Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቱሪዝም ለአገሪቱ ጂዲፒ ያለው ድርሻ ከሦስት እስከ አምስት በመቶ እንደሆነ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የቱሪስት መዳረሻዎች መሠረተ ልማት የሌላቸው ናቸው ተብሏል

ቱሪዝም ለአገሪቱ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ያለው አስተዋጽኦ ከሦስት እስከ አምስት በመቶ እንደሚገመት የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቱሪዝም ሚኒስቴርን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲገመግም፣ የቱሪዝም ዘርፍ ለአገር ውስጥ ምርት የሚያደርገው አስተዋጽኦ ከሦስት እስከ አምስት በመቶ ይሆናል ሲሉ ሚኒስትር ደኤታው አቶ ስለሺ ግርማ ገልጸዋል፡፡

‹‹የቱሪዝም ዘርፍ ለአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባሻገር ለውጭ ምንዛሪ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለአገር ገጽታ ግንባታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም አንደኛ ግምት በቀጥታ ለአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት የሚያደርገው አስተዋጽኦ በተለያዩ ጊዜያት ተለዋዋጭ ሆኖ ከሦስት እስከ አምስት በመቶ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን አበርክቶ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር የቱሪዝም ሳተላይት ሥርዓት ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት ማወቅ እንደሚቻል የተናገሩት፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ናሲሴ ጫሊ ናቸው፡፡

በቱሪዝም ሳተላይት ሥርዓት አማካይነት በዘርፉ ለአገር የሚበረከተውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ለማሳካት፣ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ለማወዳደር፣ የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን ቁጥር ለማወቅ፣ በዘርፉ የተፈጠሩ ዕድሎችና የኢንቨስትመንት መጠን፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ለጂዲፒ ዕድገት የሚያበረክተውን ድርሻ ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

በተያያዘም አገሪቱ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ሀብቶች አስፈላጊው መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው ስለሆነ፣ ለአገር ማበርከት የሚገባቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ አለመሆናቸውን ከንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጥያቄ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም ምቹ የቱሪዝም አሠራሮችን በማጠናከር የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩን፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ባለሀብቶች ግልጽ መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ ለግሉ ዘርፍ ዕድገት የሚደረጉ ማበረታቻዎች ምን እንደሆኑ ተጠይቋል፡፡

በከተማና በክልሎች የቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ በመሬት አቅርቦትና በታክስ ማበረታቻ፣ ማለትም የቱሪዝም ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዓመት አሥር አዳዲስ ሆቴሎች እንዲከፈቱ ለማድረግ ለባለሀብቶቹ ከኮንስትራክሽንና ከማጠናቀቂያ ዕቃዎች፣ እንዲሁም ለሆቴሎች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነፃ የሚፈቅድ መሆኑን በመጠቀም፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ከውጭ እንዲገባ ድጋፍ በማድረግ ባለሀብቶች እየተበረታቱ እንደሆነና ግለሰቦች ይህንን ዕድል በመጠቀም በዘርፉ ሊሰማሩ ይገባል ሲሉ አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቶች በቱሪስት መዳረሻዎች ደፍረው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የገንዘብ ሚኒስቴር የአምስት ዓመት የታክስ ዕፎይታ እንዲሰጣቸው ለማድረግ የቦታ ልየታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው አስረድተዋል፡፡

የልማት ሥራዎቹ በግል ባለሀብቶች ላይ ብቻ የተመረኮዘ ሳይሆን መንግሥት የሚጠቀማቸው ማዕቀፎች የመንግሥትና የግል ሽርክና፣ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሆናቸው የቱሪዝም ኢንቨስትመንት የመስፋፋት ሒደት መኖሩን አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡

መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው የቱሪስት መዳረሻዎች በርካታ ስለሆኑ መንገድ፣ ኤርፖርትና ኔትወርክ የማይደርስባቸው በመኖራቸው፣ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በተመረጡ የቱሪስት መዳረሻዎች የሔሊኮፕተር ማረፊያ፣ እንዲሁም ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመሆን የተስተካከሉ የመንገድ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ በመንግሥትና በግል ሽርክና በቅንጅት የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ሥራዎች በመኖራቸው፣ የግሉን ባለሀብት ለመደገፍ የመሬት አቅርቦትም ሆነ ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ ለኢንቨስትመንቱ የሚያገለግሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ናሲሴ ጠቁመዋል፡፡

የቱሪዝም መዳረሻዎችን ልማት በማስፋት የግል ባለሀብቶች እንዲሳተፉ፣ ከፌዴራልና ከክልል መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተደረጉ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ በተጨማሪ የአካባቢዎቹ ማኅበረሰቦችን በማደራጀት እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚገባ ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

ይህን ሥራ ለማከናወን ከአለም ባንክ ጋር መተባበር የቱሪዝም ሀብት ልየታ (National Resource Mapping) በዝግጅት ላይ በመሆኑ በዚህም የት አካባቢ ምን ዓይነት ሀብት አለ? ምን ዓይነት ልማት ይፈልጋል? የትኛው ባለሀብት ሊያለማው ይችላል? የትኞቹ ሀብቶች በጋራና በቅንጅት ይሠራሉ? በምን ቅደም ተከተል? የሚሉትን በተመለከተ ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት በመውሰድ የተሻለ መዳረሻ ልማት እንዲኖር ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ የቱሪዝም ዕምቅ ሀብት ያላት በመሆኗ የቱሪስት መዳረሻዎችንና አዳዲስ መስህቦችን በማልማት መሠረተ ልማቶችን ማስፋትና መጠናከር ይገባል ሲሉ የቋሚ ኮሚቴ/ዊ ሰብሳቢ ወ/ሮ አሻ ያህያ አሳስበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች