Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት በዘጠኝ ወራት ከታክስ በፊት አራት ቢሊዮን ብር በማትረፍ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ ማሳደግ መቻሉ ተመለከተ፡፡

ባንኩ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ በሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ ያስመዘገበው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ1.65 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በ2015 የሒሳብ ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው የትርፍ መጠን 2.35 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ባንኩ በዘጠኝ ወራት ያስመገበው የትርፍ መጠን በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የዕድገት ምጣኔ ያሳየበት ነውም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገብቶበት ከነበረው ችግር ተላቆ ባለፉት አራት ዓመታት በአዲስ ስትራቴጂ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወዲህ በየዓመቱ የትርፍ ምጣኔውም ሆነ አጠቃላይ አፈጻጸሙን እያሳደገ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ሰሞኑን እንዳምለከቱትም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ቀርፆ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወዲህ ከፍተኛ ለውጥ በማሳየት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ሪፎርሙ በተጀመረበት ዓመት ባንኩ ኪሳራ ያለፈ ቢሆንም ይህንን ታሪክ ቀይሮ በየዓመቱ የትርፍ ምጣኔውን በማሳደግ ላይ ሲሆን በ2015 የሒሳብ ዓመትም ከታክስ በፊት ከ6.4 ቢሊዮን ብር በላይ በማትረፍ ከአገሪቱ ባንኮች በትርፍ ምጣኔ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

ባንኩ ካስመገበው የትርፍ ምጣኔ ዕድገት ባሻገር በጠዘኝ ወራት ውስጥ በተለያዩ አፈጻጸሞቹ ስኬታማ ሆኛለሁ ብሏል፡፡ በተለይ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 44.6 ቢሊዮን ብር ብድር ማፅደቁንና ይህም ከዕቅዱ አንጻር ሲታይ የ120 በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን ገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ 25.1 ቢሊዮን የሚሆነውን ብድር መልቀቁንም ገልጿል፡፡ ይህም ከአጠቃላይ የባንኩን የብድር ክምችት ወደ 87.4 ቢሊዮን ብር ማድረስ አስችሎታል፡፡ ብድር ከማስመለስ አኳያም በዘጠኝ ወር ከ11.7 ቢሊዮን ብር በላይ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡

በሌላ በኩል ከአምስት ዓመት በፊት ከ40 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረው የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠንን ከማስተካከል አንፃር ከፍተኛ ሥራዎች ተሠርቶ በ2015 መጨረሻ ላይ ሰባት በመቶ ማድረስ መቻሉ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ ይህ ተበላሸ የብድር መጠን በ2016 የበጀት ወር መጨረሻ ላይ ደግሞ 7.8 በመቶ ሊሆን መቻሉ ታውቋል፡፡

ከዚህ መረጃ መገንዘብ እንደተቻለው የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን በ2016 የሒሳብ ዓመት መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ነው፡፡ ባንኩ የ2016 የሒሳብ ዓመት የስድስት ወር ሪፖርቱን ባሳወቀበት ወቅት የተበላሸ የብድር መጠኑ 7.3 በመቶ እንደነበር ማመላከቱ የሚዘነጋ ባለመሆኑ በሦስት ወራት የባንኩ 0.5 በመቶ የተበላሸ ብድር ጭማሪ እንዳሳየ አመላክቷል፡፡ ባንኩ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ የመጣውን የተበላሸ የብድር መጠን በ2016 የሒሳብ ዓመት መጠነኛ ቢሆንም ከፍ እያለ መምጣቱን እስከ ካለው ብድር ዕድገት ጋር የተያያዘ ሲሆን መጠነኛ የተባለው የተበላሸ የብድር መጠን ዕድገት ግን ባንኩ ብሔራዊ ባንክ ለልሣት ባንኮች ካስቀመጠው የ15 በመቶ የተበላሸ ብድር ገደብ አንፃር አሁንም በጤናማነት የሚገለጽ ነው ተብሏል፡፡

ባንኩ እያሳየ ያለውን ለውጥ አስመልክቶ የዘጠኝ ወር አፈጻጸሙ በተገመገመበት ወቅት የተገኙት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳዳር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል በበርካታ የፋይናንስ መለኪያዎች ባንኩ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን መገንዘብ መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ያስቀመጠውን ዕቅድ ከማሳካት አኳያ የውጤታማ ተቋማት ማሳያ ሆኖ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል በማለት ጭምር ገልጸውታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች