝ የራሴም ኃላፊነት ነበር፡፡ የባንኩ ሚና ብቻ አልነበረም፡፡ በዚያን ወቅት  የተሰጠኝን ትራንስፎርሜሽን ሥራ ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ ካጠናቀቅኩ በኋላ አዲስ ሥራ ለራሴ መሥራት አለብኝ ብዬ ወስኜ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ራሴን በሌላ ቦታ አገኘዋለሁ የሚል ዕቅድ ይዤ ነበር ሥራዬን ስሠራ የነበረው፡፡ በዚህም መሠረት የሁለት ዓመት በሪፎርሙ መሠረት የትግበራ ሥራዬን ዲሴምበር ላይ እንደማጠቅናቅቅ ሳስብ፣ ለራሴ ምን መሥራት እንደሚኖርብኝ ዕቅድ አወጣሁ፡፡ ይህንን የተሰጠኝን ኃላፊነት ሳልጨርስ ከባንኩ እንደማለቅ ለራሴ ቃል ገብቼ ስለነበር፣ በዚህ ዕሳቤ በቻልነው ልክ ሥራውን ሠራን፡፡ ጥሩ የሚባልም ስኬት አስመዘገብን፡፡

ሪፖርተርእንዳሉት የሁለት ዓመታት የትግበራ ሥራውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ራስዎ ሥራ ገቡ?

/ እመቤት፡- ሥራውን ከጨረስኩ በኋላ ወዲያው ወደ ራሴ ሥራ ለመሄድ ተዘጋጀሁ፡፡ እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 1 ቀን 2024 ጀምሮ እኔን የሚተካ ሰው አዘጋጅቼ ከኋላ እያገዝኩኝ የዕውቀት ሽግግሩን ማስኬድ ጀመርኩ፡፡ ሁልጊዜ እኛ አገር መሥራት ያለብን በተከታታይነት በፕላን ሥራ እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ ኃላፊ በራሱ ፈቃድ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄድ፣ ያለውን ሥራ ቆጥሮ አስረክቦ በእርግጠኝነት ሥራው እየተሠራ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ መውጣት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ ከሚጠበቅብኝ ኃላፊነት አንፃር በቅድሚያ ይህንን ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡

ሪፖርተርእንዲህ ባለ ሁኔታ ባንኩን ከለቀቁ በኋላ ሊሠሩ ያሰቡት የግል ሥራዎ ምን ነበር?

/ እመቤት፡- ትልቁ ዕቅዴ አማካሪ ድርጅት ማቋቋም ነው፡፡ ለሚቋቋመው ድርጅት ስያሜ አፅድቄ ነበር፡፡ የምሠራውም በዚሁ ፋይናንስ ዘርፍ ነው፡፡ ከማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ሰርቲፋይድ ማኔጅመንት ኮንሰልታንት ሆኜ ነበር፡፡ እሱን ሒደት ጨርሼ ነበር፡፡ ይህንን ይዤ የንግድ ፈቃድ አውጥቼ በይበልጥ ባንኮች ላይ ትኩረት በማድረግ ነው ወደ ሥራ ልገባ የነበረው፡፡ 

ሪፖርተርየራስዎን ድርጅት አቋቁመው ለመሥራት ያሰቡት በባንክ ዘርፍ ላይ እንዲያተኩር ለምን ፈለጉ?

