Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ ጭማሪዎች የሚደረጉባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎችና ሰበቦች በርካታ ናቸው፡፡

በአንድ ወቅት ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሆነ ክስተት የተባለ ጉዳይ ቢያጋጥም እንኳን በዚያ ሰበብ የተደረገን ጭማሪ ወደ ቦታው መመለስ አይታሰብም፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ውስጥ የተለመደ ሆኖ  የዘለቀ አሁንም ተጣብቶን ያለ ክፉ ልማድ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ለዋጋ ጭማሪ መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ አሳማኝ ክስተቶች በሚያጋጥሙበት  ጊዜም ቢሆን የሚደረገው ጭማሪ ወይም መደረግ የነበረበት የዋጋ ማስተካከያ ፈጽሞ የተመጣጠነ አይደለም፡፡ ጭራሽ ይህ አጋጣሚ ለብዙዎች ሠርግና ምላሽ ሆኖ የዋጋ ጭማሪውን በዘፈቀደ ለመቆለል ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፡፡

ለምሳሌ በነዳጅ ላይ በሊትር ሦስት ብር ከጨመረ ነጋዴውም ሆነ አገልግሎት ሰጪው በዚህች የጭማሪ መረጃ ብቻ 20 እና 30 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋል፡፡ የሦስት የአምስት ብር የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ቢበዛ በነሱ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጨማሪ ወጪ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አጋጣሚውን ተጠቅመው ያልተገባ ጭማሪ አድርገው ዋጋን በማናር የግብይት ሥርዓቱን እንዳሻቸው ይዘውሩታል፡፡ አሁንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ የግብይት ሥርዓቱ እየተመራ ያለው ወይም ግብይት ዋጋ የሚተምነው ኢኮኖሚያዊ በሆነ የገበያ ዋጋ ላይ ተመሥርቶ አይደለም፡፡ በተገኘው አጋጣሚ እንክበር የሚሉ ነጋዴዎች በዝተው በሚታዩበት አገር በገበያ ዋጋ መገዛት እንደ ጅልነት የሚያስቆጥር በመሆኑ ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሸማቹ እየተደቆሰ ዘልቋል፡፡

ከልምድ መታዘብ እንደቻልነው ደግሞ አግባብ ያልሆነ ዋጋ ከሚጨመርባቸው አጋጣሚዎች መካከል በዓላት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዓላትን ሰበብ በማድረግ በየዓመቱ ያልተገባ ጭማሪ እየተደረገባቸው በዚያው ከሚቀጥሉና እጅግ የተጋነነ የሚባል ዋጋ ላይ ከደረሱ ምግብ ነክ ምርቶች ውስጥ ደግሞ ሥጋን የሚስተካከል የለም፡፡

በዓል በመጣ ቁጥር የሥጋ ዋጋ የማይጨምር ልኳንዳ ቤት አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምናልባት በየበዓላቱ ፍላጎት ስለሚጨምር የሥጋ ከብቶች ዋጋ ሊጨምሩ ስለሚችሉ የተወሰነ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ተብሎ ቢታሰብ እንኳን ገበያው ከተስተካከለ በኋላም በበዓል አሳቦ የተደረገው ጭማሪ በዚያው ይቀጥላል፡፡ በተለይ የትንሳዔ በዓልን በማስታከክ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ለዓመታት ሳይቋረጥ ቀጥሎ ዛሬ የአንድ ኪሎ ሥጋ ያለ ይሉንታ ከ2,000 ብር በላይ የሚሸጥባቸው ልኳንዳ ቤቶች እንዲበረክቱ ሆኗል፡፡

በአንዳንድ ልኳንዳ ቤቶች እዚያው የሚጠባበስና የሚቀርብ ከሆነ እስከ 3,000 ብር የሚጠየቅበት ሆኗል፡፡  

‹‹ተመጣጣኝ›› ዋጋ አላቸው የሚባሉት፣ ‹‹ተመጣጣኝ›› የሚለው አግባብ መሆን  አለመሆኑ ይሰመርበትና ዋጋቸው ከ800 እስከ 1,000 ብር ገብቷል፡፡ የሌላውን ጊዜ እንተውና በዚህ የትንሳዔ ማግሥት በደንብ ያስተዋልኩትን ምሳሌ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ኪሎውን በስድስት መቶ ብር ይሸጡ የነበሩ ልኳዳ ቤቶች ከበዓሉ በኋላ ተነጋግረው የተገበሩት እስኪመስል ድረስ በአንድ ኪሎ ላይ ከ100 እስከ 200 ብር ጭማሪ አድርገዋል፡፡ በአንድ ኪሎ ጭብስ ላይ እስከ 500 ብር ጭማሪ ያደረጉ መኖራቸውን በተጨባጭ ያረጋገጥንባቸው ልኳንዳ ቤቶችም አሉ፡፡

እንዲህ ያለው የበዓል ሰሞን ጭማሪ ሳይቋረጥ ቀጥሎ እዚህ መድረሱን ስናስብ በሒደት ዛሬ የተደረሰበት የአንድ ኪሎ ዋጋ ስናሰላ በዓላት ለሥጋ ዋጋ ጭማሪ ያልተቋረጠ አስተዋጽኦ ነበራቸው እንድንል ያስገድደናል፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህም የሥጋ ዋጋ በዚህን ያህል መጨመሩ ሆቴሎች ሥጋን ግብዓት አድርገው በሚያዘጋጇቸው ምግቦች ላይ ወዲያው አስገራሚ የሚባል ጭማሪ ማድረጋቸው ነው፡፡ ከሰሞኑ የብዙዎች ምግብ ቤቶች ሜኖ በአዲስ ተቀይሮ የማየታችን አንድ ምክንያትም በሥጋ ዋጋ ጭማሪ ሰበብ እነሱም የዘፈቀደ ጭማሪ አድርገው በመምጣታቸው ነው፡፡ በአንዲት ሚጢጢ ዱለት ላይ ከ50 እስከ 100 ብር ጭማሪ የተደረገባቸው ሦስት የማውቃቸው ምግብ ቤቶችን ሆን ብዬ ሄጄ ለውጡን ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ገዝተው ለሚሄዱ ተገልጋዮችና እዚያው ጠባብሰው የሚሸጡ ልኳንዳ ቤቶች አሉና እንዲህ ያሉት ልኳንዳ ቤቶች ከትንሳዔ በኋላ ጠባብሰው በሚያቀርቡት የአንድ ኪሎ ሥጋ ላይ እስከ ከ500 ብር ዋጋ የጨመሩ እንዳሉም ታዝቤያለሁ፡፡ በሩብ ኪሎ ጥብስ ላይ ከ100 እስከ 150 ብር ጭማሪ አድርገው እየሸጡ ካሉ ከአንድ ልኳንዳ ቤት ተገልጋዮች ምሬት ሲያሰሙም አይቻለሁ፡፡ ይህ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ዋጋ አላቸው የተባሉ ቤቶች ላይ የታዘብኩት ነው፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ በበዓላት ግብይት የሚደረግ የሥጋ ዋጋ ጭማሪ በሆቴል ቤቶች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ ዋጋ እየተጠቀመ ሊቀጥል የሚችለውን ተጠቃሚ ቤት ይቁጠረው ከማለት በላይ ማቆሚያው የት ላይ እንደሚሆን ግን አጥብቀን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ሌላው መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ሆቴል ቤቶች ከልኳንዳ ወይም ከሥጋ ቤቶች ሥጋ የሚገዙበት ዋጋ አንድና ሁለት ኪሎ ገዝቶ ወደ ቤት ይዞ ከሚሄደው ሸማቾች ከሚሸጥላቸው ዋጋ ጋር አይገናኝም፡፡ ለሆቴል አገልግሎት የሚፈለግ ሥጋ ዋጋው ይቀንሳል፡፡ ምናልባት በዚህ ሰሞን ጭማሪ ሆቴል ቤቶች በአንድ ኪሎ 50 ብር ከበዛም 100 ብር ጭማሪ ተደርጎባቸው ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡ በአንድ ኪሎ መቶ ብር እንኳን ጨምሮባቸዋል ቢባል ከእነሱ በአንድ ምግብ ላይ ያደረጉት ጭማሪ በምን ዓይነት ሥሌት ቀምረው 50 እና ከዚያ በላይ ዋጋ የሚጨምሩት? ግራ ያጋባል፡፡ አንድ ኪሎ ሥጋ ቢያንስ አምስትና ስድስት ጥብስ ይወጣዋል ይባላልና በኪሎ መቶ ብር ዋጋ ስለጨመረባቸው በመቶ ብር የሥጋ ዋጋ ጭማሪ ከኪሎ ተጨማሪ 400 ብር ሸማቹ ጨምሮ እንዲከፍል የሚገደድበት ምክንያት ፈጽሞ አግባብ አይደለም፡፡ ይሄ እኮ ዘረፋ ነው፡፡ የከብት ዋጋ የቱንም ያህል ቢጨምር ዛሬ በከተማችን አንድ ኪሎ ሥጋ አንድ ሺሕና ሦስት ሺሕ ብር ሲሸጥ የሚችልበት ምክንያት ምንድነው? ለበዓሉ ከብት ተወዶ ነው ከተባለ ደግሞ ከበዓሉ በኋላ መቀነሱ ሀቅ ነውና የተከሉትን ዋጋ በዚያው መቀጠላቸውም ተገቢ ሊሆን አይችልም፡፡  

በነገራችን ላይ በዚህ በዓል የማያውቅ ሸማች ካልሆነ የሥጋ ከብቶች ዋጋ ልኳዳ ቤቶች እንደሚሉት ያን ያህል ጭማሪ አልተደረገበትም፡፡ ከቀደመው ዓመት በቅናሽ ሲቸበቸብ እንደነበር ታይቷል፡፡ ነገር ግን ሁሌም በበዓልን አሳብቦ ዋጋ እንደተወደደ አስመስሎ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በሚፈጠር ውዥንብር ገበያው እንዲተራመስ ይደረጋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንዳንዶች ሆን ብለው የበዓላት ዋዜማ ቀናት ላይ የከብት ዋጋ ይህንን ያህል ገባ በማለት በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቁት መረጃ የሸፍጡ አንድ አካል ነው፡፡

ስለዚህ የሥጋ ዋጋ እንዲህ እየተጋነነ መቀጠሉ ትክክለኛ የገበያ ዋጋ ሆኖ ሳይሆን በዚህ ‹‹ቢዝነስ›› ጥርሳችንን ነቀልን የሚሉ አንዳንድ ባለገንዘብ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው የሚፈጥሩት እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡  ከዚህ ቀደም በሥጋ ገበያ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ይህነኑ ስለማመላከታቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ግን አንዳንድ ሸማቾች ማኅበራት አንድ ኪሎ ሥጋት 500 ብር ሲሸጡ ስናይ ደግሞ በተለይ የከተማችን ሥጋ ቤቶች ምንያህል ብዝበዛ እየፈጸሙ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

ምናልባት እነሱ የሚያቀርቡት ሥጋና በልኳንዳ ቤቶች የሚቀርበው ሥጋ ይለያል ከተባለ በዚህን ያህል የዋጋ ልዩነት ሊኖራቸው ግን ፈጽሞ አይችልም፡፡ ደግሞም ውድ ዋጋ የገዛነው ሠንጋ ነው በማለት ዋጋቸውን የሰቀሉ አንዳንድ ሥጋ ቤቶች ለዓይን ዕይታ የተወሰነ ፊት ለፊት ያሳያሉ እንጂ በሕገወጥ ዕርድ በጓሮ አስገብተው የሚቸበችቡትን ሥጋ ካሰብን በሸማች ሥጋ ቤቶች በሕጋዊ መንገድ ታርዶ የሚሸጠው የበለጠ ጥራት አለው፡፡

በአፍሪካ ቀዳሚ የሥጋ ከብቶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ሥጋ በተመጣጣኝ ዋጋ ሊሸጥ ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው? ብሎ የሚጠይቀውስ ማነው? ከብቱን አደልቦና ተንከባክቦ የሚሸጠው አርሶ አደር የሸጠው ከብት ተበልቶ ምን ያል እንደተሸጠ ቢያውቅ ምን ይል ይሆን አያስብልም? እውነት እንነጋገር ከተባለ ደግሞ በተለይ የዘንድሮው የከብት ገበያ ርካሽ የሚባል ለመሆኑ ከነጋዴ ሳይሆን በቀጥታ ከገበሬው የገዙ ሸማቾችን ምስክር ማድረግ ስለሚቻል የሥጋ ዋጋ ጭማሪ ልክ እያጣ ሄዷል፡፡ ለዚህም ነው የሥጋ ዋጋ የሚጨምረው ያለአግባብ ነው ብለን ሽንጣችንን ገትረን የምንናገረው፡፡

ችግሩ ለመባባሱ ደግሞ የሥጋ ገበያ አልጠግብ ባሉ የልኳንዳ ቤት ባለቤቶች እንደፈለጉ ሲሆኑ ዝም መባላቸው አንዱ ነው፡፡ ትክክለኛ የገበያ ዋጋውን አስልቶ ሥጋ በዚህን ያህል ዋጋ መሸጥ አይገባም የሚል ያለመኖሩም የችግሩ አካል ነው፡፡  

በዚህ ሰሞን ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ የመኖራቸውን ያህል ጥቂቶች ግን መጠነኛ ጭማሪ አድርገው እያገለገሉ ያሉትን አንድ ላይ መጨፍለቅ እንደሌለብን ቢሰማኝም አብዛኛዎቹ ተግባር ግን የነሱንም ስም እያስነሳ ስለመሆኑ ማስታወስ  ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ያልተገባ የሥጋ ዋጋ ጭማሪ እንዲሁ እየተብሰለሰልንበት ብቻ የምንተወው መሆን የለበትም፡፡ በዘርፉ ተወዳዳሪ የሚሆኑ በገበያ ዋጋ የሚያምኑ ሥጋ አቅራቢዎችን ማበርከት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ሱፐር ማርኬቶች አካባቢ የተወሰነ የተጀመረ ነገር ቢኖርም ከፍላጎቱ አንፃር ገና የሚቀራቸው በመሆኑ እንዲህ ያሉትን ማበረታት ግድ ይላል፡፡ ካልሆነ ግን የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና በችርቻሮ ንግድ ውስጥ እንዲገቡ መንግሥት እንደፈቀደ ሁሉ የሥጋ ዋጋ አማረረን ብለን የውጭ ኩባንያዎች በልኳንዳ ንግድ ውስጥ ይግቡልን እንበል ይሆን? ተቸገርን እኮ ጎበዝ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት