Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለንግዱ ዘርፍ የባንክ ብድር ትኩረት ተደርጎ መሰጠቱ በአምራቾች ላይ ጫና መፍጠሩ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በዘጠኝ ወራት ብዙ ኢንቨስት የተደረገባቸው 111 ሠራተኞች ከሥራ ለቀዋል ተብሏል

በአገሪቱ ከሚሰጠው ጠቅላላ የብድር መጠን በወጪና ገቢ ንግድ ላይ ለተሠማሩ ባለሀብቶች በከፍተኛ የብድር መጠን መቅረቡ፣ በአምራች ዘርፉ ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተነገረው የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሲገመግም ነው።  

ብሔራዊ ባንክ ከወር በፊት ይፋ አድርጎት የነበረው የፋይናንስ ስቴቢሊቲ ሪፖርት (Financial Stability Report) በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ባንኮች፣ እስካለፈው ዓመት ሰኔ መጨረሻ ድረስ በሥራ ላይ ካዋሉት አጠቃላይ 1.9 ትሪሊዮን ብር ብድር ውስጥ፣ 23.5 በመቶውን የሰጡት ለአሥር ተበዳሪዎች መሆኑን ማስታወቁ አይዘነጋም።  

ይህን መረጃ መነሻ በማድረግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብቻውን ባይመለከተውም፣ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን የብድር ሥርጭቱን ፍትሐዊ ለማድረግ ምን እየሠራ ነው በማለት፣ የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ሙሉቀን አድማሱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የብድር አቅርቦቱን በሁለት መንገዶች እንደሚመለከቱት የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ ከአጠቃላይ የብድር አቅርቦት ለአምራች ዘርፉ ምን ያህሉ እየተሰጠ ነው የሚለው ቀዳሚው መሆኑን ገልጸው፣ በሁለተኛነትም ብድሩ ለማን ነው የሚቀርበው የሚለው ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል።  

‹‹በቋሚ ኮሚቴው ብድር ለማን ነው እየቀረበ ያለው ተብሎ የተነሳው በጣም አነጋጋሪና ለወደፊቱ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ብዙ የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ሥራ ፈጣሪዎች ፋይናንስ በተለያዩ አማራጮች እያገኙ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

በአገሪቱ ከሚቀርበው አጠቃላይ የብድር አቅርቦት ውስጥ ለአምራች ዘርፉ ምን ያህል ቀረበ የሚለው ሲታይ ጤናማ አለመሆኑን፣ መሥራት የሚፈልግ በርካታ ቁጥር ያለው ዜጋ የሚያነሳው አንደኛው ጥያቄ የፋይናንስ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።  

‹‹አብዛኛው ብድር እየሄደ ያለው በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ለተሠማሩ ባለሀብቶች መሆኑን፣ ይህም ኢኮኖሚውን የሚጠቅም ስላልሆነ ለአምራች ዘርፉ ተጨማሪ ብድር እንዲሰጥ ግፊት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል። በሌላ በኩል ሥራዎች በከፍተኛ የበጀት እጥረት እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት አቶ መላኩ፣ ‹‹ከመንግሥት ከሚያዝልን በጀት ይልቅ ከግሉ ዘርፍ ለምነን የምንሠራው ሥራ ከፍተኛ ነው፤›› ብለዋል።  

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 148 የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶች መሳብ መቻሉን፣ ከ129 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 526 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት መሠማራታቸው ተገልጿል፡፡

የሚኒስቴሩ ሪፖርት እንደሚያሳየው በዘጠኝ ወራት 131.3 ቶን ምርቶች ወደ ውጪ ለመላክ ታቅዶ 107.380 ቶን የተላኩ ሲሆን፣ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 336 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ፣ 202 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ተመላክቷል፡፡ ይህም በተለያዩ የምርት ዓይነቶች የተለያየ አፈጻጸም የተመዘገበበት ነው፡፡

የጂቡቲ ጉምሩክ አሠራር በየጊዜው መቀያየር (አነስተኛ የኮንቴይነር መጠን ገደብና የዶክመንት አቀራረብ ሥርዓት መለወጥ)፣ እንዲሁም በቀይ ባህር ባለው የሎጂስቲክስ ሥጋት ከባለፈው ጥቅምት ጀምሮ ግብዓት በማስገባትና በኤክስፖርት ሥራ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ፣ ከአጎአ ገበያ ጋር በተያያዘ የገዥዎች የምርት ትዕዛዝ በከፍተኛ ደረጃ መቀዛቀዝ መታየቱና በኢንዱስትሪዎች በርካታ የተመረቱ ምርቶች ክምችት እንዲፈጠር ማድረጉ፣ እንዲሁም በፀጥታ ችግር የግብርና ምርት ግብዓትን ከማሳ ወደ ፋብሪካ ማጓጓዝ አለመቻል ዝቅተኛ አፈጻጸም ለተመዘገበባቸው ዘርፎች ሚኒስቴሩ በምክንያትነት አቅርቧል፡፡ 

በተጨማሪም በአማራ ክልል ከፍተኛ የኤክስፖርት ድርሻ የነበራቸው የጨርቃ ጨርቅ፣ የምግብና የመጠጥ፣ እንዲሁም የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ኤክስፖርት አለመደረጋቸው ሌላው ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በዘጠኝ ወራት ውስጥ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት 111 ሠራተኞች መልቀቃቸውን ሚኒስትሩ በዘጠኝ ወራት ሪፖርታቸው ገልጸው፣ ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ብዙ ኢንቨስት የተደረገባቸው ሠራተኞች በመልቀቅ ወደ ግሉ ዘርፍ እየተቀላቀሉ መሆኑን አስታውቀዋል። 

የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር)፣ የአገር ውስጥ ምርቶችን ማኅበረሰቡ እንዲጠቀም የማበረታታትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መከናወን እንዳለበት አሳስበው፣ እንደ የማዕድን ሚኒስቴር ካሉ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች