Wednesday, June 19, 2024

የአሜሪካው አምባሳደር የፖሊሲ ንግግርና የመንግሥት ቁጣ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያና የአሜሪካ የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ክብረ በዓል እየተዘከረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ባለፈው ሳምንት የመንግሥታቸውን የሰብዓዊ መብት ፖሊሲ ዋና ዋና ጉዳዮችና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ የፖሊሲ ንግግር አድርገው ነበር።

አምባሳደሩ የአሜሪካ ግቢ ተብሎ በሚታወቀው የቀድሞው የአሜሪካ ሌጋሲዮን ቅጥር ግቢ ውስጥ ባደረጉት ንግግር፣ እ.ኤ.አ. በ1937 በአዲስ አበባ የተፈጸመውንና በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የተጨፈጨፉበትን የየካቲት 12 አሳዛኝ ዕልቂት አስታውሰዋል። በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በአሜሪካ ግቢ ውስጥ በማስጠለል ኢትዮጵያውያንን ከሞት ያተረፉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ የነበሩትን ኮርኔሊየስ ቫን ኤገርት በማስታወስ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር ያደረጉትን ቁርጠኝነት የተሞላበት ድርጊት በማድነቅም ምሥጋና ቸረዋቸዋል።

አምባሳደሩ ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር የየካቲት 12 ዕልቂትን ከዛሬው የኢትዮጵያ ተግዳሮቶች ጋር በማመሳሰል፣ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወጥታ ሰላም በመላ አገሪቱ እንድታሰፍን ይበጃል ያሉትን ሐሳብ አቅርበዋል።

ከየካቲት 12 ዕልቂት ጋር ያነፃፀሩት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ 

አሜሪካን ግቢ ተብሎ የሚታወቀው የቀድሞው የአሜሪካ ሌጋሲዮን ሕንፃ ከአሜሪካ ጋር ካለው ትስስር በላይ፣ በኢትዮጵያ የገዘፈ ታሪክ ያለውና ትልቅ ጠቀሜታ የነበረው ነው። ከሕንፃው መግቢያ በሮች ፊት ለፊት እ.ኤ.አ. በ1937 ማለትም ከዛሬ 87 ዓመታት በፊት ሽብር መፈጸሙን አስታውሰዋል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ የየካቲት 12 ዕልቂት ተብሎ በሚጠራው በዚህ አሳዛኝ ድርጊት፣ የጣሊያን ፋሽስቶች ወደ 20,000 (ከ30,000 በላይ የሚሉ አሉ) የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን ለሦስት አስፈሪ ቀናት እንደጨፈጨፉም ተናግረዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይቀርብባቸውና ሕግን ባልተከተለ መንገድ ዒላማ መደረጋቸውን፣ በዚያን ጊዜ በአዲስ አበባ የነበሩት የአሜሪካ ኤምባሲ (ቆንስላ) ጉዳይ አስፈጻሚ ኮርኔሊየስ ቫን ኤገርት በድፍረት ከእነዚህ የአሜሪካ የግቢ ግንቦች ጀርባ ሰባት መቶ ሃምሳ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን በማስጠለል ከሞት ማትረፋቸውንም ጠቅሰዋል። ዲፕሎማቱ ኤገርት በፈጸሙት በዚህ ድርጊት ኩራትና አድናቆት እንደሚሰማቸው፣ እሳቸውም የቀድሞውን የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚ ፈለግ በመከተል ለሰዎች በሕይወት የመኖርና የመከበር መብት እንዲሁም በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብቶችን መከበር እንደሚያስቀጥሉ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

‹‹በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በመላው ኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች ከ87 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸው ፍርኃት ዛሬ ገጥሟቸዋል፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ‹‹ሽፍቶች፣ ታጣቂ ቡድኖችና አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እነዚህን በሕይወት የመኖር፣ እንደ ሰው የመከበርና ሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥሰት ሲፈጽሙ ምንም የሕግ ቅጣት አይገጥማቸውም፡፡ ይህም የሕግ የበላይነት እንደሌለና እንደማይከበር ማሳያ ነው፤›› ብለዋል።

የቫን ኤገርትን ድፍረትና የሞራል ታማኝነት በማሰብ፣ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ታጣቂዎችና ፖለቲከኞች ኢትዮጵያውያን የተጨፈጨፉበትን የየካቲት 12 ዕልቂት በማስታወስ ትምህርት እንዲወስዱም አሳስበዋል።

በጦርነትም ሆነ በግጭት ጊዜም ቢሆን የሰዎች ሰብዓዊ ክብርና ሁሉም ዓይነት ሰብዓዊ መብቶች ብሔርን፣ ሃይማኖትንና ቋንቋን መሠረት ሳያደርጉ መጠበቅ ለአፍታም ቢሆን የሚዘነጋ ጉዳይ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም የበለጠ ጥንቃቄና ጥበቃ የሚደረገው በእንዲህ ዓይነት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹ከ87 ዓመታት በፊት በሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የመጨረሻውን ዋጋ የከፈሉበት ምክንያት ሰብዓዊነታቸው ስላልተከበረና ዋጋ ስላልተሰጠው ነው። ኢትዮጵያውያን ይህንን ከእኔ የበለጠ ያውቃሉ። አሜሪካውያን ይህንን ያውቃሉ። ዓለምም ይህን ያውቃል፤›› ብለዋል።

‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ የውስጥ ሽኩቻ ገጥሟታል። ሁሉም አገር ራሱን የመከላከል ሕጋዊ መብት እንዳለው ቢታወቅም፣ አንድ አገር ራሱን የሚከላከልበት መንገድ ደግሞ የአገሪቱን (የመንግሥትን) ባህሪ የሚገልጽና የወደፊት ግጭቶችንና በተለይም የዛሬውንና የወደፊቱን የማኅበራዊ ትስስርን እንደሚበይን ጥርጥር የለውም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የታጠቁ ኃይሎች የፖለቲካ ዓላማቸውን በውይይት ሳይሆን በሁከት ለማሳካት የሚቀጥሉ ከሆነ ንፁኃን ሰዎች የሚጠቁበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ እንደማይቀር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የታጠቁ ኃይሎች የፖለቲካ ዓላማቸውን በአመፅ ለማሳካት ሲሞክሩና መንግሥት እነዚህን ጥረቶች በኃይል ለመቀልበስ ዕርምጃ ሲወስድ በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ የማይካድ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

‹‹አገሬ አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ልምድ አላት፤›› ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ፣ በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት እንዲሁም በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ መንግስት ሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅና መንግሥትን የመከላከል አስፈላጊነትን የማመጣጠን ፈተና አጋጥመውት እንደነበር ተናግረዋል።

‹‹እናም ይህን ልምድ ይዘን፣ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ሰላማዊ ዜጎች ከሕግ ውጪ ግድያ ሲፈጸምባቸው፣ የዘፈቀደ እስራት፣ አስገድዶ መሰወር፣ ከግጭት ጋር የተያያዘ ፆታዊ ጥቃትና ሌሎች በደሎች በተለያዩ ተዋንያን እንደደረሱባቸው የሚገልጹ ሪፖርቶችን ስንመልከት በእጅጉ አዝነናል፤›› ብለዋል።

ስለዚህ እነዚህን የተፈጸሙ በደሎች በአስቸኳይና ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መንገድ እውነተኛና ግልጽ የሆነ የሽግግር ፍትሕ ሒደትን የመሰሉ ሥልቶችን በመተግበር ዕልባት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመሆኑም፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን የማስተዳድር ኃላፊነት የጨበጠው መንግሥት ለኢትዮጵያ ሰላምና እርቅ እውነተኛ ጥረት እንዲደርጉ አምባሳደሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። 

አምባሳደሩ ጥሪያቸውን በይፋ ከማቅረባቸው በፊትም፣ ‹‹ጥሪዬን ሳቀርብ ቀጥተኛ መሆን እፈልጋለሁ፤›› በማለት ይመለከታቸዋል ያሏቸውን አካላት በስም በመጥራት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአምባሳደሩ ቀጥተኛ ጥሪ 

አምባሳደር ማሲንጋ በቅድሚያ ጥሪያቸውን ያቀረቡት በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ሲሆን፣ በልዩ ሁኔታ ይመለከተዋል ያሉትን አካል በስም በመጥራትም የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።

‹‹በኦሮሚያ ላሉ ኃይሎች በተለይም ለኦሮሞ ነፃነት ጦር (ኦነግ ሸኔ)። በዳሬሰላም (በታንዛኒያ) ባደረጋችሁት ድርድር የመፍትሔ ስምምነት ላይ ለመድረስ ልባዊ ጥረት አድርጋችኋል፣ እናም አትሸነፉ። አሁንም ቢሆን መተማመንን መልሶ ለመገንባትና ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያገኘውን ሰላም ለማምጣት ጥረታችሁን ቀጥሉ። ምክንያቱም ጦርነቱ በመቀጠሉ ምክንያት ብዙ ሰዎች እየተሰቃዩ ነው፤›› ብለዋል።

በመቀጠልም በአማራ ክልል ለሚታገሉ ኃይሎች መልዕክት ያስተላለፉት አምባሳደሩ፣ በዚህም የአማራ ፋኖን በስም ጠቅሰው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

‹‹በአማራ ክልል ለሚታገሉ፣ በተለይም ራሳችሁን ፋኖ በማለት የምትጠሩ ኃይሎች እባካችሁ ውይይትን ተቀበሉ። ውይይትን አለመቀበል የሚጠቅማችሁ እንዳልሆነ ዕወቁ። እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉ በአማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት ምክንያት እየተሰቃዩ ያሉት ንፁኃን ዜጎች ናቸው። ብዙ የአማራ ህዝብ እናንተ የያዛችሁትን ጉዳይ ፍትሐዊ ነው ብሎ አጥብቆ ያምናል። ይህ ከሆነ እነዚያን ክርክሮች በኃይልና በሁከት ሳይሆን ለውይይት ማቅረብ አለባችሁ፤›› ብለዋል።

በሦስተኛ ደረጃ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በትግራይ ክልል ለሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ሲሆን፣ በዚህም ሕወሓትን በስም ጠቅሰው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

‹‹በትግራይ ለምትገኙና ለሕወሓት። ከግጭት ማቆም ስምምነቱ በኋላ ያልተመለሱ ጉዳዮችን ወይም ችግሮችን ለመፍታት ለምሳሌ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ጉዳይ ግዛትን በኃይል ለማስመለስ መሆን የለበትም። ይልቁንም ሁሉንም ያሳተፈ፣ ሥርዓት ያለውና የተከበረ ሒደት እንድትከተሉ አሳስባለሁ። እናንተ በብሔራዊ ውይይቶችና በሽግግር የፍትሕ ሒደቶች ላይ የሚኖራችሁ ሙሉ ተሳትፎ ለትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን እንድትገነዘቡ አሳስባለሁ፤›› ብለዋል።

በስተመጨረሻ ቀጥተኛ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ለመንግሥት ሲሆን፣ መልዕክታቸውንም እንደሚከተለው አቅርበዋል።

‹‹ኢትዮጵያን በማስተዳደር ኃላፊነት ላይ ለምትገኙ። አገሪቱ ከጦርነት አውድማ ይልቅ በሰላም የምታተርፈው ብዙ ነገር አለ። በፀጥታ (በኃይል) ላይ ያተኮረ አካሄድ ውስብስብ የፖለቲካ ጉዳዮችን አይፈታም። መንግሥትን የሚተቹ ሰዎችን ማሰርና ማዋከብ መፍትሔ ሊሆኑ አይችሉም። በመሆኑም ቁልፍ የፖለቲካ ሰዎችን በመፍታት ኢትዮጵያውያን አጥብቀው የሚፈልጉትን አገር አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ማገዝ ይቻላል፤›› ብለዋል።

አገር አቀፍ የተኩስ አቁም ጥሪ 

ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች በመላ አገሪቱ የሚስተዋሉ አዳዲስ የሕዝብ መፈናቀልን ጨምሮ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ በማነሳሳት ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፣ ይህ ድርጊት እንዲቆም አሳስበዋል።

‹‹ይህ መቆም አለበት። ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትንና የውኃ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረግ እንዲቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ። የተሟላና ያልተገደበ የሰብዓዊ አገልግሎት በሁሉም አካባቢ መቅረብ አለበት፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት መነሻ እንዲሆን ጥሪዬ በአገር አቀፍ ደረጃ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም መፍጠርን ያካትታል፤›› ብለዋል።

አንድን ግብ ለማሳካት ተስፋ በማድረግ ግጭትን ማስቀጠል በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የበለጠ ጉዳትና ሥቃይ ማስከተል እንጂ ሌላ ምንም ዓይነት ውጤት እንደማይኖረው አምባሳደሩ ባደረጉት ንግግር አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል። 

‹‹አሁንም ልድገመው፣ በኢትዮጵያ የትኛውም ወገን በጦር ሜዳ የሚያገኘው ድል አይኖርም፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ‹‹ለዚህም ነው የውይይት ጊዜው አሁን ነው የምለው፤›› ብለዋል። 

ምንም እንኳን መንግሥት ለማካሄድ ያቀደው አገር አቀፍ ምክክር ፍፁምና ምሉዕ ባይሆንም፣ ሁሉም ወገኖች ይህንን ብሔራዊ ዕድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የተናገረት አምባሳደሩ፣ የታጠቁ ኃይሎችን ጨምሮ ሁሉንም ድምፆች ለመስማት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የውይይት መድረክ ሁሉንም ወገኖች ወደ አንድነት ለማምጣት ያለመና ለኢትዮጵያ የተሻለ መንገድ የሚጀመርበት ቦታ እንደሆነም ገልጸዋል።

‹‹መከፋፈልን የሚያባብሱ ፅንፍ ረገጥ ተቃርኖዎች፣ የጥላቻ ንግግርና የኢኮኖሚ ፈተናዎች በኢትዮጵያ ብቻ የመጡ ችግሮች አይደሉም። ዴሞክራሲ የሚገልጸውም እንዲህ ያሉ ተግዳሮቶችን ግልጽና አሳታፊ በሆነ መንግድ ተጋፍጦ ለማለፍ በሚደረግ ጥረት ነው። ስለሆነም እውነተኛና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለኢትዮጵያ አሁን ያስፈልጋታል፤›› ብለዋል። 

‹‹ኢትዮጵያ አፍሪካን በዓለም መድረክ ትወክላለች። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና ለብዙዎች የአፍሪካ አገሮች ኩራትና መገለጫ እንደመሆኗ መጠን፣ የኢትዮጵያ ተግባር በአኅጉሪቱና በዓለም ዙሪያ በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል፤›› ብለዋል። 

የዜጎቿን መብት የምታከብር የተረጋጋችና የበለፀገች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አኅጉር መሠረት እንደመሆኗ መጠን፣ ተግዳሮቶችን በብስለት በመያዝና በማለፍ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ቀጣና በሎም ለአኅጉሪቱ ሕዝቦች ተምሳሌት ለመሆን ኢትዮጵያውያን እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጥያቄና መልስ

አምባሳደሩ የፖሊሲ ንግግራቸውን ካጠናቁቁ በኋላ ከሚዲያ ተቋማት ለቀረቡላቸው ውስን ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ግጭቶች እየተካሄዱ ባለበት ወቅት የሽግግር ፍትሕን መተግበር ውጤት ያመጣል ወይ? እንዲሁም የተቋማት ገለልተኝነት ላይ ጥያቄና ሥጋት እየቀረበ አገራዊ ምክክሩ ውጤት መጠበቅ ይቻል እንደሆነ ተጠይቀዋል።

አምባሳደሩ በሰጡት ምላሽ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ጀምሮ ካነጋገሯቸው ሰዎች መካከል አንድም ሰው ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ እንድትቀጥል የሚፈልግ እንዳላጋጠማቸው፣ ከመንግሥት ኃላፊዎች አንስቶ እስከ ተራ ግለሰቦች ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል። 

‹‹ነገር ግን ይህ ሰላም እንዴት ነው የሚመጣው ለሚለው መልስ የላቸውም። እኛም ሰላምን ማስፈን ቀላል እንዳልሆነ እንገነዘባለን፣ ነገር ግን ተስፋ አንቆርጥም፤›› ብለዋል። 

በግጭት ውስጥ ሆኖ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን የመተግበር ተቃርኖን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹በግጭት ውስጥ ሆኖ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን መተግበር ይቻላል ወይ የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ ለመውጣት ከሽግግር ፍትሕ የተሻለ ሌላ አማራጭ ሊኖራት እንደሚችል አላውቅም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ባለችበት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ፍጹም የሆነ አካሄድ ሊኖር አይችልም፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ በየአካባቢው ያሉትን ግጭቶች የመፍታት ሒደትና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን በተመሳሳይ ወቅት ከመተግበር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ጠቁመዋል። 

ሀሉን አቀፍ አገራዊ ምክክሩን በሚመራው ኮሚሽን ገለልተኝነት ላይ የሚነሱ ጥርጣሬዎችን እንደሚገነዘቡ የተናገሩት አምባሳደሩ፣ ይሁን እንጂ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሁሉም አካላት በውይይቱ እንደሚሳተፉ በግልጽ ማስታወቁን ጠቅሰዋል። 

የኮሚሽኑን ጥሩ መነሻ በማድረግም፣ ‹‹ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ወደፊት በመምጣት ኮሚሽኑ ያቀረበውን ሐሳብ እንዲፈትኑ በድጋሚ አሳስባለሁ፤›› ብለዋል።

የመንግሥት ቁጣና ተገቢነቱ 

የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋ ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር ላይ የተሰማውን ቁጣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የአሜሪካ አምባሳደር ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ‹‹ውንጀላ አቅርበዋል›› በማለት ከሷል።

መግለጫው አክሎም አምባሳደሩ፣ ‹‹መንግሥት አገሪቱን እንዴት መምራት እንዳለበት ያልተጠየቁትን ምክር ለግሰዋል፤›› በማለት ወቅሷል። 

የአምባሳደሩ ንግግር ትርጉም የማይሰጡና በበቂ ሁኔታ ያልተጤኑ ሐሳቦችን ያካተተ መሆኑን የጠቀሰው የሚኒስቴሩ መግለጫ፣ ‹‹አምባሳደሩ በንግግራቸው በምርጫ የተመረጠውን መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚሠሩ ቡድኖችን በስም ጠቅሰዋል፤›› በማለት ተችቷል። 

በማከልም በአምባሳደሩ ንግግር ተንፀባርቀዋል ያላቸውን ‹‹የፍሬ ነገር ስህተቶች›› ለማስተካከል፣ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ጋር እንደሚሠራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።

መንግሥት ያወጣውን መግለጫና በመግለጫው ላይ የቀረቡትን ክሶች በተመለከተ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት በተለያዩ የውጭ ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በአማካሪነት የሚያገለግሉ አንድ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ፣ መንግሥት በምርጫ የተመረጠውን መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚሠሩ የታጠቁ ቡድኖችን በስም ጠቅሰዋል በማለት በአምባሳደሩ ላይ የቀረበው ወቀሳ ውኃ አያነሳም ብለዋል።

ምክንያታቸውን ሲዘረዝሩም የኢትዮጵያ መንግሥት የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ቡድኖችን በስማቸው ሲጠራ ተስምቶ ባይታወቅም፣ ከስም መጥራት በላይ በመሄድ ከእነዚህ ቡድኖች አንዱ ከሆነው የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) ጋር ለድርድር መቀመጡን አስታውሰዋል።

መንግሥት ለድርድር መቀመጡ ተገቢ መሆኑ አያጠያይቅም ያሉት ተንታኙ፣ መንግሥት ለድርድር በተቀመጠበት የአሜሪካ መንግሥት ተወካዮች ታዛቢ የሚል መጠሪያ ተስጥቷቸው ውሳኔ ከማሳለፍ በመለስ፣ የድርድሩ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ሲያደርጉ አልነበረም ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል። 

መንግሥት በፕሪቶሪያ ከሕወሓት ጋር ለድርድር ሲቀመጥ፣ እንዲሁም በቅርቡ ከኦሮሚ ነፃነት ሠራዊት ወይም ኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ለድርድር በተቀመጠበት ወቅት፣ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ማይክ ሐመር በታዛቢነት መሳተፋቸው ይታወሳል ብለዋል።

የአሜሪካ አምባሳደር ያደረጉትን የፖሊሲ ንግግር በአንክሮ እንደተከታተሉት የተናገሩት የፖለቲካ ተንታኝ፣ የአምባሳደሩ ንግግር የትጥቅ ትግል አራማጆች ወደ ድርድር እንዲመጡ በመጫንና የመንግሥትን የመፍትሔ አማራጮች በማስረፅ ለመንግሥት ማድላቱን ጠቁመዋል።

‹‹የአምባሳደሩ የፖሊሲ ንግግር መንግሥትን በዚህ ደረጃ ያስቆጣው አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በፋሽስታዊው የጣሊያን መንግሥት ከተፈጸመው የየካቲት 12 ጭፍጨፋ ጋር አመሳስለው በማነፃፀራቸው ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግሥትን የሚቃወሙ የአገር ውስጥ ኃይሎችም አምባሳደሩ ካደሩጉት ንፅፅር ጋር በሚመሳሰል ስያሜ መንግሥትን እየገለጹ መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -