Monday, May 20, 2024

ለፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ትግል መቀዛቀዝ ምክንያቱ የጠራ ርዕዮተ ዓለም አለመኖር ወይስ የምሁራን መዳከም?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መሬት ላራሹ ብለው በተነሱ ተማሪዎችና ምሁራን ድምፅ የተቀጣጠለው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አብዮት፣ ከኢምፔሪያሊዝም ወደ ሶሻሊዝም በተደረገ ርዕዮተ ዓለም ለውጥ ከተደመደመ ዘንድሮ ግማሽ ምዕተ ዓመት አስቆጥሯል።

ኢትዮጵያ ከ1966 ዓ.ም. በኋላ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተደረገውን ጨምሮ የተለያዩ በትጥቅ ትግልና በተቃውሞ ጫና የተፈጠሩ ለውጦችን አስተናግዳለች።

ነገር ግን አሁን 50 ዓመታትን ያስቆጠረውን አብዮት የቀሰቀሱትም ይሁን ተከትለውት የመጡት የመሬት ባለይዞታነት መብት ጉዳይ፣ የብሔር ትግልና ማንነት ተኮር ፖለቲካ ጥያቄዎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።

እነዚህ ጥያቄዎች ላለፉት 50 ዓመታት ሳይመለሱ መቀጠላቸው የአገሪቱንም ሆነ የአገረ መንግሥቱን ግንባታ ሲፈታተኑት ይታያል።

ያለመፍትሔ እየተወሳሰቡ መሄዳቸው እስካሁን ድረስ በሒደት የመጡ የተወሰኑ ለውጦችንም ወደኋላ እንዳይቀለብሱ የሚያሠጋቸው ጥቂቶች አይደሉም።

የጥያቄዎቹ አለመመለስ በአገሪቷ ላይ የደቀኑት ሥጋት ሲነሳ ለአብነትም የሚጠቀሱት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የተቀሰቀሱና የቀጠሉ ግጭቶች፣ በሁለት የተለያዩ ጫፎች ላይ የቆሙ የማኅበራዊና የፖለቲካ ዕሳቤዎችና እንቅስቃሴዎች ናቸው።

በታሪክ ከዚህ ቀደም እንደተስተዋለው የመፍትሔ ሐሳቦችን በማፍለቅና በኅብረተሰቡ ዘንድ በማስረጽ በኩል የምሁራንም ይሁን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሚና ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀዛቅዞ መገኘቱ፣ በእርግጥም በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ እየተጋጋሉ የመጡትን ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጤት ማምጣት መቻላቸው ላይ ተስፋ ሰጪ የማይመስል አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ አንዷለም ቡኬቶ ይህን አስመልክቶ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ አሁን ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ሚናና አስተዋጽኦ በ1966 ዓ.ም. ለውጥ ማምጣት የቻሉትን ያህል ያልሆነበትንና እየቀነሰ የመጣበት ያሏቸውን የተማሪዎችን ብዛት፣ የትምህርት ጥራትና የኢኮኖሚያዊ አቅም ጉዳይ ጋር የተያያዙ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል።

መጀመሪያ ላይ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወይም ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የደረሰው ተማሪ፣ በ1960ዎቹ በጣም ትንሽ የሚሆነውን ክፍል ወይም ሕዝብ ቁጥር ነበር የሚይዘው ያሉ ሲሆን፣ ከአገር በቀል እውቀት ውጭ ላለው ለምዕራባዊውም ሆነ አጠቃላይ እውቀት በመባል ለሚነሳው ጉዳይ የተሻለ ተጋላጭነት (Exposure) የነበረው ተማሪ ነበር ብለዋል።

