Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በቅርቡ አሜሪካ ለአንድ ወር ያህል ቆይቼ ነው የተመለስኩት፡፡ በአሜሪካ ቆይታዬ በአንድ ታዋቂ የግል ባንክ ውስጥ ይሠራ ከነበረ ነባር የባንክ ባለሙያ ጋር ቨርጂኒያ ተገናኝተን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሥራው ጋር በተገናኘ የገጠመውን ነው የምነግራችሁ፡፡ ከዓመታት በፊት ከአሜሪካ የመጡ ታዋቂ የባንክ ባለሙያዎች (ባልና ሚስት ናቸው) እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ሥልጠና ሲሰጡ ነበር፡፡ ይህ ጓደኛዬም ከሌሎች መሰል የባንክ ባለሙያዎች ጋር የሥልጠናው ተሳታፊ ነበር፡፡ በዘመናዊው ዓለም የባንክ አሠራር የደረሰበትን ደረጃ አመላካች የሆኑ ገለጻዎች ሲደረጉላቸው፣ የእኛዎቹ የባንክ ባለሙያዎች ያሉበትን ሁኔታ እያጤኑ መገረም፣ መደንገጥ፣ ብሎም ማፈር ይታይባቸው ነበር፡፡ ባልና ሚስቱ ናይጄሪያውያን አሠልጣኞች የምዕራቡን ዓለም በተለይም የአሜሪካ ባንኮችን አሠራር በንፅፅር እያነሱ ገለጻ ሲያደርጉ የተገረመው ጓደኛዬ፣ ‹‹ኃፍረቱ እስካሁን አለቀቀኝም…›› ነበር ያለኝ፡፡

ጓደኛዬ እንደሚለው ባንኮቻችን ከደንበኛ መስተንግዷቸው ጀምሮ እስከ ብድር አፈቃቀዳቸውና ተጨማሪ ደንበኞችን ከመሳብ አንፃር ያላቸው ብቃት አንዱ መነጋገሪያ ነበር፡፡ እነዚህ ባልና ሚስት አሠልጣኞች በአገሪቱ ያሉትን ባንኮች የደንበኛ አያያዝ በተመለከተ የታዘቡት አንዱ ማሳያ እነሆ፡፡ በእነሱ ምልከታ መሠረት ብዙዎቹ ባንኮች አገልግሎት የሚሰጡት ደንበኞችን ወረፋ አስይዘው እያስጠበቁ ነው፡፡ ጊዜ ውድ በሆነበት በዚህ ዘመን የባንክ ደንበኛ እንዴት ወረፋ እየጠበቀ ይገለገላል? አሠራራቸውን ቀልጣፋ አድርገው ደንበኞችን ከአንድ ደቂቃ በታች ማስተናገድ እንዴት ያቅታቸዋል? እግሩ ድንገት ያመጣውን አልፎ ሂያጅ ተስተናጋጅና ኮርፖሬት ደንበኛን እኩል ማስተናገድ ምን የሚሉት አሠራር ነው?

በተጨማሪም አንድ ባንክ ከደንበኞች ጋር በሚሠራበት ወቅት እንደ ደንበኞቹ ጠቃሚነትና አስፈላጊነት ደረጃ፣ የተለያዩ የአገልግሎት አሰጣጥ መሥፈርቶችና ደረጃዎችን በማውጣት ማስተናገድ ሲገባው፣ ሁሉንም አንድ ላይ ማንጋጋት አስቂኝ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ በውጭ አገር የሚገኙ ባንኮች የበለጠ አትራፊና አስተማማኝ ሆነው ለመቀጠል ለደንበኞቻቸው እንደ ሰጡዋቸው ደረጃ፣ ሰጥ ለጥ ብለው እየተንከባከቡ ሲያገለግሉ በርካታ ደንበኞችን ይስባሉ፡፡ በኮርፖሬት ደረጃ ያሉ ደንበኞችን ደግሞ በልዩ መስተንግዶና እንክብካቤ ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ እንዲህ ማድረግ የተሳናቸው ባንኮች ደንበኞቻቸው ትተዋቸው ስለሚሄዱ ሲከስሩ፣ የተሻሉት ደግሞ የበለጠ አትራፊና ተወዳጅ ይሆናሉ፡፡ የአገራችን ግን ለደንበኞች የማይመችና ከዘመኑ ጋር መራመድ የተሳነው ሆኖ ተፈርጆ ነበር፡፡

- Advertisement -

በእርግጥም ብዙዎቹ የባንክ ቅርንጫፎች ስንሄድ አንዴ ኔትወርክ የለም፣ ሌላ ጊዜ ኤሌክትሪክ የለም፣ ሲብስ ደግሞ ሠራተኞች ለምሳ ወይም ለሻይ ወጥተው በአንድና በሁለት መስኮት ማስተናገድ የተለመደ ነው፡፡ እኔ ራሴ አንድ ጊዜ የአንድ ባንክ ቅርንጫፍ ቼክ ለመመንዘር እሄዳለሁ፡፡ መኪና ያቆምኩት ሥፍራ በጣም ከመጣበቡ የተነሳ መውጫ መግቢያው አላፈናፍን የሚል ነው፡፡ በግምት 40 ያህል ሰዎች በሦስት መስኮቶች ብቻ ሲስተናገዱ ቀሪዎቹ ሰባት መስኮቶች ተዘግተዋል፡፡ ቼኩን መዘርዘር ደግሞ የግድ ነበር፡፡ ለ20 ደቂቃዎች ያህል ቆይቼ ጉዳዬን ጨርሼ ስወጣ የመኪናዬ የኋላ ፍሬቻ ተሰባብሮ መሬት ላይ ተዘርቷል፡፡ የገጨኝ አሽከርካሪ በቦታው የለም፡፡ የአምስት ሺሕ ብር ቼክ ለመመንዘር ሄጄ ዕዳ አትርፌ ተመለሰኩ፡፡ ይህ የባንኩ ቀርፋፋ አሠራር የፈጠረው ችግር ለእኔም ተረፈኝ፡፡ ባንኮች የእሑድና የበዓላት አገልግሎት አለመስጠታቸው በራሱ የሚገርም ነው፡፡ በልዩ አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ማትረፍ ሲገባ ይተኛል፣ ያሳፍራል፡፡

የብድር አሰጣጥን በተመለከተ የተነሳው ደግሞ እንዲሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተቀረው ዓለም ባንኮች በጣም ብዙ አበዳሪዎች እንዲኖሩዋቸው ይፈልጋሉ፡፡ ከሰጡት ብድር የሚያገኙት ወለድ ትርፋቸው ነው፡፡ ባንኮቹ ብድሩን ዝም ብለው አይደለም የሚዘሩት፡፡ አዋጭ የሆኑ ቢዝነሶችና ፕሮፖዛሎች ለብድር ተፈላጊ ናቸው፡፡ ባንኮቹ ብድሩን ሰጥተው ደንበኛቸው በሚገባ እየሠራ እንዲከፍልና የበለጠ ሥራውን እያስፋፋ እንዲሄድ ያግዛሉ፡፡ ከተገኘው ውጤት ደግሞ ድርሻቸውን ያገኛሉ፡፡ ተጨማሪ አትራፊ የሆኑ ደንበኞችን በብዛት ያገኛሉ፡፡ ትርፋቸውም የዚያኑ ያህል ይጨምራል፡፡ የእኛ አገር የባንክ አሠራር የተተቸው ትልቁ ትኩረቱ ማስያዣ ሆኖ በልማዳዊ አሠራሮች ብቻ መታጠሩ ነው፡፡ በርካታ ተበዳሪዎችን በማፍራት ሥራ ከመፍጠር ይልቅ፣ የጥቂት ተበዳሪዎችን ኮላተራል ብቻ እያነፈነፉ መሥራት ኋላቀርነት ነው የተባለው፡፡

ባንኮች መረን የለቀቀ ብድር ይስጡ ሳይሆን፣ በትክክል ሥራ ውስጥ ገብተው ውጤታማ የሚሆኑ ሰዎችን ፕሮፖዛሎች ይመልከቱ፡፡ የሥራ ፈጠራና የውጤት ክህሎት ያላቸውን ሰዎች (በተለይ በትምህርት የታገዘ ዕውቀት ያላቸውን) በመሳብ ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ሲገባ፣ በየባንኩ እንቅልፋቸውን የሚለጥጡ ሚሊዮን ብሮች በዝተዋል ነው የተባለው፡፡ ‹‹ገንዘብ ያለው ይሥራ ያሠራበት…›› ከሚለው ዕድሜ ጠገብ የጥላሁን ገሠሠ የዘፈን ማሳሰቢያ በተቃራኒ፣ ገንዘብን ለተወሰኑ የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ብቻ ማሰብ ከኋላቀርነት በላይ የሚገልጸው የለም ነው የተባለው፡፡ የባንክ ባለሙያዎቹ በአሠልጣኞች የተመከሩትም ይህንን ነው፡፡

ጓደኛዬ በወቅቱ ከሥልጠናው ካገኘው ግንዛቤ የተረዳው በአገሪቱ ያለው የባንክ አሠራር ከዓለም አቀፉ ተሞክሮ በተቃራኒ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹የገባኝ ነገር ቢኖር አሠራሮቻችን በሙሉ በሴክተሩ ካሉ አሠራሮች ጋር ሲነፃፀሩ በጣም የሚቃረኑ ናቸው፡፡ አሠልጣኞቹ እንደነገሩን አንድ የውጭ ባንክ እዚህ አገር የገባ ዕለት ወዮልን፡፡ የደንበኛ አያያዛችን፣ ለዘመናዊ የባንክ አሠራር ያለን ግንዛቤ ማነስ፣ ተለምዶአዊና ባህላዊ የሆኑ ጎታች አሠራሮቻችን ዛሬም ባሉበት መቀጠላቸው ሲታሰብ በእርግጥም ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ በዘመነ ግሎባላይዜሽን በሩ የተከፈተ ዕለት ጎርፍ ነው የሚወስደን፡፡ በቅርቡ አሥር ግለሰቦች ብቻ ከ440 ቢሊዮን ብር በላይ መበደራቸውን ስሰማ ከአሥር ዓመታት በፊት የተሰጠን ሥልጠና ነበር ትዝ ያለኝ፡፡ ባንኮቻችን በቴክኖሎጂ ዘምነዋል ቢባልም ዛሬም እዚያው እያዳከሩ እንዳሉ ነው የምሰማው…›› እያለ ብዙ ነገሮች ነገረኝ፡፡ እኔ ደግሞ በባንኮቻችን ብቻ ሳይሆን እንደ አገር በተለያዩ ጉዳዮቻችን አመለካከቶቻችንንና አሠራሮቻችንን ለማዘመን ካልተነሳን ጎርፉ ወደ ባሰ መጥለቅለቅ ይቀየራል እላለሁ፡፡

(አማኑኤል ኢሳያስ፣ ከላፍቶ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...