Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየሀብት ምዝገባ አዋጁና የፀረ ሙስና ትግሉ ነገር

የሀብት ምዝገባ አዋጁና የፀረ ሙስና ትግሉ ነገር

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በታተመው ሪፖርተር ‹‹ልናገር›› ዓምድ ላይ ‹‹ሙስና እያስፋፋ ያለው የጥገኝነት መንፈስ›› የሚል ጽሑፍ አንብቤ ነበር፡፡ ጽሑፉ ለመጠቃቀስ እንደሞከረው የሙስና ወንጀል በአገራችን በትናንሽ (Petty) ይባል ትልቅ (Grand) ደረጃ ሲፈጸም መታየቱ፣ የተጀመረውን የለውጥ መንገድ ከሚያውኩ መሰናክሎች አንዱ ስለመሆኑ፣ ይህ የመልካም አስተዳደርና የፍትሐዊነት ፀር በወቅቱ ካልታረመም በአገር ደረጃ ቀውስ እንደሚያባብስ የአንዳንድ ሰዎችን አስተያየት አካቶ አቅርቧል፡፡

ጽሑፉ ዕይታው ጥሩ ቢሆንም ግን በግሌ አንድ ጉዳይ አጭሮብኛል፡፡ ይኸውም በወቅቱ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ መፈተሽ አለበት የሚል ሐሳብ ነበር፡፡ በተለይ በየደረጃው ካሉ የመንግሥት ተሿሚዎችና ሠራተኞች የሀብት ምዝገባና የተጠያቂነት ሥርዓት አንፃር በተለያዩ ወቅታዊ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ያለች አገር ብትሆንም፣ መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ማመላከት አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል፡፡ 

- Advertisement -

ካለ በቂ መረጃና ምርመራ የግለሰቦችንና የአንዳንድ ተቋማትን ስምና የገቢ ሁኔታ እያነሱ ለኅትመት ማብቃት ባይቻልም፣ መንግሥትና ሕዝብ የሰጧቸውን አደራና ኃላፊነት ተጠቅመው ሀብት ያጋበሱና የተለየ ኑሮ እየኖሩ ያሉ አካላትን እየተመለከትን በመሆኑም ጉዳዩን ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር በሕወሓት/ኢሕአዴግ አስተዳደር ወቅት በሙስና የታሙና የተጠረጠሩ ግለሰቦች ጉዳይ፣ የሀብት ማስመለስም ሥራ ሆነ ነፃ ስለመሆናቸው የተነገረ አለመኖሩንም አጀንዳውን ለማንሳት ያነሳሳል (በእርግጥ ባለፉት ዓመታት በዕርዳታ ሰጪነት በተቋቋመ ኮሚሽንና የእምነት ተቋማት ውስጥ በሚሠሩ ግለሰቦች ላይ እየተደረገ ያለ ቀላል የማይባል የሙስና ወንጀል ተገኝቶ እየተመረመረ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ 

እናም በድጋሚ ጉዳዩን በማንሳት ሀብትን ለማሳወቅና ለማስመዝገብ ከ14 ዓመታት በፊት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 668/2002 እያጣቀስኩ አንዳንድ ነጥቦችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ሌሎችም በችግሩ ላይ የሚያወያይ ሐሳበችሁን ብታካፍሉ እንደ አገር ጠቃሚ መሆኑን በማስታወስ፡፡

በአገራችን ፓርላማ ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለው ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ አዋጅ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና ከፍተኛ ባለሙያዎችን ሀብት ለማስመዝገብ ያስቻለ ሲሆን፣ በቃራኒው አዋጁ በሚያስገድደው መሠረት ሀብታቸውን ለማሳወቅና ለማስመዝገብ ዳተኝነት የታየባቸውና ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ስለማጋጠማቸው፣ በቅርቡ ራሱ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገር ተደምጧል፡፡ ያስመዝገቡትስ ቢሆኑ ምን ያህል ትክክለኛ መረጃ ሰጥተዋል? በየጊዜው የሚረጋገጥበትስ መንገድ አለ ወይ? የሚለው ግን በወጉ መፈተሽ ያለበት ነው፡፡

በመሠረቱ አዋጁ ትልቅ ራዕይ አንግቦ የወጣና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነበር፡፡ ሀብትን ማሳወቅና ማስመዝገብ የመንግሥት አሠራርን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ ለመመሥረት አስፈላጊ መሆኑን፣ በተለይ ደግሞ ሀብትን ማሳወቅና ማስመዝገብ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ሙሉ እምነትና ዓላማ ይዞ የተነሳ መሆኑ ላይም ጥርጥር የለውም፡፡

አዋጁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነትና የግል ጥቅም ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ሥርዓት በመዘርጋት፣ ሊፈጠር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለማስወገድ እንደሚረዳ ታምኖበት መፍትሔ ሆኖ የቀረበ  እንደነበርም በወቅቱ መገለጹ አይዝነጋም፡፡ ነገር ግን በርከት ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተሿሚዎች ከቦታቸው ሲነሱ በደመወዝና በጥቅማ ጥቅም ሊሰላ የማይችል ከፍተኛ ሀብት፣ ቢዝነስ ወይም ኩባንያ ባለቤት ሆነው ሲታዩ ዕውን እጃቸው ላይ የሕዝብ ሀብት አልተቀላቀለምን ያስብላል፡፡ በአዋጁ አፈጻጸም ላይ የተዓማኒነት ጥያቄም ያስነሳል፡፡

ለዚህም ነው አዋጁ ባለፉት 14 ዓመታት ቆይታው ያስገኘልን ውጤት ምንድነው? አዋጁ ይዞት እንደተነሳው ዓላማ ለምሳሌ የመንግሥት አሠራርን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ መሥርቶልናል? ሙስናና ብልሹ አሠራርን ተከላክሎልናል? መልካም አስተዳደርን አስፍኖልናል? የሚሉ ጥያቄዎች ቢቀርቡልን  ምላሹ አመርቂ አይሆንም፡፡ በቀደመው ጽሑፍ እንደተወሳም በተለይ ያለፉት ስድስት ዓመታት አገራዊ ሁኔታው በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ የከረመ ቢሆንም አዋጁን በጥብቀት ለማስፈጸም፣ ‹‹በሒደት ላይ ነን›› የሚል መልስ ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህን ሁሉ ዓመት ‹‹በሒደት ላይ ነን›› እያሉ ከተጠያቂነት ማምለጥም አይቻልም፡፡

እውነት ለመናገር የአዋጁ ዕድሜ በቆየ ቁጥር እንደ ወይን ጠጅ እየበሰለ መገኘት ሲገባው፣ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሩ ጭራሽ እየባሰበት ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመመከትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ብሔራዊ ንቅናቄ እስከ ማቀጣጠል መደረስ እንዳለበት አመላካቾቹ በርካታ ናቸው፡፡ አሁን አሁን አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በርከት ያለው ፈጻሚና የፀጥታ አካል በእጅ መነሻና መደራደሪያ አገልግሎት መስጠትን ተለማምዷል፡፡ ባለጉዳዩም በእጁ ካልሄደ እንደማይሆንለትና አስቸጋሪዎቹን የአሠራር መመርያዎችና ውጣ ውረዶች እንደማያልፍ እያሰላ አቀባይ እየሆነ ነው፡፡

የአዋጁ መኖርና አለመኖር ለመንግሥትም ሆነ ለሕዝብ ያመጣው ለውጥ የት አለ የሚያስብለው       ቁምነገር በመሬትና መሬት ነክ መስክ የተሰማሩ አንዳንድ ባለሙያዎች ይባሉ አመራሮች፣ ባለበርካታ መሬትና አለፍ ሲልም የመሬት ነጋዴ ሆነው ሲታዩ ሕዝቡ በመታዝቡ ነው፡፡ እንደ መንገድ ትራንስፖርት፣ ገቢዎች፣ በየደረጃው ያሉ የንግድና ኢንቨስትመንት ሰዎች፣ ወዘተ ከገቢያቸው በላይ ቤት፣ ተሽከርካሪ፣ የልጆች ትምህርት ቤትም ሆነ የኑሮ ሁኔታ ላይ መታየታቸው የመንግሥት የቁጥጥር ሥዓርት ልልነት ማሳያ ነው የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም፡፡

አዋጁ ሀብታቸውን ማስመዝገብ ያለባቸውን ሰዎች በሦስት ምድብ ከፍሎ ‹‹ተሿሚ፣ ተመራጭ፣ የመንግሥት ሠራተኞች›› ሲል ለይቷቸዋል፡፡ ‹‹ተሿሚ›› በሚለው ምድብ ውስጥ የሚጠቃለሉት ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከምክትላቸው ጀምሮ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ደኤታዎች፣ ኮሚሽነሮችና ምክትሎቻቸው፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ምክትሎች፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች፣ ከንቲባዎችና ሌሎች ተሿሚዎች የመደበኛና የከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና ዳኞች፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ተሿሚዎች፣ ዋና ኦዲተርና ምክትል ዋና ኦዲተር፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥዎች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ሥራ አስኪያጆች፣ ወዘተ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ ሀብታቸውን የማስመዝገብ ግዴታ አለባቸው፡፡

ሙስናው እንደ አገር እየታየ ያለው ግን መካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባሉ ተሿሚዎችና አንዳንድ ባለሙያዎች ጭምር መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይ የምርመራ ጉዳይ በሚከታተሉ አንዳንድ የግል ጥቅም የሚያስቀድሙ የባሰባቸው አካላት፣ የመንግሥት ሀብት (ግዥና ሽያጭ ወይም ድርድርና ክርክር ላይ) የሚወስኑ ለአደጋው ሲቀርቡ ይስተዋላል፡፡ የጥቅም ተጋሪ ሆነው ብቻ ሳይሆን፣ በቅንነትና በማጭበርበር ውሳኔ የሚያሳልፉላቸውን የሥራ ኃላፊዎች  ውሳኔ ጭምር ተጠቅመው፣ ሕዝብ የሚያማርሩና የሚጎዱ ጥቂቶች ለብዝኃኑ ሲባል አደብ እንዲኖራቸው መደረግ አለባቸው፡፡

በአዋጁ መሠረት ‹‹ተመራጭ›› በሚለው መደብ ውስጥ የሚጠቃለሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር ምክር ቤቶች አባላትም ናቸው፡፡ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛ›› በሚለው መደብ ውስጥ የተካተቱት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የመምርያ ኃላፊነት፣ የዳይሬክተርነት፣ የአገልግሎት ኃላፊነትና ከእዚህ ተመጣጣኝና በላይ ደረጃ ያላቸው ሠራተኞች፣ የተሿሚዎች አማካሪዎች፣ ወዘተ ፈቃድ የመስጠት፣ የመቆጣጠር ወይም ግብር የመሰብሰብ ሥራ የሚያከናውኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞችና ዓቃቤ ሕጎች፣ መርማሪዎች፣ የትራፊክ ፖሊሶች ናቸው፡፡

የሙስናና የመልካም አስተዳደር እንቅፋት ተባይ መፈልፈያ የሆኑ ምሽጎች በሙሉ በነዚህ ሦስት መደቦች ውስጥ ተለይተው ታውቀዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍጠርም ሆነ ሙስናን የሚፀየፍ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት ምንጮች እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህን ቡድኖች መከታተል (ሥራቸውንም ሆነ ኑሯቸውን በግልጽነትና በተጠያቂነት እንዲመራ ማድረግ) ከተቻለ፣ የአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የልማት ጉዞ ከመደናቀፍ እንዲድን ማድረግ ይቻላል፡፡

አዋጁ ይህን የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ሥራ በኃላፊነት እንዲሠራም ሆነ አጠቃላይ የሥነ ምግባር ብልሽትን እንዲታገል፣ ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽና ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ ዋናውና ወሳኙ ዕርምጃ ግን በመንግሥት (በተለይም በአስፈጻሚው አካል) የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡ ስለሆነም እንደ አገር የተረጋጋ አገረ መንግሥትና አስተማማኝ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ለመጀመር፣ መንግሥት አዋጁንም ሆነ አጠቃላይ የፀረ ሙስና ትግሉን ማቀጣጠል ግድ የሚለው ይሆናል፡፡

ሀብት የማሳወቅና የማስመዝገብ አዋጁ ያነገባቸው መርሆዎችን ሕዝብ በሚገባ ተረድቷቸው እንዲታገል የማድረጉ ጉዳይም የቅድሚያ ቅድሚያ ማግኘት አለበት፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም ተሿሚ፣ ተመራጭ፣ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የያዘውን መንግሥታዊ የኃላፊነት ቦታ የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ማዋል እንዳለበት፣ በማንኛውም ምክንያት ቢሆን በሥራው አጋጣሚ ያገኘውንና ሕዝብ እንዲያውቀው ያልተደረገን መረጃ ለግል ጥቅሙ ማዋል እንደሌለበት፣ እንዲሁም ተሿሚው የመወሰን ሥልጣኑን የሚፈታተን ወይም የጥቅም ግጭት የሚፈጥር ስጦታ፣ መስተንግዶ ወይም የጉዞ ግብዣ መቀበል እንደሌለበት ተደንግጓል፡፡ ዕውን ይህንን የተከላከለ አካል አለ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

በአዋጁ መሠረት ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች (ተሿሚዎች…) የሀብት ምዝገባ መረጃዎች በኮሚሽኑ አማካይነት ለሕዝብ ክፍት የሚደረጉ መሆናቸው ተደንግጓል፡፡ ስለሀብት ምዝገባ መረጃ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ጥያቄውን በጽሑፍ ለኮሚሽኑ ወይም ጉዳዩ ለሚመለከተው የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል ሊያቀርብ እንደሚችል፣ መከታተያ ክፍሉም የቀረበለትን ጥያቄ በመቀበል የምዝገባውን መረጃ ለጠየቀው ሰው መስጠት እንዳለበትም በወረቀት ላይ ተረጋግጧል፡፡ በተግባር ምን ያህሉ ዕውን እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

በእርግጥ የተሟላ ባይሆንም ኮሚሽኑ በአዋጁ መሠረት በየሁለት ዓመቱ ስላከናወነው የሀብት ምዝገባ አጠቃላይ መረጃ በሪፖርት መልክ ሲያቀርብ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ዓይነት ኮሚሽኑ ባለፉት አሥራ አራት ዓመታት ቢቀር፣ ከለውጡ ወዲህ ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ሁለቴ ወይም ሦስቴ የሀብት ምዝገባ መረጃውን በሪፖርት መልክ ማውጣቱን ማመን እንኳ ባይሆን መገመት እንችላለን፡፡ ይህ በመደረጉ የተገኘው ውጤት ግን ምንድነው? ችግሩስ ተባባሰ ወይስ ቀነሰ? ብሎ መጠየቅ በተለይ ሕዝብ ውክልና ከተሸከመው ሕግ አውጭው አካል የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገቢያ አዋጁ ይህን ያህል ግልጽ መሆኑ ላይ እምነት ካሳደርን ተግባራዊነቱን መጠየቅ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ በአዋጁ መሠረት በሦስት ምድብ ተከፍለው ‹‹ተሿሚ፣ ተመራጭና የመንግሥት ሠራተኛ›› ተብለው ከተፈረጁት ሰዎች መካከል ስንቶቹ ሀብታቸውን አሳውቀው አስመዝግበዋል? ያስመዘገቡትስ ምን ያህል ትክክለኛ ነው? የስንቶቹ ተረጋግጦ የስንቶቹ ቀርቷል? ለምን? ኮሚሽኑ ያሰባሰበውን የምዝገባ ሰነድ በየሁለት ዓመቱ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል ወይ? በምን መንገድ (ዘዴ) ሕዝቡ እንዲያውቀው አድርጓል? በኮሚሽኑ ድረ ገጽ ላይ የተለጠፈ የምዝገባ መረጃ አለ? በመንግሥታዊና በግል ጋዜጦች፣ በኤፍኤም ሬዲዮዎች፣ በኢቢሲ፣ ወዘተ ሚዲያዎች በኩል ለሕዝቡ እንዲደርስ የተደረገ ነገር አለ? ነው ወይስ ‹‹ለሚዲያ ፍጆታ አይሆንም›› ተብሎ ቀረ፡፡ በሚስጥር መያዝ ያለበት ነገር በአዋጁ መሠረት ተቀምጧል፡፡ ሚስጥር ያልሆነውን ጉዳይ መሸሸግ ግን አልተፈቀደምና ምን እየተደረገ ነው ብሎ መጠየቅ በዋናነት የፓርላማው ድርሻ ነው፡፡

እውነት ለመናገር ኮሚሽኑ የሚያቀርበው የትኛውም ሪፖርት ግልጽ እንዲሆን ሕዝብ ይጠብቃል፡፡ በመቶኛ ሥሌት ተሠርቶ ለግብር ከፋዩ ዜጋ ትርጉም በማይሰጥ መንገድ የሚቀርብ ሪፖርት ጠቃሚነትም ሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለምሳሌ ሪፖርቱ ‹‹ሀብታቸውን ማሳወቅና ማስመዝገብ ከነበረባቸው ሰዎች ከግማሽ በላይ ወይም 60 በመቶ ያህሉ አስመዝግበዋል… ከተመዘገቡት መካከል 80 በመቶ ትክክለኛ መሆናቸው ተረጋግጧል….›› ወዘተ የሚል ዓይነት መሆንም የለበትም፡፡ ግልጹን እየተናገሩ ከመሸበት ማደሩ ነው ከመጠላለፍና ቀውስ የሚያወጣው የሚል እምነት የበርካታ አገር ወዳዶች ይመስለኛል፡፡

በመሠረቱ አሠራሩ በትክክል ከተተገበረ ሕዝቡ በአዋጁ የተሰጠውን መብት የመጠቀም ዕድል እንዲያገኝ የሚያደርግ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ‹‹ይህን አዋጅ ጥሷል›› በሚለው ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ላይ ጥቆማ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ጥቆማው ደግሞ ከደጋፊ ማስረጃ ጋር በጽሑፍ ለኮሚሽኑ ወይም አግባብ ላለው የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል የሚቀርብ በመሆኑ፣ ሕዝቡ ጥቆማ መስጠት የሚችለው ሰዎቹ ያስመዘገቡትን ለይቶ ሲያውቅ ነው፡፡ ያላስመዘገቡትን ወይም አሳስተው ያስመዘገቡትን ለይቶ ከኮሚሽኑ ጋር ለመተባበር ባለው መብትና ዕድል ሊጠቀም ያስችለዋል፡፡

በአጠቃላይ አሁን ያለንበት ጊዜ የሒደት ሳይሆን፣ በፍጥነት ከወቅታዊ ፈተናዎች የመውጣትና በመደማማጥ አገራዊ ውጤት ለማስመዝገብ መሆን አለበት፡፡ እያንዳንዱ አዋጅ ለታለመለት ዓላማ መዋሉ የሚረጋገጠው በተጓዘበት ሒደት ሳይሆን፣ ባስገኘው ውጤት ነው መባሉም ይህን መነሻ በማድረግ  ነው፡፡

ምንም እንኳን አገራችን ቅድሚያ የምትሰጣቸው በርካታ ጉዳዮችና የፖለቲካ ዕርምጃዎች የሚጠብቋት ቢሆንም፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሐዊነትን የማረጋገጥ ጉዳይ በየትኛውም ሁኔታ መረሳት የሌለበት ነው፡፡ እናም ‹‹የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጁን ለማሳካት ይህንና ይህን እየሠራን ነው ያለነው… በሒደት ላይ ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው… አጠናክረን የምንቀጥልበት ሁኔታ ነው ያለው…››  ወዘተ ማለት ትርጉምም ሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ጥያቄው በአዋጁና በደንቡ የተሰጣችሁን ኃላፊነት ተወጥታችኋል? ወይስ ገና ነው? እጃችሁ ከምን? ውጤታችሁ የት አለ? በዚህን ያህል ዓመት በሒደት ላይ ከሆናችሁ ውጤቱ የሚገኘው መቼ ሊሆን ነው? መባባል ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...