Wednesday, June 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የግዕዝ ቅኔ መንገዶች ቅፅ ፩

በኅሩይ አብዱ

– የመጽሐፉ ርእስ፡ የግዕዝ ቅኔ መንገዶች ቅፅ

– አሳታሚ፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ

– አዲስ አበባ፣ 2010 .. (473+6 ገጾች) ISBN-978-99944-69-70-3

ምንም እንኳ ሽፋኑ ላይ ባይጻፍም የዚህ መጽሐፍ ደራሲ አለቃ አፈወርቅ ዘውዴ ናቸው። አለቃ አፈወርቅ ከዚህ በፊት በ1948 ዓ.ም. ጸያሔ ፍኖት፣ በ1988 ዓ.ም. ሀገረ መጻሕፍት የተባሉ የግእዝ ሰዋስው መጻሕፍትን አሳትመዋል። በተለይ ሀገረ መጻሕፍት የሀምሳ ዓመታት ስለግእዝ ሰዋስው በማስተማርና በመመራመር የደረሱበትን ጥልቅ እውቀት ያስተላለፉበት ዕፁብ መጽሐፍ ነው። የግእዝ ቅኔን በተመለከተ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ በ1980 ዓ.ም. ባሳተመው የግእዝ ቅኔያት የስነ ጥበብ ቅርስ ዝግጅት፣ የቅኔዎቹን ምሥጢር በመፍታት፣ ታሪኩን በመተረክ እንዳሁም በእርማት ተሳትፈዋል። በተጨማሪም ስለ ቅኔ ታሪክ የቅኔ ጥበብ አጀማመርና አረማመድ የሚል የ15 ገጽ መቅድም ጽፈዋል። በ1984 ዓ.ም. በታተመው የግእዝ ቅኔያት የስነ ጥበብ ቅርስ ሁለተኛ ክፍል በድጋሚ ቅኔዎቹን በመተርጎም፣ በመመሥጠርና ታሪኩን በመተረክ እውቀታቸውን አካፍለዋል። በነዚህ ሁለት የምርጥ ቅኔያት መድበሎች ውስጥ የእሳቸውም አምስት ቅኔዎች ተካተዋል። የአሳታሚውን መግቢያ ሳይጨምር፣ መጽሐፉ የአለቃ አፈወርቅ መቅድም እና አራት ዋና ክፍሎች አሉት። ክፍሎቹም 1ኛ – የሠምና ወርቅ ምሳሌ አውራ መንገዶች (ገጽ 30-54)፤ 2ኛ – የዘርፍና ባለቤት ኺደት ስያሜ (ገጽ 55-214)፤ 3ኛ – የቅጽልና ባለቤት ኺደት ስያሜ (ገጽ 215-399)፤ 4ኛ – የሳቢና የተሳቢ ኺደት ስያሜ (ገጽ 400-472) ተብለው ተሰይመዋል። መቅድሙን አለቃ አፈወርቅ የቅኔን እና የሠምና ወርቅን ትርጕም በመበየን ይጀምራሉ። ቅኔ፣ «የኹለት ተጣማሪ አርእስተ ነገር ሐተታዊ ድርሰት ሲሆን፣ ደራሲው ሊቀኝለት/ሊቀኝበት/ የመረጠው ታሪካዊ ርእሰ ነገር በወርቅ ተምሳሌት ወርቅ ይባላል … በወርቅ የተመሰለውን የዋናውን ሐሳብ ርእሰ ነገር ለማንጸባረቅና ለማጉላት የሚመረጠውና የሚጠቀሰው ተመሳሳይ ርእሰ ነገር … ሠም ይባላል» (ገጽ 2)።

የግዕዝ ቅኔ መንገዶች ቅፅ ፩ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በመቀጠልም አንድ ቅኔ መከተል ያለበትን ሕጎች ከጠቀሱ በኋላ፣ የቅኔ ዓይነቶችን በሥንኝና በሐረግ በመመጠን ይዘረዝራሉ። እነዚህ የሠምና የወርቅ ቃላት ወይም ሐረጎች የሚጣመሩበት አኳኋን፣ የሚመሰሉበት ዘዴ፣ ወይም የአቀማመጣቸው ቅደም ተከተል የቅኔ መንገድ ይባላል፡፡ አለቃ አፈወርቅ ይህንን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ያነሳሷቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናው ግን ስለ ቅኔ መንገዶች ከዚህ በፊት የተደረሱ መጻሕፍት በሚመጥን ደረጃ ርዕሰ ነገሩን ለማስረዳት/ለመተንተን አለመሞከራቸው ይመስላል። ይህንንም ለመረዳት በመጀመርያ ስለ ግእዝ ቅኔ መንገዶች የመረመሩ ሥራዎችን ልዘርዝር። በዚህ ርዕስ ዙርያ የተጻፉ ድርሰቶች ከ1700ዎቹ ጀምሮ በተዘጋጁ ብራናዎች ውስጥ ይገኛሉ፤ አብዛኛውን ጊዜም ፍኖተ ቅኔ በሚል ስም ይጠራለ – ያው የቅኔ መንገድ ማለት ነው። በመቀጠል በ1881 ዓ.ም. የታተመው የአለቃ ታዬ መጽሐፈ ሰዋስው ስለ ቅኔ መንገድ የሚያስረዳ ክፍል አለው። የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ (1948 ዓ.ም.)፣ የመምህር ዓለማየሁ ሞገስ ሰዋስወ ግዕዝ (1950 ዓ.ም.)፣ የዮሐንስ አድማሱ የዲግሪ መመረቂያ ጽሑፍ (1958 ዓ.ም.)፣ የሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት (1962 ዓ.ም.)፣ የፍቅረ ድንግል በየነ የሰምና ወርቅ ሰዋስው (1974 ዓ.ም.)፣ የመምህር አፈወርቅ ተክሌ መጽሐፈ ታሪክ ወግሥ (1997 ዓ.ም.)፣ የመምህር ተክለ ማርያም አምላኩ ኆኅተ ቅኔ (2007 ዓ.ም.)፣ የመምህር ዐቢይ ለቤዛ ዓምደ ግዕዝ (2010 ዓ.ም.) ስለ ቅኔ መንገዶች በተለያየ ደረጃ አቅርበዋል። የአለቃ አፈወርቅ ዘውዴም የምርምር ሥራ አሁን ባለበት መልክ የተዘጋጀው በ1970ዎቹ ነበር። አለቃ አፈወርቅ እንደሚሉት አብዛኛዎቹ ሥራዎች የተለያዩ የቅኔ መንገዶችን ሥሞች ይደረድራሉ ወይንም ከቅኔው መንገድ ስም ቀጥሎ ለምሳሌ የሚሆን የግእዝ ቅኔ ያስቀምጣሉ። አንዱ መንገድ ለምን ያ ስም እንደተሰጠው፣ ለምሳሌ የቀረበው ቅኔ እንዴት መንገዱን እንደተጠቀመ የሚያስረዳ ግን ብዙ ሥራ የለም። ደራሲው እንደሚሉት፣ «እነሆ ጥንታውያን አበው መምህራን መንገድ/ጎዳና/ ቅኔዎችን ሲያዘጋጁ የግዕዝን ንባብ ብቻ ጽፈውታል፤ … የመንገዶችን ኺደት በየዐይነቱ አልከፈሉትም፣ መንገድ ቅኔዎችን የሰየሙባቸውን የምሳሌ ቃላትን ምንነትና … ያላቸውን ምሥጢራዊ ዝምድናቸውን … በእነዚህ የምሳሌ ቃላት እንዲሰየሙ ያደረጓቸውን የግዕዝ ቃላት የትኛው የትኛው እንደሆኑ በትክክል በመጠቀም የሠምና ወርቁን ምሥጢር በመግለጽ ለደቀ መዛሙርት የማስረዳት ልምድ ግን በብዙዎቹ መምህራን ዘንድ አልነበረም፣ ሾላ በደፈናው ነበር።» (ገጽ 28)

ከላይ ከተዘረዘሩት ሥራዎች መሀል የዮሐንስ አድማሱ የመመረቂያ ጽሑፍ ስምንት መንገዶችን በሰፊው ይተነትናል። የፍቅረ ድንግል በየነም ሥራ ወደ አስር የሚሆኑ መንገዶችን በአማርኛ ሠምና ወርቅ ምሳሌዎች ያስረዳል። ከአለቃ አፈወርቅ ረቂቅ ዝግጅት በኋላ ከታተሙት መጻሕፍት መካከል የመምህር ዐቢይ ለቤዛ ሥራ አስራ አምስት መንገዶችን ከነምሳሌያቸው ያቀርባል። በተለይ የመምህር ተክለ ማርያም መጽሐፍ የቅኔውን መንገድ ስም፣ የምሳሌውን ቅኔ ትርጉም ከመቶ ለሚበልጡ መንገዶች ይሰጣል። አለቃ አፈወርቅ ዘውዴ ከሁሉም በላቀ ሁኔታ በዚህ አንደኛ ቅጽ 310 የቅኔ መንገዶችን ከስያሜው አንስተው እስከ ምሳሌና ምሥጠራ አሳይተዋል። የሳቸውም ሥራ እንዴት እንደሚለይ ሲያስረዱ፣ «ከዚኽ መጽሐፍ ግን በምስጢር አንድ ሲሆኑ አበው መምህራን የተለዩባቸውን ስያሜዎች በማዛመድ፣ መንገድ ቅኔዎችን የሰየሙባቸውን የምሳሌ ቃላትን በመተርጎምና በማብራራት፣ ለመንገድ ቅኔዎች መሰየሚያ የሆኑት የምሳሌ ቃላት ከተሰየሙባቸው ቅኔዎች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ በመግለጽ … ተዘጋጅቷል።» (ገጽ 26) እያንዳንዱ መንገድ በተቻለ መጠን ለተጠቃሚው ግልጽ እንዲሆን «ንባቡን ከእነትርጓሜው፣ ስያሜውን ከእነክሥተቱ፣ ኺደቱን ከነማፍታቻው፣ ሠምና ወርቁን በማናበብና በመተረክ …» እንደተዘጋጀ ያስረዳሉ። በተጨማሪም ይህን ሥራ ከሌሎቹ የተሻለ የሚያደርገው እነዚህን 310 የቅኔ መንገዶች ወደ አራት ዋና ዋና ክፍሎች መቦደናቸው ነው። የሠምና ወርቅ ምሳሌ አውራ መንገዶች የተባለው የመጀመርያ ክፍል ስምንት መንገዶችን ያካትታል፡፡ ይህም ክፍል የሠምና ወርቅ የአመሳሰል ዘዴ (ሰዋስው፣ ቃል፣ ስመ ተጸውዖ፣ ታሪክ፣ ተረት፣ ጥቅስ፣ ኅብረ ትንቢት፣ ኅብረ አምሳል) ላይ ተመሥርቷል፡፡ የተቀሩት ሦስት ክፍሎች አመዳደብ፣ የሠሙ ሐረግና የወርቁ ሐረግ የት የትኛውን የሰዋስው ክፍል እንደሚወክለ በማየት የተመሠረተ ነው፡፡ ክፍል ሁለት – የዘርፍና ባለቤት ኺደት – 131 የቅኔ መንገዶችን በውስጡ አካቷል፡፡ ዘርፍና ባለቤት፣ በተናባቢ ቃላት (ለምሳሌ ቤተ-መንግሥት፣ ክፍለ-ሀገር) ውስጥ ያሉት የሰዋስው ክፍሎች ናቸው፡፡ ቤተ-መንግሥትን ብንወስድ ቤት ባለቤት ሲሆን፣ መንግሥት ዘርፍ ነው፤ ክፍለ-ሀገር ላይ ክፍል ባለቤት ሲሆን ሀገር ዘርፍ ነው፤ የሁለቱ ተናባቢ ቃላት ትርጉምም የመንግሥት ቤት እና የሀገር ክፍል ነው፡፡ ስለዚህ በክፍል ሁለት የተመደቡት የቅኔ መንገዶች የሠምና የወርቁን ሐረጎች አንዳቸውን ዘርፍ ሌላኛውን ባለቤት በማድረግ የተጣመሩ ናቸው፡፡ ክፍል ሦስት – የቅጽልና ባለቤት ኺደት – 129 የቅኔ መንገዶች አለት፡፡ ደራሲው እንደሚሉት ቅጽል፣ ‹የስም ዐይነቶችን፣ ሥራውን፣ መጠኑን፣ ኹኔታውን ለመግለጥ ያለመናበብ ስምን ተጠግቶ የሚገባ ቃል› ነው (ገጽ 215)፡፡ ስለዚህ ሰፊ ሀገር ሲል፣ ሰፊ ቅጽል ሀገር ደግሞ ባለቤት ይሆናል፡፡ የቅኔ መንገዶቹ የሠምና የወርቁን ሐረጎች አንዳቸውን ቅጽል ሌላኛውን ባለቤት ያደርጋሉ። ክፍል አራት – የሳቢና የተሳቢ ኺደት – 50 የቅኔ መንገዶችን ይዟል፡፡ ደራሲው፣ ‹ሳቢ የሚባለት … ሳቢ ዘሮችና፣ ዐበይት አንቀጾች(ና) ንኡሳን አናቅጽ ናቸው፡፡ ተሳቢ የሚባሉትም ወደ እነርሱ የሚጠጉት ነገሮች ናቸው› ይላሉ (ገጽ 400)፡፡ ለምሳሌ ውሀ መጠጣት በሚለው ሐረግ፣ መጠጣት ሳቢ ሲሆን፣ ውሀ ደግሞ ተሳቢ ነው፡፡ በክፍል አራት የተመደቡት የቅኔ መንገዶች የሠምና የወርቁን ሐረጎች አንዳቸውን ሳቢ ሌላኛውን ተሳቢ በማድረግ ተጣምረዋል። አለቃ አፈወርቅ ከዚህ በፊት ለመረዳት አታካች የነበረውን የቅኔ መንገድ ጉዳይ እንዴት በቀላሉ በሚገባን ዘዴ ለኛ አቀረቡ? እሳቸው የደረሱበትን የዕውቀት አድማስ ለመጠጋት ተመራማሪ አእምሮ እና የዳበረ የቅኔ ትምህርት ያስፈልጋል። የቅኔ ትምህርታቸውን ለመቃኘት የቀለም ሐረገ ትውልዳቸውን ማየት ያስፈልጋል – ከዚህም እንደምንረዳው አለቃ አፈወርቅ ከዋነኞቹ የቅኔ ቤቶች (ዋድላ፣ ዋሸራ፣ ጎንጅ፣ ጎንደር) እና ሊቃውንት ተምረዋል፡፡

 የአለቃ አፈወርቅ የቀለም ሐረገ ትውልድ

«በወሎ በኩል ከባሕታዊ ወልደማርያም እና ከአለቃ ጥሩነህ በዋድሎችም ቤት፤ በጎጃም ውስጥ ከዲማ ጊዮርጊስ ሊቃውንት፣ ከትርጓሜና ቅኔ መምህር ወልደ ማርቆስ ብርሃኑ፣ ከቅኔ ፈጣሪው ከመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ፣ ከትልቁ የደብረ ኤልያስ ሊቅ ከመምህር ገብረ ሥላሴ ክንፉ፤ በጎንጆች በእነ ቄሰ ገበዝ በቃና፣ በእነ ቄስ ገበዝ ካሳ ቤት፤ በሜጮች በእነ ማዕበል ወልደ ሕይወት ቤት፤ በዋሸሮችም በእነ መምህር ተክሌ፣ በእነ መምህር ቀሥሙ ቤት፣ ከስመ ጥሩው መምህር ይኄይስ ወርቄ፤ ከጎንደሩ በለሳ ታላቅ ሊቅ ከመምህር ባሕርይ ቤት››

መጽሐፉ ይህንን ለብዙ መቶ ዓመታት ውስብስብ ሆኖ የቆየውን የቅኔ መንገድ ጉዳይ በአራት ዋና መደቦች ከፍሎ ከተለያዩ መንገዶች ስም አልፈን ዋናው ቁም ነገር ላይ እንድናተኩር ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ጅብ ሲወጉ በአህያ ይጠጉ የሚባለውን የቅኔ መንገድ ደራሲው በሦስተኛው ክፍል (የቅጽልና ባለቤት ኺደት) ውስጥ ይመድቡታል፡፡ ሲያስረዱም ‹‹ቅጽሉ ወርቅን ተጠግቶ ለሠሙ ስለተቀጸለ ነው ጅብ ሲወጉ በአህያ ይጠጉ የተባለው›› (ገጽ 207)፡፡ ከዛም ከአንድ ቅኔ ስንኝ ወስደው መንገዱን ያብራራሉ፣ ስንኙንም ‹በጥልልት ኤልሳቤጥ ሐረገ ወይን› – በለመለመች የወይን አበባ ኤልሳቤጥ ብለው ተርጉመው፣ ‹‹ጥልልት ኤልሳቤጥን አልፎ (ሐረገ ወይንን) ስለተቀጸለ ነው›› እንዲህ የተሰየመው ብለው ያስረዳሉ፡፡

 እንዲሁም የደራሲው ባህላዊ እና የቋንቋ ዕውቀት በሰፊው የሚታይበት የምርምር ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን እንደ አሸን የፈላው ‹ተግዳሮት› የሚለው ቃል (እንቅፋት፣ መሰናክል፣ ችግር ተብሎ አሁን የሚፈታው)፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንኳን ትርጉሙ የተለየ እንደነበር ማየት ይቻላል፣ ‹‹ተግዳሮት … ቅጥጥብ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ደንቆሮውን ዐዋቂ፣ ሰነፉን ልባም ብል በመናገር ማሾፍ ነው፡፡ በአንጻሩ ያልኾነውን ሰው ያው ያልሠራውን ሙያ ሠራ ማለት ተግዳሮት ተብሎኣል፡፡›› (ገጽ 470)

 አካዴሚው ይህንን የአለቃ አፈወርቅ ሥራ ማሳተሙ ለቅኔ አፍቃሪዎችና ተመራማሪዎች ትልቅ ውለታ ነው፤ ሁለተኛውንም ቅጽ ቶሎ እንዲያሳትም ማበረታታት የሚገባ ይመስለኛል። ሥራው የበለጠ የተዋጣለት እንዲሆን፣ ደራሲው የጻፈው አርታኢው ካስተካከለው ወይም ከጨመረው እንዲለይ ምልክት ቢደረግ ይሻላል፡፡ ከዚህ በፊት በርዕሱ ዘርያ የተዘጋጁ ሥራዎች አሁን ከታተመው ሥራ ጋር እንዴት እንደሚነጻጸሩ መግቢያው ቢያሳይ ለአንባቢው የበለጸገ ዐውዳዊ መረጃ ይሰጣል። በመጨረሻም መጽሐፉ ውስጥ በዝተው የሚታዩትን የፊደል ስህተቶችና ግድፈቶች በአግባቡ በመልቀም ጥናቱ የሚገባውን አርትዖት መሥራት ያስፈልጋል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles