Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹መንግሥት በኮሪደር ልማቱ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ የሚመጣ ተቃውሞ አለ ብሎ አያምንም›› የውጭ...

‹‹መንግሥት በኮሪደር ልማቱ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ የሚመጣ ተቃውሞ አለ ብሎ አያምንም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ቀን:

  • የኮሪደር ልማቱ ከሚነካቸው ኤምባሲዎች ጋር ምክክር እየተደረገ እንደሆነ ተሰምቷል

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የተወሰኑ ኤምባሲዎች የግቢ አጥር የሚነካ እንደሆነ ቢነገርም፣ ‹‹መንግሥት ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ የሚመጣ ተቃውሞ አለ ብሎ እንደማያምን›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኮሪደር ልማቱ በሚያልፍባቸው መስመሮች በተለይ ግንባታ በተጀመረባቸው የፒያሳ-አራትኪሎ-መገናኛ መስመሮች በርካታ የማፍረስ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በተጠቀሱት መስመሮች የሚገኙ የኤምባሲ አጥሮች ለአብነትም የሩሲያ፣ የኬንያ፣ የቤልጂየም፣ የእንግሊዝና የኡጋንዳ ኤምባሲዎች አጥሮቻቸው አልተነኩም፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪም የቦሌ-ሜክሲኮ-ቄራ-ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከቦሌ-መስቀል አደባባይ ባሉ መስመሮች የኮሪደር ልማቱ የሚነካቸው ኤምባሲዎች እንደሚኖሩ የተገለጸ ሲሆን፣ መንግሥትም በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የሚያስችለውን ሥራ እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ  ነብዩ ተድላ (አምባሳደር) በሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንደተናገሩት፣ የከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማት ሲጀምር ከነዋሪዎች በተጨማሪ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ እንዲሁም ከ134 በላይ ኤምባሲዎች መቀመጫ ለሆነችው አዲስ አበባ እንደሚጠቅም ታስቦበት ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ምንም ዓይነት ተቃውሞ ይኖራል ብለው እንደማያምኑ ገልጸው፣ ‹‹ይህ ፕሮጀክት የሚቃወሙት ዓይነት ባለመሆኑ እኔ እስከማውቀው ከየትኛውም ኤምባሲ ምንም ዓይነት ችግር አልገጠመንም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሮቶኮል ዲፓርትመንት በኩል ከኤምባሲዎች ሊመጡ የሚችሉ ማንኛውንም ዓይነት ዕርዳታና ድጋፍ የሚፈልጉ ወይም የግልጽነትና ያለመግባባት ችግር ቢፈጠር፣ ማብራሪያ የሚሰጥ ራሱን የቻለ ክፍል መቋቋሙን ቃል አባዩ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ከአንድ ሳምንት በፊት የሰጡትን መግለጫ በተመለከተ፣ ‹‹የመግለጫው ዓውድና ፋይዳ በእኛ በኩል ገንቢነት የሌለው ነው ብለን እንወስዳለን፤›› ብለዋል፡፡ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ከዚህ ቀደም በተለመደው አግባብ የሉዓላዊ መንግሥትንና የወዳጅ አገሮችን እኩልነት መሠረት በማድረግ፣ መስመሩን በጠበቀ መንገድ በሚደረጉ ምክክሮች ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ አምባሳደር ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በአሜሪካ ግቢ ሰብዓዊ መብቶችንና አገራዊ ውይይቶችን በተመለከተ ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ መንግሥት ኢትዮጵያን እንዴት ማስተዳደር እንደሚገባው ያልተጠየቁትን ምክር ሰጥተዋል የሚል ዕሳቤ በመንግሥት በኩል መኖሩን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡

‹‹በተለይ የፖሊሲ ጉዳዮች ሲሆኑ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከሚሰጥ አቅጣጫ ተነስቶ ምክክር ይደረጋል እንጂ፣ በየአደባባዩ በሚገባ ተጠንተው ባልተዘጋጁ ጉዳዮች የሚደረግ ግለሰባዊ ንግግር ላይ በሚመሠረት አይደለም የሚል ዕሳቤ አለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹መግለጫው በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን ታሪካዊና ጠንካራ ወዳጅነት አይመጥንም፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ መደበኛና የተለመዱ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አሠራር ሒደቶችን የጣሰ በማለት ገልጸውታል፡፡ ስለዚህ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት በሁነቶች (Incident) ላይ ከመመሥረትና መንጠልጠል አልፎ፣ ስትራቴጂካዊ ሆኖ ውይይቱ ሊካሄድ እንደሚገባ አስረድተዋል

‹‹ግንኙነቱ አገሪቱ ባጋጠሟት የተለያዩ ወቅታዊና ጊዜያዊ ብሎም ልትሻገራቸው በምትችላቸው ችግሮች ልክ ሳይሆን ሊሆን የሚፈለገው፣ ባለው አቅምና ታሪካዊ ግንኙነት ልክ ሊሆን ይገባል የሚል እምነት አለን፤›› ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ በመግለጫቸው ያካተቷቸው ጉዳዮች እንደ አንድ ወዳጅ መንግሥት የቀረቡ ከነበሩ አብሮ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ክፍተቶችን ለመሙላት፣ መስመሩን በጠበቀ መንገድ በንግግርና በምምክር አብሮ በመሥራት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ችግር አጋጥሞታል ማለት አይደለም ብለዋል፡፡

የአሜሪካ አምባሳደር በተጠናቀቀው ሳምንት በተመሳሳይ ከሚዲያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከዚሁ ጉዳይ ጋር ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ለአብዛኛዎቹ መልስ ባይሰጡም፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መንገድ ለመፍታት ከእኔ በላይ ያውቁበታል፤›› የሚል ምላሽ ስጥተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከሳምንት በፊት በሰጡት የ24 አምባሳደሮች ሹመት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ሲሠሩ የቆዩ ግለሰቦችን ብቃትና የዲፕሎማሲ ልምድ መሠረት ያደረገ፣ በትምህርት ዝግጅታቸው ለቦታው እንደሚመጥኑ ታምኖት የተሰጠ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

ለቦታቸው እንደሚመጥኑና የተሰጣቸውን ሥራ መከወን ይችላሉ ተብለው የተመዘኑ፣ በተለያዩ የሥራ ዕርከኖች በከፍተኛና በመካከለኛ የሥራ ኃላፊነት ያሉ ዲፕሎማቶችን ወደፊት ያመጣ ሹመት እንደሆነ አክለዋል፡፡

የአምባሳደሮች ሹመት በዋናነት ችሎታን መነሻ ያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፣ ከዚህ ቀደም ለአምባሳደርነት የሚሾሙ ሰዎች በአብዛኛው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ አልነበሩም ብለዋል፡፡ በዚህኛው ሹመት ምናልባት ሁሉም አምባሳደሮች ከተቋሙ በሥራቸውና በልምዳቸው ታይተው የተመረጡ በመሆናቸው፣ በቅርብ ዓመታት የተቋሙ ታሪክ ውስጥ ይህንን መሰል የሥምሪት ኃላፊነት ሲሰጥ የመጀመሪያው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...