Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ስካት ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና ዳይሬክተር

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን እያከበሩ ነው፡፡ በዚህ ግንኙነት ሒደት አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ባሉ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዓዊ አደጋዎች ምክንያት ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸውና ለተቸገሩ ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ከሚያቀርቡ አገሮች ቀዳሚውን ደረጃ ትይዛለች፡፡  ከ20 ዓመታት በፊት በሌላ ተመሳሳይ የሥራ ተልዕኮ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩትና አሁን የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና ዳይሬክተር ስካት ሆላንደር፣ በኢትዮጵያ እየጨመረ ያለውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያና አሜሪካ 120 ዓመታት የዘለቀ ዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን እያከበሩ ነው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት የዘለቀውን ግንኙነት በተመለከተ አጠር ያለ ማብራሪያ ቢሰጡን?

ስካት ፡- ብዙ ነገሮች ተከናውነዋል፡፡ እንግዲህ እንደምታውቁት ለ120 ዓመታት እዚህ አልነበርኩም፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ለኢትዮጵያ በመስጠት ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡ በኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት የዘለቀ ታሪክ አለኝ፡፡  እ.ኤ.አ. በ2005 ለሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራ መጥቼ በነበረበት ወቅት ነበር ኢትዮጵያን መረዳትና መገንዘብ የጀመርኩት፡፡ በወቅቱ የነበረውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት፣ የድህነቱን መጠንና የነበሩ ችግሮችን አውቅ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ የአሜሪካ ሕዝብ በሚከፍለው ግብር በኢትዮጵያ የምግብ ዕርዳታዎችን ከማቅረብ ባለፈ ለመልማት አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን አድርገናል፡፡ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ በጤናው ዘርፍ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት በማከናወን፣ የራሳቸውን ሚና ከሚጫወቱ አገሮች ቀዳሚዎቹ ውስጥ ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍም ቢሆን ፊድ ዘ ፊውቸር (Feed the Future) በተሰኘው ድርጅት አማካይነት ባለፉት አምስት ዓመታት 550 ሚሊዮን ዶላር በመበጀት፣ በሴፍቲኔት ፕሮግራም አማካይነት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ በተመሳሳይ በ500 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ የንፁህ መጠጥ ውኃና የንፅህና አጠባበቅ ሥራዎችን በገጠርና ከተማ፣ በቆላማና ደጋማ አካባቢዎች፣ በትምህርት፣ በዴሞክራሲ፣ እንዲሁም አስተዳደርን ጨምሮ ያደረግነው ድጋፍ በአጠቃላይ የሰብዓዊ ዕርዳታና የልማት ሥራችን ማሳያና ድምር ውጤት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት ብዙ ጠንካራ አጋርነት ተመዝግቧል፡፡ አሁን ግን እንደሚታወቀው በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች እያየናቸው ባሉ ግጭቶች እጅግ አሳሳቢ የሆኑ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ገጥመውናል፡፡ የድርቅና የአየር ንብረት ተፅዕኖ፣ እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የመሳሰሉ አስፈላጊ ግብዓቶች መወደዳቸው ኢትዮጵያን እየጎዱ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ተጋላጫነታቸው ከፍተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጉዳቱ አመዝኖባቸው እያየን ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎችን እያየን ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳው ከ21.4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ አሜሪካ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ነው፡፡

አሜሪካ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ለኢትዮጵያ በተደረገው የሰብዓዊ ዕርዳታ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ 153 ሚሊዮን ዶላር በመለገስ ከዓለም አገሮች ቀዳሚ ነበረች፡፡ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከሚደረግ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ 60 በመቶ የሚሆነውን ትሸፍናለች፡፡ የዚህ ዓይነቱ ተግባር ለአሜሪካ የተለመደ ባህል ነው፡፡ አሁንም ፍላጎቶች እየጨመሩ ነው፣ ያደረግነው ድጋፍ ደግሞ በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም እነዚህን የበረቱ ቀውሶች የሚጋፈጡትን በተለይም ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ የተቸገሩና ሕይወት የከበዳቸውን ዜጎች ለመድረስ ብዙ ይጠበቃል፡፡      

ሪፖርተር፡- የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ያለው የተሳትፎ ስኬት ጉዞ ምን ይመስላል?

ስካት ፡- ስለስኬት ስንናገር ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 21.4 ሚሊዮን ዜጎች ስናስብ ጉዳዩ ከባድ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በእርግጠኝነት እኔ እንደማስበው የጤናው ዘርፍ ጉልህ ስኬት ያየንበት ነው፡፡ በሕይወት የመኖር ዕድሜ ጣሪያ ወደ 69 ዓመት ከፍ ብሏል፡፡ ምንም እንኳ የወባ በሽታ ሥርጭት እንደገና እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ እንደ ሳንባ ነቀርሳና ወባ ያሉ አስከፊ በሽታዎች ላይ የተገኙ ጥሩ ውጤቶችን እያየን ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ባደረግነው ድጋፍ የመሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች ተሻሽለዋል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ውስጥ ግን የአሜሪካ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በርካታ ለጋሽ መንግሥታት ብዙ ሠርተዋል፡፡ በአገሪቱ ዙሪያ ግጭቶች ሲከሰቱ እነሱ እዚህ ያደረሷቸው የኢንቨስትመንት ትሩፋቶች አደጋ ውስጥ እየወደቁ ነው፡፡ በዚህ መጠን የሚታዩ ግጭቶችና ጦርነቶች ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የልማት ሥራዎችና ኢንቨስትመንቶች እንደ ትምህርትና የጤና ተቋማት የመሰሉ መሠረተ ልማቶች ላይ አደጋ ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሀብት ማፈላለጊያ ዝግጅት በአሜሪካ መንግሥት ይፋ ከተደረገው የ150 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ፣ ለተያዘው ዓመት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ይፋ ሊደረግ የሚችል ሌላ አዲስ ፈንድ ይኖራል? 

ስካት ፡- እንግዲህ 153 ሚሊዮን ዶላር አዲስ ገንዘብ ነው፡፡ በአገሪቱ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው 450 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ዕርዳታ እ.ኤ.አ. ከ2023 ያደረ ከለጋሽ አካላት ጋር በመሆን በተመረጡ ቦታዎች እየተሠራጨ ነው፡፡ ይህ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ትልቅ ቁጥር ነው፡፡ ይህን ቁጥር በግብርና፣ በንፁህ መጠጥ ውኃና በጤና ኢንቨስትመንት ላይ ከሚደረገው ድጋፍ ጋር ስታገናኘው በጣም ትልቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዕርዳታን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይም የፖለቲካና የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሣሪያ አድርጎ በመውሰድ የሚመጣው ገንዘብ እምብዛም ለታለመለት ዓላማ የሚውል አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

ስካት ፡- ይህንን የጥርጣሬ ስሜት በደንብ እረዳለሁ፡፡ ለረዥም ጊዜ ዕርዳታ እንዴትና ወዴት እንደማይሄድ ካላየህ ለመረዳት ከባድ ነው፡፡ ለዚህም ነው እኔም ከሠራተኞች ጋር በመሆን ዕርዳታው የሚሰጥበትን አካባቢ ታች ድረስ ወርደን የምንከታተለው፡፡ ነገር ግን ገንዘቡ ለታለመለት ዓለማ እየዋለና ለውጥ እያመጣ ነው፡፡ ባለፉት ወራት የአሜሪካ መንግሥት ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ረድቷል፡፡ ይህንንም በሁለት ጊዜ የመስክ ጉዞ መመልከትና መረዳት ችያለሁ፡፡ አፋር ተገኝቼ በተንቀሳቃሽ ክሊኒክ ሕፃናት ክትባት ሲያገኙ፣ በተለይም የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሕፃናት ጤናቸው እንዲያገግም ሕክምና ሲደረግላቸው አይቻለሁ፡፡ ከዚያ በፊትም በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሞ አካባቢ ተገኝቼ የብዝኃ ሕይወትን በመደገፍ ረገድ የአሜሪካ መንግሥት ያደረገው ሥራ፣ በተጨማሪም በትምህርት ዘርፍ የተደረገው ድጋፍ በጣም ግዙፍ የሚባል ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ጥርጣሬዎችን ለማስወገድ በሚዲያ መረጃዎችን እንሰጣለን፡፡ ግልጽነት በመፈጠሩ ተገቢ የሆነውን መረጃ ማስተላለፍ አለብን አምናለሁ፡፡ የተጀመሩ ሥራዎችን በተለይም በሁሉም ዘርፎች የታዩ ለውጦችን ለማሳየት የበለጠ ልንሠራ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ሰብዓዊ ዕርዳታ ተጋላጭ ዜጎችን በምን ዓይነት ዘዴ ይለያቸዋል?

ስካት ፡- የምንችለውን ያህል በመረጃ ለመመራት እንሞክራለን፡፡ ነገር ግን ይህ የነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የአሜሪካ መንግሥት በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ለብዙ ዓመታት ኢንቨስት አድርጓል፡፡ ይህ በመረጃ የተደገፈ አመላካች ደግሞ ፍላጎት የቱ እንደሚበልጥ ይነግረናል፡፡ እኛም በዚህ ላይ ተመሥርተን የትና እንዴት መወሰን እንዳለብን እናውቃለን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የምግብ ዋስትና ኃላፊነት መንግሥት ላይ የሚወድቅ በመሆኑ ሥራውን ከመንግሥት፣ ከተራድኦ ድርጅቶች፣ ከተመድና ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ማን ምን ማግኘት እንዳለበትና የቱ ጋ መድረስ እንዳለብን እንወስናለን፡፡ ስለዚህ ለአሠራሩ እኛ አለን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አለ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አለ፣ በእነዚህ ሁሉ በትትብርና ምክክር ይሠራል ማለት ነው፡፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ሥራ በመላ አገሪቱ ዋነኛ የሥርጭት መርሁ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ብዙዎቹ ሥራዎቻችን በግጭቶች ምክንያት ተስተጓጉለዋል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ለመሥራት እጅግ ፈታኝ እየሆነብን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያደርሱ አካላት እየገጠማቸው ያለውንና እየታየ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ነው፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ አስፈጻሚዎቻችን ፅናትና ድፍረት የተሞላበት ተግባር፣ ዕርዳታ የሚፈልጉ ወገኖች በተገቢው ጊዜ ዕርዳታው እንዲደርሳቸው የሚወስዷቸው ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች ለሙያቸው ያላቸውን ቆራጥ ውሳኔ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች መፍትሔው ሊመጣ የሚችለው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአማራ ክልል ግጭት ከተከሰተ በኋላ በሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ላይ ምን ዓይነት ጉዳትና አደጋ ደርሷል?

ስካት ፡- በአጠቃላይ ከሰማሁት የቅርብ መረጃ እስካሁን አሥር ሠራተኞች ሕይወታቸውን እንዳጡ ነው፡፡ ከአጋሮቻችን የምንሰማው ደኅንነቱ ያልተጠበቀ አካባቢ፣ ለመገመት የሚያዳግት የሰላም ሁኔታ፣ ነገሮች በቅጽበት የሚቀያየሩበትና በነገሮች በፍጥነት መቀያየር ውስጥ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ሕይወት አደጋ ውስጥ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለሰብዓዊ ዕርዳታ ጥያቄ ምላሽ አሰጣጡ ጠንካራና የተጠናከረ መረጃ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ጥራት ያለው መረጃ ላይ ተመሥርታችሁ ነው የምትሠሩት?

ስካት ፡- እኔ በሥራዬ በማገኘው መረጃ ረክቼ አላውቅም፡፡ በዚህ ረገድ ጠንካራ መረጃ ለማግኘት ቀጣይነት ያለው ፈታኝ የሥራ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች መረጃ ማግኘት ግጭት ከሌለባቸው አካባቢዎች የበለጠ ከባድ ነው፡፡ ይህ ሁላችንም በአንድ ላይ በመሥራት ልናስተካክለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሌም ምኞቴ የተመጣጠነ ምግብ የሚያስፈልጋቸው፣ ሁኔታዎች በየጊዜው የሚቀያየሩባቸውና አስገዳጅ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን አካባቢዎች ለመድረስ የሚያስችል ጠንካራ መረጃ ማግኘት መቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከክልል ቢሮዎችና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የተጠናከረና የተሰናዳ መረጃ በመያዝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር እየሠራን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ከ21 ሚሊዮን በላይ ወይም ከሃያ በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ዕርዳታ ጠባቂ ነው ማለት ነው? በዚህ ረገድ የመንግሥት ዝግጁነት እንዴት ይታያል?

ስካት ፡- እንግዲህ 21.4 ሚሊዮን ሕዝብ በጣም ብዙ ነው፣ ለመርዳትም ይከብዳል፡፡ ከወራት በፊት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ረዳት አስተዳደር ሶናሊ ኮርዴ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፣ አፋርና ትግራይን በጎበኙበት ወቅት አብሮ የመጓዝ ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ያየነው ችግር ከአቅም በላይ ነው፡፡ በዚህ ሙያ በቆየሁባቸው ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን ሠርቻለሁ፡፡ ነገር ግን ከባዱ ነገር ልጅን መመገብ ባለመቻሏ የምትሰቃይ እናትን ማየት ነው፡፡ ከጭንቅላትህ የሚወጣ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ የምነግርህ ነገር ይህችን እናት መርዳት መቻል፣ ያ የተቸገረን ቤተሰብ መርዳት መቻል፣ ማኅበረሰቡን መርዳት መቻል፣ ቢያንስ የሚያስፈልጋቸውን የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ መቻል፣ የሚያስፈልጋቸውን ንፁህ ውኃ ማቅረብ መቻል፣ በከፍተኛ ሁኔታ አስፈላጊ ነው፡፡ እኔ እንደማስበው በጋራ ለመቅረፍ መሞከር ያሉብን በርካታ ፈተናዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ባለሥልጣናት በአገር ውስጥ የተመረተው ስንዴ ከሚፈለገው መጠን በላይ ነው ይላሉ፡፡ በተቃራኒው የዕርዳታ ጠባቂዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው ይባላል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች እንዴት ይገለጻሉ? ድርጅታችሁ ከኢትዮጵያ መንግሥት ስንዴ ገዝቶ ያውቃል?

ስካት ፡- አንዳንዴ የዕርዳታ ፕሮግራሞች የአገር ውስጥ ግዥን ያካትታሉ፡፡ እኔ እስከማውቀው የዓለም ምግብ ድርጅት የአገር ውስጥ ግዥ ይፈጽማል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ብንነጋገር ሊሰጡ ከሚችሉት አንድ ምክንያት፣ የምግብ አቅርቦትን ለማንቀሳቀስ ሎጂስቲክስ ፈታኝ ሁኔታ ስለመሆኑ ነው፡፡ ይህ አንዱ ትልቅ መሰናክል ነው፡፡ ነገር ግን መረጃ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ የቅርብ መረጃ ማግኘት መቻልና ባለው ጉዳይ ላይ መግባባት በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ወደ አማራ ክልል የተላከው የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና አጠቃላይ የግብርና ሥራ ግብዓቶች ከዚህ በፊት እንደታቀደው አለመሆናቸውን እናውቃለን፡፡ ሰላም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ይፈታል፡፡ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና መሰል ግብዓቶችን ለማድረስ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር አለበት፣ ይህ ካልሆነ መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ የሚያልሙት ግብ ላይ መድረስ አይችሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ሰብዓዊ ዕርዳታና የልማት ሥራ የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ነገር ግን የዕርዳታ ሥራ ቀጣይ ሆኖ ወደ ኢንቨስትመንት ካላሸጋገረ፣ እነዚህ የኅረተሰብ ክፍሎች የዕርዳታ ጥገኛ ሆነው የሚቀጥሉት እስከ መቼ ነው?

ስካት ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እኛ የምናቀርበው የልማትና የሰብዓዊ ዕርዳታ ብልህ እንዲሆኑና ዕርዳታን ከማቅረብ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሔዎችን ማምጣት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የምግብ ዕርዳታ በራሱ ሰዎች ከዕርዳታ እንዲወጡ የሚጠቅም ነገር አይደለም፡፡ የተሻለ ዕድልን መፍጠር፣ ገበያ ማግኘት፣ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ መቻል፣ የተሻለ የጤናና የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ማግኘት የዚህ ሁሉ አካል መሆን አለባቸው፡፡ የልማቱ ማሳያ የሰዎችን ሕይወት ሲቀይር ማየት መሆን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ዩኤስኤአይዲን ጨምሮ ሁሉም የልማትና የተራድኦ ድርጅቶች የተረዱት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ረገድ በጣም አስፈላጊ በሆኑ ዘርፎች ለመሥራት አቀራረባችን በተሻለ መንገድ በማዋሀድ ላይ ነን፡፡ ለምሳሌ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙሰጠፌ መሐመድ ሁሉንም ድርጅቶች በአንድ ጊዜ በማሰባሰብ፣ ተጠቃሚዎችን በሚረዳ መንገድ እርስ በርስ መደጋገፍ እንዲኖር የሚያደርግ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡ በአጠቃላይ የመጨረሻውንና የሚፈለገውን ዕድገት ለማምጣት ሰላም መፍጠር በየትኛውም ዓለም ያለ እውነታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ዕርዳታ ለሚሹ ዜጎች የሚቀርበው ዕርዳታ ተዘርፏል መባሉን ተከትሎ፣ ዩኤስኤአይዲን ጨምሮ የዓለም የምግብ ድርጅትና ሌሎችም በጋራ የሚያደርጉትን ሥርጭት ለወራት አቁመው እንደነበር ይታወሳል፡፡ የተጠያቂነቱ ሥራ ተከናወነ ወይ?

ስካት ፡- ጉዳዩ ለዩኤስኤአይዲ ዋና ኦዲተር ተልኳል፡፡ ይህን በተመለከተ ለሚፈለገው መረጃ ሁሉ እነሱን በየትኛውም ጊዜ ማናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ምርመራው እንደቀጠለ ነው፡፡ ወደኋላ ልመልስህና የተፈጠረው ዕርዳታ በጊዜያዊነት የማገድ ውሳኔ ላይ መድረሳችን የሚያሳዝን ነበር፡፡ በተለይ ከእነዚህ ዕርዳታ ፈላጊ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመደበኛነት ለሚሠሩ ባለሙያዎች ይህ ውሳኔ አሳዛኝ ቢሆንም፣ በተከሰተው ችግር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የነበረውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ስርቆት ማገድ የግድ ነበር፡፡ ማኅበረሰቡን በአመጋገብ ሥርዓቱ፣ በትራንስፖርት መስመሮችና በተለያዩ መንገዶች ስንመለከት ከፍተኛ የሆነ የዕርዳታ አቅርቦት ይደርሳል ብለን የምናስበው ቦታ አለመድረሱን ተገነዘብን፣ የእኛ ሥራ ዕርዳታውን ለሚፈልጉት ሰዎች መድረሱን ማረጋገጥ ነው፡፡ እሱን ስናረጋግጥ ግን ውሳኔው ግድ ነበር፡፡ የአሜሪካ ግብር ከፋይ ሕዝብም የሚጠብቀው ይኼን ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስተት አጋጥሞ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ዕርዳታውን ለጊዜውም ቢሆን ማስቆም ነበረብን፡፡ የችግሩ ምንጭ የት እንደሆነ መረዳት ነበረብን፡፡ በተጨማሪም እኛ የምንሰጠው ድጋፍ የተሻሉ ዘዴዎች ላይ ተመርኩዞ መጀመርና ማካተት፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭቱ በትክክለኛ ቦታው መዋሉን ለማረጋገጥ ይረዳናል፡፡ እነዚህን ወሳኝ ለውጦች ከዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተቀራርበን አድርገናል፡፡

ይሁን እንጂ የምግብ ዕርዳታው በጊዜው ቢቆምም የተመጣጠነ አመጋገብ ፕሮግራም አላቆመም ነበር፡፡ በዚህ ረገድ እ.ኤ.አ. በ2023 ብቻ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ በተለይም ከፍተኛና መካከለኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላለባቸው ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ድጋፍ አድርገናል፡፡ በአጠቃላይ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ረገድ ግን ውይይቶች ተደርገው ጉልህ የሚባሉ ለውጦች ካደረግን በኋላ የሎጂስቲክስ፣ የትራንስፖርትና የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት ኃላፊነቶች ወደ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ተዋንያን እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ ይህ ውሳኔ በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ጉዳይ ነበር፡፡ የረድኤት ድርጅቶች ወደፊት እንዲመጡና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው፣ የተረጂዎችን ዝርዝር እንዴት እናዘጋጃለንና እንዴት አድርገን እንለያለን የሚለው ስምምነት መፈጠሩ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት አዲስና በተጋላጭነት ላይ የተመሠረተ የተረጂዎች ልየታ አሠራር ሥርዓትን ከሌሎች ገጽታዎች ጋር በማጣመር የተሠራው ሥራ፣ አጋሮቻችን እስከ ቤተሰብ ድረስ ወርደው ድጋፍ የሚፈልገውን አካል ለመለየት ይረዳቸዋል፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ብዙ የፈጠራ ውጤቶች አሏቸው፡፡ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በጠቋሚ መሣሪያ ዕርዳታው የሚፈለገው ቦታ መሄዱን እናረጋግጣለን፡፡ በዚህም መተማመን ተፈጥሮ ነው እ.ኤ.አ. በታኅሳስ 2023 ዕርዳታውን እንደገና መጀመር የተቻለው፡፡  

ሪፖርተር፡- ዕርዳታውን እንደገና ለመጀመር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ምን ዓይነት ስምምነት አደረጋችሁ?

ስካት ፡- በአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል ከመንግሥት ጋር መደራደር በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ገና መከናወን ያለባቸው ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ አሁንም እነዚህ ለውጦች በሕግ እንዲቀመጡ እንፈልጋለን፡፡ በዚያ ልክ ነው የመንግሥት ሚና እንዲሆን የምንፈልገው፡፡ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት መርሆዎች እንዲከበሩና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ነፃነት በማክበር በተጋላጭነት ላይ የተመሠረተና ለችግር የተጠቁ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ መሥራት አለበት፡፡ ይህ የሚወሰነው በየደረጃው ካሉ የፌደራል፣ የክልል፣ የወረዳና የማኅበረሰብ መስተጋብርን መሠረት በማድረግ ሲሆን፣ እነዚህን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የሚፈጽሙ ባለሙያዎች ደኅንነት ማረጋገጥን ያካትታል፡፡ በዚህ አዲስ አሠራር የተነሳ ከዚህ ቀደም የሚገባቸውን ሙሉ ድርሻቸውን አግኝተው የማያውቁ ተረጂዎች በአዲሱ የመረጃ አመላካችና ጠቋሚ አማካይነት፣ ተጠቃሚዎች እንዴትና ለምን እንደሚመርጡ በትክክል ምን ማግኘት እንዳለባቸው የተጣራ መረጃ አግኝተናል፡፡ በዚህ ጊዜ በተለይም ቁጥሩ እየሰፋ በመሄዱ በትክክለኛው መረጃ ዕርዳታ ማግኘት የሚያስፈልጋቸውን ሲያገኙ እያየን ነው፡፡ ከዕርዳታ ጠባቂው ሕዝብ አንፃር በእጃችን ያለው ሀብት ከፈላጊው ሕዝብ በጣም ያነሰ በመሆኑ፣ ይህንን ለማሻሻል ከመቼውም ጊዜ በላይ በበለጠ የተሻለ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ እኔ ያየሁት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተልዕኳቸው ተዓማኒና ቁርጠኛ የሆኑ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የሠራተኞች ስብስብ መኖራቸውን ነው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ናቸው የማኅበረሰቡን ሥቃይ እየተመለከቱ ያሉት፡፡ በዚህ ረገድ ያሉ የሳይንስ ፈጠራዎችን ሥራ ላይ ለማዋል ከማይታክቱ የዩኤስኤአይዲ ሠራተኞች በላይ ማንም የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ተፈጸመ የተባለው ስርቆት ላይ የተጀመረው ምርመራ ምን ደረጃ ላይ ነው?

ስካት ፡- በስርቆት የተሰማሩ አካላት አሁንም ተጠያቂ እንዲሆኑ መግፋታችንን እንቀጥላለን፡፡ ነገር ግን የምርመራ ሥራው ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ዋና ኦዲተር በጉዳዩ ላይ እየሠራ ነው፡፡ ጊዜ እንደሚወስድ ይጠበቃል፡፡ ያም ሆኖ በኢትዮጵያ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልል ባሉ አካላት የምርመራ ሥራው ተጠናቆ ውጤቱ እስኪታወቅ መግፋታችንን አናቆምም፡፡

ሪፖርተር፡- ከአማራና አሮሚያ ክልሎች ውጪ ለመንቀሳቀስ አደገኛ የምትሏቸው ቦታዎች አሉ?

ስካት ፡- በሚያሳዝን ሁኔታ አማራና ኦሮሚያ ብቻ ሳይሆኑ የድንበር አካባቢዎች፣ በተለይም የቤንሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎች አካባቢዎች በፀጥታ ዕጦት የተሞሉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ድንበር አካባቢ የነበረው ሁኔታ የማይገመትና አደገኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህንን ምናልባት ራስህም ታውቀዋለህ፡፡ ከአዲስ አበባ ለመውጣት እንኳን በጣም ከባድ ሆኗል፡፡ ለሁሉም አጋሮቻችን በሚታየው የዕገታ ችግርና የግጭት ክስተት ከሌሎች አስተማማኝ ካልሆኑ የደኅንነት ሁኔታዎችና አደጋ ላይ ከሚጥሉ ጉዳዮች ጋር ተደማምሮ ዕርዳታ ማድረሱን የበለጠ ከባድ ያደርገዋል፡፡ አጋሮቻችን የደኅንነት ባለሙያዎችን በመያዝ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ ሁልጊዜ ይሠሩበት ከነበረው ይልቅ የደኅንነት ባለሙያዎችን እያመጡ የተለመደውን አሠራራቸውን እየቀየሩ ነው። ይህ የፀጥታ ችግር ደግሞ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡ ተፅዕኖው ደግሞ ሕንፃዎችንና መሠረተ ልማቶችን ማፍረስ ብቻ አይደለም፡፡ በዋና ዋና ከተሞች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የፀጥታው ሁኔታ ስለማይታወቅ መውጣት አይችሉም። የዚህ ተፅዕኖ ለዩኤስኤአይዲ ሥራ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሰብዓዊ ዕርዳታና የልማት ሥራ የሚሠሩ አገልግሎቶት ሰጪዎች ጭምር ነው፡፡ በአዕምሮ ጤና ረገድም በዚህች አገር ውስጥ ብዙ ሰዎች አሰቃቂ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ዕርዳታውን የሚያደርሱትም ሆነ ሕዝቡ ማለቴ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እኛ ለመሥራት እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡-  በስዊዘርላንድ ጀኔቫ ለኢትዮጵያ በተዘጋጀው የፈንድ ማሰባሰቢያ መድረክ የተለያዩ አገሮች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎችና የቪዛ አሠራር ጉዳዮች ላይ ማነቆዎችን እየፈጠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው እንዲስተካከል አሳስበው ነበር፡፡ የረድዔት ድርጅቶች የገጠማቸው ችግር ምንድነው?

ስካት ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ከረድዔት ድርጅቶች አጋሮቻችንና ከመንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራን ነበር፡፡ በተለይም የረድዔት ድርጅቶች ባለሙዎች በትክክለኛው ጊዜ አስፈላጊውን መሣሪያ ይዘው ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ለማረጋገጥ የሚሉትንና መሰል ጉዳዮች በተመለከተ፣ በቀጣይ ውይይቶች የሚፈልጉና እንደ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድርጅት መከታተል የምንፈልጋቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሰብዓዊ ሠራተኞች ቪዛ መሰጠቱን በማረጋገጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ሌላኛው ቁልፍ ጉዳይ የደኅንነት ጉዳይ ሲሆን፣ ለዚህም ከመከላከያ ጋር ግንኙነት በማድረግ ሰብዓዊ ዕርዳታ በኮንቮይ ታጅቦ እንዲሄድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ያለማቋረጥ እየሠራንበት ያለነው ጉዳይ ነው፡፡ እናም እኔ እንደማስበው ይህ ግጭት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ሪፖርተር፡- የቪዛ ጉዳይ  አሁንም እንቅፋት ሆኖባችኋል ማለት ነው?

ስካት ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው የቪዛው ወቅታዊነት፣ ሲፈቀድም እንኳን አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ቪዛ ለመውሰድ ከሚጠብቀው በላይ ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ሁለተኛው የሒደቱ ግልጽነት ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ለምንና ማንን እንደሚጠይቁ አይታወቅም፡፡. ቪዛ ለማራዘም ወይም ለእድሳት ማንን መጠየቅ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ በአጠቃላይ አጋሮች እየገጠማቸው ያለው የአሠራር ግልጽነትና ግልጽ የሆነ የጊዜ ገደብ መኖሩን አለማወቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግጭቱ ቢቀጥልም የአሜሪካ መንግሥት ሰብዓዊ ዕርዳታ እያደረገ ነው፡፡ ግጭቱ ግን ማለቂያ የሌለው ቢመስልም። የዕርዳታ አቅርቦት የሚያስተጓጉሉ ግጭቶችና መሰል ጉዳዮች በተከሰቱ ቁጥር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕርዳታ ከማድረግ ባለፈ ምን ማለት ይፈልጋሉ?

ስካት ፡- እኔ እንደማስበው ከሁሉም በፊት ሰላም ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከሁሉም የበለጠ ቀጥተኛና የመጀመሪያው ዕርምጃ ሁሉም ወገኖች አንድ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው ችግሩን መፍታት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪንግ ማሲንጋ በብዙ አጋጣሚዎች የሰጡትን መግለጫ ስታይ በጣም ቁርጠኛ መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው፡፡ ከባድ ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን እኛ ማከናወን ያለብን ሥራችንን ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ከአሁን በኋላ ዕርዳታ የማይፈልግበት፣ የልማት ኢንቨስትመንቶቻችንና ተግባሮቻችን ትልቅ ተፅዕኖ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሰብዓዊ ዕርዳታን ቁጥር ለመቀነስ የሚያስችል መንገድ ማመቻቸት የእኛ ሥራ መሆን አለበት፡፡ የተለያዩ ቡድኖች ተቀምጠው በልዩነቶቻቸው ላይ በመነጋገር ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጡ የሚችሉበትን መፍትሔ ማምጣት ይችላሉ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...