Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየምርጫ 97 ትውስታ!

የምርጫ 97 ትውስታ!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

     መሰናዶ

ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና የኢኮኖሚ ግስጋሴ ከማምጣት ወይ ከመንኮታኮት ፈተና ጋር መተናነቅ የያዘው በበርካታ መሠረታዊ ችግሮቹ እንደተቀፈደደ ነበር፡፡ ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ ሆኖና ከተቃዋሚዎቹ ጋር ተቀራርቦ የመጓዝ ጎዳና ለሥልጣኑ አስፈሪ ሆኖበታል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ሲከምሩት የቆዩት የወንጀል መአት ያስፈራል፡፡ ቀዳዳ ካገኙ ቀብሩን ከማሳመር እንደማይመለሱ ይሰጋል፡፡ ሕዝብ እንደመረረው ምርጫ 97 ቢመጣ ሌላ ጣጣ ነው፡፡ ሕዝብ ያሳተፈ የመልካም አስተዳደር ለውጥንና የኢኮኖሚ ልማትን በመስበክ ሕዝብን ለመያዝ  ከመፍጨርጨር ጋር እነ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን ሕዝብን ለጥ ሰጥ አድርገው እያሰሩ ፈጣን ዕድገት ያሳዩበትን ሥልት አጎዳኝቶ፣ ኅብረተሰቡን በእንጀራ ገመድና በከባድ ቅጣቶች እያስፈራራ ተቃዋሚዎችን ሳያስቀርብ ብቻውን የሚመሰገንበት ለውጥና ልማት ለማሳየት መራወጥንና ማራወጥን የተሻለ አማራጭ አድርጎ ወሰደ፡፡

- Advertisement -

ገበሬው እስከ ጎጥ ድረስ “ተጠርንፎ” በስብሰባ፣ በመዋጮና “በወል ሥራ” ዘመቻ መጠመዱ ባሰ፡፡ ይህ አሠራር ተለሳልሶ ወደ ከተሞችም ተላለፈ፡፡ የልማት መዋጮ በመኖሪያ ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ተስፋፋ፡፡ ለስብሰባ በተገኘ ሰው ተወስኖ በሌላው ላይ ሁሉ የሚፀና ከግዴታ ያልተሻለ መዋጮ የደንብ ያህል ሆነ፡፡ አልከፍልም ያለ በልማት ፀርነት ይታያል፣ በሌላ መንገድ ለመታሸት ይጋለጣል፡፡ ተማሪዎች ካልከፈላችሁ ለፈተና አትቀመጡም/የትምህርት መረጃ አታገኙም በሚል ማስፈራሪያ ተሰንገው ይተፋሉ፡፡ አዲስ የሚገባ ተማሪም ከዓመት ወደ ዓመት የደንቡን ጠብ እንዲያደርግ እየተገደደ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እንኳ “ነፃ” መባሉ ትርጉም አጣ፡፡ የልማት ሩጫውን፣ የብክነትና የስርቆት ወጪውን ሁሉ ለመሸፈን የሚፈለገው  የገንዘብ መአት ግብሩን አናረው፡፡ ግብሬን በጊዜ ከፍያለሁ ብሎ ያምን የነበረ ነጋዴ ሁሉ የማያቀውንና በእጅ በያዘው ሰነድ ላይ የማይታይ ቀሪ ግብር (ስትከፍል የቆየኸው በታሳቢነት ነበር እየተባለ) በርካታ ገንዘብ ይጠየቅ ጀመር፡፡ ቅጣቶችና የቦታ ካርታ እደላ ሁሉ የመንግሥት ገቢ ማዳበሪያ ዘዴ ሆኑ፡፡ የተጨማሪ እሴት ቀረጥ ተጨማሪ እሴት በሌለበት ሁሉ ዋለ፡፡

      የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ አውታር እስከ ውጭ አገር ሰፍቶ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በመሠረተ ልማትና በመልካም አስተዳደር ስለታየ መሻሻል መጮህ፣ ኮንፈረንሶችን፣ ስብሰባዎችን፣ ስለተሠሩና እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎች ዘገባዎችን ማንደቅደቅ ታላቅ ሥራው ሆነ፡፡ በ1997 ዓ.ም. ደግሞ ጆሮና ዓይንን ማሸሻ እስኪጠፋ ድረስ ሁለመናው ፕሮፓጋንዳ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀን ሥርጭት (ከ6 ሰአት እስከ 8)  ከፍቶ የተሠራጩ ዝግጅቶችን እያገላበጠ ማስጠናት ያዘ፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሌላ የቴሌቪዥን መሥመር ከፍቶ ይነዘንዝ ገባ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ በሚደጋገሙ ፕሮፓጋንዳዊ ዝግጅቶች ሲያታክቱ የኢሕአዴግ ሬዲዮ ፋና ግን በትኩስና በፈጣን ዜና አድራሽነት፣ በትንታኔ ስፋትና ሁለገብነት የክልል ፕሬዚዳንቶችንና ሚኒስትሮችን በስልክ ሁሉ እየጠየቀ ፈጣን ማብራሪያ በማቅረብ “የሚያስንቅ” ሆነ፡፡ ለአዲስ አበባና አካባቢው አድማጭ ከጧት እስከ አሥር ሰዓት ድረስ የአማርኛ ሥርጭት ዘርግቶ በጤና፣ በሕግ፣ በቤተሰብ ችግሮች ዙሪያ ከባለሙያ ጋር ያወያይና ምክር ያስገኝ ጀመር፡፡ ይህ ሁሉ ሕዝብን “የመማረክ” አካል ነበር፡፡

      ጊዜ ሳይታወቅ በረረ፡፡ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ዕዳ፣ ስብሰባ፣ መዋጮና የግዳጅ ሥራ የፈጠረው ብሶትና መሰላቸት፣ በንግዱ ሥራ አካባቢ ግብርና እና ቅጣት የፈጠረው ቅያሜ፣ በመንግሥት ሠራተኛው ዘንድ “የስቪል ሰርቪስ ማሻሻያ” የፈጠረው መፈናቀልና ሥጋት እንዳለ ነው፡፡ ይህንን የሚጋርድና ደረት የሚያሰነፋ ለውጥ ገና አልተገኘም፡፡ የምርጫ ጊዜው ተገፍቶ ትንሽ ጊዜ ኢሕአዴግ ቢያገኝ በወደደ፡፡ ተቃዋሚዎቹም መራዘሙን ይፈልጉት ነበር፡፡ ግን አራዝሞ እነሱን እንዲሰረጫጩና እንዲጠናከሩ ዕድል መስጠት ሌላ ዕዳ ሆነበት፡፡ የጊዜ ለውጥ ሳያደርግ ተሳኩልኝ የሚላቸውን ሥራዎች እያብለጨለጨ፣ ከምርጫው ጊዜ መቃረብ ጋር በተገናዘበ ሁኔታ አጓጊ የሥራ ዕቅዶችንና ውሳኔዎችን እየደቀነ እንደ ምርጫ ዘመቻ እጅ መንሻ እየተጠቀመ ተቃዋሚዎቹን ሊበልጥ ሞከረ፡፡ የ13 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ዕቅድ፣ የኤሌክትሪክና የሞባይል አገልግሎትን ለዚህ ለዚህ ቦታ ላዳርስ ነው ባይነት፣ የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤትን በረዥም ጊዜ ግዢ ላይ ዝቅተኛ ገቢ ላለቸው እገዛ ማድረግ፣ የጋራ  ሕንፃ ሊሠሩ ላመለከቱ መሬት ማደል፣ የግብር መቀጮ ምኅረት፣ እነዚህን የመሳለሉት ሁሉ የጉቦ ባህርይ ያላቸው ነበሩ፡፡

      የ97 ምርጫ እንዳለፉት ጊዜያት በተቃዋሚዎቹ ላይ እየተቆነነ ባገጠጠ ማጭበርበር አሸንፌያለሁ ማለት የሚቻልበት እንደማይሆን አየሩ ሲነግረው ቆይቷል፡፡ በ92 ምርጫ በሃዲያ ዞን ያየው ቅሌት አይረሳም፡፡ ከዚያ በኋላ በደቡብ፣ በኦሮሚያ አካባቢዎችና በአዲስ አበባ ሲከሰቱ የቆዩት ቅዋሜዎች የሃድያ ዞን ዓይነት ብዙ ቅሌቶች ሊመጡ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ነበሩ፡፡ ተቃዋሚዎቹም እንዳለፉት ጊዜያት በትዕቢት እንዲኖር በድክመታቸው የሚያግዙት አይመስሉም፡፡ የወንበር ሒሳብ ፀቡን ተባብለው፣ ማፈንገጡን፣ የተናጠል ጉድኝት ውህደትና መቆራረሱን፣ በሃሜት መታመሱን ሁሉ አከናውነው ሁለት ዋና ስብስቦች ሠርተውበታል፡፡ አዳዲስ ቡድኖችም እየመጡበት ነው፡፡  [በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት ውስጥ ባሉ ቅንጥብጣቢ ቡድኖች መዋጥ ያልጣማቸው ኢዴፓና መኢአድ (የቀድሞው መአሕድ) ሄድ መለስ እያሉና የበኩላቸውን መሳሳብና ጉድኝት ፈጥረው ራሳቸውን ለማግዘፍ ሲሠሩ ቆዩ፡፡ ኢዴፓ ኢዲህን ዋጠ፡፡ ኢዴፓን የወያኔ የውስጥ አርበኛ ነው በሚል አሉባልታ ነክሶ የሚጠጋው ለማሳጣትና ከሕዝብ ለማቆራረጥ ዘመቻ ተካሄደ፡፡ ከኢዲሕ የተወሰነ ቡድን ወደ ኢዴሃህ አቀና፣ የመአህድን ነባር ስም ያጠበቀ ቡድንም እንዲሁ፡፡ ኢዴፓ በበኩሉ መድህንን ቦጭቆ ወሰደ፡፡ በመጨረሻ ኢዴፓን ተጠራጥሮ ርቆ የነበረው መኢአድ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ከፈጠሩት ቀስተደመና ለዴሞክራሲና ለማኅበራዊ ፍትሕ ከሚባል ድርጅትና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሊግ (አዲሊ) የሚባል ሌላ ድርጅት አንድ ላይ ገጥመው ቅንጅት ላንድነትና ለዴሞክራሲ ባጭሩ “ቅንጅት” የሚባለውን ድርጅት ፈጠሩ፡፡ ሌሎች አዳዲስ ፓርቲዎችም የመላ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የገዳ  ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ ፓን አፍሪካኒስት ፓርቲ የሚባሉ ተከስተዋል]፡፡ ተቃዋሚዎቹ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት እንዲሟሉ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎችም ጆሮ ዳባ ልበስ ሊል አይቻለውም፡፡ ጌቶቹ አገሮች የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ይፈልጉታል፡፡ ለተሰባሰቡት ተቃዋሚዎችም ክብደት የሰጡ ይመስላል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ለኤርትራ ላቀረበው ባለአምስት ነጥብ የሰላም ሐሳብ አሜሪካ እሰየው አላለችም፡፡ የኢሕአዴግን መንግሥትም በሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚወቅስ መግለጫ በምርጫው መዳራሻ ላይ ማውጣቷም ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሚያሰኝ ሰበብ ሰጥቶ ተቃዋሚዎቹን ቢያስኮርፍና ምርጫው የኢሕአዴግና የመሰሎቹ መንቦጫረቂያ ቢሆን ከሕዝብም ከረጂዎቹም ጋር ተላትሞ መውደቅ ሊከተል ይችላል፡፡ ይህ በማይሆንበት አቅጣጫ ሁኔታዎችን ለመቀየር የዴሞክራሲዊነት ወጉን ማሳማር ግድ ነው፡፡

      ኢሕአዴግ የምርጫ ቦርዱን ሳያስነካ ተቃዋሚዎቹ በሌሎች የምርጫ ሕጎች ዙሪያ ካነሷቸውም ጥያቄዎች ጋር ራሱን አስታረቀ፡፡ የውጭ ታዛቢዎችም እንዲገቡ ተስማማ፡፡ ተቃዋሚዎቹም የምርጫ ቦርድ ባዲስ ካልተደራጀ ብለው ዘወር አላሉለትም፡፡ የተስማማባቸው ጉዳዮች በሕግ መልክ ተቀርፀው እስኪወጡ የምርጫ ምዝገባ መርሐ ግብር ለውጥ ሳያደርግ በነባሩ ሕግ ሲሠራ ቆየ፡፡ የተሻሻለው ሕግ ፀድቆ ከወጣ በኋላ የምዝገባ ጊዜ እንዲራዘም የተጠየቀውን ጥያቄ ለስድስት ቀናት ብቻ በመፍቀድ ተቃዋሚዎቹን ሊሸመቅቅ  ሞከረ፡፡ በጊዜ ጥበቱ ላይ የምዝገባ ሥራ በማጓተት፣ በሥራ ቦታ ላይ ባለመገኘትና ዕጩዎችን በማደናባር የተቃዋሚዎችን ዕጩዎች ከምዝገባ ጊዜ ገደብ ውጪ ለማድረግ ተጥሯል፡፡ እንደዚያም ተደርጎ ተቃዋሚዎቹ ለአሸናፊነት የሚያበቃ የዕጩዎች ብዛት ለማስመዝገብ ቻሉ፡፡

ተቀዋሚዎች ኢሕአዴግን ማስጨነቅ ቢችሉም የአገሪቱን ውስብስብ የፖለቲካ ጉዳዮች ባግባቡ ለማስተናበር የሚያስችል ዝግጅት ይቀራቸው ነበር፡፡ ኅብረቱ (ኢዴኃኅ) በ1996 ክረምት ማለቂያ ላይ ጉባዔ ካካሄደ በኋላ ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው ቢያሸንፍ ያሰበው የኅብረቱ አባላት የሆኑትን ድርጅቶች ያቀፈ ጥምር የሽግግር መንግሥት ሊያቋቁም ነበር (ኢትኦጵ ጋዜጣ ጳጉሜን 3 ቀን 1996)፡፡ ተቃዋሚዎችን ከሞላ ጎደል ያጠቃለለበት ሁኔታ እንዳለመኖሩ በምክር ቤቱ ውስጥ ባነሰ ድምፅም ቢሆን ሊገቡ የሚችሉ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖችን እይታው ውስጥ አላስገባም፡፡ የተመረጥክበትን ሕገመንግሥት ጥለህ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም አትችልም፣ ሕገወጥ ነህ የሚል ውዝግብም የሚጠራ ነው፣ ይህ ቀላሉ ነው፡፡ የኅብረቱ አሸናፊነት ሁሉንም አካባቢዎች ላይሸፍን ይችላልና ኅብረቱ በአባል ድርጅቶች የሽግግር  መንግሥት አዋቅራለሁ ሲል ነፃነት አውጄያለሁ የሚል ሊመጣበት ይችላል፡፡

ከተቃዋሚዎች ከፍተኛውን የዕጩዎች ቁጥር ያቀረበው (1,400) ቅንጅት የሽሽግር መንግሥት የሚባል መፈክር ባይኖረውም የብሔር መብት ከሚባል ነገር ጋር መደራረስን ይፈራል፣ በብሔር ከተደራጁ ቡድኖች ጋር የሚጎዳኝበትም መንገድ የለውም ድርጅቱ የፕሮፈሰር መስፍን ወልደ ማሪያምን እሰበቶች ያጣቀሰ መሆኑ ሌላው ችግር ነው፡፡

 ክርክሩና ቅስቀሳው ብዙ ጭቃ አወጣ

ሀ) ኢሕአዴግ የዴሞክራሲ ግንባታዬ አካል የሚለው የ97 ምርጫ ዘመቻ ከእስካዛሬው ይበልጥ የሞቀና አዳማጭ ያገኘ ነበር፡፡ ተቀዋሚዎች ኢሕአዴግን፣ ኢሕአዴግም እነሱን (በተለይ ቅንጀትን) በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ዋጋ ቢስ አድርጎ ድምፅ ለማፈስ ለፉ፡፡ ኢሕአዴግ ቁጥር እየደረደረና ከመቶ ዓመት ክንዋኔ ጋር የራሱን እያነፃፀረ የተሻለ ውጤት አስገኝቻለሁ ሲል፣ ተቃዋሚዎቹ በሕዝብ ኑሮ እያሸቆለቆለ መሄድ መጡበት፡፡ አገኘሁ የሚለውን የቁጥር ውጤት በሕዝብ ቁጥር እያካፈሉና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የነፍስ ወከፍ ድርሻ ጋር እያነፃፀሩ የኢትዮጵያን ውራነት ተናገሩበት፡፡ ኢሕአዴግ ከ95-97 ባሉት ሦስት ዓመታት የተራወጠበትን ጅምርማሪ ለውጥ እያነሳሳ አዲስ መንገድ ያዝኩ ለማለት ሲሞክር፣ ሥልጣን ከያዝክ እኮ ሦስት ዓመትህ አይደለም፣ አልቻልክም፣ 14 ዓመታት ታይተህ ከውድቀት ሌላ ያመጣኸው የለም አሉት፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን ከመልካ ዋከና በቀር አንድም የኃይል ማመንጫ አልሠራም ሲል፣ ተቃዋሚዎቹም ኢሕአዴግ ሠራሁ የሚለው ሁሉ በደርግ የተጀመረ ስለመሆኑ ተናገሩ፡፡ “መሬት ይሸጥ የሚሉት ገበሬውን እንደገና ጭሰኛ ሊያደርጉት ነው” እያለ ኢሕአዴግ ሲቀስቅስ ተቃዋሚዎች ገበሬው የመንግሥት ጭሰኛ ነው፣ መሬትን የመሸጥ መብት ካልተረጋገጠ ልማት አይኖርም ባይነትን አደመቁ፡፡ ኢሕአዴግ በገጠር ልማቱ ስላስገኘው ውጤት ሲያወራ ተቃራኒዎቹ ደግሞ ገጠርና-ግብርና መር ልማቱን የድህነት ማዕከል አድርገው ገለጹት፡፡ የውኃ ማቆር ፕሮጀክት ተጥላላ፡፡ የግብርና ልማት ሠራተኞች ግብር ሰብሳቢና ካድሬ ተባሉ፡፡

      ክፉን በክፉ መመላለሱ እየተወለጋገደ ቀጠለ፡፡ ከተቃዋሚዎች በኩል በገበሬ ማሳ የትም አይደረስ፣ የመስኖና ሰፋፊ የእርሻ ልማት ያስፈልጋል ሲባል፣ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች የአነስተኛ ገበሬ ልማት አያሻም እያሉ ነው፣ እነሱ የቆሙት ለጥቂት ሀብታሞች ነው፣ እኛ ደግሞ ሚሊዮኖች ካፒታሊስቶችን ለመፍጠር ነው እያለ ለፈለፈ፡፡ ኢሕአዴግ የአበባ ልማቱን ሲያሞጋግስ፣ አበባ አይበላ፣ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለዳቦ የሚልም ጉድ ተሰማ፡፡ ኢሕአዴግ በትምህርት ጉልህ ለውጥ አመጣሁ፣ በሥርጭትና በቅበላ አቅም እመርታ አሳየሁ ሲል፣ በተቃዋሚዎች አካባቢ ተዘውትሮ የሚነገረው የትምህርት ፖሊሲው “ትውልድ ገዳይነት” ተደገመ፣ በጥራት በኩል ያለው ችግር የትኩረት ነጥብ ሆነ፡፡ ኢሕአዴግም በጥራት ጉድለት ሲያደርስ የቆየውን ጥፋት ከማየት ይልቅ ትርጉም አጣምሞ ተቃዋሚዎች በጥራት ስም የትምህርትን ለብዙኃኑ መዳረስ ተቃወሙ፣ በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ሰፊ የትምህርትና የሥልጠና ዕድል ያገኘኸውን ወጣት ተቃዋሚዎች ሙያና ዕውቀት የሌለው ዋጋቢስና የሞተ ትውልድ ይሉሃል እያለ ሲቀሰቅስ ታየ፡፡ ተቃዋሚዎች የወጣቱ ማኅበራት ነፃ ሳይሆኑ የኢሕአዴግ መንግሥት ፕሮግራም ማስፈፀሚያ መሣሪያ ናቸው ማለታቸው ዘወር ተደርጎ የወጣቱን መደራጀትና በልማት ሥራ መሰማራት ተቃዋሚዎች ይኮንናሉ ለሚል የስሜት ጨዋታ ዋለ፡፡ ተቃዋሚዎችም “አደገኛ ቦዘኔ”ን በተመለከተ የወጣው ሕግ ኅብረተስቡን መግቢያ መውጫ ያሳጣውን ወንብድና በማስተንፈስ ረገድ ላለው ዋጋ ቦታ ሳይሰጡ (ሕጉ የፖለቲካ ሰዎችን ለማጥቂያ ቀዳዳ የሚሰጥና ለዚያ እየተሠራበት ከሆነ በማጋለጥ ፈንታ) ኢሕአዴግ ወጣቱን አደገኛ ቦዘኔ እያለ ያሳድዳል፣ ሥራአጥ ያደረጉትን ትውልድ ቦዘኔ ማለት ተገቢ አይደለም እያሉ ወጣቱን ሊማርኩ ሲጥሩ ታዩ፡፡ የሕጉ መውጣት ከውንብድና ጋር የተያየዘውን የአገሪቱን ማኅበራዊ ቀውስ አከፋፍ የሚያንፀባርቅ መሆኑን፣ ወጣቱ ብቻ ሳይሆን መላ ኅብተሰቡ እስከ ፖለቲካ መሪዎች ድረስ እየወመነ የመጣበትን አስደንጋጭ ሀቅ የሚያሳይ ጠፋ፡፡ የግፍና የጨለማ ዘመን የኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን መግለጫ ሆነ፣ በኢትዮጵያ አገዛዝ እንጂ መንግሥት የለም ሲባል ተሰማ፡፡ በመስክ ቅስቀሳ ላይ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ነኝ ከማለት ይልቅ ሰው ነኝ ብሎ ማለት ትክክል ነው እየተባለ ተሰበከ፡፡

      ማጥላላት ራስን ጠልፎ ሲያንገዳግድም ተስተዋለ፡፡ ኢሕአዴግ አንድ ሁነኛ መመኪያዬ የሚለው የጋራ መኖሪያ ሕንፃ ግንባታ፣ “ጥራት የለሽ፣ ለምርጫ ዘመቻ የተቀየሰ፣ ደሃውን ሁሉ ባለ ቤት ትሆናለህ የሚል ማጭበርበር የሚካሄድበት፣ ሰብዓዊ መብት ተረግጦ ነዋሪው በማይሆን መጠለያ እየተጣለ የሚሠራ ወዘተ” የሚል ውግዘት ተደረደረበት፡፡ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች የከተማውን ልማት ይቃወማሉ ፀረ ልማት ናቸው እያለ አድብቶ ቆየና፣ በ30 ከመቶ የመንግሥት ድጎማና ከወለድ ነፃ በሆነ የረዥም ጊዜ ክፍያ (በቂ ገቢ የሌለውንም በቤት ግንባታው ሥራ ውስጥ በቅጥር በማሳተፍ) ደሃውን ባለመኖሪያ ቤት የማድረግ መርሐ ግብርን ይዞ አደባባይ ወጣ፡፡ ደረቱን ነፍቶ፣ “ለሕዝብ ወገንተኛ በመሆናችንና አዲስ አበባ የጥቂት ሀብታሞች አገር እንዳትሆን በመሥራታችን ተቃዋሚዎች ያወግዙናል” በሰብህዊ መብት ስም፣ ግድግዳውና ጣሪያ ከተጣበቀ ቤት ሕዝቡ ለምን ይላቀቃል ይላሉ እያለ አንጀት ሊበላና ተቃዋሚዎችን ተከታይ ሊያሳጣ ሞከረ፡፡ ተቃዋሚዎች (ቅንጀት) የግዳቸውን የቤት  ልማትን አንቃወምም፣ ከኢሕአዴግ በተሻለ ጥራቱን አሻሽለንና አብዝተን እናለማለን ሲሉ ተሰሙ፡፡ ኢሕአዴግ ይችን ይዞ “ሲጨንቅ የመጣች የመገለባበጥ አቋም፣ ተቃዋሚዎች አቋም የለሽ መሆናቸው ታየ” እያለ አዋደቀ፡፡ የተቀናቃኝን ጥንብ-እርኩስ ማውጣት በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ዋጋ የሚያሰጥ የመምሰሉ ብዛት፣ እስካሁን የተሠራው ሁሉ ዋጋ አይኖረውም? እንደ ደርግና እንደ ኢሕአዴግ ከዜሮ ሊጀመር ነው ማለት ነው? የሚሉ የጭንቅ ጥያቄዎችን አስነሳ፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ጉትጎታ ምሥጋና ይግባና ተቃዋሚዎች እኛ እንደ ኢሕአዴግ አደደለንም፣ መልካሙን ይዘን የሚስተካከለውን እያስተካከልን ነው የምንቀጥል የሚል መልስ ሲሰጡና የሚያሻሽሉትን ሲደረድሩ ታዩ፡፡

      የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላም ነገር ተመለከተ፡፡ ኢሕአዴግ ዕለት ከዕለት በመንግሥታዊ መገናኛዎቹ፣ በተቀጥላ ማኅበራቱና በመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች (ከሥራ ጋር እያዘማመደ) የምርጫ ፕሮጋንዳውን ሲያዘንብ ውሎ ቢያመሽም ተቃዋሚዎቹ በውስን የክርክር መድረኮችና በሳምንት ሦስት ጊዜ ለስድስት ደቂቃ አካባቢ የሚሰነዝሩትን የቅስቀሳ በትር መመከት ከብዶት ሲንጨረጨርና መቀለጃ ሲሆን ታየ፡፡ ልማደኛ ሸፍጡ ያለክንብንብና ያለቅባት ነጥቶና ገጦ እዚያው በዚያው በአደባባይ ደጋግሞ ወጣ፡፡ ተቀዋሚዎቹን ዝርዝር አማራጭ አምጡ በማለት እበልጣለሁ ሲል፣ አንተ አማራጭ በታንክ ጭነህ መጣህ እንዴ? እዚሁ በመንግሥት ባለሙያ አይደል ያሠራኸው የሚል ዱላ ቀመሰ፡፡ ተቃዋሚዎቹን ከኦነግ ጋር በአሸባሪነት ለማጎዳኘት እሞክራለሁ ሲል፣ “በሌላው አገር እየሄዳችሁ ትጥቅ ያነሱ ተቃዋሚዎችን ከመንግሥት ጋር ስታስታርቁ፣ ያን ያህል በደል ከፈጸመው ሻዕቢያ ጋር እንታረቅ ስትሉ ምነው ከኦነግ ጋር ለመታረቅ ሞት ሆነባችሁ?” በሚል ጥያቄ ራሱን አስወጋ፡፡ “እንታረቅ የሚለው አካሄድ ዴሞክራሲን መግደል ነው” የሚል የተለመደ ማፈሪያ መከራከሪያውን አምጥቶ ቀለለ፡፡ በመድረክ ክርክር ላይ አንድ የተቃዋሚ ተወካይ ከውይይት ርዕስ ለምን እንወጣለን በሚል አንድምታ “ኦነግ ለኦሮሞ ነፃነት የሚታገል” ብሎ ያለበትን ሐረግ፣ ኢሕአዴግ ቆርጦ ወስዶ በቅስቀሳ ሀተታው ላይ፣ “ይኸውላችሁ ተቃዋሚዎች የኦነግ ሽብር ደጋፊዎች ናቸው” ብሎ በማሰረጃነት ጠቀሰ፡፡ የሴቶችን ጉዳይና የሴት ማኅበራትን ሙጥኝ ማለቱና “እኔ ያቀረብኩት የሴት ዕጩ በርካታ፣ የተቃዋሚዎች ግን ጥቂት” እያለ መገበዙ ሳያንሰው “ተቃዋሚዎች ሴቶችን ይንቃሉ፣ ሬሳ ተከትሎ ከመሄድ የተሻለ ነገር አያውቁም ይላሉ” ብሎ ቀሰቀሰ፡፡ የቅንጅቱ ፕሮፌሰር መስፍን ሕገ መንግሥቱ ከተጻፈበት ወረቀት በላይ ዋጋ አላገኘም (በተግባር እየሠራ አይደለም)፣ በተግባር እየሠራ ያለው “ሕገ አራዊት” (ጉልበት) ነው ያለበትን የመድረክ ንግግር ቆርጦ ቀጥሎ ሕገ መንግሥቱ ሕገ አራዊት ተባለ እያለና እያስባለ ዘመቻ አካሄደ፡፡ ተቃዋሚዎች ምርጫ ቢጭበረበር ከሕዝብ ጋር በሰላማዊ ትግል ለማጋለጥ ማቀዳቸውን በፀረ ሰላምነትና በሕገወጥነት ተረጎመ፡፡

 በአንድ የክርክር መድረክ ላይ ትልልቅ የሚባሉት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ተቃዋሚዎች የአገር ሉዓላዊነትን የማያውቁ ጥገኞች ናቸው፣ የመሬት ፖሊሲን ለመለወጥ ሕዝብን ማሳመን ሲጠበቅባቸው አሜሪካ ምክር ቤት ሄደው ደጅ ጠኑ እያሉ ሲነዘንዙ ቆዩ፣ በጥያቄም አፋጠጡ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ቅንጅትም ሆነ ቀስተ ደመና የሚባሉ ድርጅቶች ከመፈጠራቸው በፊትና አሜሪካ በነበረበት ወቅት የአሜሪካ ምክር ቤት በረሃብ ጉዳይ ላይ እንዲያስረዳ ጠርቶት ከዚያ ጋር በተያያዘ ስለመሬት ይዞታ መናገሩን ከተረከ በኋላ፣ እነዚያን የሚያካክሉ ባለሥልጣናት ሲሰርቅ እንደተያዘ ከመቁለጭለጭ በቀር አንድም ቃል አልተናገሩም ነበር፡፡ መታወቂያና ፓስፖርት ላይ ፎቶ ነቅሎ ከመቀየር ያልተለየ ተራ አጭበርባሪነት በአደባባይ ምን ይሉኝ ሳይባል ሲካሄድ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስኪበቃው አየ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገዙት ሰዎች የአደባባይ ጨዋነት እንኳ ያልፈጠረባቸው መሆናቸውን አስተዋለ፡፡ ስለተቃዋሚዎች የሚያቀርቡትን ውንጀላ የሚያምን ጠፋ፡፡ ፕሮፓጋንዳቸው ሀቅን በማጣመምና በውሸት የተሞላ መሆኑ በቀጥታ ገጠመኝ (እንዲህ አሉ ባይ ሳያሻ) ታየ፡፡ በአዲስ አበባ በ39 ቁጥር አውቶብስ ላይ ፈንጂ ተጠምዶ ተገኘ፣ በምርጫ ወቅት እንዲህ ያለ አሻባሪነት ለማንም አይበጅም በሚል ገዳዳ መግለጫ ሕዝብን ከተቃዋሚዎች ሊያጣሉ ቢሞክሩ የሚደነግጥና  አውቶብስ ከመሳፈር የሚሸሽ ጠፋ፡፡ በስተኋላ ያመጡትን ተቃዋሚዎችን ጥያቄ ያለመጠየቅ ስምምነትንም ተቃዋሚን ከመናቅ የሚቆጥረላቸው አልተገኘም፣ የሚስቅባቸው እንጂ፡፡ በእነዚህ ሰዎች በሚመራ መንግሥት የሚካሄድ ምርጫ ምን ያህል “እንከንየለሽ” እንደሚሆንም መገመት ይቻል ነበር፡፡

) ከመጀመሪያ አንስቶ ተቃዋሚዎች ከሽሙጥና ከልግጫ ጋር በክርክር መብለጣቸው እየታየ፣ የግል ጋዜጦች አራጋቢነትም ታክሎ የተቃዋሚዎች ድጋፍ (በተለይም ለተወካዮች ምክር ቤት ወደ አራት መቶ አካባቢ ዕጩዎች ያቀረበው የቅንጅት) እየጨመረ መሄድ፣ በየክርክሩ ማጠቃለያ ላይና በብዙኃን መገናኛ ቅስቀሳ ላይ የ97 ምርጫ ከሲኦልና ከባርነት መውጫ እየተደረገ መሰበኩ ኢሕአዴግን አስፈራው፣ አበሳጨው፡፡ ተቃዋሚዎች ይበልጡኑ ደግሞ ቅንጅቶች ስለማሸነፋቸው በእርግጠኝነት እስከመለፈፍ ሄዱ፣ ትንቅንቁ መረረ፡፡

      በማጥላላትና ከሕዝብ ጋር በማላተም አቅጣጫ የሚጓዘው ትግያቸው ከፋ፡፡ የዱሮ ውንጀላዎች ተመልሰው መጡ፡፡ ኢሕአዴግ ቀድሞ ይል እንደነበረው “ሥርዓት ሊቀለብሱና የነፍጠኛ ሥርዓት ሊያነግሡ ነው፣ አንድ ብሔር አንድ ሕዝብና አንድ ቋንቋ ይላሉ፣ በየክልሉ ሥልጣን መከፋፈሉን ይቃወማሉ” እያለ መቀስቀስ ያዘ፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም “አማራ በተራራ ላይ የሚኖር ሕዝብ ማለት ነው” ያለበትን ንግግር ከፕሮፌሰር መስፍን “አማራ የለም” ባይነት ጋር አዛምዶ እስከ ማቅረብ  ድረስ የሚይዝና የሚጨብጠውን አጣ፡፡

በተቃዋሚዎቹ በኩልም የኢትዮጵያ ባንዲራ ጨርቅ፣ የትግራይ ልጅ በመሆኔ እኮራለሁ፣ የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው መባሉ ተቆጠረ፣ ለተባበሩት መንግሥታት ደብዳቤ ጽፎ የገዛ አገሩን ያስገነጠለ መሪ በዓለምም በኢትዮጵያም የታየው በኢሕአዴግ ጊዜ ነው ተባለ፡፡ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ወታደር በትኖ ለሞትና ለልመና መዳረጉ፣ ከሻዕቢያ ጋር የአገሪቱን ወታደራዊ ግንባታዎች የመነቃቀል ወንጀል መፈጸሙ፣ ሻዕቢያ ለወረራ ሲዘጋጅ አይወረንም እየተባለ አገሪቱ ለጥቃት እንድትጋለጥ መደረጉ ሁሉ ተመዘዘ፡፡ በአፍ ጠለፋና ቁስል በመነካካት ድጋፍ የማሰባሰብ ጨዋታቸው ሁለቱንም እያሳሳበ ወደ አደገኛ ቅስቀሳ ውስጥ ወሰዳቸው፡፡ በጋምቤላ ተፈጽሞ የነበረው ጭፍጨፋ የኢሕአዴግ መንግሥት ካደረሳቸው ጭፍጨፋዎች አንዱ ተደርጎ ሲጠቀስ ተሰማ፡፡ ከድጋፍ ፍለጋ ጋር የብሔር ጉዳይ አልዋጥ አልተፋ ብሎ ያስቸገራቸው ቅንጅቶች ከሕዝብ ውሳኔ ውጪ የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ከመቃወም አልፈው እነ ጋምቤላ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ሲሆኑ እነ ሲዳማና እነ ወለይታ ለምን ክልል አልሆኑም ብለው ጠያቂ ሆኑና የእነ ሲዳማ ችግር ክልል በመሆንና ባለመሆን ላይ የተንጠለጠለ ለሚያስመስል ብዥታ ድርሻ አዋጡ፡፡ ሳያውቁት ለብጥስጣሽ ክልሎች መፈጠር ካድሬ ሆኑ፡፡ ኢሕአዴግ በፊናው ተቃዋሚዎች የቡድን መብትን የማይቀበሉ አድርጎ ከብሔሮች ጋር ብቻ ሳይሆን ከሙስሊሙም ጋር ሊያቃርን ሞከረ፡፡

      ተቃዋሚዎች በቀድሞ የሠራዊት አባላት ላይ የተፈጸመ በደልን ሲያክኩ፣ ኢሕአዴግ ደግሞ ተቃዋሚዎች ሠራዊት ሊበትኑ ነው ከሚል የውስጥ ቅስቀሳ አልፎ በይፋ መግለጫ፣ የኢሕአዴግን ሠራዊት ነባር የትግል “ውለታ” የሚቆጥር አስመስሎ መከላከያ ሠራዊቱን በአመጣጥ፣ በዕይታና በተልዕኮ ከኢሕአዴግ ጋር ያጣበቀ ቅስቀሳ ሲያካሂድ ተሰማ(ኢሕአዴግ የከፋ ችግር ቢመጣ የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ጠቆመ)፡፡ተቃዋሚዎቹም አካሄዱ ገብቷቸው ሠራዊት የመበተን ዓላማ እንደሌላቸው፣ እንዲያውም ዓላማቸው የኢሕአዴግን ጥፋቶች ማረም (ጡረታ እንዳያገኙ የተደረጉትን መካስ፣ ያለ በቂ ምክንያት የተቀነሱትን ማሰባሰብ፣ የጦር ጉዳተኛ ቤተሰብ በአግባቡ መንከባከብ) እንደሆነ የማሳወቅ ትግል ተያያዙ፡፡

      እስከ ዛሬ ተቋጥሮ የቆየውን ብሔር ነክ ጥላቻ አደገኛነት እያሳዩ የመበተን ሙያ ጠፋና ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግን በሚያወግዙበት በብሔር/በጎጥ ከፋፋይነት ግቢ ውስጥ ገብተው (በተለይ ቅንጅት)፣ የሕወሓትንና የጭፍሮቹን የሥልጣንና የኩባንያዎች ድርሻ በብሔር/በክልል እያሰሉ አነፃፀሩ፡፡

ሕዝቦች በየብሔር/በየክልል ግቢ ውስጥ የሥልጣንና የኩባንያ ድርሻን እያሰቡ ወያኔና ትግራይ ላይ ዓይናቸውን እንዲያሳርፉ ተጋበዙ፡፡ ንቧ ከኦሮሚያ አበባ እየቀሰመች ማር የምትሠራው ግን ሌላ ቦታ ስለመባሉ ተወራ፡፡ ኢሕአዴግ የሠለጠነበትን አጠላልፎ መጣል እኛም እናቅበታለን ተብሎ ነው መሰል ሕወሓት ነፃ አውጪ የሚል ቅጥያውን ያልጣለው ለክፉ ጊዜ ይሆነኛል ብሎ ነው በሚል ትርጓሜ፣ ሕወሓትን በፀረ ኢትዮጵያዊነትና በከሃዲነት ለማሳነቅ ተሞከረ፡፡ የሕወሓት “ዘረኝነት” ከአንድ ብሔር-ክልል አልፎ በአውራጃ ተመነዘረና የትግራይ ሕዝብ በአውራጃ እንዲናቆርም ተጋበዘ፡፡

      እልህ በእልህ ተያይዞ አዘቅት መውረዱ ቀጠለ፡፡ ቅንጅት (መጋቢት 28/97) ኢሕአዴግ ወያኔ ከዘረኛም ዘረኛ የወረደ ዘረኛ፣ ያ ሁሉ ኩባንያ በአንድ ድርጅት በአንድ ብሔር ተይዞ ይህ ነው እኩልነት? የሚል የቅስቀሳ ሃተታ በቴሌቪዥን አሠራጨ፡፡ ኅብረቱም እኛ ለአገር ስንዋጋ (በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት) እሱ ልቡ ከሌለ ኖሯል? እኛን በጦርነት ለመቀነስ ኖሯል ፍላጎቱ፣ መበጣጠሱ ገና ይቀጥላል የሚል ዘፈን እያዘፈነ መርዘኛ ቅስቀሳ በተነ፡፡ በሌላም ጊዜ ያንኑ ዘፈን ለቆ በማዘፈን የሁለት መንግሥትና የሁለት አገር መሪ ኢትዮጵያ አትሻም ብሎ ለፈፈ፡፡

      ኢሕአዴግ ምን ያህል ሊያባላ የሚችል ችግር እንደሰነቀረ ሊታየው ይቅርና ጎሰኛ ጥላቻንና ግጭትን የሚታገል አስመስሎ ሌላ መርዝ አነሳ፡፡ አንደበቱን መጠበቅ የተሳነው ትልቅ የቅንጅት ተከራካሪ በዘር በጎሳ ሳይሆን እንድመረጥ የምሻው በአስተሳሰቤ ነው በማለት፣ ሒደት ውስጥ በስሜት እየተነዳ እንስሳ አይደለሁም ዘር አልቆጥርም ሰው ነኝ ብሎ ይናገራል፡፡ ኢሕአዴግ ይህችን ጠልፎ ሕዝቦችን በእንስሳ ደረጃ የማየት ዘለፋ ተካሄደ፣ በጎሳ መኖር እንስሳነት ነው ተባለ የሚል መግለጫ አስነገረ፡፡ የወላይታ ሕዝብ ወላሞ ተባለ እያለ ቀሰቀሰ፡፡ በመለስና በሕወሓት የሥልጣንና የኩባንያ አግበስባሽነት ላይ የተነሳውን ቅዋሜ በአንድ ግለሰብና በአንድ ሕዝብ ላይ የሚካሄድ ዘመቻ ሲል ገለጸ፡፡ እሱ ራሱም የሚያጨፋጭፍ እሳት እየበተነ ተቃዋሚዎች የሩዋንዳ ዓይነት ጭፍጨፋ ሊያይዙ ነው፣ ሊቆጣጠሩት የማይችሉትን ቦዘኔም እያነሳሱ ነው የሚል ዘመቻ ከፈተ፡፡ እነዚህ ሁለት ወገኖች በሚያወዛውዙት እሳት ቱግ የሚል ቢገኝ ኢትዮጵያ መትረፊያም ባልነበራት፡፡ ኢሕአዴግ ወያኔ ሲጨንቀው የሆነ ጎሰኛ ጥፋት አቀናብሮ የተቃዋሚዎች የቅስቀሳ ውጤት ይኸው በማለት ቅዋሜን ሊመታ እንደሚችል የቅስቀሳ ሥልቱ ይጠቁማል፣ ተቃዋሚዎቹም ተባብረውታል፡፡ የኢትዮጵያውያንን መጨፋጨፍ ጥቅሜ ለሚል መሰሪ ቡድንም በርካታ ማላኮሻ ነድ እየሰጡ መሆናቸውን ሁለቱም ወገኖች የተረዱት አይመስሉም፡፡

      የኢሕአዴግ መንግሥት የምርጫ 97 ዴሞክራሲያዊነት ተጓድሎ ተቃዋሚዎች “ሰበብ እንዳያገኙ” ላይ ላዩን እየለፋ (የሥነ ምግባር መመርያ አዘጋጅቶ ለአባላቱ እያስተማረ፣ ከደንብ ውጪ ሲሠሩ የተገኙና ገለልተኛ ላለመሆናቸው ማስረጃ የተገኘባቸውን የምርጫ አስፈጻሚዎች እያስቀየረ፣ ወዘተ) ውስጥ ውስጡን ግን በሠለጠነበት የሸፍጥ መንገድ መሥራቱን ቀጠለ፡፡ የተቃዋሚዎቹን ዕጩዎች እያስፈራራ፣ በጥቅም እየደለለና ተቃዋሚ አስመሰሎ ባሰረጋቸውም እየተጠቀመ “በገዛ ፈቃድ” ከዕጩነት ራሳቸውን እንዲሰርዙ በማድረግ ተቀናቃኞቹን ይቀንሳል፡፡ የተቃዋሚ አባላትና ዕጩዎች በተለይ ገጠር ገጠሩን የሚያካሂዷቸውን የዕለተ ገበያ የምርጫ ዘመቻዎች በተለያየ ሥልት ያወለካክፋል፡፡ “መንግሥት የለም ግብር አትክፈሉ” የሚል ሕገወጥ ቅስቀሳ ተካሄደ እያለ ተቃዋሚዎቹን ያሯሩጣል፡፡ ስብሰባዎችን ተንኩሶ ወደ ረብሻና ፀብ ይቀይራል፣ ይገድላል፡፡ ከናካቴው በገበያ ቦታ መቀስቀስ (200 ሜትር ርቆ ካልሆነ) የተከለከለ ይሆናል፡፡ ያም ሆኖ ሕዝብ በሰላይ ፍርኃት ከገበያ በተነጠለ ስብሰባ ከመሳተፍ አልተቆጠበም፡፡ ኢሕአዴግም እየተነኮሰ ወደ አምባጓሮ መቀየሩ፣ ተቀዋሚዎችን በአመፅና በሽብር መወንጀሉ፣ ማዋከቡ፣ ማሰሩና በድንገተኛ ፀብ እያስመሰለም መደቆሱ እየበረታ ሄደ፡፡

      ከባርነት መውጪያ እየተባለ ተስፋ የተዘራበትን ምርጫ፣ በስተኋላ ነፃና ፍትሐዊ አይደለም ብዙ አፈናና ማሸበር እስራትና ግድያ እየተካሄደብን ነው፣ የምርጫ ቦርድ ነፃ ምርጫ ለማስፈጸም አቅምና ብቃት የለውም፣ የገዥውም ፓርቲ መመርያ ተቀባይ ነው፣ የምርጫ ካርዱ የቤት ቁጥር መጻፊያ  ስለሌለው ለማጭበርበር የተመቸ ነው ማለት መጣ፡፡

      ታሪክ ምሥጋና ይግባትና ሲቸግር ቅንጅትና ኅብረቱ የየብቻ ሩጫቸው እንደተጠበቀ ቢሆንም ተቀራረቡ፡፡ ለአንዳቸውም አስተማማኝ ባልሆነ አካባቢ የድምፅ ሽሚያ ማድረግ ተቀናቃኛቸውን መጥቀም መሆኑን አስተዋሉ፡፡ በተቻለ በድምፅ ለመተጋገዝ አንዳቸው ቢያሽንፉ ሌላው ተባባሪ ሊሆን የብቻ አሸናፊነት ከጠፋ የጋራ ጥምር መንግሥት ሊመሠርቱ ተስማሙ (ኢትኦጵ ጋዜጣ ሚያዚያ 26 ከፀ 97)፡፡ በመድረክ የነገር አቀዳደድና የሽሙጥ ብልጫ አንጀትን ከማራስ ባለፈ ኢሕአዴግን በዘዴ አለሳልሶ መያዝ አዋቂነት መሆኑም ልብ ተባለ፡፡

      የጨነቀው ኢሕአዴግ ግን የሚለሳለስ አልሆንም፡፡ ተቃዋሚዎችን በሥርዓት ቀልባሽነት፣ በሽብርና በጎሳ ጭፍጨፋ አራማጅነት ከማውገዝና ለማስወገዝ ከመጣር አልተመለሰም፡፡ በቀይ ሽብር ተጎጂዎችና የመታሰቢያ ሐውልት ግንባታ ማኅበር በኩል ያቀናበረው ክርክርም የዚህ አንድ መታያ ነበር፡፡ ኢሕአዴግና ቅንጅት ተጋጠሙ፡፡ ኢሕአዴግ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ለፍርድ ቤት በሰጡት ምስክርነት ደርግ አልጨፈጨፈም ያሉ እያስመሰለና ይህንንም የቅንጅት አቋም እያደረገ ቀይ ሽብር ለዴሞክራሲ የታገሉ ወገኖች የተጨፈጨፉበት የግፍ ተግባር የመሆኑን ግማሽ ሀቅ አደመቀ፡፡ ቅንጅቶች ደግሞ ሌላውን ግማሽ አጥብቀው የፖለቲካ ወገን ተለይቶ ከሁለት አቅጣጫ ጥፋት መድረሱን፣ ከዚያም ወዲህ (በኢሕአዴግ ጊዜ) ቂም በቀል የፈጠሩ ጥፋቶች መፈጸማቸውን እየጠቀሱ የዕርቅን አስፈላጊነት አስታጋቡ፡፡

      ግጥሚያው ከዚህም አለፈ፡፡ “ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ቅብጥርሶ ብላችኋል፣ የትግራይ ሕዝብ የፋብሪካ ዕቃ ተብሏል፣ ብሔሮችን እንስሳ ብላችኋል፣ እመኑ ይቅርታ ጠይቁ፣ የብሔሮች መብት አይዋጥላችሁም፣ “የኢንተርሃሞይ” ዓይነት የጥላቻ ፖለቲካ ታራምዳላችሁ” የሚል ትግያ መጣ፡፡ ቅንጅቶች በብሔር ለማጋጨት መሞከር ለማንም አይጠቅምም፣ ኧረ አደገኛ ነው! ኧረ ተው! እያሉ ተማፅነው የወተር፣ የአረካ፣ የጎንደር፣ ወዘተ ጭፍጨፋን እያስታወሱ ኢንተርሃሞይነትን ወደ ኢሕአዴግ አስጠጉ፡፡ “እንስሳ” ብላችኋል የሚለው ውንጀላም (ቃሉ በስህተት አፌ ላይ መጥቶ ነው የሚል ይቅርታ እንኳ ሳይጠየቅ)፣ እኔ ብሔሬን በተጠየቅሁ ጊዜ መመረጥ የምሻው በአስተሳሰቤ እንጂ በብሔር ማንነቴ አይደለም ነው ያልኩት፣ እኔ ወርቅ ከሆነው የትግራይ ሕዝብ ተወለድኩ አላልኩም፣ መናገር ካላብኝ ዛሬ እናገራዋለሁ ወርቅ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የተወለድኩት በሚል ጮካነትና አክሮባት ታለፈ፡፡

      ከዚህም የባሰ ተባለ፡፡ ከተሳታፊ መሀል አንድ የኢሕአዴግ ደጋፊ ፕሮፌሰር መስፍን ሕዝብን ካንሰር ብሏል ብሎ ያልተባለ ለደፈ፡፡ ኢሕአዴግን ወክሎ መድረክ ላይ የተቀመጠ ተከራካሪ (በስመ ማኅበራት ለፕሮፓጋንዳ የተመቻቸ ክርክር የማዘጋጀት ሚስጥሩ ባርቆበት) ማንም ሳይጠይቀውና ሳይወቅሰው፣ ይህንን መድረክ ኢሕአዴግ አዘጋጀው የምትሉት ጥያቄ ስለተጠየቃችሁ ነው? እናንተን የሚያጋልጥ ጥያቄ ከመጣ ኢሕአዴግ አቀናብሮት ነው ማለት ነው? እያለ ሲቀባጥር ታየ፡፡

      በመጨረሻም ቅንጅት ብሐራዊ ዕርቅና የወንጀለኛ ተጠያቂነት አይደበላለቅ፣ ትናንት ብቻ ሳይሆን በሕግ መጠየቅ ያለባቸው ወንጀለኞች ዛሬም አሉ፣ ብሔራዊ ዕርቅ ሁላችንንም አሻናፊ ያደርገናል ብሎ ሲያጠቃልል፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ተቃዋሚዎች ሥልጣን ቢይዙ የመጀመሪያ ዕርምጃቸው የታሰሩትን ወንጀለኞች መፍታት ነው፣ ከኢሕአዴግ ደርግ ይሻላል ባዮች ናቸው ሲል ዘጋ፡፡ ለእኛ ለአድማጮቾቹ ያስቸግራል እንጂ ለእነሱ ያለ ወረፋ አንድ ላይ ቢለፈልፉም ልዩነት አልነበረውም፣ ጆሮአቸውን ጠቅጥቅው ተጯጩኸው በስተመጨረሻ ተቃቀፉ፡፡ (ይቀጥላል)

[የሰሚ ያለህ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እሪታ በበቀለ ሹሜ 1999 መጽሐፍ የተወሰደ]

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...