/ እመቤት፡- የአገራችን የፋይናንስ ዘርፍ ብዙ ክፍተቶች አሉበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በግል ያደረግሁት ግምገማ (Assessment) ይህንን አመላክቶኛል፡፡ በተለይ ከሰው ኃይልና ከአመራር አኳያ ውስን ነው፡፡ ዶክትሬቴን ስፔሻላይዝ ያደረጉት በቢዝነስ ሊደርሽፕ ላይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ከመሰማራቴ አንፃር ላሳደገኝ ዘርፍ ወይም እስካሁን እኔ ላይ ለለፋብኝን ዘርፍ እኔ ደግሞ ትንሽ መመለስ አለብኝ የሚል ዕቅድ ነበረኝ፡፡ ይህንን ከማሳካት አንፃር ገለልተኛ ሆኜ መሥራት የምችለው ደግሞ አማካሪ ድርጅት በማቋቋም ነው የሚል ሐሳብ ነበረኝ፡፡ ሁለተኛ ውሳኔዬ ደግሞ በዚሁ ዘርፍ ሴቶች ላይ ለመሥራት ነው፡፡ ይህንን ያሰብኩትም በፋይናንስ ዘርፉ እኔም በቅርብ እንዳየሁት የሴት መሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብዬ ስፈትሽ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ተረዳሁ፡፡ ለምሳሌ እኛ ሴቶች ራሳችን ችግሮችን ተጋፍጦ መውጣት ላይ ትንሽ ውስንነቶች ይታዩብናል፡፡ ማኅበረሰቡም ላይ ያለው አመለካከት ‹‹ሴት ናት ይህን ትችለዋለች ወይ?›› የሚል ነገርም የራሱ ተፅዕኖ ስላለው ያልተለወጠ ነገር እንዳለ ዕሙን ነው፡፡ እኔን በተመለከተ የውጭ ተግዳሮት ብዙ አያስጨንቀኝም፡፡ በግሌ ሌላ ሰው የሚያደርስብኝ ተግዳሮት ወይም አጥር አያስጨንቀኝም፡፡ ሰው የውስጡን አጥር ነው ማፍረስ ያለበት እንጂ፣ የሆነ ሰው ከውጭ የሚያጥርብህ  ሊረብሽህ አይገባም፡፡ አንተ ራስህን አጠንክረህ ከወጣህ አጥሩን ታልፋለህ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ የተነሳ በተለይ በባንክ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት እህቶቼ ላይ መሥራት አለብኝ ብዬ ከሥራዎቼ ውስጥ በዕቅድ ይዤ ነበር፡፡ ዕቅዴ ውስጥ ያለው እንዲያውም ሴቶች ለምንድነው በአጥር የሚገደቡት የሚለው ጥያቄ ሁሌ ስለሚያሳስበኝ በሴቶች ጉዳይ ላይ ከሚሠሩ ድርጀቶች ጋር መሥራት ነበር፡፡

ሪፖርተርከንግድ ባንክ ከወጡ በኋላ ለረዥም ጊዜ ሲያስቡት የነበረውን የአማካሪ ድርጅት አቋቁመው የመሥራት ዕቅድዎ አሁን አልሆነም፡፡ ወደ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ መጥተዋል፡፡ የቀደመ ዕቅድዎን ለውጠው ንብ ባንክን ለመቀላቀል እንዴት ወሰኑ? እንዴትስ ለዚህ ኃላፊነት ቦታ ታጭተው ተመረጡ?

/ እመቤት፡- ቀደም ብዬ እንዳልኩት ወደ ራሴ ሥራ ለመግባት ስዘጋጅ በነበረበት ጊዜ ነው የንብ ባንክ ጉዳይ የመጣው፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መልቀቄን ያወቁ ሰዎች ብዙዎች በራሳቸው መንገድ ቀርበው አናግረውኛል፡፡ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስለሚፈልግ እዚያ ብትሞክሪ የሚል ጥያቄ መጣልኝ፡፡ መጀመሪያ ላይ ይህን ሥራ ለማግኘት ብዙም አላሰብኩበትም ነበር፡፡ ትኩረቴ ልሠራ ወደ ተነሳሁበት ሥራ ያጋደለ ነበር፡፡ 

ሪፖርተርወደ ንብ ባንክ እንዲመጡ ጥያቄው ሲቀርብልዎ እምብዛም የነበሩበት ምክንያት ስለንብ ባንክ ይሰሙ የነበሩ ነገሮች ናቸው? ባንኩ ችግር እንደገጠመው የሚገልጹ መረጃዎችስ በወቅቱ ነበረዎት?

/ እመቤት፡- በጥልቀት ባይሆንም እንኳን መረጃው ነበረኝ፡፡ በጣም ያስደነቁኝ ብሔራዊ ባንክ የሄደባቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ አሥራ ሁለት የቦርድ አባላት ስለመነሳታቸውና የመሳሰሉት መረጃዎች ነበሩኝ፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ሰምቻለሁ፡፡ ወደ ንብ ባንክ እንድገባ ሲገፋኝ የነበረው ሰው እኔ ልሠራ ያሰብኩትን ነግሬው በዚሁ መንገድ እንደምሄድ ገልጬለት ነበር፡፡ እሱ ግን ባንኩ ያለበትን ችግር መፍታት በራሱ ትልቅ ስኬት ነው አለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እንደሞክረው ተስማማን፡፡ መጨረሻ ላይ ጥያቄው በይፋ መጣ፡፡ በተፈጥሮዬ ተግዳሮት በጣም ነው የምወደው፡፡ መደበኛ የሆነ የተለመደ ሥራን መሥራት አልወድም፡፡ ማንም ሰው ይሠራዋል ብዬ ነው የማምነው፡፡ የሰው ልጅ ተፈትኖ ካላለፈ ወይም እኔ ታግዬ ካላለፍኩ አቅሜ የቱ ጋ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በነበርኩበትም ድርጅት በዚያ ነው የምታውቀው፡፡

ሪፖርተርንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የገጠመውን ችግር በተወሰነ ደረጃ እንደሰሙ ገልጸውልኛል፡፡ አለ የሚባለውን ችግር ገብቼ አስተካክላለሁ ብለው አምነው ኃላፊነቱን ተቀብለዋል ማለት ይቻላል? በእርግጥ ችግሩን እፈታለሁ ብለው ያምናሉ?

/ እመቤት፡- መቶ በመቶ አስተካክላለሁ ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ ይህ ባይሆን ኃላፊነቱን አልወስድም ነበር፡፡ ወደ እዚህም መምጣት አላስብም ነበር፡፡

ሪፖርተርእርግጠኛ ነዎት?

/ እመቤት፡- በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ በነበሩኝ ውይይቶችም ሆነ ምክክሮች ይህንኑ ነው ሳነሳ የነበረው፡፡ የማልቀይረው ከሆነ ለምን እመጣለሁ? ለመውደቅ በፍፁም ዝግጁነት የለኝም፡፡

ሪፖርተርበነገራችን ላይ ይህንኑ ኃላፊነት ከተረከቡ የቀናት ዕድሜ ቢሆንም፣ በባንኩ ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ጥልቀት በደንብ ለመመልከት ዕድል አግኝተዋል?

/ እመቤት፡- አይቻለሁ፡፡

ሪፖርተርአሉ የተባሉት ችግሮች የሚስተካከሉ ናቸው? እኔ ልለውጠውና ላስተካክለው የምችለው ነው ብለው አምነዋል? ምናልባት ከገቡ በኋላ ያዩት የተለየ ነገር ካለ ብዬ ነው?

/ እመቤት፡- መቶ በመቶ አስተካክለዋለሁ አልኩህ እኮ፡፡ በነገራችን ላይ እኔ  ብቻዬን አይደለሁም፡፡ ይህ በባንኩ ላይ የመጣ ችግር የቅርብ ጊዜ አይደለም፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ቀስ በቀስ እያደገ፣ አሁን የደረሰበት ደረጃ የደረሰው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ‹‹Banking is a Matter of Trust›› (ባንክ እምነት የሚጣልበት ሥራ) ነው፡፡ በንብ ባንክ ተፈጠሩ የተባሉት ችግሮች ደንበኛን እምነት እንዲያጣ አድርገውታል፡፡ ቀላል ነገር እኮ ነው፣ የባንክ ሥራን በሰው ብር ነው የምታሠራው፡፡ ቢዝነሱ በሰው ብር የሚሠራ ነው፡፡ ይህ ማለት ሰውዬው የሰጠንን ገንዘብ አስቀምጠህ በሚፈልግበት ሰዓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መመለስ ማለት ነው፡፡ ባንኩ ያንን ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡ ይህን የተረዳ ደንበኛ ግንኙነቱን እንዲገደብ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ የእኔም የመጀመሪያ ሥራዬ ያንን እምነት ማምጣት ነው፡፡

ሪፖርተርእንዴት?

/ እመቤት፡- አንደኛ ንብ ባንክን እንዲሁ ስታስበው ትልቅ ባንክ ነው፡፡ ‹‹ፈርስት ጄኔሬሽን›› ባንክ ነው፡፡ ትልቅ ሀብት ያለው ባንክ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ሕንፃ ሠርቶ የሚንቀሳቀስ ባንክ ነው፡፡ ትልቅ ገጽታ ያለው ባንክ ነው፡፡ እኔ የማውቀው ንብ ባንክ የታታሪዎች ባንክ መሆኑን ነው፡፡ ባንኩን እዚህ ያደረሱ ታላላቅ፣ ለውጥ የሚፈልጉ የሥራ ሰዎች የሠሩት ባንክ ነው፡፡ እነዚያ የሥራ ሰዎች አሁንም አሉ፡፡ ምናልባት ትንሽ ርቀው ሊሆን ይችላል፡፡ ለምን ራቁ? በነበሩበት ጉዳዮች ርቀውም ቢሆን የባንኩን ውድቀት ግን በፍፁም አይፈልጉም፡፡ ሌላው ትልቁ እንደ ጀርባ አጥንት ሊሆነኝ ይችላል ብዬ የማስበውና የነበረውን ችግር መቶ በመቶ እቀይራለሁ ብዬ እንድተማመን የሚያደርገኝ፣ ከእነዚያ ሰዎች ጋር የምሠራ በመሆኔ ጭምር ነው፡፡ እነዚያ ሰዎች ይህ ባንክ እንዴት ይቀየራል የሚል ጥልቅ ምልከታ ያላቸው ናቸው፡፡ እኔም ለባንኩ የሚመጥን ዕውቀትና ልምድ አለኝ፣ ፈጣሪም ይረዳኛል፡፡

ሪፖርተርበነገራችን ላይ እርስዎረዥም ጊዜ መንግሥታዊ ባንክ ውስጥ ነው የሠሩት፡፡ አሁን ወደ ግል መጥተዋል፡፡ የመንግሥት ባንክ መምራትና የግል ባንክ መምራት ልዩነት ሊኖረው ይችላል?

/ እመቤት፡- በነገራችን በመንግሥት ባንክ በብዙ ነገሮች ታጥረን ነው የምንሠራው፡፡ የግል ባንክ ስትሠራ የተለየ ነገር ቢኖርም በጥቅል ስታየው ግን ልዩነት የለውም፡፡ እኔ ስሠራ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ስለሆነ ብዙዎች ባንኩ በመንግሥት እየተደገፈ የሚሠራ ይመስላቸዋል፡፡ በእርግጥ ከመንግሥት የሚገኝ ድጋፍ አለ፡፡ ያንን ድጋፍ መንግሥት ለግል ባንኮችም ይሰጣል፡፡ ሲቋቋም ባለቤትነቱ የግል ይባል እንጂ በሲስተሙ ባንኮች በመንግሥት ሥር ናቸው፡፡ 

ሪፖርተርንብ ባንክ ሥራ ከጀመሩ በኋላ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መክረዋል፣ ከማኔጅመንት አባላትና ከደንበኞች ጭምር ተነጋግረዋልና ባንኩን ሪፎርም ከማድረግ አኳያ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድዎ ምንድነው? ለምሳሌ የመቶ ቀናት ዕቅድዎ ምንድነው? ባንኩ አሁን ካለበት ሁኔታ የት አደርሰዋለሁ ብለው ያምናሉ?

/ እመቤት፡- አንደኛ የምነግርህ በነበሩን የፕላኒንግ ውጥኖች የመቶ ቀናት ፕላን ስናስብ፣ በ50 ቀናት ውስጥ ማጠናቀቅ የሚለውን ነው የማስበው፡፡ እዚህ እንደመጣሁ ለሁሉም ከፍተኛ የባንኩ ኃላፊዎች ይህንን ነው የነገርኳቸው፡፡ የባንኩን የለውጥ ሒደት ከዚህ በፊት በተለመደው መንገድ ሊሠራ ስለማይችል ለውጡን ማፍጠን አለብን፡፡ ለውጡን ከማፍጠን አንፃር ሥራውን በጀመርኩባቸው የመጀመሪያዎቹ ቀናት በአሥር ቀናት ሊሠሩ የሚገባቸውን ነገሮችን ለመሥራት ነው የሞከርኩት፡፡ ይህ ማለት ባንኩን ችግር ውስጥ ያስገባው መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው የሚለውንና የቢሮ አካባቢያዊ ቅኝት (ኢንቫይሮመንት ስካኒግ) የመሳሰሉ ነገሮችን መሥራት የመጀመሪያ ዕቅዴ ነበር፣ ይህንን አደርጋለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ምን ዓይነት መፍትሔ ነው ባንኩ የሚፈልገው የሚለውን ለይተን ጨርሰናል፡፡ ችግር ፈጣሪ የነበሩ ጣልቃ ገብነቶችም የትኞቹ ነበሩ የሚለውንም ለይተን አውቀናል፡፡ ከዚያ ወዲህ ቦርዱ በሠራቸው ትልልቅ ሥራዎች አሁን ያለው የባንኩ ገጽታ ከሦስት ወራት በፊት እንደነበረው አይደለም፡፡ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ለውጥ አሳይቷል፡፡ ደንበኞች ገንዘብ ለማውጣት ወደ ባንካችን ሲመጡ ቆዩ የሚባልበት ሁኔታ አሁን የለም፣ የገንዘብ እጥረትም የለም፡፡

ሪፖርተርደንበኞች ገንዘብ ለማውጣት ሲፈልጉ የነበሩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ እንደሌሉ ማረጋገጥ ችለዋል?

/ እመቤት፡- አረጋግጫለሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ትልቁ የባንኩ ችግርም እሱ ነበር፡፡ እኔም ከመምጣቴ በፊት ቦርዱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ባደረጓቸው ርብርቦች እጅግ በጣም ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ስለዚህ እነሱ ይህንን ከባዱን ጉዳይ በተወሰነ መንገድ ተሻግረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በቀጣይ ደግሞ የምንወስደው ዕርምጃ ባንኩን ሪፎርም ማድረግ ነው፡፡ ባንኩ ትልቅ ሪፎርምና ትራንስፎርሜሽን ይፈልጋል፡፡ 

ሪፖርተርባንኩ ትልቅ ሪፎርም እንደሚያስፈልገው አምነዋል?

/ እመቤት፡- ባንኩ የተደራጀበትን መዋቀር ከገመገምን በኋላ፣ በቀጣይ ውጤታማ ሥራ የሚሠራበትን ሥልት ዘመናዊነትን በዋጀ መንገድ መሆን እንደሚጠበቅበት ተገንዝቤያለሁ፡፡ አሁን ያሉ ባንኮች ደንበኞችን ማዕከል አድርገው መሥራት አለባቸው፡፡ ደንበኛ ተኮር መሆን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ደንበኛ ተኮር የሚያደርገንን መዋቅርና ስትራቴጂ መቅረፅ አለብን፡፡ ያንን ስትራቴጂ ማውረድ የሚያስችል መዋቅርና ለዚያ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል በተገቢው ቦታ መመደብ አለብን፡፡

ሪፖርተርይህ ሥራ በምን ያህል ነው ጊዜ የሚተገበረው?

/ እመቤት፡- በቀጣይ ከ15 እስከ 30 ቀናት ውስጥ የምንሠራቸው ይሆናሉ፡፡

ሪፖርተርከውጭ እንደሚሰማው ባንኩ ካለው አቅምና ዕድሜ አንፃር የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቱ በአጠቃላይ ከአይቲ ጋር የተያያዙ የመሠረተ ልማት ግንባታው ያን ያህል የሠራ እንዳልሆነ ይጠቀሳል፡፡ ይህ እሠራዋለሁ ላሉት ነገር ተፅዕኖ አይኖረውም? የአይቲ መሠረተ ልማቱን ምን ለማድረግ አስበዋል?

/ እመቤት፡- በመቶ ቀናት ዕቅድ ውስጥ አንዱ ደንበኛ ተኮርና በዲጂታል የታገዘ ባንክ መሥራት የሚል ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በተለይ ለንብ ባንክ ይህ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደጠቀስከው ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ በባንኩ ውስጥ ክፍተት እንዳለ አይቻለሁ፡፡ የዲጂታል ፕላትፎርሞች ውስኑነት ያለባቸው ናቸው፣ ይበልጡን የሚሠሩ አይደሉም፡፡ ከዚህ አንፃር የደንበኛ መሠረትን አስፍቶ የመሄድ ውስንነት አለ፡፡ ከዚህ አኳያ የሚሠራው  ትልቅ ሥራ ደንበኞች ከቅርንጫፍ አገልግሎት ወደ ዲጂታል ፕላትፎርሞ እንዲመጡ ማስቻል ነው፡፡ በአጭሩ ስለዚህ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ሪፎርም ትልቁ ዕቅዳችን ይሆናል፡፡

ሪፖርተርእርስዎ ወደዚህ ኃላፊነት ሲመጡ ባንኩን ሪፎርም ለማድረግ ብቻ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም የባንክ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ውድድር ውስጥ እንዳለ ይታወቃል፡፡ የውጭ ባንኮችም እንዲገቡ ተፈቅዷልና በባንኩ ኢንዱስትሪ ውስጥ ውድድሩ እንደሚጠነክር ይታሰባል፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ አንድ የትልቅ ባንክ መሪ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊመጣ የሚችለውን ውድድር ለመወጣት ምን ዓይነት ዝግጅት ይኖርዎታል? በዚህ ውድድር ውስጥ ባንኩንስ ምን ያህል ብቁ ተወዳዳሪ አደርገዋለሁ ብለው ያስባሉ?

/ እመቤት፡- እርግጥ ነው በአሁኑ ጊዜ ለአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ከባድ ተግዳሮት ነው የሚሆነው፡፡ ውድድሩ እየጠነከረ ነው፡፡ እኛ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ያለን ተዋንያን እየተገበርን ያለነው የሞደርናይዜሽን ደረጃ ሕዝቡ ከሚጠብቀን አንፃር ለመሆን የሚቀረው ነገር አለ፡፡ ትንሽ ክፍተት አለ፡፡ ይህንን ክፍተት ማጥበብ ወይም መድፈን አለብን፡፡ በተጨማሪ ደግሞ በውጭ ባንኮች በሩ ሊከፈት ነው፡፡ ለዚህም ነው አጠቃላይ ግምገማ (Comprehensive Assessmnet) ያሰብኩት፡፡ ይህ ዕሳቤ ለአጭር ጊዜ ሪፎርም የታሰበ አይደለም፡፡ አጠቃላይ ግምገማው ያሳየኝ በአንድና በሁለት ዓመታት ወይም ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ሲስተም ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብን ሁሉ ይጠይቃል፡፡ ዓለም አቀፋዊም ሆነ የአገሪቱ ማክሮ ሲስተም ለንብ ባንክ የሚያመጣው ነገር ምንድነው? በየት መንገድ ልሂድ? የሚለውን በወቅቱ በሚገኘው ግኝት ላይ ተመሥርቼ የማመጣቸው ነገሮች ይኖሩኛል፡፡ ከዚያ በላይ ግን ባንኩ ያሉበትን ክፍተቶች በመድፈን ቴክኖሎጂ ላይ አተኩራለሁ ያልኩበት ዋናው ምክንያትም ተወዳዳሪ ለመሆን ነው፡፡ የውጭ ባንክ ሲመጣ ይህንን ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ በነገራችን ላይ ከኢትዮጵያ ባህል አንፃር የበለጠ መተማመን የሚኖረው ለእኛ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን እኛ አስፈላጊውን አገልግሎት ስንሰጠው ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ማተኮር አለብኝ፡፡ የውጭ ባንኮች ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ አብዛኛው ተጠቃሚነት የእኛ ነው፡፡

ሪፖርተርየውጭ ባንኮች መግባት ሊያስፈራ አይችልም የሚሉ ይመስላሉ፡፡ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የሚያመጣው ተፅዕኖ አይኖርም? ተግዳሮት አይኖረውም?

/ እመቤት፡- ብዙ ተግዳሮት አለው፡፡ ተግዳሮት የሚያመጣው ግን በእኛ ውጤታማነት ደረጃ ነው፡፡ እኛ ባንኮች የምንሠራበት ዓውድና ባህል ይወስነዋል፡፡ በትንሹ ሀብት እየተደባበቅን የምንሠራውን ዓይነት አይደለም ማሰብ ያለብን፡፡ የበለጠ ትኩረት ሰጥተን ሪፎርም እያደረግን ደንበኛው ምን ይፈልጋል? የሚለውን በመለየት አስፈላጊውን አገልግሎት ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ የውጭ ባንኮች ቢመጡ ዋና ዓላማቸው ይሆናል ብዬ የምገምተው ኮርፖሬት ደንበኛ ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የውጭ ድርጅቶች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በጣም እንከን የለሽ የባንክ አገልግሎት ይፈልጋሉ፡፡ ደንበኞቻችን በእኛ ላይ ያላቸው እምነት እንዲያድግ መሠረተ ልማት ላይ ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡ 

ሪፖርተርየውጭ ባንኮች ተወዳዳሪ ሊሆኑበት ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ አገልግሎቶችን ለመተግበር አይቻልም? ከዚህ አንፃር አገር በቀል ባንኮች ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚችለውን አሠራር ለመተግበር ለምን አይችሉም? ምንድነው የሚቸግራቸው?

/ እመቤት፡- የሚቸግረን መሥራት ነው፡፡ ከሠራን ይለወጣል፡፡

ሪፖርተርከዚህ አንፃር በእርስዎ ተቋም ውስጥ ሊፈጠር የሚችል አዲስ ለውጥ ይኖራል?

/ እመቤት፡- እንደ አዲስ ብዙ ነገሮችን ወደ ሲስተም ለመቀየር እንሠራለን፡፡ ከደንበኛ ጋር የሚደረግ ግንኙነትና ሞዴላችን መቶ በመቶ ይቀየራል፡፡ አንድ ደንበኛ በአንድ  ማኔጀር መስተናገድ አለበት፡፡ ይህንን አሁን ባለው የባንኩ ሲስተም የምሠራው ነው፡፡ ሁለተኛው በፋይናንስ ተደራሽነት ያልተካተቱና ርቀው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ፣ እነዚህንም ታሳቢ በማድረግ ወደ ባንክ ማምጣት አለብን፡፡ ይህንን ተደራሽነት እናበጃለን፡፡ 

ሪፖርተርከአገላለጽዎ መረዳት እንደቻልኩት ንብ ባንክን ነበረበት ከተባለው ችግር ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ የለውጥ ሥራዎችን የሚተገብሩ መሆንዎን ነው፡፡ እነዚህን ዕቅዶችዎን ወደ መሬት ለማውረድ ግን ብቁ የሰው ኃይል ይፈልጋል፡፡ ወጪም የሚጠይቅ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የባንክዎን ቦርድ ፈቃደኝነት የሚጠይቅ ነው፣ ማሳመንም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ባለአክሲዮኖችም በዓመት ትርፍ የሚጠብቁ ከመሆናቸው አኳያ ይህንን ፍላጎትማሟላት በራሱ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በዙሪያዎ ያሉ አካላትን ሁሉ ፍላጎት በጠበቀ መንገድ ዕቅድዎን ለማስፈጸምና ውጤታማ ለመሆን ተግዳሮት ይሆንብኛል ብለው የሚሠጉት ነገር የለም?

/ እመቤት፡- ትክክል ነህ፡፡ ይህ ከምን የመጣ መሰለህ? እነዚህ ሥራዎች በራሳቸው ወጪን መቀነስና ቅልጥፍናን (Cost Reduction and Effieciency) ነው የሚያመጣው፡፡ በወረቀት ስንሠራ ብዙ ወረቀቶች እየተጻፈባቸው፣ እንደገና ሌላ ብክነት ፈጥረው የቢሮውን ገጽታ ሁሉ ያጠፋሉ፡፡ ዝም ብለን ስናስብ ይህ ወጪ አይመስለንም፡፡ ወደ አዲሱ አሠራር ስንገባ ግን የተወሰነ ወጪ ያስወጣል፡፡ ይህ ወጪ ግን ኢንቨስትመንት ነው፡፡ እንደ ወጪ ሊታሰብ አይገባም፡፡ ትልልቅ ቢዝነሶችን ስንሠራ በረዥም ጊዜ ሊገኝ የሚችለውን ዘላቂ ጥቅም ታሳቢ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በሌለኝ ነገር ላይ ሠርቼ ሰኔ ላይ ትርፍ ላስመዘግብ እችላለሁ፡፡ ሀብት ሰብስቤ በማበደር ብቻ ላይ ከተወሰንኩ ከሰኔ በኋላ ግን ሊኪውዲቲ (የገንዘብ እጥረት) ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህ አጭር ዕሳቤ ነው፡፡ ስለዚህ ዘላቂ የሆነ ጠቀሜታ ለማምጣት ደረጃ በደረጃ ውጤት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ፡፡ ቃሌን አምኜ መሥራት አለብኝ፡፡ ሁለተኛ ኢንቨስትመንቱን አዋጪ ኢንቨስትመንት ማድረግ አለብኝ፡፡ ቅድሚያ ለሚሰጠው እየሰጠህ መሥራትን ሁሉ ይጠይቃል፡፡ ሁሉንም በአንዴ ማድረግ አይቻልም፡፡

ሪፖርተርየመጨረሻ ጥያቄዬ ልክ የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ቢሮዎ ብመጣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ምን ደረጃ ላይ ደርሶ አገኘዋለሁ?

/ እመቤት፡- እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ያሰብኳቸውን ወደ ተግባር እቀይራቸዋለሁ፡፡ ቦርዱም፣ ሠራተኛውም፣ ማኔጅመንቱም ተናበው በመሥራት ዕቅዶችን በማስፈጸም ጥሩ ውጤት ይመዘገባል፡፡ እንዲሁም እንደ ተቆጣጣሪ ብሔራዊ ባንክም፣ ደንበኞችም ሆኑ ሌሎች ባድርሻ አካላት ተባብረው በመሥራታቸው በአጭር ጊዜ እንደ ባንክ ጥሩ ተሂዷል፡፡ ስለዚህ የዛሬ ዓመት ጥሩ ትርፍ አስመዝግበን ሁለትና ሦስት አዳዲስ አገልግሎቶችን ጀምረን፣ ከሰው ኃይል አንፃር ጥሩ አመራር ያለው ማኔጅመንት ተደራጅቶ ከቦርዱ ጋር ተናብቦ የሚሠራ አካል ይፈጠራል፡፡ ቢቻል አርዓያ የምንሆንበትን ውጤት ለማስመዝገብ እንሠራለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተግዳሮት መልካም ዕድልም ስለሚሆን የዛሬ ዓመት ከብዙ ለውጦች ጋር እንገናኛለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...