Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዋሽ ባንክ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን 215 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ36 ምርጥ የአፍሪካ ባንኮች ለሦስተኛ ጊዜ አንዱ ሆኖ መመረጡም ተገልጿል

አዋሽ ባንክ በ2016 የሒሳብ በጀት ዓመት ዘጠኝ ወር ላይ የተቀመጠ የገንዘብ መጠኑ ከ215 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገለጸ፡፡

ባንኩ በግሎባል ፋይናንስ መጋዚን ለሦስተኛ ጊዜ መመረጡን በማስመልከት የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጸሐይ ሽፈራው ባለፈው ሐሙስ እንዳስታወቁት፣ ባንኩ ዕድገቱን እየጨመረ በመሄድ የአስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥርም ከ21.1 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ችሏል፡፡ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ ከ178 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም አቶ ፀሐይ ገልጸዋል፡፡

ግሎባል ፋይናንስ መጋዚን ባንኩን ምርጥ የአፍሪካ ባንክ ሆኖ በተመረጠበት ዙሪያ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያም፣ መጋዚኑ ይህንን ውድድር ያደረገው ለ31ኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እ.ኤ.አ. 2024 የምርጥ ባንኮች ምርጫን ይፋ ባደረገው መሠረት በምርጫው ከተካተቱት 36 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ከተመረጡት ምርጥ የአፍሪካ ባንኮች መካከል፣ አዋሽ ባንክ ከኢትዮጵያ ምርጥ ባንክ በመሆን ለሦስተኛ ጊዜ መመረጡን አስረድተዋል፡፡  

መጋዚኑ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን ዕድገት በየዓመቱ በመተንተንና ደረጃቸውን በማውጣት የሚታወቅ መሆኑንም፣ በመግለጽ ባንካቸው አንዱ ሆኖ መመረጡን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህንንም የምርጥ ባንክነት ክብር ሲያገኝ የአሁኑ ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከኢትዮጵያ  ብቸኛው  ባንክ ሊሆን መቻሉንም ጠቅሰዋል።

እ.ኤ.አ. በ2024 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ከ150 በላይ ባሉ አገሮች የሚሠሩ ባንኮች የተካተቱበት ሲሆን፣ እንደተቋሙ መግለጫ ምርጫው የሚለኩና (Quantitative Objective) በመረጃ ላይ የተደገፉ የማይለኩ (Informed Subjective) መሥፈርቶችን ያካተተ ነው ተብሏል። በዚህም መሠረት ባንኮቹ ያስመዘገቡት ውጤት በተለይም በትርፋማነት፣ በሀብት ዕድገት፣ በተደራሽነት፣ ባሳዩት ውጤታማ ሥልታዊ አመራር፣ በተመዘገቡ አዳዲስ የገበያ ማስፋፋትና የፈጠራ ሥራዎች ከመሥፈርቶቹ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ምርጫው የትላልቅ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎችን፣ ታዋቂ አማካሪዎችን እንዲሁም የባንክ ባለሙያዎችንና የዘርፉ አጥኚዎችን አስተያየት ከግምት ያስገባ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የምርጫው ውጤትና የአሸናፊዎቹ ዝርዝር እ.ኤ.አ. ሜይ 2024 በግሎባል ፋይናንስ መጋዚን ላይ እንደሚወጣ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በግሎባል ፋይናንስ መጋዚን መስፈርት መሠረት አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2024ዓ.ም ባስመዘገበው ጠቅላላ ሀብትና አጠቃላይ ዓመታዊ ትርፍ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አሥር ምርጥ ባንኮች አንዱ ለመሆን የነደፈውን ቪዥን  2025  ስትራቴጂው ከተያዘለት ጊዜ በፊት ለማሳካት በመቻሉ እንደሆነም አቶ ፀሐይ ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለአሸናፊ ባንኮች የሚሰጠው ዕውቅናና ሽልማት ሥነ ሥርዓትም የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ በዋሺንግተንዲሲ እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 2024 ስብስባቸውን በሚያደርጉበት ወቅት  እንደሚከናወን ታውቋል፡፡

ግሎባል ፋይናንስ በየዓመቱ የዓለምና የየአኅጉሮችን ምርጥ ባንኮችን የሚመርጥ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ስታንዳርድ አዋሽ ባንክ የአፍሪካ ምርጥ ባንክ ተብሎ መመረጡንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውሰዋል።

ግሎባል ፋይናንስ መጋዚን እ.ኤ.አ. በ1987 ዓ.ም. የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፣ በ193 አገሮች ከ50,000 በላይ ለሆነ አንባቢያን ተደራሽ የሆነ መጋዚን ነው፡፡ የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት የሚገኘው ኒውዮርክ ከተማ ሲሆን፣ በተለያዩ ዓለማት ላይ የራሱ ቢሮዎች ያሉትና በትላልቅ የኩባንያ ኃላፊዎችና የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ተነባቢ የሆነ ታዋቂ መጋዚን ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች