Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፕሪቶሪያው ስምምነት ተጥሶ በጠለምት አካባቢ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ላይ ትንኮሳ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

የፕሪቶሪያው ስምምነት ተጥሶ በጠለምት አካባቢ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ላይ ትንኮሳ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በጠለምት አካባቢ ባሉ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ላይ ትንኮሳና ወረራ እየተፈጸመ ነው ሲል አካባቢውን የሚያስተዳድረው የጠለምት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡ ኮሚቴው ሐሙስ ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በግልጽ በመጣስ የራያ አካባቢን እንደወረሩት ሁሉ፣ በጠለምት ላይም ታጣቂ አደራጅተው በከባድ መሣሪያዎች በመታገዝ የወረራ ትንኮሳ እያደረጉ ነው ብሏል፡፡

ከተከዜ የኃይል ማመንጫ ግድብ እስከ ወልቃይት ስኳር ፋብሪካ 460 ኪሎ ሜትር ከትግራይ ክልል ከጠለምት አካባቢ ጋር ወሰን እንደሚጋራ የሚገልጸው ኮሚቴው፣ ሕዝቡ የአማራ ማንነቱ እንዲመለስለትና ወደ አማራ ክልል እንዲካለል በይፋ መጠየቁን ይናገራል፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተዋረድ እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የደረሰ ጥያቄን በሰነድ አስደግፎ ቢያቀርብም እስካሁን ጥያቄው ምላሽ ሳያገኝ እንደቆየ አትቷል፡፡

ከሕልውና ዘመቻው በኋላ አካባቢውን እያስተዳደረ መሆኑን የጠቀሰው ኮሚቴው፣ ሦስት ቀበሌዎች ከትግራይ ኃይሎች ነፃ ባይወጡም ለፕሪቶሪያው ስምምነት ለመገዛት ሲል 22 ቀበሌዎችን እያስተዳደረ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

የትግራይ ኃይሎች በግልጽ በወረቀት ከሰፈሩ የስምምነቱ አንቀጾች በሚቃረን ሁኔታ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመተርጎም ስምምነቱን ጥሰው ወረራ ፈጽመውብናል የሚለው ኮሚቴው፣ 95 ሺሕ ሔክታር በሚሸፍነው የዋልድባ ገዳም በረሃን መቆጣጠራቸውን ገልጿል፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም ታጣቂዎች እያስገቡ ትንኮሳ እየፈጸሙ ነው ያለው መግለጫው፣ የአካባቢያችንን ሕዝብ ሰላምና እረፍት ያጣ አድርገውታል ይላል፡፡

ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ በሰጡት መግለጫ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለማስፈጸም ከፌደራል መንግሥት ጋር የጋራ ማስፈጸሚያ ዕቅድ መዘጋጀቱን ተናግረው ነበር፡፡ የትግራይ አካል የነበሩ አካባቢዎችን የማስመለስ ግብ እቅዱ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ አካባቢዎች የተቋቋመውን ሕገወጥ አስተዳደር የማፍረስ፣ የታጠቁ ሕገወጥ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታትና የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ›› ሥራ መጀመሩንም በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ሌተናንት ጄኔራል ታደሰ የአጨቃጫቂ አካባቢዎች የፀጥታ ማስከበር ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ ለትግራይ የፀጥታ አካላት መስጠቱን ተናግረው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የጠለምት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አለነ አሰጋ፣ የትግራይ ኃይሎች በተፈናቃዮች መልሶ ማስፈረም ስም በአማራ መሬቶች ላይ ወረራ ነው የከፈቱት ብለዋል፡፡

ወደ 260 ሺሕ ሕዝብ መኖሪያ ነው ያሉት የጠለምት አካባቢ ነዋሪ፣ በአማራ ክልል ሥር ለመተዳደር ከአንድም ሦስት ጊዜ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የ68 ሺሕ 763 ሰው ፊርማ የያዘ ሰነድ መግባቱን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይህ ጥያቄያችን ሳይፈታ የፕሪቶሪይው ስምምነት ተጥሶ አራተኛ ዙር ወረራ እየተፈጸመብን መሆኑ ይታወቅልን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠለምት አካባቢ በተደጋጋሚ በድርቅ የተጠቃ እንደሆነ አመልክተው፣ በአማራም በትግራይም አቅጣጫ ሰብዓዊ ዕርዳታ በበቂ ሁኔተ እየቀረበለት አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሰው ከረሃብ ጋር እየታገለ ሕይወቱን ባለው አቅም ለማቆየት በሚታገልበት በዚህ ወቅት ደግሞ ሌላ ዙር ወረራ ተከፍቶበታለ ብለዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በጀት ሳይመደብለት መደበኛ አገልግሎት ሳይጀመር በቆየው አካባቢ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት ሲደርስበት ዝም ማለቱ እንዳሳዘናቸውም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...