Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሃይማኖት ተቋማት የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርታቸውን ለመንግሥት እንዲያቀርቡ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

የሃይማኖት ተቋማት የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርታቸውን ለመንግሥት እንዲያቀርቡ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

ቀን:

ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርቱን ለሰላም ሚኒስቴር ማቅረብ እንደሚኖርበት፣ ከውጭ አገር የሚመጣ የገንዘብ ዕርዳታ በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ እንደሚኖርበት የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ፡፡

‹‹የሃይማኖት ጉዳዮች አዋጅ›› የተሰኘውና ሪፖርተር የተመለከተው ረቂቅ አዋጅ፣ የሃይማኖት ተቋማቱ ተቀባይነት ያለው የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚኖርባቸው፣ የኦዲት ሪፖርታቸውንም ለሰላም ሚኒስቴር ማቀረብ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ 

የሃይማኖት ተቋማቱ የሚጠቀሙት የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት የገቢ፣ የወጪና አጠቃላይ የንብረት ዝርዝር የያዘ መሆን እንደሚኖርበትና የገቢ አሰባሰብና የወጪ አስተዳደር በሕጋዊ መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ አንድ የሃይማኖት ተቋም በራሱ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በሚያከናውንበት ጊዜ፣ ለዚሁ ሥራ የተለየ የባንክ ሒሳብ መክፈትና የተለየ መዝገብ መያዝ እንዳለበት ደንግጓል፡፡

በተጨማሪም ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ከውጭ አገር የሚላክለትን የገንዘብ ዕርዳታ፣ ስጦታ ወይም ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችን በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ እንደሚኖርበት አስቀምጧል፡፡ ሲያሳውቅም የለጋሹን ድርጅት ወይም ግለሰብ ስምና አድራሻ፣ የተለገሰው የገንዘብ፣ ስጦታ ዓይነትና መጠን፣ እንዲሁም ስጦታው ወይም ድጋፉ የተሰጠበት ልዩ ዓላማ መካተት እንዳለበት ተገልጿል፡፡

ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሃይማኖት ተቋማቱ ኦዲት ሪፖርታቸውን ለሰላም ሚኒስቴር ያቅርቡ የሚለው የረቂቁ ክፍል ላይ ተቃውሞ የላቸውም፡፡ ከውጭ የሚላክን ገንዘብ አስመልክቶ በረቂቁ ላይ የተቀመጠው ገንዘቡን ማሳወቅ ከሆነም ችግር እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከፋይናንስ ደኅንነት ወይም ከሌላ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ጋር የሚያገናኝ ከሆነ ጣልቃ መግቢያ በር እንዳይሆን ሥጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በሦስት ወራት ውስጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በገለልተኛ ኦዲተር ማስመርመር እንዳለበትና የኦዲተሩን አቋምና የውሳኔ ሐሳብ መያዝ እንዳለበት በረቂቁ ተመላክቷል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር የደረሰውን የኦዲት ሪፖርት አመቺ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንዳለበትም ተደንግጓል፡፡ 

የአምልኮ ወይም የመቃብር ቦታ አሰጣጥን በተመለከተም ለሃይማኖት ተቋማቱ የመሬት አቅርቦት በመሬት አጠቃቀምና የሊዝ ሕጎች መሠረት እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡ ለአምልኮ ወይም ለመቃብር ቦታ በተጠየቀበት አካባቢ ለሃይማኖት ተቋሙ ለተመሳሳይ ዓላማ የተሰጠ ቦታ አለመኖሩ ወይም ተጨማሪ ቦታ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት፣ እንዲሁም በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል የሚኖረው ርቀት ቢያንስ 500 ሜትር መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

ትምህርትና የሃይማኖት ተግባራትን በሚመለከትም በረቂቁ ላይ ዝርዝር ጉዳዮች ተቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መደበኛ ትምህርት በሚሰጡ የመንግሥት ወይም የግል ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ሃይማኖታዊ ይዘት የሌለው መሆን እንደሚኖርበት አንዱ ሲሆን፣ በትምህርት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርትን ማስተማር ወይም በቡድን ማምለክ የተከለከለ ነው የሚለው ሌላኛው ነው፡፡

በተጨማሪም ማንነትን ለመለየት የሚያስችሉ ሃይማኖታዊ አለባበሶችን ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደማይገባ ተደንግጓል፡፡ ይህን የረቂቁን ክፍል አስመልክቶ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሃይማኖታዊ ምልክቶችን እንደ ቤተ እምነቱ አስገዳጅ ሕግጋቶች ልዩ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ መደንገግ ሲገባው፣ ሙሉ ለሙሉ ከትምህርትና ሥራ ገበታ የሚያስገድዱ ድንጋጌዎችን መያዙ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ለሰላም ሚኒስቴር በላከው አስተያየት፣ ቅሬታና የመፍትሔ ሐሳብ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥት ኃላፊዎች መንግሥትን ወክለው በሃይማኖት በዓላት አከባበር ላይ መገኘት እንደማይችሉ በረቂቁ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በትምህርት ቤት፣ በመኖሪያ ቤትና በሕክምና ማዕከላት አካባቢ የሚደረግ አምልኮ በአካባቢ ጥበቃ ሕግ የተቀመጠውን የድምፅ መጠን ያከበረ መሆን እንደሚኖርበት፣ ካልተፈቀደ በስተቀር ማስተማርን ጨምሮ ሃይማኖታዊ ተግባራትን በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች መፈጸም እንደማይችል ረቂቁ ይደነግጋል፡፡

የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በበኩሉ ይህ የረቂቅ አዋጁ ክፍል በልዩ ሁኔታ በወንጌል አማኞች ላይ ጫና የሚፈጥርና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው መሆኑን በመግለጽ፣ ሊስተካከል ይገባል በማለት ለሚኒስቴሩ በላከው ደብዳቤ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...