Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

ቀን:

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከተሾሙበት የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ምንጮች ገለጹ።

ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ሹመታቸው ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት መዋቅር በመልቀቅ በግል ተቀጥረው በሙያቸው ለማገልገል ማቀዳቸውንም ምንጮቹ ገልጸዋል። ስለሺ (ዶ/ር) በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን ወቅት የፓርቲ አባል ሳይሆኑ የመንግሥት መዋቅርን መቀላቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚያ አስቀድመው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በውኃ ምኅንድስና ሙያቸው በግል ተቀጥረው ሲያገለግሉ ነበር። ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከአሜሪካ አምባሳደርነታቸው በመልቀቅ ወደ ቀደመ የግል ሥራቸው ለመመለስ መፈለጋቸውን የጠቀሱት የሪፖርተር ምንጮች፣ ጥያቄያቸውንም ለመንግሥት አቅርበው ተቀባይነት ማገኘቱን ገልጸዋል።

አምባሳደር ስለሺ በቀለ መልቂቂያ ስለማቅረባቸውና መልቀቂያውም ተቀባይነት ማግኘቱን በመጥቀስ መረጃውን እንዲያረጋግጡ የጠየቅናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ (አምባሳደር)፣ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

- Advertisement -

ቃል አቀባዩ አምባሳደር ነብዩ በሳምንቱ ውስጥ የተካሄዱ የውጭ ግንኙነት ጉዳዮችን አስመልክቶ ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰሞኑን ለ24 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረቦች የአምባሳደርነት ሹመት መስጠታቸውን ተናግረው ነበር። 

ከዚህ ቀደም በአምባሳደርነት የሚመደቡ ተሿሚዎች ከውጭ ጉዳይ ይመረጡ እንዳልነበረ ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፣ ሰሞኑን ሹመት ያገኙት 24ቱም አምባሳደሮች ግን ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተመረጡ መሆናቸውንና ይህም በተቋሙ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል። 

ሹመቱ ብቃትንና ልምድን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ሁሉም አምባሳደሮች በዲፕሎማሲ ዘርፍ አገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጣለበትን ከፍተኛ አገራዊ አደራ ለመወጣት የሚያግዙና ለቦታው ይመጥናሉ ተብሎ የታመነባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የተሾሙት 24 አምባሳደሮች የሥራ ምደባ (የሚመደቡበት አገር) በሚቀጥለው ሳምንት የሚታወቅ ይሆናል።

መንግሥት አምባሳደር ስለሺ ያቀረቡትን ጥያቄ ከመቀበሉ ባሻገር እርሳቸውን የሚተካ ሌላ አምባሳደር ለመመደብ መሰናዳቱንም የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል። እንደ ምንጮቹ መረጃ፣ አምባሳደር ስለሺ በቀለን (ዶ/ር) በመተካት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የሚመደቡት በአሁኑ ወቀት በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ናቸው። ነገር ግን፣ ሪፖርተር ይህንን መረጃ ኦፊሳላዊ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ አልቻለም።

በአሜሪካን የኒውዮርክ ግዛት ውስጥ በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋናው መሥሪያ ቤት፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች ክፍል የኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት አማካሪ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ስለሺ (ዶ/ር)፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት መዋቅርን የተቀላቀሉት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር በነበሩበት ወቅት ወዳጅና ባልደረባቸው የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባቀረቡላቸው ጥሪ ነበር። 

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አገራቸውን እንዲያለግሉ ያቀረቡላቸውን ጥሪ በመቀበል፣ ከተመድ የአማካሪነት ሥራቸው ለቀው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ስለሺ (ዶ/ር) የውኃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር በመሆን የሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. ተቀላቅለዋል።

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትርነት የተሾሙት ስለሺ (ዶ/ር)የገዥው ፓርቲም ሆነ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልነበሩ ከመሆናቸው ባሻገር፣ በ2012 ዓ.ም. ከሚኒስትርነት ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጭምር ጥያቄ አቅርበው የሚተካቸው ሰው እስኪገኝ ደረስ በኃላፊነት እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር። በኋላ ግን ብልፅግና ፓርቲን በመቀላቀል በ2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ተወዳድረው በማሸነፍ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል። ነገር ግን ምርጫውን ተከትሎ በ2014 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በተመሠረተው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቢኔ ውስጥ በሚኒስትርነት ሳይሾሙ ቀርተዋል። በኋላም የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል።

የውኃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ሆነው ካገለገሉ አምስት ዓመታት በኋላም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአምባሳደርነት ያገለገሉት ስለሺ (ዶ/ር)፣ በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪ በመሆን ባበረከቱት ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በስፋት የሚታወቁ ሲሆን፣ አንድ የውጭ ሚዲያ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ከግብፅ ጋር በመሆን በጋራ ለማስተዳደር ፈቃደኛ ትሆን?›› ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ግድቡ የኔ ነው!›› በማለት በሰጡት ምላሽ ከፍተኛ ዝናን አትርፈዋል።

አምባሳደር ስለሺ በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውካስል በሃይድሮሊክ ኢንጂኒየሪንግና ሃይድሮሎጂ አግኝተዋል። በኋላም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ጀርመን አገር ከሚገኘው ከድሬስደን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ አግኝተዋል።

አምባሳደር ስለሺ (ዶ/ር) ከመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ለመልቀቅ የወሰኑት፣ ቀጣይ ጊዜያቸውን ከዚህ ቀደም ወደነበሩበት ተመድ ወይም መሰል ዓለም አቀፍ ተቋም በመመለስ በሙያቸው በማገልገል ለማሳለፍ በመፈለጋቸው እንደሆነ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...