Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበኪነ ጥበብ ሥራዎችና በባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ ጥሪ ቀረበ

በኪነ ጥበብ ሥራዎችና በባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ ጥሪ ቀረበ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ‹‹ኪነ ጥበብን ማፈን የሐሳብ ነጻነትን መጋፋት ስለሆነ ተገቢ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል›› ሲል፣ በኪነ ጥበብ ሥራዎችና በባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች ይቁሙ ሲሉም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ማዕከሉ ዓርብ ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ኪነ ጥበብ የአንድ አገር የሥልጣኔ ደረጃ መገለጫ ከሆኑት ነገሮች አንዱና ዋነኛው መሆኑን፣ የአገሪቱ ጠቃሚ ዕሴቶች እንዲጎለብቱ፣ ጎጂ የሆኑት ደግሞ እንዲታረሙ ለማድረግ፣ ማኅበረሰብን ለማስተማርያነትና የሕዝብ ልብ ትርታም የሚገለጽበት የማኅበረሰብ እሴት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የጥበብ ሥራዎች ወይም የኪነ ጥበብ መድረኮች ላይ እየደረሱ ያሉ ወከባዎች፣ ክልከላዎች፣ እስሮችና ጫናዎች ከዕለት ዕለት እየበረቱ መምጣታቸው እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡

- Advertisement -

ከእነዚህም ውስጥ በጥር ወር 2016 ዓ.ም. ወቅታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት ተከታታይ ‹‹ፖለቲካ›› የተሰኘ የቴአትር መድረክ መከልከሉን አስታውሷል፡፡

በተመሳሳይ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም. ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት ‹‹ዕብደት በኅብረት›› የተሰኘው የመድረክ ተውኔት ሥራ፣ እንዲሁም የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚቀርቡባቸው የጥበብ መድረኮች የስብሰባ ፈቃድ ያስፈልጋችኋል በሚል መስተጓጎላቸውን ማዕከሉ በመግለጫው አትቷል፡፡

ኪነ ጥበብ የሕዝብ ሀብት ከመሆኑም ባሻገር ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና በተለይም ሐሳብን በነፃነት ለማሠራጨት የሚጫወተውን ጉልህ ሚና ከግምት በማስገባት፣ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚከታተላቸው የሰብዓዊ መብት ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቅሶ በጥበብ ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

መሰል ገደቦች ማኅበረሰቡ ሐሳቡን በነፃነት እንዳይገልጽ የሚያደርጉ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ወይም ነፃነትን የሚጋፉ መሆናቸውን ጠቅሶ በሕገ መንግሥቱም ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸው መደንገጉን አስረድቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቃቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም፣ የማኅበረሰቡ  ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መገለጫ የሆኑ ጉዳዮችን በነፃነትና በድፍረት ኪነ ጥበባዊ በሆኑ መንገድ የሚያሳዩ የጥበብ ሰዎች ላይ የሚደርስ በደል፣ ጋዜጠኞች በሙያቸው እውነታን ሲያወጡ የሚደርሰባቸው በደል ዓይነት አድርገው እንደሚወስዱት ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሰብዓዊ መብቶች መጠበቅን ብቻ ሳይሆን የማበረሰቡን ችግርና የዕለት ተዕለት መስተጋብርና ዕሳቤ፣ እንዲሁም አኗኗር የሚንፀበረቅባቸው በመሆናቸው፣ ዕገዳው ባለሙዎችን ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰብን የሚጎዳ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ይህ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቃቸው በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል  የሪጅን ዳይሬክተር  ሰላማዊት ግርማይ፣ ወደ ተቋማቸው አቤቱታ እንደሚመጣ ጠቅሰው ክትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በመግለጫው በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ላይ ጥበቃ የተደረገለትን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲያከብርና በዘፈቀደ እንዳይጣስም ጥበቃ እንዲያደርግ ለመንግሥት ጥሪ አድርጓል፡፡

መንግሥት ጥበብ ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለፖለቲካዊ ዕድገት ያለውን ፋይዳ ከግንዛቤ በማስገባት፣ ለጥበብ ባለሙያዎችና ሥራዎቻቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ ምኅዳሩን በማስፋት ድርሻውን እንዲወጣ፣ በሥራቸው ምክንያት የታሰሩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከእስር እንዲፈቱ ወይም የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኙም ጠይቋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ላይ በግልጽ ጥበብ እንደ አንድ ሐሳብን በነፃነት የመግለጫ መንገድ የሕግ ከለላና ዕውቅና ስለማግኘቱ ጠቅሰው፣ የተከለከሉ የኪነ ጥበብ መድረኮችም በነፃነት እንዲሠሩ አሳስቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...