አቶ አንዷለም ‹‹ከዚህ አንጻር ተማሪ ቁጥሩ ትንሽ በመሆኑ ብቻ የመሪነት ሚና ነበረው። እንደ መሪም ይታይ ነበር። ከቤቱ ተማሪ የወጣበትም ቤተሰብም በልዩ ሁኔታ ነበር የሚታየው። በወቅቱ ተማሪ የተሳሳተ ሐሳብ እንኳን ቢኖረው በዚያን ወቅት በሕዝቡ ዘንድ የመቀበል ነገር ነበር። ምንም ቢሆን የሚያውቁት ነገር አለ ተብሎ ስለሚታመን። ያደጉት አገሮች የደረሱበትን ነገር ሰምተዋል አውቀዋል ተብሎ ስለሚታሰብ። በአገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በሕዝቡ ዘንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነበት ሚና ነበረው፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ለአሁኑ ትውልድ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ሁኔታ እንደሆነ የገለጹት የሕግ ባለሙያው፣ የተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን በማንሳት ይህ ብቻ እንደ መሪ የሚታይበትን አቅም እንደሚቀንሰው ገልጸዋል።

በሁለተኛነት በ1960ዎቹ ጊዜ የነበረው የትምህርት ጥራት ደረጃና አሁን ያለው ልዩነት አስተዋጽኦም ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።

በወቅቱ የነበሩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስን መሆን በፈጠረው ሁኔታም ጭምር ከማኅበረሰቡ ውስጥ እጅግ በጣም ጥቂት የሚባሉ ተማሪዎች ተጣርተው የሚያልፉበት አሠራር እንደነበረ በመግለጽ፣ ዩኒቨርሲቲን ይቀላቀሉ የነበሩት ጥቂት ባለብሩህ አዕምሮ ባለቤቶች ነበሩ፡፡ ይህ በመሆኑ ብቻ በዕውቀታቸው ልህቅና ላይ ተዓማኒነት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።

በተቃራኒው አሁን ያለው የትምህርት ጥራት ወድቋል ያሉት አቶ አንዷለም፣ ይህን ወላጅም፣ ቤተሰብም ሆነ የወጡበት ማኅበረሰብ በጠቅላላ የሚረዳው እውነታ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

‹‹አሁን ላይ ተምሮ የመጣውም ካልተማረው ብዙም ልዩነት የለውም። ስለዚህ ተማሪ  የኢኮኖሚም ይሁን የማኅበራዊ ወይም የፖለቲካ ጥያቄዎችን አንስቶ ቢወጣ እንኳን በሕዝቡ ዘንድ ይህን ልጅ አናውቀውም እንዴ? ምን ተምሮ? ምን አውቆ? ነው ተብሎ የሚጠየቅበት ዝቅተኛ ቦታ ተሰጥቶታል። ተማሪ በሕዝቡ ዘንድ የሚሰጠው ቦታ እንደ ድሮ አይደለም፤›› ያሉ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት የተማሪ የመሪነት ሚናው ቀንሷል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በ1960ዎቹ የለውጥ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ተማሪዎች በሥርዓቱ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከሚያገኝ ሀብታም ቤተሰብም ጭምር የወጡ እንደነበሩም ተጠቅሷል። ይህ ደህና የሚባል የኢኮኖሚ ደረጃ ሁኔታ ተማሪዎቹ የሚያጡት ነገር አልነበረም ሊያስብል የሚችል ማለትም የገዛ ቤተሰባቸውን ጥቅም የሚያስቀሩና የሚቃረኑ ሐሳቦችንም ያነሱ እንደነበር ሲገለጽ፣ አብዛኛዎቹ የቀድሞ ተማሪዎች የነበራቸው ነገር ተምሬ ቤተሰቤን ልርዳ የሚል ጫና የሚፈጥር (survival) ጉዳይ እንዳልነበራቸው ተገልጿል።

ይህ ሁኔታም መሬት ላራሹን ጨምሮ የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች የማንሳት ዕድል እንደሰጣቸው ተነግሯል። ከዚህ በተቃርኖ አሁን ይህ አስቻይ ሁኔታ በእጅጉ የተመናመነ ነው ተብሏል።

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም ‹‹አሁን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገባው አብዛኛው የደሃ ልጅ፣ እንዲሁም ከትምህርት ቤት ቢባረር መጠጊያ መውደቂያ የሌለው ነው። ከዚህ አንጻር የአሁን ተማሪ ያ መታገል የሚያስችለው የኢኮኖሚ አቅም የለውም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ታዋቂ የነበሩ በስልሳዎቹ ዓመታት ወቅት የተማሪዎችን ትግል ይመሩ የነበሩ ሰዎችን እናገኝ ነበር፡፡ አስተማሪዎቻችንም ነበሩ፣ ከትምህርት ቤት ተመርቆ ከተማሪዎች ትግል ላለመራቅ ሲባል የወቅቱ ተማሪዎች ሆነ ብለው የተወሰኑ የትምህርት ዓይነቶችን በመውደቅ የቆይታ ዓመታት ይጨምሩ እንደነበር ሲገለጽ፣ በአሁን ወቅት ግን እንደዚህ ዓይነት ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም ተብሏል።

የ1966 አብዮትን የፊት ለፊት ገጽ ሆነው የኅብረተሰቡን ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ያስተጋቡት እና የትኛውንም ጫና ተቋቁመው የተጋፈጡት ተማሪዎችና ምሁራን እንደነበሩ የተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ሲያስረዱ፣ በአሁን ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ግን የሕዝብ ጥያቄ በሆኑ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ሌሎችም ጉዳዩች ላይ ጥያቄ ማንሳት ጋር እንኳን ሳይደርስ የትኩረት ጉዳያቸው የመሆኑ ሁኔታ ከሚጠበቀውም ይሁን ከሚፈለገው አንጻር ሲታይ ይህን ያክል ተብሎ ሊጠቀስ የማይችል መሆኑም በተለያዩ መድረኮች ላይ በሚቀርቡ ወቀሳዎች እንዲሁም በሚነሱ ሐሳቦች ላይ ይስተዋላል።

አቶ አንዷለም የተማሪዎች ፍላጎትና ተነሳሽነት ማጣትን አስመልክቶ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ የፖለቲካ ጥያቄ የሚባለው በጊዜ ብዛት ወደ ብሄር ተሻግሮ አንድ ጥግ ይዟል ይላሉ።

‹‹ያን ጊዜ ተማሪ ያነሳ የነበረው ጥያቄ፣ ተማሪውን ሊበትን የሚመጣው አድማ በታኝ እንኳን፣ የሚነሳውን ጥያቄና ሐሳብ ውስጥ ለውስጥ ይጋራው ነበር። ለምሳሌ ከ60ዎቹ የተማሪ ጥያቄዎች መካከል የኑሮ ውድነትን ወይም መሬት ላራሹ እንደነበር መጥቀስ ይቻላል። እነዚህን አንስተው ሲታገሉ አድማ በታኙም ፖሊስ ቢሆን፣ ወታደሩም ይሁን ደህንነቱ ወይ አርሶ አደር አባት ያለው አልያም ደግሞ ደሃና ለጥያቄው መነሻ ያለው ነው። ስለዚህ በግላጭም ባይሆን ይደግፈው ነበር፤› ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ያለው ሁኔታ ከዚህ በእጅጉ የራቀ እንደሆነ ተብራርቷል። የፖለቲካ ጥያቄው ቅርጹን ከመቀየር ባሻገር ያልቆመ ቢሆንም አሁን በየኮሌጁና ዩኒቨርሲቲው የሚነሳው የፖለቲካ ጥያቄ የብሔር እንደሆነ ግልጽ ነው።

‹‹በየከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ የፖለቲካ ጥያቄን ቅርጽ የያዘ የብሔር ግጭት ነው ያለው። በብሔርና በጎሳ ቡድን ይቧደኑና ይፈነካከታሉ፣ ትምህርት ይቋረጣል፣ በባለፉት አምስት ዓመታት ስናየው የነበረ ነው›› ብለዋል አቶ አንዷለም።

ይህ የተማሪዎቹ ሁኔታ ወደ ኅብረተሰቡ ወርዶ የመሪነት ሚና ሊያሰጥ እንደማይችልና የኅብረተሰቡ ጥያቄም ሊባል እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡

ይህን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው የሚከታተሉ ምሁራን እንደሚገልጹት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የብሔር ጥያቄ የሚነሳው ከሚኖሩበት የተወሰነ ቦታ ወጥተው በሌላ አካባቢ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለመደባደብ፣ ለመጣላትና ጸብ ለማንሳት ያክል እያደረጉት ያሉት እንጂ፣ ይህ ነው ተብሎ ሊጠቅስ የሚችል የወጡበትን ማኅበረሰብ የሚወክል ወሳኝ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጥያቄ ተማሪ አነሳ ሊያስብል የሚችል እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም ይህን አስመልክተው ‹‹የብሔር ፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ ፖለቲካ አይደለም ባልልም፣ አድማ በታኙ ትግላቸውን እንዲቀላቀል የሚያስችላቸው ግን አይደለም። ምክንያቱም አድማ በታኙ፣ ፖሊሱ ወይም ደኅንነቱ የተቃዋሚው ብሔር አባል አይደለም። በዚህም ምክንያት ተቃውሞው የሕዝብ ጥያቄ አነሳ የሚያስብል አይደለም›› ብለዋል።

የ66 ዓ.ም. አብዮትን ያስቻሉት ተማሪዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች የቡድን እንዳልነበሩ፣ ይልቁንም አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚያስማሙ ጉዳዩች ላይ ያተኮሩ እንደነበሩና አሁን እንደ እነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ያን ያክልም እንደማይስተዋሉ፣ በአገሪቱ የታሪክና የፖለቲካ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው አንቱ የተባሉ ምሁራን በተለያዩ መድረኮች በስምም ሲገልጹት ይታያል።

አቶ አንዷለም ከዚህ ጋር አያይዘው አሁን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለ ተማሪ፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ከገባች በኋላ የተወለደ እና በስርዓቱ ውስጥ ያደገ እንደሆነ በማንሳት፣ ይህም ካለፉት አርባ ዓመታት በላይ እየጎለበተ ከመጣው የብሔር ፖለቲካ ጋር ሲተያይ በተማሪዎች የሚነሳ ጥያቄ ሰፊ ድጋፍ ያገኛል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ሥር ለ700 ዓመታት እየተመራች ስትቆይ፣ የነበረው ፖለቲካ በቤተ መንግሥት ተወስኖ ማን ይንገሥ ማን አይንገሥ በሚል ላይ ተገድቦ መቆየቱን ያነሱ ሲሆን፣ ሰፊው ሕዝብን ያማከለ ፖለቲካ ግን እንዳልነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

ሰፊውን ሕዝብ ያማከለ ፖለቲካ ከተጀመረ በኋላ ባለው ጊዜ ግን ለአብነትም፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ከመንበር ያወረደው ፖለቲካ የሚመስለው የነበረው የምሁራን ተሳትፎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው ቢሆንም፣ በስተመጨረሻ ግን ሥልጣን የተረከበው ወታደራዊ ኃይሉ እንደነበር ይታወቃል።

ከዚህም በኋላ ይህን ወታደራዊ ኃይል ለመታገል የተፈጠሩ አንዳንድ የፖለቲካዊ አደረጃጀቶች ጅምር ቢታይም፣ የደርግን ወታደራዊ ኃይል የጣለው ግን ሌላ ወታደራዊ ኃይል ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዩታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እንደነበር ይታወሳል።

ልክ እንደ ተማሪዎች ሁሉ፣ የምሁራንም የፖለቲካ ሚና ቀንሷል ሲሉ የሚሟገቱት የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም፣ የኢሕአዴግንም ኃይል ከሥልጣን ያነሳው ቅንጅትን የመሳሰሉ ትልቅ ድጋፍ አግኝተው የነበሩ ወይም ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይሆኑ፣ ከራሱ ከኢሕአዴግ ውስጥ የወጣ ሌላ ኃይል ነው ይላሉ።

እንደ እርሳቸው አስተያየት፣ እነዚህ ተከታታይ የታሪክ ኩነቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካውን በእውቀት መለወጥ ሳይሆን ጉልበት ነው የሚቀይረው የሚል እየዳበረ የመጣ ዕሳቤ እንደያዙና ተስፋ የመቁረጥ ነገር እንደሚታይ አውስተዋል፡፡

‹‹አሁንም ድረስ ኃይል ያላቸው አካላት እርስ በርስ ሲጣጣሉ ይታያል። ወይም ኃይል ላይ ያለው ቡድን እርስ በርስ ይከፋፈል ይሆናል እንጂ ምሁራን ተሰብስበው የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመው፣ ፕሮግራሞቻቸውን ጽፈው፣ ታግለው ምን አመጡ የሚል አመለካከት አለ›› ሲሉ ተናግረዋል።

በተደጋጋሚ በኃይል በተደረገ እንቅስቃሴ የመንግሥት ሥልጣን ለውጥ ስለተደረገ የዚህ ልምምድ የፖለቲካ ሐሳብን በጠመንጃ የማራመድ ሁኔታ ይሁንታን ያገኘ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በማብራሪያቸው አሁንም የመንግሥትን ሥልጣን የያዙት አካላት ምሁራን በዕውቀታቸው ያመጡት ለውጥ እንደሌለ፣ ይልቁንም በኃይል በተደረገ እንቅስቃሴ እንደሆነ የመታየት ነገር መኖሩንና ይህ ደግሞ ደርግን በጣለው በኢሕእዴግ የአገዛዝ ዘመንም ይስተዋል የነበረ ኩነት መሆኑን ጠቅሰዋል። አክለውም ከእነዚህ ነጥቦች በመነሳት የምሁራን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦም ይሁን ሐሳባቸው በሕዝብ ዘንድ ያለው የተቀባይነት ደረጃ መቀነሱን ገልጸዋል።

በዚህ ሒደት ውስጥ የአገሪቱ ምሁራን በተለያዩ መድረኮች፣ በንግግሮቻቸው፣ አደረግን የሚሏቸውን ጥናት ጠቅሰው በሚያቀርቧቸው ጽሑፎች በኩል ሲታዩ ሁለት የተለያዩ ጫፎች ላይ ቆመው ሲሟገቱ ይስተዋላሉ፣ በአንድ ጎራ አሁን ያለው የክልሎች በወሰን ተከልሎና በቋንቋ ተከፋፍሎ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአስተዳደር ሒደት መፍረስና የቀደመው አንድነታዊ አካሄድ መመለስ አለበት የሚሉ ምሁራን ሲኖሩ፣ በሌላኛው ጥግ ደግሞ በትንሹ የክልል አስተዳደር ከፍ ሲልም ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌዴራሊዝም በፍጹም መነካት የለበትም የሚሉ ሙግቶችን የሚያቀርቡ ምሁራን፣ ሕዝቡን የሚጠቅመው የእኔ ሐሳብ ብቻ ነው የሚሉ አካሄዶች ላይ የመጠመዳቸው ትዝብት የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን ብዙዎች ያነሳሉ።

ይህን ዓይነት የምሁራን ክፍፍል የሕዝቡን የየዘርፍ ጥያቄዎች የ66 ዓ.ም ዓይነት አብዮት መፍጠር የሚያስችል አስተዋጽኦ እንዳይኖራቸው አግዷቸዋል፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን ነስቷቸዋል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

በሌላ በኩል ምሁራን አሁን ባለው ሁኔታ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተቀባይነት እንዲመነምን ካደረጓቸው ጉዳዩች መካከል፣ ትኩረታቸው በመደብ ወይም ሰፊውን ሕዝብ በአጠቃላይ በሚመለከት የኢኮኖሚ ጉዳይ ከመሆን ይልቅ፣ እርስ በርሳቸው የየራሳቸውን የግል ማንነት ወይም ብሔር ጋር የተያያዘውን ጉዳይ ብቻ ተንተርሰው ቆመው መገኘታቸው፣ በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን አመኔታ እንደሸረሸረውም የሚገልጹ አሉ።

‹‹ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ›› (Human Rights First) የተባለ አገር በቀል የሲቪል ማኅበር ዋና ዳይሬክተርና የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተስፋለም በርሃ በበኩላቸው፣ በስልሳዎቹ ወቅት የበላይነት የነበረው የርዕዮተ ዓለም ትግል እንደነበር አውስተዋል።

በዓለም አቀፍም፣ በአኅጉርም ሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ የነበረው የርዕዮተ ዓለም ትግል እንደነበረ ገልጸው፣ ይህ አካሄድ የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ ዓለም አቀፉን ትግል የሊበራሊዝም ወገን ካሻነፈ በኋላ፣ የመደብ ትግል ተቀዛቅዞ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን እየሆነ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ (nationalism) ትግል ነው ብለዋል።

አቶ ተስፋለም፣ ‹‹በኢትዮጵያም እየታየ ያለው ከሐሳብ ወይም ከርዕዮተ ዓለም ይልቅ ማንነት መሠረት ያደረገ ትግል ነው ወይም ብሔርተኝነት ነው ጎልቶ እየወጣ ያለው። በአገሪቱ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ማንነትን መሠረት ያደረግ ትግል ጠፍቷል የለም። ወደ ብሔር ወርዷል፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

በማብራሪያቸው ድሮ ድሮ የመደብ ትግል ያገናኛቸው ነበር። ለላብ አደር፣ ለአርሶ አደር ወዘተ እየተባለ ሁሉንም ብሔር የሚያገናኝ፣ አብረው እንዲሠሩ የሚያደርግ የመደብ ትግል ነበር። ምሁራንም ይሁኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች በእዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን ‹‹አሁን ግን ወደ ብሔርተኝነት ስለወረደ ሁሉም የየራሱን ወገን ይዞ፣ የትግራዩም ስለትግራይ ነው የሚታገለው፣ የኦሮሞውም ስለኦሮሞ ነው፣ ሌላውም እንደዚያው›› ሲሉ ገልጸውታል።

‹‹ከመንግሥት ጀምሮ አሁን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በሐሳብ አይደለም፣ ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ሁንሉንም የሚያስማማ ሐሳብ የለውም። ወጥ የሆነ ትግል እንዳይካሄድ ያደረገው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የኩነቶች ለውጥና በሀገሪቷ ያለው የፖለቲካ እሳቤ ያደረገው ሽግግር ነው›› ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በምሁራን መካከል የውይይት አጀንዳ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል፣ ከ1966ዓ.ም አብዮት እስካሁን ድረስ ባሉት ዓመታት የተደረጉ የመንግሥታት ለውጦች ላይ ከተስተዋሉ ኩነቶች መካከል፣ በዋናነት ተጠቃሾቹ ሥልጣን የሚይዘው ኃይል አንድነታዊ ኃይል ሲሆን፣ የብሔርተኞች ተቃዋሚ ኃይል ሆኖ መገኘትና ብሔርተኛው ኃይል መንበር ሲይዝ ደግሞ የአንድነቱ በተቃርኖ የመቆም ጉዳይ ተጠቃሽ ናቸው።

ይህ ሁኔታ እንደዚህ ዓይነት የልዩነት ጫፎችን እንዴት ነው አስታርቆ መቀጠል የሚቻለው ወይስ ሌላ አማራጭ ሊበጅ ያስፈልጋል? የሚለውን ጥያቄ ፈጥሯል።

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል በየትኛው ወገን ነው ያለው የሚለው ጉዳይ ግራ አጋቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

‹‹እርግጥ ነው በብሔር የተደራጀ ኃይል ነው ሥልጣን የያዘው ምንም ጥያቄ የለውም። ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ፖለቲካዊ ርዕዮተ አለሙና ሊደርስበት የሚፈልገው ግብ አንጻር ግን በእርግጥም ብሔርተኛው ኃይል ነው ሥልጣን ላይ ያለው ብዬ ለመወሰን ይከብደኛል›› ብለዋል።

ለሐሳባቸው ማስረጃ ያቀረቡት ምክንያት፣ የሚፈልገው ኃይል ነው የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዳለ ሆኖ፣ ነገር ግን የአንድነት ኃይል የሚባለውንም ሥልጣን እንዲጋራው ማቅረቡን በመጥቀስ፣ የብሔርተኛ ኃይል ሥልጣን ይዞ የአንድነት ኃይል ተቃዋሚ ሆነ የሚለው ሁኔታ ላይ መገኘቱን ግን የሚያስረግጥ አካሄድ አይደለም ያለው ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ሲታሰብ የአንድነት ኃይል ነው የሚመስለው›› ብለው ‹‹ወረድ ሲባልና መሬት ላይ ያለው ሲታይ ደግሞ የጎሳ ፖለቲካ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጨመረው አሁን ነው። እንደ ግብ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት እየሄደ ያለው ወደ ብሔርተኝነት ነው ብዬ አላምንም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

የአንድነት ኃይል መገለጫዎች ምንድናቸው የሚለው ጥያቄ ከሰንደቅ ዓላማም ይሁን ከቋንቋ አንፃር ወይም ሌላ ትክክለኛ መገለጫዎቹ ምንድናቸው የሚለው ጉዳይ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በምሁራን መካከል ምላሽ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል።

በአሁን ወቅት ለሚታየው ለፖለቲካም ይሁን ለኢኮኖሚ ለውጥ የሚደረጉ ሰላማዊ ትግሎች መቀዛቀዝ ምንጭ ወሳኝ የሆነና በግልጽ የተቀመጠ ርዕዮተ ዓለም መታጣት ነው የሚሉ የክርክር መነሻ ሐሳቦች ከተለያዩ ወገኖች ይደመጣሉ።

እነዚህን ሐሳቦች የሚያነሱት አካላት በማስረጃነት የሚያቀርቡትም ለ66 ዓ.ም. አብዮት ሶሻሊዝምን እንደ ፍቱን አማራጭ አድርገው የያዙ ብዙኃን የነበሩት መሆኑን፣ የ83 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥም አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለውን ይዞ መምጣቱን በመጥቀስ አሁን ላይ የሚደረጉ የፖለቲካ ትግሎች ግን ይህ ነው የሚባል ርዕዮተ ዓለም ሐሳብ ይዘው የሚነሱ አለመሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

የሕግ ባለሙያው ይህ በግልጽ የሚታይ ክፍተት ነው ያሉ ሲሆን፣ በምሳሌነትም አሁን ያለው መንግሥት እየተመራበት ያለው ርዕዮተ ዓለም መደመር ነው ከተባለ፣ መደመር ርዕዮተ ዓለም ነው የሚለው ጉዳይ ግራ አጋቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክንያት አድርገው ያቀረቡትም፣ አንድ ርዕዮተ ዓለም አንድን አገር ለመምራት ደርሷል ተብሎ መታየት የሚችለው መጀመሪያ በእውቀት ደረጃ ተንሸራሽሮ፣ በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች፣ በፀሐፊዎችና በሌሎችም ደረጃ በውይይት ዳብሮና ቀስ እያለ አድጎ ርዕዮት ዓለም ለመባል ሲበቃ ነው ብለዋል።

ሶሻሊዝምም ቢሆን በአንድ ጊዜ ርዕዮተ ዓለም ለመባል እንዳልበቃ፣ ይልቁንም የማርክስን የመነሻ ሐሳብ ይዞ በዓመታት ውስጥ ዳብሮ ተቀባይነት ለማግኘትና ለመተግበር ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው፣ በኢሕእዴግ ተግባራዊ የተደረገው አብዮታዊ ዴሞክራሲም ርዕዮተ ዓለምም ቢሆን በተለያዩ የዓለም አገሮች ተግባራዊ የተደረገ ርዕዮተ ዓለምን ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ይመጥናል ተብሎ በታሰበው መንገድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለሕዝቡ እንደሚገባው መጠን ከርክመው ወደታች ያወረዱት ርዕዮተ ዓለም ነው በማለት አብራርተዋል።

የ66 ዓ.ም. አብዮትን በተመለከተ ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለትውልድ የተሸጋገሩ የአብዩቱ ትሩፋቶችና ዕዳዎች በተመለከተ በተደረገ ውይይት ላይ፣ የመሬት ጥያቄ አብዮቱን ካቀጠጣለው የመሬት ላራሹ ጥያቄ ተነስቶ አሁን ተመልሶ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች መሬት እንዳሻቸው የሚሰበስቡበት ሁኔታ ላይ ደርሷል፡፡ እዚህ ላይ አስተያየታችሁ ምንድነው በሚል ከታዳሚዎች ለተነሳ ጥያቄ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አቶ ዘገዬ አስፋው ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ዘገዬ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን፣ የመሬት አዋጅ በሚወጣበት ጊዜ አዋጁን በማረም በኃላፊነት ተሳትፈዋል። የ1983 ዓ.ም. ለውጥ ተከትሎ በተቋቋመው የሽግግር መንግሥት የሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደት ላይም ተሳትፈዋል።

የመሬት ጉዳይን በተመለከተ ላለፉት 50 ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት አቶ ዘገዬ፣ ከታዳሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በአሁን ወቅት ከመሬት ጋር ተያይዞ የተነሳው ሙሰኝነት በዚህ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን አገሪቷን ካጥለቀለቀው ሙሰኝነት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

በገጠር መሬት አዋጅ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ተብሎ የተደነገገው በአዋጁ መሠረት ራሱን እንደ ባለርስት ከሚቆጥረው አርሶ አደር ላይ ባለሀብት በማታለል መሬትን እንዳይሰበስብ ለማድረግ የተካተተ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አልተለወጠም ብለዋል።

ነገር ግን በመሬት ላይ ሙስና መስፋፋቱን ድርጊቱም በድብቅ ብቻ ሳይሆን በይፋ እየተደረገ የሚገኝ እየታየ የሚያስቆም ኃይል መጥፋቱ እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል።

አቶ ዘገዬ ‹‹የመሬት ጉዳይ ላይ የሚታይ ሙስና በአጠቃላይ አሳሳቢና ማንም ደፍሮ የማይነካውም ስለሆነ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደፍሮ አንድ ትልቅ ውይይት የሚያካሂድበት ካልሆነ በስተቀር አገራችን እየጠፋት ያለች ይመስለኛል፤›› ብለዋል።

ከመሬት ጋር በተያያዘ ስላለ የሕግ ክፍተት ሲያብራሩም፣ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በነበረው የሽግግር መንግሥት የቀረበው የሕገ መንግሥት ረቂቅ የመንግሥት አስተዳደር ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የአንድ ግለሰብ ንብረት የሆነ መሬት ለመውሰድ ሲያስብ የሚወስነው በራሱ ሳይሆን ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲሆን የሚያዝ፣ የካሳ ክፍያ መጠኑም እንዲሁ በችሎት የሚወሰን እንደሚሆን የሚገልጽ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ኢሕእዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ በሥራ ላይ ባለው በፀደቀው ሕገ መንግሥት ግን ይህ እንዳልተካተተ ይልቁንም የመንግሥት አስተዳደር መሬት ከሕዝብ ላይ ሲወስድ ካሳ ብቻ እንደሚከፍል እንደሚገልጽ አስታውሰዋል።

አቶ ዘገዬ ‹‹በዚህ ምክንያት ነው በየቀበሌውና በንዑስ ወረዳዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ መሬት ያስፈልጋል ብለው ሰው የሚያስነሱበት ሁኔታ የተፈጠረው›› ብለዋል።

አያይዘውም ወደፊት ይህ አንቀጽ የሚሻሻል ከሆነ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚያመች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ለመሬት ሙስናው መባባስ አንዱ ምክንያት መሬት የሚያስተዳድረው የመንግሥት አካል የተማከለ አለመሆን እንደሆነ ገልጸዋል።

‹‹በአንድ ክልል እንኳን ብንወስድ ብዙ የመንግሥት የስራ ክፍሎች እጃቸውን በመሬት አስተዳደር ውስጥ ያስገባሉ። የመሬት አስተዳደርን የተማከለ ብናደርግ በአንድ አመራር ቢመራ፣ ጡንቻ ያለው የወረዳ አስተዳዳሪ ሁሉ ለከተማው ስፋት ያስፈልጋል ተብሎ ሕዝብን የሚበድልበት ምክንያት አይኖርም›› ሲሉ ተናግረዋል።

ብዙ ማጭበርበርና የመሳሰለው ነገር የሚከሰተው ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደሆነ አብራርተዋል።

አያይዘውም ‹‹የመሬት ጉዳይ እንደ ተራ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቆጥሮ ግራና ቀኝ መሸጥ የለበትም ያሉ ሲሆን፣ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ለማስከበርም ይሁን ወደፊትም የመሬት ነጠቃውን ለማስቆም በአንድ አካል መሬት ቢተዳደር በጣሙን ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ይመስለኛል›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -