Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዘንድሮ የወጭ ንግድ ገቢ ከዕቅዱም ሆነ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ ገቢ በተያዘው የበጀት ዓመትም የታቀደውን ያህል ገቢ እንደማያገኝና ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይም ዝቅተኛ ገቢ የሚገኝበት እንደሚሆን ተመላከተ፡፡ 

በተለይ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሚከታተላቸው የወጭ ንግድ ምርቶችና ከቡና እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ መጠን ከቀዳሚው ዓመትም ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸው ሆነዋል፡፡

ሰሞኑን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በበጀት ዓመቱ በአሥር ወራት ውስጥ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 1.78 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ የአሥር ወሩን አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት መረጃ፣ ሚኒስቴሩ ከሚከተላቸው የወጭ ንግድ ዘርፎች 772.25 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ 

ይህም የዕቅዱን 85.1 በመቶ ማሳካት መቻሉን የገለጹ ሲሆን፣ የአሥር ወራት ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 907 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ ከቡና ምርት ኤክስፖርት አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አመልክቷል፡፡ ይህም በበጀት ዓመቱ ይገኛል ተብሎ በዕቅድ ተይዞ ከነበረው ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ አመልክቷል፡፡

የበጀት ዓመቱ ሊጠናቅቅ ሁለት ወራት እየቀሩት ከወጭ ንግድ ዘርፍ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 1.78 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ከሁለቱ ተቋማት የተገኙት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከሌሎች ዘርፎች የወጭ ንግድ ገቢ ተደምሮ በአሥር ወራት የተገኘው አጠቃላይ ገቢ ሲሰላም ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ያነሰ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም በዘንድሮው በጀት ዓመት ለማግኘት ታቅዶ ከነበረው 5.3 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ሰፊ ልዩነት ይታይበታል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዘጠኝ ወራት የተገኘው የወጭ ንግድ ገቢ 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር መግለጹ አይዘነጋም፡፡ የአገሪቱ የወጭ ንግድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ መሻገር ችሎ የነበረው በ2014 በጀት ዓመት ሲሆን፣ በወቅቱ 4.14 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱ ይታወሳል፡፡ ይህ አፈጻጸም በቀጣይ ዓመታት እያደገ ይሄዳል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ውጤቱ ግን ከዕቅድ ብቻ ሳይሆን ከቀደሙት ዓመታትም አፈጻጸም ጭምር ያነሰ ሆኗል።

በተለይ ቡና በ2014 የሒሳብ ዓመት ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ መሆኑ ይታወሳል ይህንን ገቢ ማስቀጠል ሳይችል ቀርቶ በ2015 የበጀት ዓመት ዓመታዊ የቡና ወጭ ንግድ ገቢው 1.3 ቢሊዮን ዶላር ሊሆን መቻሉ አይዘነጋም፡፡ ዘንድሮም በአሥር ወሮች ያገኘው ገቢ አንድ ቢሊዮን ዶላር በመሆኑ በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ሊገኝ የሚችለው ገቢ ቢኖርም ይህ ገቢ ከቀደሙት ዓመታት ብልጫ ይኖረዋል ተብሎ ስለማይታሰብ የ2016 የአገሪቱ አጠቃላይ የወጭ ንግድ ገቢ ከቀዳሚው ዓመትም ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ፡፡

በበጀት ዓመቱ የወጭ ንግድ በታሰበው ልክ ሊሆን ያልቻለባቸው የተለያዩ ምክንያቶች እየተጠቀሱ ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ ማሻቀብ በዋናነት እየተጠቀሰ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ሌላ ከቡና የወጭ ንግድ ግብይት ጋር በተያያዘ የተተገበሩ አዳዲስ አሠራሮች እንደ ምክንያት ሲጠቀሱ እየተሰማ ነው፡፡ 

ከቡና የተገኘው ገቢ ዝቅተኛ ቢሆንም ከኢትዮጵያ የሚላከው የቡና መጠን ግን እያደገ መሆኑን አኃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያመለክተውም፣ በ2016 በጀት ዓመት በአሥር ወር አንድ ቢሊዮን ዶላር የተገኘው 209 ሺሕ ቶን ቡና በመላክ ሲሆን፣ ይህ የቡና መጠን በ2015 በጀት ዓመት አሥር ከተላከው ጋር ሲነፃፀር በ29 ሺሕ ቶን ብልጫ ያለው ነው፡፡ 

ባለሥልጣኑ በ2014 በጀት ዓመት በታሪክ ከፍተኛ የተባለውን የ1.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከቡና ያገኘው 290 ሺሕ ቶን ቡና ልኮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በ2015 በጀት ዓመትም 1.3 ቢሊዮን ዶላር የተገኘው 240 ሺሕ ቶን ቡና ተልኮ የነበረ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ 248 ሺሕ ቶን ተልኮ 907 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች