Friday, June 21, 2024

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው ጀርመናዊ ሳይንቲስት ፍሪትዝ ሀበር ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያ ቅመማ የሠራው፡፡ ሰውዬው እ.ኤ.አ. በ1909 ያዘጋጀው የአፈር ማዳበሪያ የዓለምን ታሪክ ሙሉ ለሙሉ የቀየረ ታላቅ ግኝት ነበር፡፡

የሰው ልጆች የዘሩት ሰብል የተሻለ ምርት እንዲሰጥ ለማድረግ ከዚያ ቀደም የአዕዋፍ ኩስን እንደ ማዳበሪያነት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ጉዋኖ ይባል የነበረው የአዕዋፍ ኩስ ለማግኘት ሰዎች አገር ከማሰስ ጀምሮ በአገሮች መካከል ጦርነት እስከማካሄድ የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጉዋኖ ውዱ የዓለማችን ሸቀጥ ነበር ይባላል፡፡

ቅኝ ገዥዎች ለየሰፋፊ እርሻዎቻቸው ጉዋኖ ለማግኘት ብዙ ይማስኑ እንደነበር፣ እ.ኤ.አ. በ1850ዎቹ አጋማሽ አንድ ፓውንድ እስከ 76 ዶላር ይሸጥ እንደነበር ይነገራል፡፡

ሳይንሱ እንደሚናገረው የሰው ልጅ አካል ከኦክስጂን፣ ከካርቦን፣ ከኃይድሮጂንና ከናይትሮጂን የተገነባ ነው፡፡ ሰዎች ለሰውነት የሚያስፈልገውን ናይትሮጂን የሚያገኙት ደግሞ ከሚመገቡት ምግብ ነው፡፡ ሰብሎች ለመብቀልና ምርት ለመስጠት ናይትሮጂን ከአፈር ማግኘት አለባቸው፡፡  ሰብሎች (ተክሎች) በቅለው ለምግብነት እስኪበቁ ባለው ሒደት ከአፈር ውስጥ ያለውን ናይትሮጂን አሟጠው ይጠቀሙታል፡፡ ስለዚህ አፈር ምርታማ እንዲሆን በናይትሮጂን ንጥረ ነገር መታከም አለበት ይባላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ቴክኖሎጂ ከመተዋወቁ በፊት ጉዋኖ (የወፍ ኩስ) መፍትሔ ሆኖ ነበር የቆየው፡፡

ጉዋኖ በተለይ ምዕራብ ላቲን አሜሪካ ጠረፎች አቅራቢያ በብዛት የሚገኝባቸው ትናንሽ ደሴቶች ነበሩ፡፡ አንዳንድ አገሮች እነዚህን ደሴቶች ለመቆጣጠር ጦር እስከመስበቅ ደርሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ የዓለም ሕዝበ ቁጥር መጨመሩ የአፈር ማዳበሪያ ቴክኖሎጂን ለመፍጠር የሚደረግ ምርምርን ግዴታ አደረገው፡፡ የሰው ልጆች በናይትሮጂን እጥረትና በረሃብ የተነሳ በ30 ዓመታት ከምድረ ገጽ ይጠፋሉ የሚል ትንበያ የሚሰጡ ምሁራን ነበሩ፡፡

በዚህ መሀል ነው እንግዲህ የጀርመኑ ቀማሚ ፍሪትዝ ሀበር የአፈር ማዳበሪያን በፋብሪካ የመቀመም ፈጠራ ይዞ የመጣው፡፡ ተመራማሪው በሥራው እ.ኤ.አ. የ1918 የኖቤል ተሸላሚ የሆነበት ይህ ፈጠራ መላው ዓለምን ለወጠ፡፡ የአፈር ማዳበሪያ ከተሠራ በኋላ የሰው ልጆች ጠግቦ የማደር ጥያቄ ተፈታ፡፡ ሰዎች ከዚያ ቀደም ከሚያገኙት በአራት እጥፍ የሚበልጥ ምርት ማግኘት ቻሉ፡፡ የዓለም ሕዝብ ቁጥርም ከዚያ በኋላ በአራት እጥፍ ጨመረ፡፡ ይህ የአፈር ማዳበሪያ ግኝት ዓለማችንን የቀየረ ወሳኝ ግኝት እንደሆነ በማሳያነት የሚቀርብ ታሪክ ነው፡፡

ማዳበሪያ ከምርምር ታሪኩ ባለፈ አሁንም ድረስ የዓለም እጅግ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ሸቀጥ ነው፡፡ የማዳበሪያ ጉዳይ ከአገሮች አልፎ ዓለምን የሚንጥ ከባድ የፖለቲካ አጀንዳን የያዘም ጭምር ነው፡፡ የማዳበሪያ አምራች አገር ከመሆን ጀምሮ፣ የዓለምን የማዳበሪያ አቅርቦትና ግብይት እስከ መወሰን ደረጃ ያለው ሚና አገሮችን የሚያፋልም ነው፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ እ.ኤ.አ. ከ2020 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ዓለምን ባመሰበት ወቅት፣ የማዳበሪያ ግብይት በመናጋቱ በርካታ ችግር በዓለም ገበያ ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡ የኮሮና ተፅዕኖ ገና ሳይወገድ በዋነኞቹ የዓለም ማዳበሪያ አቅራቢ አገሮች በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ጦርነት መፈንዳቱ ደግሞ የዓለም ማዳበሪያ ገበያን የበለጠ አናግቶታል፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከውጭ ማዳበሪያ በሚያስገቡ አገሮች ላይ ከባድ ተፅዕኖ አሳርፎ ቆይቷል፡፡

የአፍሪካ አገሮች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ሆነው እ.ኤ.አ. በ2006 የአቡጃ ዲክላሬሽን የተባለ አዋጅ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡ አገሮቹ ማዳበሪያን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ሸቀጥ ነው የሚል ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ ምርትና አቅርቦቱን ለማሳደግ ቃል ተገባብተው ነበር፡፡ አፍሪካ የማዳበሪያ ማምረቻ ጥሬ ዕቃ ያላት በመሆኗ ምርቱን በማሳደግ ከሌሎች ጥገኝነት መላቀቅ አለባት የሚል ዕቅድ በወቅቱ የያዙ ሲሆን፣ ድንበር ሳይገድበው የማዳበሪያ ንግድ እንቅስቃሴ በስፋት እንዲደረግም ወስነው ነበር፡፡ በአቡጃ ዲክላሬሽን መሠረት እ.ኤ.አ. እስከ 2015 ባሉት ዓመታት በአኅጉሩ የማዳበሪያ አጠቃቀምን ከ22 ኪሎ ግራም በሔክታር ወደ 50 ኪሎ ግራም ለማሳደግ ግብ ተይዞ ነበር፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ በአንድ በሔክታር የምትጠቀመውን የማዳበሪያ መጠን ወደ 88 ኪሎ ግራም ማድረስ መቻሏንና የአቡጃ ዲክላሬሽን ግብን ከማንም አገር በተሻለ ማሳካቷን ተናግረው ነበር፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም የኢትዮጵያ የማዳበሪያ የግብይት ሰንሰለት እንደ ብዙ የአፍሪካ አገሮች በብዙ ችግሮች የተተበተበ ስለመሆኑ በሰፊው ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል የተፈጥሮ ጋዝና የፖታሽ ማዕድን ክምችት በሰፊው ቢኖራትም እስካሁን ራሷን አልቻለችም፡፡ አገሪቱ በሌላ የውጭ ምንዛሪ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር በዓመት ማዳበሪያ ከውጭ ለመግዛት ታውላለች፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ጀምሮ “Freedom from Hunger” በተባለ ፕሮጀክት አማካይነት ማዳበሪያን የለመደው የኢትዮጵያ መሬት፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ ፍጆታውን እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በ1970ዎቹ ወደ 3,500 ቶን ማዳበሪያ ነበር የሚገባው፡፡ በ1980ዎቹ መጠኑ ወደ 34 ሺሕ ቶን ሲያድግ፣ ይህ መጠን በ1990ዎቹ 140 ሺሕ ቶን መድረሱ፣ ከዚያም እ.ኤ.አ. በ2012 የአገሪቱ ዓመታዊ የማዳበሪያ ፍጆታ 650 ሺሕ ቶን መድረሱ ይነገራል፡፡ በዚሁ ጊዜም አገሪቱ ለማዳበሪያ ግዥ የምታወጣው ወደ 350 ሚሊዮን ዶላር አድጋ ነበር፡፡

የማዳበሪያ አቅርቦትና ሥርጭት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ሲመራ ቆይቷል፡፡ በሒደት ግን ከመንግሥት ጎን ለጎን በሥርጭቱ የሚሳተፉ የግል ተቋማትን ማሳተፍ አስፈላጊ ነው በሚል ‹‹የኢትዮጵያ አማልጋሜትድ ሊሚትድ›› የተባለ አንድ የግል ድርጅት ወደ ዘርፉ ንግድ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በሒደት የፖለቲካ ድርጅቶች ንግዱን በሞኖፖል ወደ መያዝ እንደገቡ ይነገራል፡፡ የኢሕአዴግ ድርጅቶች የፈጠሯቸው ድርጅቶች የግል ድርጅቶች በሚል ስም ንግዱን መያዝ ጀመሩ፡፡ የብአዴን ንብረት የሆነው አምባሳል ንግድ ሥራዎች ወደ ማዳበሪያ ገበያ ቀድሞ ገባ፡፡ የኦሕዴዱ ዲንሾ፣ የደኢሕዴን ወንዶ፣ እንዲሁም የሕወሓቱ ጉና ንግድ ሥራዎች የማዳበሪያ ንግድን በግል ድርጅት ስም ተቆጣጥረውት እንደነበር ብዙ የባለበት ነው፡፡

መንግሥት የግብርና ግብዓት አቅራቢ ኮርፖሬሽን ብሎ ዘርፉን በበላይነት እንዲመራ የመሠረተው ተቋም፣ በሒደት የግብርና ግብዓት አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ የሚል ስያሜ አግኝቶ ነበር፡፡

ተቋሙ በየጊዜው ማንነቱ፣ ኃላፊነቱና ተጠሪነቱ ሲለዋወጥ መቆየቱ ይነገራል፡፡ ያም ቢሆን ግን የማዳበሪያ አቅርቦትና ሥርጭት ጉዳይ ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ ችግር ሆኖ መዝለቁ በብዙ አጥኚዎች ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ “Fertilizer Supply Chain in Ethiopia Structure Performance and Policy Analysis” በተባለ ጥናት 40 በመቶ የኢትዮጵያ ገበሬ ብቻ ማዳበሪያ እንደሚጠቀም የተቀመጠ ሲሆን፣ የሚጠቀመውም በመጠን ውስን እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ “Assessment of Fertilizer Distribution Systems of Opportunities for Developing Fertilizer Blends in Ethiopia” በተባለ ጥናት ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው የማዳበሪያ አጠቃቀም ውስን ብቻ ሳይሆን፣ በማዳበሪያ ዓይነትም ሆነ በሚመረተው ሰብልም አስፈላጊ የሚባሉ የምግብ ይዘት ንጥረ ነገሮች እንደማያሟላ ያብራራል፡፡ በሌላኛው “Fertilizer in Ethiopia an Assessment of Policies Value chain and Profitability”  ጥናት ላይ ደግሞ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር የአገሪቱን ፖሊሲ የፈተነ መሆኑ ተወስቷል፡፡

ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ግብ የያዘው ግብርና መር የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ (ADLI) በመሠረታዊነት የማዳበሪያ አቅርቦትና ሥርጭትን በወጉ መምራት ባለመቻሉ ሲደናቀፍ መቆየቱ ይነገራል፡፡

ጥናቶች ይህን ቢሉም በኢሕአዴግ ሥልጣን ዘመን ሲነገር እንደቆየው ሁሉ፣ አሁንም ድረስ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በግብዓት አቅርቦት መፈተኑ ብቻ ሳይሆን ተከታታይ ዕድገቱና ስኬቱ ነው ተደጋግሞ የሚነገረው፡፡ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ (ዶ/ር) በቅርቡ ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት ሪፖርት የዘርፉን ስኬት በሰፊው አውስተዋል፡፡ ‹‹ባለፉት አራት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ከ4.3 በመቶ ተነስቶ አምና 6.3 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት 6.2 በመቶ አድጓል፡፡ በአጠቃላይ በአሥር ዓመቱ የኢኮኖሚ ዕቅዳችን በስድስት በመቶ እያደገ እንዲሄድ ግብ አስቀምጠናል፡፡ ይህን ግብ እያሳካን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ለግብርናው ምርታማነት ዕድገት ዕገዛ ያላቸው የቴክኖሎጂና የግብዓት አቅርቦት በተሻለ አፈጻጸም መከናወኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለሦስት ዓመታት የሚሆን የዘር አቅርቦት ፍኖተ ካርታ ሠርተናል፡፡ ባለፈው መካከለኛ ዘመን በዓመት አንድ ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርጥ ዘር ስናቀርብ ነበር፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአማካይ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ለማቅረብ አቅደናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የማዳበሪያ አቅርቦትን በሚመለከት ዝርዝር ጉዳዮችን ያስረዱት ግርማ (ዶ/ር)፣ አምና ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የነበረው ችግር እንደማያጋጥም ተናግረዋል፡፡

‹‹ዘንድሮ 2.3 ሚሊዮን ቶን ወይም 23 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እናቀርባለን ብለን ነው ያቀድነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በዘጠኝ ወራት 20 ሚሊዮን ኩንታሉን ልናቀርብ አቅደን ነበር፡፡ ለማዳበሪያ ግዥ የተመደበልን ደግሞ 930 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ አምና ግን 1.59 ቢሊዮን ዶላር ለማዳበሪያ ግዥ አውለን ነበር፡፡ ዘንድሮ የ100 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ያለው በጀት ቢመደብልንም፣ ነገር ግን ግዢውን የተሻለ ለማድረግ አገራዊ አቅም ፈጥረናል፡፡ ወቅትን ጠብቀን በመግዛታችን የተነሳ በ930 ሚሊዮን ዶላር 19.4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ገዝተናል፡፡ ይህ በማዳበሪያ ግዥ ታሪክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ አምና ለትግራይ ክልል ተብሎ ከተገዛው በፊት 12.8 ሚሊዮን ኩንታል ተገዝቶ ነበር፡፡ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ 800 ሺሕ ኩንታል ተጨማሪ ተገዝቷል፡፡ በአጠቃላይ 13.6 ሚሊዮን ኩንታል ነው የተገዛው፡፡ ዘንድሮ ግን 19.4 ሚሊዮን ተገዝቷል፤›› በማለት ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሪፖርቱን በፓርላማው እስካቀረቡ ዕለት ብቻ 11.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ከጂቡቲ ወደብ ወደ አገር ውስጥ መጓጓዙንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ አምና የተገዛውን የሚያህል የማዳበሪያ መጠን ዘንድሮ እስከ ግንቦት መጀመሪያ ከጂቡቲ ተጓጉዞ አገር ውስጥ መግባቱንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ግባችን ማዳበሪያ ገዝቶ ማስገባት ብቻ አይደለም ለገበሬው ማድረስ እንጂ፤›› ሲሉ የተናገሩት ግርማ (ዶ/ር) እስካሁን ባለው ሒደት፣ ‹‹እጃችን ላይ ካለው 11 ሚሊዮን ኩንታሉ 50 ከመቶ ወደ አርሶ አደሩ ተሠራጭቷል፤›› በማለት ነው የገለጹት፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ይህን ቢልም ነገር ግን የፓርላማው የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች አቅርበዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ደግሞ፣ ‹‹በዘጠኝ ወራት 900 ሺሕ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ 342 ሺሕ ኩንታል ወይም 38 በመቶ ነው የቀረበው፡፡ ወደ 750 ሺሕ ኩንታል እንደሚሠራጭ ታቅዶ 256 ሺሕ ኩንታል (34.1 በመቶ) ብቻ ነው ተሠራጨ የተባለው፡፡ ስለሆነም ምርጥ ዘር በወቅቱና በጊዜ ለምን ማሠራጨት አልተቻለም?›› የሚል ጥያቄ ይገኝበታል፡፡

ማዳበሪያን በሚመለከት ደግሞ አምና በአቅርቦት ሰንሰለቱ አጋጥሞ የነበረውን ጉድለት በማንሳት ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ጠንካራ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡ አምና በተመሳሳይ ጊዜ ሚኒስቴሩ ሪፖርት ሲያቀርብ እስከ ሰኔና ሐምሌ አጋማሽ ማዳበሪያ ለማዳረስ ቃል ቢገባም፣ ባለው መሠረት ባለመከናወኑ ተቃውሞን ጨምሮ ብዙ ችግር በአገሪቱ ስለመፈጠሩ ተነስቷል፡፡ ዘንድሮም ይህ እንዳይከሰት ምን ዋስትና አለ የሚል ጥያቄ ከቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተጠይቋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ደኤታዋ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ለዚህ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ማዳበሪያ ዘርፍን የምንመራው ሳናውቀው አይደለም፡፡ የእኔ ዘርፍ ሥራ ከ90 በመቶ በላይ ማዳበሪያን መከታተል ነው፡፡ በግምታዊ መረጃ ሳይሆን በየቀኑ እየተከታተልን ነው መረጃ የምናቀርበው፡፡ የዘንድሮ ማዳበሪያ ሥርጭት በሁለትና በሦስት ሳምንታት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፤›› ሲሉ ጠንከር ያለ ምላሽ በመስጠት ከአምናው ሁኔታ ጋር ሊነፃፀር አይገባም ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ደኤታዋ ሲቀጥሉም አምና ለደቡብና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ በጋራ 780 ሺሕ ኩንታል ነበር የቀረበው ብለዋል፡፡ ዘንድሮ ግን ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብቻ 800 ሺሕ ኩንታል መቅረቡንና እስካሁን 50 በመቶ መሠራጨቱን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልልን በተመለከተ 4.9 ሚሊዮን ኩንታል መቅረቡን የገለጹ ሲሆን፣ ሪፖርቱን እስካቀረቡበት ጊዜ ድረስ 47 በመቶ መሠራጨቱን አስረድተዋል፡፡ ከሦስት ሳምንት በፊት በክልሉ የነበረው ሥርጭት 25 በመቶ እንደነበር በማስታወስ፣ በጥቂት ቀናት ሥርጭቱን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

አምና በማዳበሪያ አቅርቦት ችግር መዘዝ ተቃውሞ የተነሳበትን የአማራ ክልልን በሚመለከት ዘንድሮ 4.4 ሚሊዮን ኩንታል እንደቀረበለት አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 56 በመቶውን ማሠራጨት እንደተቻለ የተናገሩ ሲሆን፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎን ጨምሮ ሰሜን ሸዋ ዞኖች ቀድሞ እንደቀረበላቸው ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስትር ደኤታዋ ሶፊያ (ዶ/ር) በፀጥታ ችግር ሳቢያ ወደ ወረዳና ወደ አርሶ አደሩ ጋር ለማድረስ በክልሉ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ ዞን ለመጋዘኖች ከፍተኛ መጠን ያለው ማዳበሪያ መድረሱን፣ ይህም በተቻለ ፍጥነት ለሕዝቡ እንደሚሠራጭ አስረድተዋል፡፡ የአምናው ዓይነት ቀውስ እንደማይፈጠርም ተናግረዋል፡፡

በውጭ የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ጥገኛ የሆነችውና በየዓመቱ ለግዥ አንድ ቢሊዮን ዶላር የምትገፈግፈው ኢትዮጵያ የዘርፉን አቅርቦትና ሥርጭት ውጤታማ በሆነ መንገድ በመምራት በኩልም ከፍተኛ ችግሮች ሲገጥማት ይታያል፡፡ ዘንድሮ የግብርና ሚኒስቴር ቃል በገባው መሠረት የአቅርቦትና ሥርጭቱ ሁኔታ ይሻሻል ይሆን የሚለው በጥቂት ሳምንታት እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -