Monday, June 17, 2024

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ ዕድልና ተስፋ ያላት አገር ግን ፈተናዋ በዝቶ የግጭት፣ የድህነት፣ የተረጅነትና የተስፋ ቆራጭነት አባዜዎች ሊለቋት አልቻሉም፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚመነጩት ከታሪኳና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካሉት ውጣ ውረዶች ጋር ቢሆኑም፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ድርጊቶች ከድጡ ወደ ማጡ እያንሸራተቷት ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ የኢኮኖሚ መንገዳገድ፣ የምግብ ዋስትና ዕጦት፣ ክልላዊ ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና የሙስና መስፋፋት፣ እንዲሁም ከትምህርትና ከጤና ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች መበራከት በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ዜጎችን ያሳስቧቸዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቀውሱን እያባባሱት መሆናቸውም በስፋት ይነገራል፡፡

በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው አገር የሚጎዱ ችግሮችን ለመቅረፍ የተባበረ ጥረት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ይህ ጥረት ሊሳካ የሚችለው ደግሞ ከመንግሥት ጀምሮ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ምሁራንና ልሂቃን፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ተዋንያንና ሌሎች ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች በጋራ እንዲረባረቡ መደላድሉ ሲመቻች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና፣ ብሩህ ተስፋና የማደግ ትልም ቀናውን ጎዳና እንዲይዝ ሁሉን አካታች የሆነ ምክክር፣ ድርድርና የጋራ የዕድገት ራዕይ ያስፈልጋል፡፡ አንዲት ኢትዮጵያን በአፍሪካ አኅጉር ተወዳዳሪና ተመራጭ ማድረግ የሚቻለው ሰላማዊ ድባብ ሲኖር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብሔር ተኮር ግጭቶችንና ከፋፋይ አስተሳሰቦችን መግታት የግድ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ዜጎች በፍትሐዊነት ሊስተናገዱበት የሚችል ሥርዓት ተባብሮ ማነፅ ሲገባ፣ በአጓጉል ትርክቶች ትውልዱን መበከል ውጤቱ አገር ማፍረስ ነው፡፡

ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን ለማስወገድ ከሚረዱ ዓበይት መፍትሔዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት አካታች የአስተዳደር ሥርዓት ማዋቀር፣ የተለያየ አመለካከት ባላቸው ወገኖች መካከል ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግና ሀብትና ሥልጣንን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መከፋፈል ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ኢትዮጵያን በአገር ውስጥና በውጭ ጭምር ስሟን በስፋት የሚያስነሳ ችግር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ማክበር፣ የመብት ጥሰት ፈጻሚዎች በሕግ እንዲዳኙ ማድረግ፣ የሲቪል ማኅበረሰቡንና የሚዲያውን ነፃነት ማስከበር ያስፈልጋል፡፡ የመብት ጥሰቶች በስፋት እየተፈጸሙ እንዳላዩ መሆን የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የኃላፊነት መጥፋት ዋነኛ ምልክት ነው፡፡ በሕግ ዋስትና የተሰጣቸው የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መጣሳቸው በስፋት ሲቀጥል፣ አመፅና አለመረጋጋት እየተበራከተ ሰላም ደብዛው ይጠፋል፡፡ ለአገር ዕድገት መዋል የሚገባው የሰው ኃይልና ሀብት ይጎዳል፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ በኢኮኖሚው ላይ የሚስተዋለው መቀዛቀዝ ነው፡፡ ሰላም ሲጠፋ የሰዎች፣ የምርቶችና የአገልግሎቶች እንቅስቃሴ ይታወካል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት ሥራቸው ሲታወክ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሲዳከምና የዜጎች ኑሮ ሲቃወስ አገር ለከፍተኛ ችግር ትጋለጣለች፡፡ በመንግሥትና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ትንበያዎች ኢኮኖሚው ከዓመት ወደ ዓመት ዕድገት እንደሚያሳይ ቢነገርም ድህነት፣ ሥራ አጥነትና የገቢ አለመመጣጠን በስፋት እየተስተዋለ ነው፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት ከሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በስተቀር የብዙኃኑ ዜጎች ኑሮ ከመጠን በላይ እየከበደ ነው፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ በፍጥነት ሰላም በማስፈን በመሠረተ ልማቶች፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በመሳሰሉት ዘርፎች ኢንቨስትመንቶች በስፋት ካልተስፋፉ የሚጠቀሰው የማደግ ተስፋ አያስተማምንም፡፡ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚን በማበረታታት ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን ካልታገዘ ችግሩ በስፋት ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰላም አስፈላጊ ነው፡፡

ሌላው ተጠቃሽ ችግር በምግብ ራስን አለመቻል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያን በምግብ ራሷን እንዳትችል ካስቸገሯት ምክንያቶች መካከል በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ፣ ግጭትና የግብርና ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ መሆን ናቸው፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችሉ ምክረ ሐሳቦች ቢቀርቡም፣ በየጊዜው የተለዋወጡ መንግሥታት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ለምሳሌ ድርቅን የሚቋቋሙ የሰብል ዘሮችን በብዛት ለመጠቀም ዳተኛ መሆን፣ የመስኖ ልማት በሚፈለገው መጠን ለማስፋፋት አለመፈለግ፣ በማኅበራዊ ሴፍቲኔት አማካይነት ዜጎችን በማንቀሳቀስ የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራዎችን ለማከናወን በስፋት መንቀሳቀስ ሲቻል መንቀርፈፍና የመሳሰሉትን እንቅፋቶች ይጠቅሳሉ፡፡ ከላይ ለተጠቀሱት ምክረ ሐሳቦች ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በቂ ሀብት መድቦ ኢንቨስት ማድረግ ቢቻል፣ በምግብ ራስን መቻል ከመፈክር አልፎ በተግባር እንደሚረጋገጥ የብዙዎቹ እምነት ነው፡፡

ሙስና እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ችላ ማለት የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ሄድ መለስ እየተባለ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ግን አስተዛዛቢ ነው፡፡ በአገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች ግዴታ እስኪመስል ድረስ ከሚጠየቀው ጉቦ ጀምሮ፣ በተለያዩ መስኮች የሚፈጸመው ዘረፋ አገርን እንደ ነቀዝ እየበላ ነው፡፡ ሙስና የአገርን የልማትና የዕድገት ውጥኖች ከመገዳደሩ ባሻገር፣ ዜጎች በመንግሥታዊ ተቋማት ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን መተማመን በእጅጉ እየሸረሸረ ነው፡፡ ለፀረ ሙስና ትግል የሚያገለግሉ ሕጎች ማስፈጸሚያ ጠንካራ ማዕቀፍ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነትን በተግባር የሚያረጋግጡ የአሠራር ሥልቶች፣ መንግሥታዊ ተቋማትን ከሙስና የሚያፀዱ መዋቅራዊ ለውጦችና የመሳሰሉት ላይ በአንድነት ካልተተኮረ አገር የዘራፊዎች መጫወቻ ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያን የሚታደጋት የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...