Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተረፈ ፕላስቲክን ጠቃሚነት የገደበው የግንዛቤ ችግር

የተረፈ ፕላስቲክን ጠቃሚነት የገደበው የግንዛቤ ችግር

ቀን:

ዓለም አቀፍ ምርቱ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣው ፕላስቲከ ለአያያዝ ምቹ፣ ዋጋው ዝቅተኛና ለማሸጊያ ተስማሚ ቁሳቁስ ሆኖ መገኘቱ በሁሉም ሥፍራ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡

የፕላስቲክ ቁሳቁሶች ለሰው ልጅ የሚሰጡት አገልግሎት በርካታ ቢሆንም፣ ከሰው ልጆች ቸልተኝነት የተነሳ ከተመረተው ፕላስቲክ 80 በመቶ የሚሆነው ብክለት እያስከተለ ነው፡፡ በዓለም ቁጥር አንድ የውኃ አካላት በካይና ገዳይ እየሆነም መጥቷል፡፡

የተረፈ ፕላስቲክን ጠቃሚነት የገደበው የግንዛቤ ችግር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በተለያዩ አገሮች በከፊል ሪሳይክል
ከተደረጉ የፕላስቲክ ምርቶች የተለያዩ
የግንባታ፣ የቤት ቁሳቁስና አልባሳት
ይሠራሉ

ፕላስቲክና መልሰው ጥቅም ላይ የማይውሉ የፕላስቲክ ውጤቶች  በሚያስከትሉት የአየር ብክለት፣ ሰዎችን ለበሽታዎች፣ የባህር ዓሳዎችና  እንስሳትንም ለህልፈት ሲዳረጉ ይስተዋላል፡፡

የአካባቢ ብክለቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ያለ ጊዜ እንዲሞቱ ምክንያት እንደሚሆን ዓለም ባንክ በ2022 ያወጣው መረጃ አመላክቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ከአራት እስከ ስድስት ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ የኢኮኖሚ ኪሳራም አስከትሏል፡፡ በኢትዮጵያ የሚያደርሰው የገንዘብ ኪሳራም ቀላል አይደለም፡፡

በአዲስ አበባ 66.6 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በሀዋሳና በባህርዳር 2.8 እና 2.5 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ በተከታታይ ማስከተሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ባወጣው መረጃ ጠቁሟል።

የአየር ብክለት ጉዳቱ በመላው ዓለም በሚኖሩ ሰዎች፣ እንስሳት፣ በሰማይ በሚበሩና በውኃ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ እንስሳት ጭምር ቢሆንም፣ በተለይ እንደ አፍሪካ ባሉ በድህነት አረንቋ በሚዳክሩ አገሮች የሚያስከትለው ጉዳት የጎላ ነው፡፡ 

እዚህ ግባ የሚባል የፕላስቲክ ውጤቶች አወጋገድና የመልሶ መጠቀም ሕግ  በሌላቸው፣ ቢኖራቸውም ለተፈጻሚነቱ ትኩረት በማይሰጥባቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገሮች ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች የፕላስቲክ ጠርሙሶችንና የፕላስቲክ ውጤቶችን ከየወንዙ፣ ከየመንገዱና ከየተቋማቱ እየሰበሰቡ ለመልሶ መጠቀም የሚያዘጋጁ በርካታ ማኅበራት ቢኖሩም፣ በየጥጋጥጉ የወዳደቁ የፕላስቲክ ጠርሙሶችና ከአንድ ጊዜ በላይ አገልግሎት የማይሰጡ ፌስታሎችን ማየት ተለምዷል፡፡

በውኃ መሄጃ ቱቦዎች ተወትፈው የሚገኙ የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ በዘፈቀደ የሚጣል የደረቅና የፈሳሽ ዕቃዎች የፕላስቲክ ማሽጊያዎች፣ ከተሽከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝና መሰል የአየር ብክለትን የሚያፋጥኑ መንስዔዎች በተለይ በከተሞች አካባቢ ጎልተው ይታያሉ፡፡

ችግሩን ለመፍታት መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ሕጎችንና ስምምነቶችን መነሻ በማድረግ በየዓመቱ የተለያዩ ንቅናቄዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የሚፈለገው ውጤት እንዳልመጣ ይስተዋላል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የጣለ ድንገተኛ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡ ለዚህ አንዱ መንስዔ ደግሞ የጎርፍ መሄጃ ቱቦዎች በፕላስቲክና መሰል ቆሻሻዎች በመዘጋቱ እንደሆነ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለሥልጣኑ ከፕላስቲክ ፋብሪካ ባለቤቶች፣ የፕላስቲክ ምርቶችን በስፋት ከሚጠቀሙ ሱፐር ማርኬቶች፣ የገበያ ማዕከላትና ሌሎች የፕላስቲክ ምርቶችን በስፋት ከሚጠቀሙ አካላት ጋር ለመወያየት ባዘጋጀው መድረክ ተነግሯል፡፡

በፕላስቲክ ውጤቶች ተጠቃሚዎች፣ አምራቾችና አቅራቢዎች በኩል በቂ ግንዛቤ አለመኖር፣ እንዝህላልነት እንዲሁም ችግሩን ለመከላከል የወጡ ሕጎችና መመሪያዎች  በአግባቡ አለመፈጸም ለችግሩ መባባስ ጥቂቶቹ ምክንያቶች ስለመሆናቸው አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ እ.ኤ.አ ከ2007 እስከ 2022 የአገሪቱ የፕላስቲክ ፍጆታ ከ4,500 ወደ 22,4000 ከፍ ብሏል፡፡

ባለፉት ዓመታት የፕላስቲኮች የነፍስ ወከፍ ፍጆታ በስድስት ኪሎ ግራም ከፍ ያለ ሲሆን፣ በ2022 ወደ 26 ኪሎ ግራም ደርሷል፡፡

በአዲስ አበባ ከሚመነጨው ቆሻሻ 13 በመቶ ፕላስቲክ ሲሆን፣ በዓመት 80,000 ቶን ይመነጫል ተብሎ እንደሚገመት በባለሥልጣኑ የአካባቢ ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ለሚሳ ጉደታ ተናግረዋል፡፡

ከሚመነጨው የፕላስቲክ ቆሻሻ በዓመት 40,000 ቶን ያህሉ ሪሳይክል ተደርጎ መልሶ ጥቅም ሊሰጥ እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡት አቶ ለሚሳ፣ ክምችቱ በዚህ ከቀጠለ ለሰው ልጅ ጤናም ሆነ ለአካባቢ አደገኛ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በውኃ ውስጥ የሚኖሩ አካላት ላይ የተዛባ የሥነ ምኅዳር መስተጋብር እንደሚያስከትል፣ በእንስሳት፣ በዕፅዋት፣ በባክቴሪያና አጠቃላይ በውኃ ውስጥ የሚኖሩ ሕይወት ያላቸው ነገሮችን እንደሚጎዳም አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ለሚሳ፣ በርካታ ቆሻሻዎችን እንደምታመነጭ የተነገረላት አዲስ አበባ፣ 64 በመቶ የሚሆነውን ብክለት ከ30 ዓመታት በላይ ዕድሜ ካስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ከሚወጣ በካይ ጋዝ፣ 46 በመቶው ከፕላስቲክ ቦርሳዎች (ፌስታሎች)፣ 34 በመቶ ከውኃና ከለስላሳ መጠጥ ጠርሙሶችና 16 በመቶ ገደማው ከቤት ዕቃዎች የሚመነጩ ናቸው።

በመሆኑም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣውን የፕላስቲክ መጠን በከተማዋ ለመቀነስ  የወጡ ሕጎችና መመሪያዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ ባለሥልጣኑ አስታውቋል።

ፕላስቲክ በማምረትና በመሸጥ ላይ ያሉ ድርጅቶች ምርታቸውን ከወዲሁ ወደ ወረቀትና በጨርቅ ምርቶች እንዲተኩ ባለሥልጣኑ አሳስቧል።

መመሪያውን ሳይቀበሉ ወይም ችላ በማለት በተለይ በመመሪያው መሠረት ውፍረታቸው ከ0.03 ማይክሮ ሜትር በታች በሆነ መጠን ፕላስቲኮችን ሲያመርቱ የተገኙ የፋብሪካ ባለቤቶች የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ተነግሯል። 

አምራች ድርጅቶች በበኩላቸው፣ የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት  ለጋራ ጥቅምና ደኅንነት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ስስና መልሰው ጥቅም ላይ የማይውሉ ፕላስቲኮችን ማምረት ሕግን የተላለፈ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መቆም አለበት ተብሏል።

በዚህ ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች ምርታቸውን ወደ ወረቀትና ጨርቅ ከረጢት በመቀየር ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ ባለሥልጣኑ ያሳሰበ ሲሆን፣ ከእነዚህ መገልገያዎች ጋር የዕለት ተዕለት ቁርኝት ያላቸው አከፋፋዮች በሥራቸው ላይ አደጋ እንደሚደቀንባቸው አንስተዋል።

ኅብረተሰቡ በአንድ ብርና አንዳንዴም በነፃ ሲገለገልባቸው የነበሩ ፌስታሎችን በማስቀረት የአምስት ብርና የአሥር ብር መገልገያ እንዲገዙ ማድረግ የኑሮ ውድነቱን ማባባስ ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ድዳ ድሪባ በበኩላቸው፣ ዳቦ አከፋፋዮች፣ ልብስ መሸጫ ቤቶች፣ ሸቀጣ ሸቀጥ ቸርቻሪዎች ዕቃ ሲሸጡ ከደረጃ በታች በሆኑ የፕላስቲክ ውጤት አሽገውና ጠቅልለው ከመስጠት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ከዚህ ይልቅ ለረዥም ጊዜ የሚያገለግሉ ምርቶችን እንዲጠቀሙ ማለማመድ ተገቢ ነው ብለዋል።

ሸማቹ ማኅበረሰብ ከቤቱ ሲወጣ የሚገዛውን ዕቃ የሚይዝበትን ከረጢት አብሮ እንዲያስታውስና እንዲላመድ ማድረግ የሁሉም ድርሻ እንደሆነም አክለዋል፡፡

‹‹ዳቦ፣ ስኳር፣ ቡናና የመሳሰሉትን የሚሸጡ ነጋዴዎች፣ በሕገወጥ መንገድ በተመረተ ፌስታል ቋጥራችሁ አትሽጡ›› ያሉት አቶ ድዳ፣ ይኼን ሰበብ አድርገው በሸቀጦች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋደዎች ካሉ ኃላፊነቱ የራሳቸው ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እሳቸው እንደዚህ ይበሉ እንጂ፣ ለአብነት በሺዎች የሚቆጠር ዳቦ ለተጠቃሚው የሚያከፋፍሉ በከፍተኛ ወጭ የተመረቱ ከረጢቶችን ሲጠቀሙ በዕቃው ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ እንደማይቀር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በአምራቹ፣ በተጠቃሚውና በባለሥልጣኑ በፕላስቲክ ዙሪያ ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ የነገሩን የኢትዮጵያ የፕላስቲክና ራበር አምራቾች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳምሶን ከተማ፣ ፕላስቲክ የማይገባበት ቦታ እንደሌለና ለብዙ ጥቅም እንደሚውል፣ ዳግም ለመጠቀምም ሆነ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል (ሪሳይክል) ለማድረግ ግንዛቤ ፈጥሮና ቴክኖሎጂን አምጥቶ ከጉዳቱ ይልቅ ጠቀሜታውን ማጉላት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ ላይ ፕላስቲክ እንጨትና ብረትን የሚተካበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ በየቤቱ  ያለው ቁሳቁስ፣ ጫማ ሆነ ብርድ ልብስ እንዲሁም በርካታ የሰው ልጅ መጠቀሚያዎች ከፕላስቲክ የተሠሩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ብክለት እያስከተሉ ነው የሚባሉ ተረፈ ፕላስቲኮችንም በአግባቡ መጠቀም፣ ሪሳይክል ማድረግ  ከኢትዮጵያ ይጠበቃል፣ እዚህ ላይ ግንዛቤ መፍጠርም ጥሩ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ፌስታል በወረቀትና በጨርቅ መያዣዎች ይተካ ሲባል፣ እንዲህ በቀላል የሚተገበር እንዳልሆነ፣ መጀመርያ ግብዓት መሟላት እንዳለበት፣ ለመጽሐፍ ማተሚያ ወረቀት ማግኘት ከባድ በሆነበት፣ በኢትዮጵያም ወረቀት የሚያመርት የለም ማለት በሚቻልበት፣ ጨርቅ የምንለውም በምርት ሒደት የፕላስቲክ ግብዓት የሚጠቀሙ በርካቶች በሆኑበት ሰፊ ጥናት መደረግ እንዳለበትም አክለዋል፡፡

የፕላስቲክ ምርትን ውፍረቱን መጨመር ብቻ የፕላስቲክ ብክለትን ሊያስቀር እንደማይችል፣ ውፍረቱ ሲጨመር የፕላስቲኩ ዋጋ በሚገዙ ዕቃዎች ዋጋ ላይ መጨመሩ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር፣ ችግሩ የፕላስቲክ ምርቱ ጥራት ከሆነ ተቆጣጣሪው አካል መቆጣጠር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

‹‹እኛ እንደ ማኅበር ግንዛቤ እየሰጠን ነው፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች አገሮች ስንነፃፀር ፕላስቲክን መልሰን ገና መጠቀም አልጀመርንም፡፡ የምንሰበስባቸውን ፈጭተን ውጭ ነው የምንልከው›› በማለትም፣ እዚሁ አገር ውሥጥ ለተለያዩ ጥቅሞች እንዲውሉ ሁኔታዎች መመቻቸት ችንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡  

ከፕላስቲክ ከመልሶ መጠቀም የተሠሩ ልብሶች፣ ቦርሳዎችና በርካታ የሰው ልጅ መጠቀሚያዎች እንዳሉ፣ ፕላስቲክ እንዲበከል ሳይሆን እንዲጠቀም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና አሠራሩን ማዘመን እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ተዋናዮች ይመክራሉ፡፡

ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ካሉ እነሱን ማስተካከል፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ፕላስቲክን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችል የሕግና የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን ማመቻቸት የፕላስቲክ ብክለትን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለማስቀረት እንደሚያግዝ አስተያየት ሰጪዎች ነግረውናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...