Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየኢትዮጵያ የፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት እምን ላይ ነው?

የኢትዮጵያ የፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት እምን ላይ ነው?

ቀን:

የዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ ሊካሄድ ሁለት ወር ከአንድ ቀን ቀርቶታል፡፡ ኢትዮጵያም እንዳለፉት ኦሊምፒያዶች ሁሉ በአሁኑ የ33ኛው ኦሊምፒያድ ጨዋታዎች ላይ በተለይ ውጤታማ በሆነችበት የመካከለኛና የረዥም ርቀቶች እንዲሁም በማራቶን ብርቱ ተወዳዳሪ ሆና ለመገኘት ዝግጅቷን ተያይዛዋለች፡፡

 የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅትን በተመለከተ ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዋናነት በምትሳተፍበት አትሌቲክስ፣ በማራቶን የሚወዳደሩ ከነተጠባባቂያቸው ተመርጠውና ካምፕ አድርገው ልምምምድ የጀመሩ ሲሆኑ፣ በሌሎች ውድድሮች የሚሳተፉት የመጨረሻ ተሰላፊዎች ዝርዝር ለሚኒማ ማምጫው በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት የሚታወቁ ይሆናል፡፡ ሰኔ 7 ቀን በስፔን ማላጋ በሚከናወነው የማጣሪያ ውድድርም የ10 ሺሕ ሜትርና የሌሎች ርቀቶች ተወዳዳሪዎች ይለያሉ ተብሏል፡፡

- Advertisement -

ለማራቶን ሁለት አሠልጣኞች፣ ለረዥም ርቀት አራት አሠልጣኞች፣ ለ3000 ሜትር መሰናክል ሦስት አሠልጣኞች ለዕርምጃ ውድድር አንድ አሠልጣኝ ተመርጠው፣ መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ቤል ቪው ሆቴል ተጠቃለው በመግባት በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ በማሠራት ላይ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ኦሊምፒኩ ኢትዮጵያውያንን እንዲያሳትፍ ‹‹ኢትዮጵያ ትወዳደር ተወዳድራም ታሸንፍ›› በሚል መሪ ቃል እስከ 200 ሺሕ የሚደርሱ ዳያስፖራዎች በውድድሩ ስፍራ እንዲገኙ በፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኦሊምፒክ ዝግጅቱት የተሟላና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የባለቤትነት ስሜት ይኖረው ዘንድ እስካሁን በሰባት ክልሎች የችቦ ቅብብል መደረጉ፣ በቀሪዎቹ ክልሎችም በተመሳሳይ ከተከናወነ በኋላ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ በአዲስ አበባ እንደሚፈጸም የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በቅርቡም መንግሥት፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብና ባለሀብቶች የሚታደሙበት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እየተዘጋጀ መሆኑም አክለዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫ ከተነሱት ጥያቄዎች አንዱ የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊዋ ሱቱሜ አሰፋ ለምን አልተመረጠችም የሚለው ሲሆን የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምላሻቸውም ‹‹የምርጫ መሥፈርት የተዘጋጀው የፓሪስ 2024 አሊምፒክ ዝግጅት ከመጀመሩ በፊት ነው፡፡ መሥፈርቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ዋና ውድድር ተወዳድሮ አስፈላውን ሰዓት ያስመዘገበ/ች ይላል፡፡ እንደተባለው ሱቱሜ አሰፋ በዚህ ዓመት ቶኪዮ ላይ ተወዳድራ አሸናፊ ብትሆንም፣ ከቶኪዮ በፊት ችካጎ ላይ ተወዳድራ 15ኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ሊያስመርጣት አልቻለም፤›› የሚል ነው፡፡

የአትሌቲክስ ማዘውተሪያን በተመለከተም ችግሩ የከረመና የታወቀ መሆኑን፣ አትሌቶቹ እስካሁን እየሠሩ የሚገኙት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ ትራክ ላይ መሆኑን፣ ችግሩ እንደ አገር የሁላችንም በመሆኑ ምክንያት ማድረግ አንፈልግም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) በሚገኘው ግቢው ውስጥ ያስገነባው ደረጃውን የጠበቀ ትራክ፣ ለአትሌቲክሱ በጣም ተስፋ ሰጭ መሆኑን ያወሱት ፕሬዚዳንቷ፣ የምዕራፍ አንድ ዝግጅት በአዲስ አበባ ካበቃ በኋላ የቢሾፍቱውን ትራክ ለሁለተኛው ምዕራፍ ዝግጅት እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል፡፡ የቢሾፍቱ አየር ፀባይ ከፓሪስ ጋር የሚቀራረብ መሆኑ ጠቀሜታ እንዳለው አውስተዋል፡፡

የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት በተመለከተ የተናገሩት የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት፣ ‹‹ከሁለቱ ተቋማት ጀርባ ትልቅ ሕዝብ እንዳለ መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ የኦሊምፒክ ጉዳይ የሕዝብ እንጂ የግለሰቦች ጉዳይ ተደርጎ መወሰድም የለበትም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዝግጅቱ ባለቤት ኦሊምፒክ ቢሆንም፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ግን በዋናነት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊነት ሆኖ እየተናበብንና እየተግባባን በጋራ አቅደን ውጤት ለማምጣት እንሠራለን፡፡ እየሠራንም ነው፤›› ብለዋል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ችግር የመንግሥት ወይም የአንድ ተቋም ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ፣ ጉዳዩ ኦሊምፒክን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የሚመለከት እንደሆነ ጭምር ተናግረዋል፡፡

‹‹የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ለምን የለም?›› ለሚለው ጥያቄም ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ሲመልሱ፣ ‹‹ይህ ጉዳይ ጥናትን መሠረት አድርጎ የተወሰነ መሆኑ አውቃለሁ፡፡ የለም ጉዳት አለው የሚል ነገር ከመጣ ደግሞ ጥናቱን እንደገና መለስ ብሎ መመልከት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ይህንኑ ምላሽ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት በመጋራት ውሳኔው የኦሊምፒክ ወይም የፌዴሬሽኑ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የአሠልጣኞች ምርጫ የተደረገውም ‹‹ባስመረጠው አትሌት ልክ›› ስለሚል አንዳንድ አሠልጣኞች አትሌት ይዋዋሳሉ በሚል ይተቻሉ ለሚለውም፣ ፌዴሬሽኑ የተረጋገጠ ማስረጃ ባይኖረውም፣ ሲነገር በመስማቱ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንና ማስረጃ ሲገኝ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ አሠልጣኞች አመራረጥ እንዴት ነው ለሚለውም ጥያቄም መመርያው ላይ የተቀመጠው ‹‹ብዙ ባስመረጠ›› የሚል ስለሆነ ይህንኑ መሠረት አድርጎ መከናወኑን ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች አስምረውበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...