Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየማዳበሪያ ግዥ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 97 በመቶ መሳካቱ ተገለጸ

የማዳበሪያ ግዥ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 97 በመቶ መሳካቱ ተገለጸ

ቀን:

  • ከዞን ወደ ወረዳ በሚደረገው ሥርጭት ላይ ችግር መኖሩ ተጠቁሟል

ግብርና ሚኒስቴር በተያዘው በበጀት ዓመቱ ውስጥ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ አቅዶት ከነበረው 2.3 ሚሊዮን ቶን ወይም 23 ሚሊዮን ኩንታል የማዳበሪያ ግዥ ውስጥ 19.4 ሚሊዮን ኩንታል ለመግዛት አቅዶ ከ97 በመቶ ወይም 19.4 ሚሊዮን ኩንታል ግዥ መፈጸም መቻሉንና ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል እንዳሳየ አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የ2016 በጀት ዓመት የማዳበሪያ ግዥ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም 20 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት አቅዶ 19.4 ሚሊዮን ወይም ከ97 በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገብ፣ በታሪክ የመጀመርያና እጅግ የተሳካ የሥራ ክንውን መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣ ዕቅዱ ተይዞ የነበረው ከአገር አቅም አኳያ ነው፡፡ በመሆኑም በበጀት ዓመቱ ለማዳበሪያ ግዥ የተመደበው 930 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ላለፈው ዓመት በጀት ተመድቦ የነበረው ግን 1.59 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከዚህ ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የ100 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አለው፡፡ ነገር ግን ሚኒስቴሩ የማዳበሪያ ግዥ አሠራሩን በማዘመኑ የማዳበሪያ ግዥውን በወቅቱ መፈጸም በመቻሉ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 19.4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት መቻሉንና ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያው ግዥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

- Advertisement -

ባለፈው በጀት ዓመት (ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት) የተገዛው ጠቅላላ ማዳበሪያ 12.8 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ 800 ሺሕ ኩንታል ተጨምሮ ጠቅላላ ግዥው 13.6 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበርና በዘንድሮው በዘጠኝ ወራት ከተገዛው አፈጻጸም ጋር እንደማይደራረስ አብራርተዋል፡፡

ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን ሲያቀርቡ (ሚያዚያ 8 ቀ ን 2016 ዓ.ም.) ቆየት ያለ ዳታ መሆኑን አስታውቀው፣ በዕለቱ ግን ተጨማሪ 11.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱንና ለክልሎች እየተሠራጨ መሆኑንም ግርማ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

‹‹ግባችን ማዳበሪያን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ብቻ አይደለም›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚ ማድረግና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ባላቸው መረጃ መሠረት በአሁኑ ጊዜ (ግንቦት ወር መጀመርያ ሳምንት) ከ50 እስከ 52 በመቶ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ መሠራጨቱንም አክለዋል፡፡

የማዳበሪያ ግዥው በጥንቃቄና በወቅቱ በመፈጸሙ 20 ቢሊዮን ብር ከብክነት ማዳን መቻሉንም ግርማ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ አጠቃላይ በሚኒስቴሩ ሥር ያሉ ተቋማትን የሥራ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው በዝርዝር አቅርበው እንዳጠናቀቁ፣ የማዳበሪያ ግዥንና  ሥርጭትን በሚመለከት ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡

የዘንድሮን በጀት ዓመት የማዳበሪያ ግዥንና ሥርጭት አፈጻጸምን በሚመለከት ካለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ማወዳደር እንደማይቻል በመግለጽ ጥያቄ ያቀረቡ የቋሚ ኮሚቴው አባል፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ለሚገኙ ወረዳዎች በቂ ማዳበሪያ እንዳልቀረበና ከ100 ሺሕ በላይ ሕዝብ በሚኖርበት ግሼራቢ ለሚባል ወረዳ አንድ ኩንታል ማዳበሪያ እንኳን እንዳልደረሰ አስታውቀዋል፡፡ በወቅቱ እንዳይሰባሰብ አካባቢው በልግና መኸር አብቃይ በመሆኑ ሁለቱንም ሊያስተናግድ እንደሚችል አክለዋል፡፡ በመሆኑም ሥርጭቱን እስከ ታች ድረስ ወርዶ ማጣራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

ሌላዋ የፓርላማ አባል ባቀረቡት ጥያቄ፣ ሚኒስቴሩ የሥራ አፈጻጸሙ ጥሩ ቢሆንም፣ ማዳበሪያ ሥርጭቱ ትኩረት ያደረገው ለስንዴ አምራች አካባቢዎች ብቻ በመሆኑ፣ ድንች አምራች የሆኑ የምዕራብ አሩሲ ቆሬ ወረዳ አካባቢዎች ግን እየደረሰ ባለመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ዓምናና ዘንድሮን ማነጻጸር ተገቢ አይደለም፡፡ ዓምና አገር የነበረችበት ችግር ይታወቃል፡፡ ደግሞም ለቋሚ ኮሚቴው የደረሰው የአፈጻጸም ሪፖርት ማዳበሪያን በሚመለከት ያለው አፈጻጸም 16 በመቶ መሆኑን ገልጾ ሳለ፣ ዛሬ (ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም.) አፈጻጸሙ 52 በመቶ ደርሷል ማለት፣ እንዴት በ15 ቀናት ውስጥ እዚህ ሊደርስ ቻለ?›› የሚል ጥያቄ በሌላኛው የቋሚ ኮሚቴው አባል ቀርቧል፡፡ በደንብ ታች ድረስ መከታተል፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና ዩኒየኖችን ክትትል ማድረግና መፈተሽ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት ‹‹የምንሠራው ማዳበሪያን ሳናውቀውና በግምት ሳይሆን ሠርተን ነው፡፡ በሰሜን ሸዋ አንዳንድ አካባቢዎች ችግሮች ስላሉ ደብረብርሃን ከተማ ማዕከል በሚገኘው መጋዘን ውስጥ ማዳበሪያ አስቀምጠን የቻልነውን ያህል እያደረስን ነው፡፡ በእርግጥ በፀጥታ ችግር ምክንያት ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ሊኖሩ ይችላሉ›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የማዳበሪያ ሥራ 90 ከመቶ በላይ የእሳቸው ዘርፍ መኑን አስረድተው፣ ለምክር ቤቱ የሚያቀርቡት ሪፖርት ግምታዊ ሳይሆን በትክክል ክትትል የተደረገበትና እውነተኛ መሆኑን ምክር ቤቱ እንዲገነዘባቸው ጠይቀዋል፡፡ ማዳበሪያ ከጂቡቲ ወደብ መነሳት ስለነበረበትና የአማራ ክልልን ድርሻ ወደ ሌላ መወሰድ ስለሌለበት፣ ከክልሉ ጋር በመነጋገር ደቡብ ወሎ፣ ሰማን ወሎና ሰሜን ሸዋ የመጀመርያው የአፈር ማዳበሪያ እንዲደርስ መደረጉን ሶፊያ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትር ደኤታዋ እንደገለጹት፣ ማዳበሪያ ጂቡቲ ደርሶ ለክልሎች ማድረስ ያልተቻለበት ሁኔታ የለም፡፡ ጎንደርን በሚመለከት በኮማንድ ፖስቱ (መከላከያ) ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው፣ ሾፌሮችም መስዋዕትነት እየከፈሉና በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ ጭምር ለአርሶ አደሩ እየደረሰ ነው፡፡ በግምገማ ማረጋገጥ የተቻለውም በጎንደር አካባቢ እጥረት ያጋጠመው ሾፌሮችን የሚያጅብ ባለመኖሩና በተፈለገበት ቦታ መሄድ ባለመቻሉ ከዘጠኝ እስከ አሥር በመቶ እጥረት ሊያጋጥም መቻሉን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በሰሜን ሸዋ አንድም ኩንታል አልደረሰም መባሉን ለመቀበል እንደሚያዳግታቸው ገልጸዋል፡፡ ምንም ይሁን ምንም አርሶ አደሩን መታደግ ግድ ስለሆነ ሁሉም መስዋዕትነት እየከፈለና እየሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

ማዕከላዊና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎችን በሚመለከት ስላለው የማዳበሪያ ሥርጭት ያብራሩት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ባለፈው በጀት ዓመት ሁለቱ ክልሎች አንድ ላይ ስለነበሩ 780 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ መሠራጨቱን ጠቁመው፣ በዚህ ዓመት በጀት ግን 800 ሺሕ ኩንትል ማዳበሪያ ተገዝቶ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ሪፖርቱ እስከቀረበ ድረስ ከ50 በመቶ በላይ ማቅረብ መቻሉንና ሥርጭትን በሚመለከት ግን ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ 280 ሺሕ ኩንታል ያልተሠራጨ ማዳበሪያ መኖሩን አስታውሰዋል፡፡

በአጠቃላይ የዘር ወቅት መሆኑንና አሁን ላይም ማዳበሪያ እየገባ መሆኑን ሶፊያ (ዶ/ር) ጠቁመው፣ አንዳንድ ቦታ በተለያዩ ምክያቶች ሊደርስ ባይችልም፣ በተቻለ መጠን ግን አንድም ኩንታል ቢሆን ለሁሉም አርሶ አደር ለማዳረስ በትጋትና በመናበብ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩና ክልሎች በተቻለ መጠን እየተናበቡ እየሠሩ ቢሆንም ከዓምናው ሥርጭት አንጻር ዘንድሮም ችግር ይገጥማል የሚል ሥጋት እየተስተጋባ ቢሆንም፣ ልዩ ክትትልና ግምገማ በየሁለት ቀኑ እየተደረገና እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ አዲስ የአሠራር ሲስተም በመዘርጋቱ ፈጥኖ ለማድረስ መዘግየት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ሥርጭቱ 47 በመቶ መድረሱንና በአማራ ክልል ደግሞ 56 በመቶ መድረሱን ወይም ለኦሮሚያ 4.9 ሚሊዮን ኩንታል፣ ለአማራ ደግሞ 4.4 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ መቻሉንና ሥርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አሩሲ አካባቢ ድንች አምራች አርሶ አደሮችን በሚመለከት የቀረበውን ጥያቄ ሚኒስትር ደኤታዋ ሲመልሱ፣ አርሶ አደሮቹ አልደረሰንም፣ እጥረት አለብን ሲሉ ከክልሉ ጋር በመነጋገር እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ አሁን ላይ እጥረት ካለ ይታያል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሚኒስቴሩ ካለው አደረጃጀትም ሆነ የሰው ኃይል አንጻር ሁሉንም ወረዳዎችና ቀበሌዎች ማድረስ እንደማይችል ተናግረው፣ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ክልሎች እንዲያስፈጽሙ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው እሑድ በሪፖርተር ጋዜጣ ቁጥር 2510 ዕትም ገጽ 3 ላይ ‹‹ግብርና ሚኒስቴር የማዳበሪያ ሥርጭትን ጨምሮ የሥራ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን ጥያቄ አስነሳ›› በሚለው ዘገባ ውስጥ በተዛባ ሁኔታ ለተጠቀሱት የአኃዝ ግድፈቶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱንና አንባቢዎቻችንን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...