Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኦሊምፒክ ማራቶን አትሌቶች ምርጫ በመሥፈርቱ መሠረት መከናወኑ ተገለጸ

የኦሊምፒክ ማራቶን አትሌቶች ምርጫ በመሥፈርቱ መሠረት መከናወኑ ተገለጸ

ቀን:

  • የረዥም ርቀት አትሌቶች ምርጫ በሰኔ መጀመሪያ ያበቃል

ዓለም በከፍተኛ ጉጉት እየጠበቀው ያለው የ2024 ኦሊምፒክ በፓሪስ ሊከናወን የቀናት ዕድሜ ቀርቶታል፡፡ አገሮች ተወዳዳሪዎቻቸውን ይፋ ማድረግ ከጀመሩም ሰነባብተዋል፡፡ በአትሌቲክሱ ኦሊምፒክን በጉጉት እንዲጠበቅ ከሚያደርጉ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የማራቶን ቡድኗን ይፋ አድርጋለች፡፡ የጽናትና የአሸናፊነት ተምሳሌቱ ቀነኒሳ በቀለ በምርጫው ተካቷል፡፡

ለወትሮው ከምርጫ ጋር ተያይዞ አቧራ ሲያስነሱ የነበሩት ክፍተቶች በዚህኛው እነማን እንዴት ተመረጡ? የሚሉ እሰጣ ገባዎች እስካሁን ባለው ሰላማዊና ሙያዊ በሆነ አግባብ እየተከናወነ እንደሚገኝም እየተነገረ ይገኛል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በተለይም  በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት፣ ኢትዮጵያ ከውጤት ባሻገር እንደ አገር ማግኘት የነበረባት፣ ነገር ግን በነበረው ሁኔታ ያጣችው ነገሮች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ለፓሪስ ኦሊምፒክ በጋራ ማቀድና መሥራት መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡

ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በፓሪስ ኦሊምፒክ በማራቶን የሚወዳደሩ አትሌቶች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል፡፡

አትሌቶቹ የተመረጡት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ ተወዳድረው ሰዓት ያስመዘገቡ፣ ነገር ግን ከውጤቱ ጎን ለጎን አትሌቶቹ የተወዳደሩባቸው ቦታዎች በዓለም አትሌቲክስ ያላቸው ደረጃ ማለትም የወርቅ፣ የብርና የነሐስ የሚለው፣ በተቋማቱ አመራሮች እምነት በተጣለባቸው ባለሙያዎች አማካይነት በአግባቡ ታይተውና ተመርምረው በሴቶች፣ ቀዳሚዎቹ ትዕግሥት አሰፋ፣ አማኔ በሪሶና መገርቱ ዓለሙ ሲሆኑ ተጠባባቂዎች ጎተይቶም ገብረሥላሴና ቡዜ ድሪባ ሆነዋል፡፡

በወንዶች ቀዳሚዎቹ ሲሳይ ለማ፣ ደሬሳ ገለታና ቀነኒሳ በቀለ ሲሆኑ፣ ተጠባባቂዎች ደግሞ ታምራት ቶላና ኡሴዲን መሐመድ ሆነዋል፡፡ አትሌቶቹ መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ቤል ቪው ሆቴል ተሰባስበው ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ 

በሌላ በኩል ከማራቶን አትሌቶች በተጓዳኝ የ10,000 እና የ5,000 ሜትር ተወዳዳሪዎች እንዲሁም ከ800 ሜትር ጀምሮ የመካከለኛ ርቀት ተወዳዳሪ ብሔራዊ አትሌቶች ምርጫ ጋር ተያይዞ የመጨረሻዎቹ አትሌቶች ማንነት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት አልታወቀም፡፡ በየርቀቶቹ በፓሪስ ኦሊምፒክ እንደሚሳተፉ የሚጠበቁት አትሌቶች ከሰሞኑ በተለያዩ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ ሲሳተፉ ይታያሉ፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፣ በተጠቀሱት ርቀቶች የሚወዳደሩ አትሌቶች እስካሁን ባለው የመጨረሻዎቹ አለመለየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በተለይ ከ800 ሜትር ጀምሮ 3,000 ሜትር መሰናክልና ቀጥታ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች፣ የሚወዳሩባቸው ርቀቶች ያን ያህል የማገገሚያ ጊዜ ስለማይጠይቁ ተደጋጋሚ ውድድሮችን እንዳያደርጉ ቁጥጥር ማድረግ ካልሆነ ሆቴል ማስቀመጡ ከሙያ አኳያ እንደማይመከር በብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ስለታመነበት የመጨረሻው ምርጫ እንዲዘገይ ስለመደረጉ ነው የሚናገሩት፡፡

ኃላፊው የ5,000 እና የ10,000 ሜትር ምርጫን በተመለከተም በሰኔ ወር መጀመሪያ ምርጫው ተደርጎ ወደ ፓሪስ የሚያቀኑት የመጨረሻዎቹ ብሔራዊ አትሌቶች ሆቴል እንዲገቡ ተደርጎ ዝግጅቱ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...