Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊለረድኤት የተዘረጉ እጆች

ለረድኤት የተዘረጉ እጆች

ቀን:

ምሕረተአብ ሙሉጌታ ይባላል፡፡ ለተቸገሩት፣ ላጡት፣ ደጋፊና አይዞህ ባይ ለሌላቸው፣ ጎዳና ላይ ለወደቁ፣ ባለው አቅምና በቻለው ልክ ለመታደግ ይፈጥናል፡፡ እነርሱን ለመደገፍና ከወደቁበት ለማንሳት እጁን ይዘረጋል፡፡

ምሕረተአብ የተወለደውና ያደገው አዲስ አበባ ‹‹ገዳም ሠፈር›› ነው፡፡ እናትና አባቱን አያውቃቸውም፡፡ በአራት ዓመቱ በሞት እንደተለዩት ይናገራል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በርካታ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አልፏል፡፡ መኪና በማጠብ፣ ፒያሳ አካባቢ ይገኝ በነበረው አትክልት ተራ ከመኪና ላይ የተለያዩ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን በማውረድ፣ ወደ ክፍለ ሀገር በሚንቀሳቀሱ ዕቃ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ላይ ረዳት በመሆን ኑሮን ለማሸነፍ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡

‹‹ለሕይወትህ መለወጥ፣ ለኑሮህ መሻሻል ግድ የማይሰጣቸው በርካቶች እንዳሉ ሆነው ለአንተ የሚቆሙና የሚነሱ ሰዎችን እግዚአብሔር ይሰጥሃል፤›› የሚለው ምሕረተአብ፣ እሱም በሕይወት አጋጣሚ የተገናኛቸው ወዳጆች የሕይወት መስመሩን እንደለወጡት ይናገራል፡፡

- Advertisement -

በአሁኑ ወቅት በማማከር ዘርፍ ተሰማርቶ እንደሚገኝና ፋይናንስ የሚፈልጉ ፕሮጀክቶችን በውጭ አገሮች ከሚገኙ ኩባንያዎች በማገናኘት በፋይናንስ እንዲደገፉና ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በፀሐይ፣ በንፋስ ኃይልና በሃይድሮ ፓወር ላይ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመሥራት ላይ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በሪልስቴትና በሌሎች ቢዝነሶች ከተሰማሩ ግለሰቦች ጋር ሽርክና በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ያክላል፡፡

ምሕረተአብ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በመገኘት 7,500 ለሚሆኑ አረጋውያን ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ገንዘብ የምሳ ግብዣ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም ለማዕከሉ ሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበርክቷል፡፡ አልባሳትና ሌሎች ልብሶችን ለአረጋውያን አስረክቧል፡፡

‹‹የሰው ልጆች በሕይወት አጋጣሚ የተለያዩ ዕክሎች ይገጥሟቸዋል፡፡ በተለያዩ የጤና ችግሮች ውስጥም ያልፋሉ፡፡ በሆነ የቀን ጎዶሎ ውስጥ ሰዎች ወድቀው ይገኛሉ፡፡ በመቄዶንያ ያየሁትም ይህንን ነው፡፡ በማዕከሉ የሚገኙ ወገኖች በብዙ ፈተናና በብዙ ችግሮች ውስጥ ናቸው፡፡ ገሚሶቹ በአዕምሮ ሕመም ገሚሶችም በልዩ ልዩ ችግሮች ተይዘው ዛሬም የኢትዮጵያውያንን እጆች ይሻሉ፤›› ሲል ይናገራል፡፡

በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በተለያዩ ዘርፎች ለአገራቸው ውለታ የዋሉና ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ፣ ኢትዮጵያን አፅንተው ያቆሙ ስለመሆናቸው የሚገልጸው ምሕረተአብ፣ ሕይወት ፊቷን አዙራባቸው በማዕከሉ የተገኙትን መደገፍና መርዳት እግዚአብሔርን እንደማገልገል በመሆኑ ሁሉም የድርሻቸውን ሊወጣ ይገባል፡፡

እንደ ምሕረተአብ ከመቄዶንያ በተጨማሪ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶችን እየደገፈ ይገኛል፡፡ በ‹‹ካሊድ ፋውንዴሽን›› የገንዘብና የቁስ ድጋፍ ማበርከቱንም ይገልጻል፡፡ በ‹‹ሜሪጆይ ኢትዮጵያ››፣ ከሲስተር ዘቢደር ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችንም ሠርቷል፡፡

ሜሪጆይ ኢትዮጵያ ‹‹አስኮ›› አካባቢ ለሚገነባው ሆስፒታል ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ‹‹አንድ ሰው አንድ ኮሪደር›› በሚለው መርህ አንድ ኮሪደር ለመገንባት አንድ ሚሊዮን 500 ሺሕ ብር የሚያስፈልግ በመሆኑ ይህንን ሊያደርጉ የሚችሉ ባለሀብቶችን በማስተባበር በኩል ትልቅ አበርክቶ ማድረጉን ይናገራል፡፡

በዓመቱ የትምህርት ዘመን መጀመሪያ በድርጅቱ ለሚገኙና እናትና አባት ለሌላቸው ተማሪዎች በሚሊዮን ብር የሚገመት የደብተር፣ የእስክሪብቶ፣ የቦርሳና ሌሎችም የትምህርት መረጃ ቁሳቁሶችን ወዳጆቹን በማስተባበር መለገሱንም ይገልጻል፡፡

የአዲስ ዓመት የበዓል መባቻን ምክንያት በማድረግ፣ ወላጅ አልባና በጎዳና ላይ ኑሮአቸውን ያደረጉ ልጆችን በሜሪጆይ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹መዓድ በማጋራት›› ፕሮግራም በዓሉን እንዲያሳልፉ አድርጓል፡፡

ሲስተር ዘቢደር በዱባይ በነበራት ቆይታ፣ በሪልስቴት የሙያ ዘርፍ ከተሰማራውና የዱባይ ነዋሪ ከሆነው መሐመድ ራምዜል ከተባለ ግለሰብ ጋር እንድትገናኝ በማድረግ እርሱም መቶ ልጆችን ለማሳደግ ቃል እንዲገባ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዱባይ በነበራት ቆይታም ‹‹ለአንድ ጎዳና ተዳዳሪ አንድ ዳያስፖራ›› በሚል የኢትዮጵያ ቀን ፌስቲቫል ላይ ከዱባይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ፕሮግራሙን ለማሳካት ችሏል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ለድርጅቱ ገቢ ሊገኝ መቻሉንም አክሏል፡፡

‹‹እግዚአብሔር ዕድሜና ጤናውን በሰጠኝ ልክ በችግር ለወደቁ ለበርካታ እናቶችና አባቶች፣ ወጣት ወንድም እህቶች አሁን እያበረከትኩት ካለሁት በበለጠ መጠን ማድረግ እሻለሁ፡፡ መንግሥትም እንደ መቄዶንያ፣ ሜሪጆይና መሰል ድርጅቶችን ከጎናቸው ሆኖ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ድርጅቶቹ እየሸፈኑ የሚገኙት የመንግሥትን ሥራና ኃላፊነት በመሆኑ ቀርቦ ሊያግዛቸው ይገባል፤›› በማለትም ተናግሯል፡፡

የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና ዳይሬክተር ሲስተር ዘቢደር ዘውዱ እንደተናገሩት፣ ምሕረተአብ በጎ ማድረግ የሚያስደስተው፣ ችግረኞችን የሚረዳና የወደቁትን የሚያነሳ ነው፡፡ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ላይ በመገኘት ከሚረዳው ይልቅ በግሉ የሚረዳቸውና የሚደግፋቸው ብዙ ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ለማገዝ በቀን ብዙ ብር ያወጣል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት ድንቅ ነገር ያደረገ በመሆኑ የሰጠኝን መልሼ በመስጠት ያጡትን እደግፋለሁ›› የሚል መርህ ያለው ሰው ነው ብለዋል፡፡

 ምሕረተአብ ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ በገንዘብ እኛን ከሚደግፈው በላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲያግዙንና እንዲደግፉን፣ ውጭ አገሮች ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችም እንዲተባበሩን የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከዕድሜው በላይ የሚያስብ ቅን፣ ሩህሩህ፣ አዛኝ ልብ ያለውና ተቸግረናል ላሉ ሁሉ ፈጥኖ የሚደርስ ነው በማለት ይገልጻሉ፡፡

የመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ መርጃ ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ በበኩሉ፣ ምሕረተአብ ሀብታም ሆኖና ከተረፈው ሳይሆን፣ ካለው ላይ ለድርጅቱ የሰጠ ነው ብሏል፡፡ መቄዶንያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች መሰል ድርጅቶችን ለዓመታት ሲደግፍና ሲያግዝ መኖሩን ጠቅሶ፣ ይህ ድርጊትና ሥራውም እንዲነገርለትና ዝና ሆኖ እንዲወራለት እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...