Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የሥልጣን መንበር ሲረከብ፣ በርካታ ገፊ ምክንያቶችና የፖለቲካ አታጋዮች አጅበውት እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ የሕዝቡም ሆነ የፖለቲካ ተዋንያን ፍላጎትም በርካታ መሆን ብቻ ሳይሆን አንዳንዱ እሳትና ጭድ ሲባል ቆይቶ፣ ግን ተቀራርቦ መነጋገርና መደማመጥን በእጅጉ የሚፈልግ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ነገሮች በታሰበው ፍጥነትና ልክ ወደ ክብ ጠረጴዛ ባለመምጣታቸው የሚመለከታቸው የፖለቲካ ተዋንያን ምሁራንም የድርሻቸውን ከማበርከት ይልቅ፣ የለውጥ ኃይሉን ቆሞ በመታዘብ መልክ ዳር በመውጣታቸው ግን እንደቀደሙት የአገራችን ለውጦች ሁሉ ይህኛውም በበርካታ ግጭቶች፣ የፖለቲካ ውዝግቦችና የንፁኃን ዕልቂቶች ታጅቦ እነሆ ስድስተኛ ክረምቱ ላይ ተቃርቧል፡፡ ተስፋ ሰጪ የልማት ጅምሮች ቢኖሩም ፖለቲካዊ ቀውሱ እንዳጠላባቸው ናቸው፡፡

- Advertisement -

የአገራቸን ፖለቲካ ተቃርኖ የከራረመና ከመደብና ከሐሳብ ትግል ይልቅ ወደ ብሔር ጭቆናና ማታገያ ሥልት ከተሻገረ ወዲህ የሕዝቦችን አብሮ የመኖር፣ በጋራ የማደግና ተመጋግቦ የመበልፀግ ሕልም ክፉኛ ሲፈትነው ቆይቷል፡፡ ፖለቲከኞቻችንም ቢሆኑ ምንም እንኳን ለሕዝቡ ጠብ የሚልለት ነገር ባይኖርም፣ በዚሁ ስሱ አጀንዳ ላይ በመሽከርከር ከአምስት አሥርት ዓመታት በላይ አውዳሚ አካሄድን ሲከተሉና ባልተረጋጋ አገረ መንግሥት ውስጥ አገር እንድትዋልል ተፅዕኖ ሲያደርጉባት ቆይተዋል፡፡

በእንዲህ ያለው ሁኔታ መሀል ብቅ ያለው የለውጥ መንፈስ ታዲያ በአንድ በኩል የኢሕአዴግ መንግሥት ይከተለው የነበረውን እጅግ ከፋፋይ የብሔር ፖለቲካና አካታች ያልሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በመግራት፣ በሌላ በኩል ካለፈው ታሪክ ጋር ተያይዞ አገራችን የተወሰኑ ወገኖች ቤት ብቻ የምትመስልበትን ትርክት በማረም ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ብሎም እኩልነትና መተሳሰብ የሚስተዋልበት አገረ መንግሥት እንደምትገነባ ተስፋ ተጥሎ ነበር፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ በዓለ ሲመታቸው ሲከናወን  ካደረጉት ንግግርና በፍጥነት ጭምር ከወሰዷቸው ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች አንፃር፣ ሒደቱን በደስታና በአንክሮ ያልተከታተለም አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ በፈተናዎችና በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥም ቢሆን እየታለፈ፣ ነገሮች በተስፋ ወደፊትና ወደ ሌላ ምዕራፍ ከመሻገር ይልቅ በተመጣበት ጠባብ ብሔርተኝነት እንቅፋቶች እየተቸገሩ ይቆያሉ ብሎ ያሰበ ይኖራል ማለት አይቻልም፡፡

እንደ አገር የተመጣበት የተሳሳተ መንገድና እሱን ለማወራረድ ደፋ ቀና በመባሉ እንጂ፣ እውነት ለመናገር አሁን በሥራ ላይ የዋለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 88 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ያስቀመጠው ቁምነገር ብቻ፣ መንግሥት በሕዝቦች አንድነትና አብሮነት ጥበቃ ረገድ የወደቀበትን ኃላፊነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነበር፣ እንዲህ ይላል፡፡

ከዚህ  መሠረታዊ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ አንፃር በአገሪቱ በተለይ የሕዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት ያለበትን ደረጃ መፈተሽ ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ የተጣለበት መንግሥትም ቢሆን ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ማንነት፣ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ በእኩልነት መከበርና መስፋፋት ረገድ የሰጠውን ትኩረት ያህል ለሕዝቦች አብሮነት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ወንድማማችነት መስፈን ምን እየሠራ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡

እውነት ለመናገር ብልፅግና ራሱን የቻለ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲና ከዚህ ቀደም በታዳጊ ክልል ውስጥ የነበሩ አጋር የሚባሉ ፓርቲዎችን ያቀፈ ውህድ አገራዊ ተቋም መስሎ ሲመጣም ሌላ ተስፋ ጭሮ ነበር፡፡ አሁን እየታየ እንዳለው ግን ፓርቲው ክልሎችን ከማንነት አጥር ያላወጣና በውስጡ ያቀፋቸው ክልላዊ ፓርቲዎችም ስያሜ፣ ፕሮግራምና ሕገ ደንብ ላይ ባይለያዩም በየራሳቸው ማንነት ተኮር የትግል ሥልት የተቀነበቡ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

ይህም ሌላው ቀርቶ በየክልል መሪዎቹና የብልፅግና ወኪሎች አማካይነት ወጥነት የሌለውና የራስን ማንነት የማስቀደም አካሄድ ተንሰራፍቶ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን አንዱ የብልፅግና ቅርንጫፍ (ክልል) ከሌላኛው ጋር በማይስማማባቸው ትርክቶች ላይ አቋም እየያዘ መወጋገዝና ሕዝብን ማደናገር የቀን ከቀን ሥራው ሆኗል፡፡ የጎራ መደበላለቁም በቀላሉ የሚታይ አልመሰለም፡፡

እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ደግሞ በአንድ በኩል አገራዊ አንድነትና መተባበርን የሚያዳክሙ፣ በሌላ በኩል ብልፅግናስ ቢሆን ከኢሕአዴግ የማንነት ተኮር ፖለቲካ የተለየ (ያውም በመንቀሳቀስና በየአካባቢው ሠርቶ በመኖር ረገድ የቀደመው የተሻለ ሆኖ) ምን ጠቃሚ ነገር አለው የሚያስብል ሆኗል፡፡

ከዓመታት በፊት ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከየት ወዴት? (ፈተናዎችና መልካም ዕድሎች)›› በሚል ርዕስ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ተካሂዶ ነበር፡፡ በሸራተን አዲስ በተካሄደና የለውጡ መምጣት ዋዜማ ላይ በተካሄደ መድረክ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከምሁራንና የንግዱ ማኅበረሰብ የተወከሉ ግለሰቦች የመወያያ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ የዚህ መድረክ ተሳታፊዎች የተስማሙበት አንድ ጉዳይ እንደነበር በመድረኩ ስሳተፍ ተመልክቼ ነበር፡፡

ይኸውም በአገራችን እየመጣ ካለው የኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ከኅብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ጋር ተመጣጣኝነት ያለው ዴሞክራሲያዊ አንድነት አለመዳበሩን የተመለከተው ነበር፡፡ አንዳንዶች ሕገ መንግሥቱን በመጥቀስ የሕዝብ አንድነትን አያስጠብቁም ያሏቸውን አንቀጾች እስከ መጠቃቀስ ደርሰው ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለብሔረሰቦች የተለጠጠ ሥልጣንና ዕውቅና በመስጠቱ ኢትዮጵያዊ ማንነትና አንድነት ዋስትና አጥቷል ያሉም ነበሩ፡፡

በእርግጥም አሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለው የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በብሔር ለመነጣጠል ለሚነዙ ውዥንብሮች ተጋልጠዋል፡፡ ጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎችና በአቋራጭ ሥልጣን የሚሹ ወገኖች የሚያናፍሱት ዘረኝነትን የተላበሰ ቅስቀሳ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማለያየት ምቹ መሠረት ያገኘውም ከዚሁ በመነሳት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለውጡ ከጀመረ ወዲህ ቢያንስ በሦስት ክልሎች የተካሄዱት አውዳሚ ጦርነቶችና በየክልሉ ሲከሰቱ የከረሙት ማንነት ተኮር ግጭቶች የብሔር ፌዴራሊዝምን ዳፋ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ሆነዋል፡፡

ለነገሩ ትናንትም ሆነ ዛሬ የአገራችን ሕዝቦች በገዥዎችና አወናባጅ ፖለቲከኞች አለማወቅ፣ ጥቅመኝነትም ይባል ሴራ ብሎም በዘመናዊው የፖለቲካ ትውልድ ጥገኝነት እንዲለያዩ መገፋታቸው እንጂ፣ ለአብሮነትና ወንድማማችነት የቀረቡ መሆናቸው ዓለም ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድስ ቢሆን ያለፉ እንከኖችን በማረም፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ፖለቲካ እንዲያብብ በማድረግ የአገር አንድነትን ከማፅናት በላይ ምን ራዕይ በሰነቀ ነበር?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጨምሮ በርከት ያሉ የአገር መሪዎች ስለሕዝቦች አንድነትና አገር እንዳትፈርስ ተባብሮ ስለመጠበቅ ሳይናገሩ ውለው አያድሩም፡፡ በእርግጥም ታሪካችንን በጥልቀትና በሀቀኝነት ለመረመረው እንኳን ኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካውያንም አንድ የነበርን ሕዝቦች ነበርን/ነን፡፡ በአስተዳደር በደልም ሆነ በሥልጡን ፖለቲካ ዕጦት መገዳደል፣ መገፋፋትና መበዳደል መኖሩ የኖርንበትና የዓለም ታሪክ አካል ቢሆንም፣ በጋራ ቆሞ ጠላቱን እየተፋለመና አገሩን ጠብቆ በነፃነት ለትውልድ ያስተላልፉ እንደ ኢትዮጵያውያን ያለ ማንስ አለ ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡

ሎሬት ፀጋዬ ገብሬ መድኅን በአንድ ወቅት የተሰናሰለ ማንነታችንንና የማይበጠስ ትስስራችንን አስመልክተው ከከተቡት ሐሳብ ጥቂት ልውሰድ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአይሁዳዊያንና ከሮማዊያን በፊት ጀምሮ፣ ከግሪኮችና ከፈርኦኖች በፊት ከልቡ ሀቅ የሚያከብር ነው፡፡ ከልቡም ክህደትን ይጠላል፡፡ ሕዝብ በታሪክ ከጂዎች እየተጠለፈ እንጂ፣ ሁላችንም ከኩሽና ከሴም የተቀየጥን የአንድ እናት ልጆች መሆናችንና ከሰማይም አለመውረዳችንን ያውቃል፡፡ አስተዳደጋችን ግን በመቻቻል ላይ ሳይሆን በመበላለጥና በመሸናነፍ ላይ ስለተመሠረተ፣ በሃይማኖቶችና በቋንቋዎች አጥር ታግዶ፣ በባላባቶች ዝርፊያ ስለተካረረ… የዛሬዎቹም እንደ በቀደሞቹ ያለ መተማመን ጎዶሎዎች ሆነናል፡፡

‹‹ፈተናችን የሚመነጨውም ከዚሁ የመንፈስ ጎዶሎነት ነው፡፡ ሰሜነኛውም ሆነ ደቡበኛው፣ የሱማሌው ቤታ ሆነ የጋዳ ቤት፣ ክርስቲያኑ ሆነ እስላሙ፣ ምሁሩ ሆነ ማይሙ፣ ፍጹም የመሰለው ቀይ ሰውም ሆነ ኑግ የመሰለው ሻንቅላ በተለይ ትንሽ ሥልጣን በቀመሰ ማግሥት ቶሎ የመካድና በትምክህት የመወጠር አዚም ይጠናበታል፡፡ እንጂ በዘር ግንድ አመጣጡ ሁሉም የአንድ እናት ልጅ ነው፡፡

“ሰልስቱ ታላላቅ ሼኮች የምላቸው”፣ ታላቁ ሳይንቲስትና አንትሮፖሎጂስት ሼክ አንታ ዲዮጵ፣ ታላቁ ባለቅኔ ሼክስፔር (Shakespeare)፣ ታላቁ ንግርተኛ (Oraculation) ሼክ ሁሴን ጅብሪል በጥልቀት ቢያስተምሩንም እኛ ከትምክህትና ከክህደት አዚም መላቀቅና መገላገል አልቻልንም እንጂ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን፣ ኪስዋሊሃያዊንና ኤርትራውያን የአንድ እናት ልጆች ነን›› (ጦቢያ መጽሔት 1997 ዓ.ም.፡፡

ከላይ በተጠቀሰው ዓይነት የታሪክ ዕሳቤም ሆነ ከቅርቦቹ የትውልድ መጋባትና መዋለድ ብሎም መሰናሰልና መተሳሰር ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ዕጣ ፈንታችን ከብሔራዊ አንድነታችን ውጭ እንዳልሆነ ሕዝቦች አንድነትና አብሮነትን መፍራት እንዴት እንደ ነገሠብን ግራ ያጋባል፡፡ ምልዓተ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ኃይሎችና ራሱ መንግሥትስ አገር የቆመችበትን መሠረት መመርመር የተሳናቸው ለምን ይሆን ያስብላል፡፡

በመንደርደሪያው በተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ መሠረት ደግሞ መንግሥት የሕዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት የማጠናከር ግዴታ እንዳለበት ሊካድ አይችልም፡፡ በእርግጥ በኢሕአዴግ የማብቂያ ዓመታትም ይህን ተግባር ለማጎልበት እየተወሰዱ የነበሩ ጥቂት በጎ ዕርምጃዎች መኖራቸው አይካድም፡፡ በተለይ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን፣ በመከላከያ ቀን፣ በሰንደቅ ዓላማ ቀን፣ በአገራዊ የድል በዓላት የሚካሄዱ ሥነ ሥርዓቶችን… መጥቀስ ይቻላል፡፡

በማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማትና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ሕዝብን ከሕዝብ ለማስተሳሰርና አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት እየተሞከረ የነበረው ሥራም (ምንም እንኳን የፍትሐዊነትና ያልተመለሱ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች የበረከቱበት ቢሆንም)፣ ቀላል ግምት የሚሰጠው አልነበረም፡፡ ቢያንስ የሕግ የበላይነትና ጠንከር ያለ የፀጥታ ሥራ ይሠራ ስለነበር ሕዝቡ ለመንቀሳቀስም ሆነ ለመኖር ዋስትና ነበረው፡፡

እነዚህ ጥረቶች ብቻ ግን በቂ ሊሆኑ አልቻሉም ነበር፡፡ ከ2010 ዓ.ም. መጀመሪያ የፀደይ ወራት አንስቶ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መልካቸው የመብትና የፖለቲካ ጥያቄ የሚመስሉ ግጭቶች፣ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመቶች በስፋት ነበር የተከሰቱት፡፡ ዜጎች ለዘመናት በኖሩበት አካባቢ በማንነታቸው ብቻ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ለዘመናት በላባቸው ለፍተውና ጥረው ያፈሩት ሀብት ወድሞባቸዋል፣ ተዘርፈዋልም፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው ብሎ መመርመርና ዘላቂ መፍትሔ ማስገኘት ለነገ የሚባል ሥራ አልነበረም፡፡

በአገራችን ተስፋ የተጣለበትና ብዙዎችን ያማለለው ለውጥ ከመጣ በኋላም በጅግጅጋ፣ በቡራዩ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሻሸመኔና ዝዋይ፣ በሐዋሳ፣ በማይካድራ፣ ወዘተ እና መሰል የአገራችን አካባቢዎች ማንነትና የእምነት ተኮር ጥቃቶች ተፈጽመው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፡፡ ሚሊዮኖች ለድህነት ተዳርገዋል፣ ተፈናቅለዋል፡፡ እሳት የበላውና የተዘረፈው የአገርና የሕዝብ ሀብትም እንዲህ እንደ ቀላል የሚተካ አልሆነም፡፡ በድርጊቱ የአገር ገጽታ መጨለሙም የሚታወቅ ነው፡፡ (ይህን መረጃ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና ተሟጋቾች አሁን ድረስ በመረጃ አስደግፈው እያቀረቡት ነው)፡፡

ከእነዚህና አሁንም ድረስ ከሚታዩት መደፋፈጦችና መካረሮች አንፃር ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያያቸው ለዘመናት የኖሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማንነትን በመፈለግ ስም ለምን ወደ መነጣጠል ገቡ? መባል እንዳለበት መጠራጠር ግን አጉል ግብዝነት ይመስለኛል፡፡ በየአካባቢው በትልልቅ ባለሀብቶች ላይ ይቅርና በተራው ዜጋ ላይም ሳይቀር እንደ ልቡ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የሚያውክ ዘረኛ አመለካከት እንዴት ሊያቆጠቁጥ ቻለ? የሚሉ ጥያቄዎች ሊፈተሹ ካልቻሉም እውነትም አገራዊ ራዕያችን ላይ መግባባት እንዳልቻልን ያሳያል፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ከሚፈጥሩት ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ይልቅ፣ መነጣጠላቸውን የሚሹ የውጭ ጠላቶች እንዳሉም አስታዋሽ አያሻውም፡፡ በየጎራው በጠባብነት በሽታ ተሰንክለው ጥላቻና የተወናበደ ትርክት በትውልድ ላይ ካልረጩ ጥቅማቸው የሚቀርባቸውና የተጎዱ የሚመስላቸው የፖለቲካ ጥገኞችም፣ ከተጠናወታቸው ደዌ ለመፈወስ ጠንካራ መተማመንና ዕርምጃ ያስፈልጋቸዋል፡፡

እየተጓዝንበት ያለው አገራዊ መንገድ ግን ተወደደም ተጠላም አንድ ቦታ ላይ ቆመ ተብሎ በጋራ መፈተሽና ጠንካራ ዴሞክራስያዊ ምክክርን ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ቀዳሚ መፍትሔውም መንግሥት፣ ምሁራንና የፖለቲካ ኃይሎች ብሎም መላው ሕዝብ (በወኪሎቹ አማካይነት) የተደቀነውን ሴራ አደገኝነት ተገንዝበው ለመመከት እውነተኛ የፖለቲካ ምክክርና አካታች ፈለግን መከተል ሲችሉ ነው፡፡

በተለይ መንግሥት የሕዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት የማጠናከር ግዴታውን በንቃት የመወጣት ታሪካዊና ሕጋዊ ኃላፊነት ስላለበት፣ አገረ መንግሥትን ሊያድን የሚችል የዕርቅና የአንድነት መድረክና ሕዝበ ውሳኔን ስለማስቀደም ሊያስብ ግድ ይለዋል፡፡ በተለይ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ በራሱ መዋቅር ውስጥ ተወሽቀው ጠባብነትን የሚያቀነቅኑ ኃይሎችንም አንቅሮ ሊያስወግድ ካልቻለ፣ አገራዊ አንድነትና የሕዝቦች መተማመንን በቀላሉ መመለስ የሚቻል አይመስልም፡፡

ከሁሉ በላይ በስፋት ባይኬድበትም በብልፅግና ደረጃ እንደተጀማመረ በሚነገርለት የጋራ አገራዊ ትርክትና የጋራ እሴቶችን ማጉላት ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ በዕርቅና ምክክር ኮሚሽን አመቻችን ሁሉ አቀፍ ንግግርና ሰላም የማፈላለግ የዕርቅ ሥራ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና መተሳሰብ የሚያጎለብቱ ሥራዎችን መጀመርም ለነገ መባል የለበትም፡፡

ለዚህ ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የትምህርት ተቋማትና የሲቪክ ማኅበራትን የመሰሉ አካላትም የየድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፣ ያስፈልጋልም፡፡ የሕዝባችን አንድነትና ዕርቅን በመፍራት ግን፣ አገረ መንግሥትን ማፅናት የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...