Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሰጡ ድጋፎችንና መሥፈርቶችን ያካተተ አዲስ መመሪያ ወጣ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ወስጥ ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የቦታና የብድር አቅርቦት ጨምሮ ሌሎች ልዩ ልዩ ድጋፎችን የሚያቀርብበት አዲስ መመሪያ በማውጣት ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑን አስታወቀ።

‹‹የአምራች ኢንዱስትሪዎች ልማት የአገልግሎትና ድጋፍ ማዕቀፍ›› በሚል ርዕስ የወጣው አዲስ መመሪያ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከዚህ በኋላ ተፈጻሚ ሊያደርጋቸውና ሊደረግላቸው የሚገቡ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ መመርያው ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሰጡት የመሥሪያ ቦታዎች በምን አግባብና ምዘና እንደሚሰጡም የሚያመላክት ነው፡፡ ቦታ ተጠቃሚ አምራች ኢንዱስትሪዎች ልየታና ምልመላ በማድረግ የሚተገበር ሲሆን፣ የተጠቃሚዎች ልየታና ምልመላን በተመለከተም ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል።

በማኅበር ተደራጅተው በተለያዩ የምርት ዘርፎች ለሚሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሊሰጥ የታቀደውን ድጋፍ በስፋት የሚዘረዝረው ይህ መመሪያ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የድጋፍ ማዕቀፎችን በመቅረፅና ተግባራዊ በማድረግ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለከተማዋ ብሎም ለአጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከትን ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የተቀፀረ ነው ተብሏል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የዕድገት ደረጃና ፍላጎት መሠረት ያደረገ ድጋፍ በመስጠት፣ ጥራትና ምርታማነታቸውን በማሻሻል ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ ለማድረግ በማስፈለጉ፣ በሚደረግላቸው ድጋፍና በሚያከናውኑት የምርታማነት ዕድገት መሠረት የላቀ የዕድገት ደረጃ ሽግግር እንዲያደርጉ ለማስቻል ይህ መመሪያ ስለመውጣቱም ይጠቅሳል፡፡ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የዕድገት ደረጃ አወሳሰንና ሽግግር ሒደት ላይ እንዲሁም በድጋፍ ማዕቀፍ አተገባበር ሒደት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ለመፍታት ታሳቢ አድርጎ መመሪያው መውጣቱን በጉዳይ ላይ የተሰጠው ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ 

በዚህ መሠረት አምራች ኢንዱስትሪው በመመሪያ ላይ በተቀመጡት መሥፈርቶች መሠረት የተለያዩ ድጋፎችን ማግኘት የሚችሉበትን አሠራር በመከተል አገልግሎት የሚደረግለት ይሆናል፡፡ ድጋፉ በአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስተባባሪነት የሚሰጥ ሲሆን ከብድር ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኙ የሚያስችሉ አንቀፆችም በመመሪያው ተካተዋል።

በዚህም መሠረት ቢሮው ወይም ጽሕፈት ቤቱ የካፒታል ዕቃና ሊዝ ፋይናንስ ወይም የብድር ፍላጎት ያላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች የካፒታል ዕቃ ወይም ሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ወይም አበዳሪ ተቋማት ባዘጋጁት ወይም በሚያዘጋጁት መመሪያ ወይም አሠራር መሠረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያመቻችላቸው ይሆናል፡፡ 

የካፒታል ዕቃ ወይም የሊዝ ፋይናንስ ብድር ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችም በቢሮው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አስተባባሪነት ከፋሲሊቴሽንና ካይዘን ዘርፍ ጋር በመሆን የፍላጎት ጥያቄውን በጥናትና መረጃ አስደግፎ ለቢሮ ስትራቴጂክ ካውንስል አቅርቦ በማፀደቅ ከካፒታል ዕቃ ወይም ከሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋም ብድሩ እንዲለቀቅላቸው የሚያደርግ መሆኑን መመሪያው ያመለክታል፡፡ በተያያዥነትም ይህ የብድር አገልግሎት በከተማው አስተዳደር የተደራጁ ወይም በግላቸው አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የካፒታል ዕቃ ወይም የሊዝ ፋይናንስ ድጋፍ ጥያቄ በማናቸውም ጊዜ ከካፒታል ዕቃ ወይም የሊዝ ፋይናንስ አበዳሪ ተቋማት ጥያቄያቸውን በቀጥታ በማቅረብ ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው መመሪያ እንዲህ ያለውን አሠራር በግልጽ ያላስቀመጠና አሻሚ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

የካፒታል ዕቃ ወይም የሊዝ ፋይናንስ ብድር የሚጠይቁ አምራች ኢንዱስትሪዎች ድጋፉን ለማግኘት ማሟላት የሚገቧቸው መሥፈርቶችንም መመርያው አካቷል፡፡ በመሥፈርትነት ከተጠቀሱት መካከልም የማኑፋክሪንግ አምራች ኢንዱስትሪ መሆን፣ የሚሠራበት የመሥሪያ ቦታ ያለው፣ የዕድገት ደረጃቸው አነስተኛና ከዚያ በላይ የሆነ፣ የፈጠረው የሥራ ዕድል፣ ተኪ ምርት ወይም ኤክስፖርት ላይ የተሰማራ መሆን፣ የተሻለ የማምረት አቅምና ምጣኔ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት፣ የዘመኑን የገቢ ግብር ግዴታ መወጣት የሚሉት ይገኙበታል።

ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች የብድር ድጋፍ እንዲያገኙ ከማመቻቸት ባሻገር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው እንደሚደረግም መመሪያው ያመለክታል። በዚህም መሠረት  በአካባቢ፣ በክልልና በውጭ አገር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የሚደረግ መሆኑን ለዚህም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ እንዲሁም በግል ተቋማት የሚገኙ የገበያ መረጃዎችን በማሰባሰብና አጋርነትን በመፍጠር ለአምራች ኢንዱትሪዎቹ የገበያ ትስስር እንደሚመቻችላቸው መመሪያው ይጠቅሳል፡፡ 

በአገርና ከአገር ውጭ የገበያ መዳረሻዎችን በጥናት በመለየት አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስተሳሰር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረግ ስለመሆኑም መመሪያው ይጠቁማል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግዥ መመሪያ መሠረት ለምአራች ኢንዱስትሪዎች ወይም ኢንተርፕራይዞች በተሰጣቸው ወይም በሚሰጣቸው ልዩ አስተያየት የገበያ ትስስር ተፈጻሚ እንዲሆንላቸው ጭምር የሚገለጸው ይህ መመሪያ አምራች ኢንዱስትሪዎች በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁና እንዲሸጡ ድጋፍ እንደሚደረግም ይገልጻል፡፡ 

አምራች ኢንዱስትሪዎች የራሳቸውን የንግድ ስምና መለያ እንዲኖራቸው በማድረግ ተወዳዳሪነታቸው ጭምር እንደሚደግፍ የሚጠቅሰው ይህ መመሪያ ከመንግሥት  ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው ቢሮው የሚሠራ መሆኑን በዚህ መመሪያ ላይ ጠቅሷል፡፡ 

የገበያ ዕድሉን የሚፈጥረው ተቋም በሚያወጣው መሥፈርት መሠረት ምልመላ ከተናወነ በኋላም ከመንግሥት ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው እንደሚደረግ መመሪያው ይገልጻል። መመሪያው እንደተገለጸው ለአንድ አምራች ኢንዱስትሪ ከአንድ ጊዜ በላይ ትስስር ሊፈጠር የሚችለው በተመሳሳይ ዘርፍ ውስጥ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከሌሉና በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሠረት በድጋሚ ተራው ሲደርሰው ብቻ ይሆናል። 

የገበያ ትስስር የሚፈርጠላቸው አምራቾች የሚፈጠርላቸው የገበያ ትስስር የዕድገት ደረጃን መሠረት ያደረገ እንደሚሆን፣ በዚህም መሠረት ለአነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ600,001 እስከ 10,000,00 የገበያ ትስስር የሚፈጠርላቸው መሆኑን ያመለክታል።

ለመካከለኛ አምራች ኢንዱትሪዎች ደግሞ ከ10,000,001 እስከ 90,000,000 የገበያ ትስስር የሚፈጠርላቸው ሲሆን፣ ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ90,000,001 በላይ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የሚደረግላቸው ስለመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የተመለከተው ይኸው አዲስ መመሪያ ያመለክታል፡፡ 

ይህ የገበያ ትስስር በተለያዩ የግብይት ሥልቶች የገበያ ትስስሩ የሚፈጠር መሆኑነም በማመልከት ሥልቶች ያላቸውን በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ከነዚህም መካከል በንዑስ ተቋራጭነት የግብይት ሥልት አምራች ኢንዱስትሪዎች ሥራውን ከወሰደው አካል ጋር ውል በመግባት የገበያ ትስስር መፍጠር አንዱ ሲሆን፣ ሌላው በአውት ሶርሲንግ የግብይት ሥልት በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት አውትሶርስ ሊደረጉ የሚገባቸውን ሥራዎች በጥናት በመለየት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ማድረግ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ሌሎች ሥልቶችም መመሪያው አካቷል፡፡ 

መመሪያው የገበያ ትስስር  የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎችም ያካተተ ነው፡፡ የገበያ ትስስሩ የሚቋረጥባቸው ምክንያቶች ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ የተሰጠውን ሥራ በገባው ውል መሠረት መፈጸም ሳይችል ሲቀር፣ የተጭበረበረ መረጃ አቅርቦ ሲገኝ፣ በዕድገት ደረጃው የተቀመጠለትን የገበያ ትስስር ጣሪያ ሲያልፍ፣ ሕጋዊ ሰውነት በሕግ አግባብ ሲታገድና ሲፈርስ፣ የዕድገት ደረጃ ሽግግር ሰርትፊኬት ያላገኘ ወይም ያላሳደሰ ከሆነ፣ ሌሎች አሳማኝና አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ነው ይላል፡፡ 

መመሪያው እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ላይ እንዲሳተፉ ዕገዛ የሚያደርግ ሲሆን፣ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ በኤግዚቢሽኖች ላይ ሲሳተፉ ክልከላ የሚደረግባቸውን ጉዳዮችም የያዘ ነው፡፡ በኤግዚቢሽንና ባዛር ወቅት የሚደረግ ክልከላ የሚደረግባቸው ናቸው ብሎ በመመሪያው የሰፈሩት የውጭ አገር ምርቶችን ይዞ መገኘት፣ አምራች ኢንዱትሪው ከራሱ ምርት ውጭ ይዞ ከገቡ ወይም ከተገኙ፣ የኤግዚቢሽንና ባዛር ቦታ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለሦስተኛ ወገን ካስተላለፉና የመሳሰሉት ተደንግገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ሳይፈቀድለት ተሳታፊ ሆኖ ከተገኘ፣ ያልተፈቀደና የተከለከለ ምርት ይዞ መገኘትም ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ  ኤግዚቢሽንና ባዛር ክልከላን በሚተላለፍ ላይ የሚወሰድ ዕርምጃዎችንም መመሪያው አካቷል፡፡ 

ይህ መመሪያ አምራች ኢንዱስትሪዎች በዘርፉ ማኅበራት ደረጃ እንዲደራጁ የሚያስገድድም ነው፡፡ ይህንኑ የተመለከተው አንቀጽ የዘርፍ ማኅበራት አደረጃጀት ‹‹አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደ ሥራ ባህሪያቸውና እንደተሰማሩበት ዘርፍ ወይም ንዑስ ዘርፍ መብቶቻቸውንና ጥቅሞቸውን ለማስጠበቅ በማኅበር ይደራጃሉ፤›› ይላል፡፡  አደረጃጀቱም በክፍለ ከተማና በከተማ ደረጃ ይሆናል፡፡ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት ሲመረጥ ከአምራች ኢንዱትሪ ዘርፍ ሆኖ ንዑስ ዘርፉን መሠረት በማድረግ አባላት መመረጥ እንዳለበት እንዲሁም በክፍለ ከተማ ደረጃ የዘርፍ ማኅበራት በጋራ በመሆን በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት የክፍለ ከተማ የዘርፍ ማኅበራት እንዲመሠርቱ የሚደረግ እንደሚሆንም ይደነግጋል፡፡ በየደረጃው የሚደራጁ የዘርፍ ማኅበራት በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ግዴታቸውን በመወጣት ጥቅሞቻቸውን በማስጠበቅና የሚገጥማቸውን ችግሮች በጋራ እንዲፈቱ የሚደረግ መሆኑን በመጠቆምም በመሥፈርቱ መሠረት ተመዝነው በደረሱበት የዕድገት ደረጃ ሰርተፊኬት የሚሰጥ ይደረጋል፡፡  ማንኛውም አምራች ኢንዱስትሪ በዕድገት ደረጃ መሥፈርት ተመዝኖ ከመቶ ያገኘው ውጤት ወደ ሌላ የዕድገት ደረጃ ሊያሸጋግረው የሚችል ቢሆንም በዚህ መመሪያው ላይ የተቀመጠውን ዕድገት ደረጃ ሽግግር የሀብት መጠን ያላሟል መሸጋገር እንደማይኖርበት ጠቅሷል፡፡ አንድ አምራች ኢንዱስትሪ በሦስት ዓመት ውስጥ ከነበረበት የዕድገት ደረጃ ከፍ ወዳለ ደረጃ ወይም ወደ ቀጣይ የዕድገት ደረጃ መሸጋገር የሚኖርበት ሲሆን፣ የዕድገት ደረጃ የሚሰጣቸው አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ያወጡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይሆናል፡፡ በዚህ ዘርፍ ብዙ ጊዜ አጨቃጫቂ ሆኖ የቀየውን የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት ደረጃዎች በተመለከተ በዚህ መመሪያ ግልጽ የሆነ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ 

በዚህም መሠረት የአምራች ኢዱስትሪዎች የያዙትን የሰው ኃይልና የሀብት መጠን መሠረት በማድረግ በሦስት ደረጃዎች በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ እንዲያልፉ የሚደረግ ሲሆን የሚሰጣቸው የድጋፍ ዓይነትም ያላቸውን የዕድገት ደረጃ ያገናዘበ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡ 

ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለማደግ መሟላት የሚገባቸው መሥፈርቶችንም በተመለከተ በሥራ ዕድል ፈጠራ በሀብት፣ በገበያ፣ በትርፋማነትና በምርታማነት መጠን እንደ ዋና መሥፈርት አስቀምጧል፡፡  ከዚህም ሌላ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሚደረግ የአምራች ኢንዱስትሪው ባለቤትን፣ የቤተሰብ አባላትና ተቆጣጣሪ ሠራተኞችን ጨምሮ ከ51 እስከ 100 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረና የሚያንቀሳቅሰው የሀብት መጠን ከአሥር ሚሊዮን ብር እስከ 90 ሚሊዮን ብር መሆን እንደሚኖርበት ያመለክታል፡፡ ከጠቅላላ ሀብቱ ውስጥ 40 በመቶና በላይ ለቋሚ ንብረት ያዋለው መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አምራች ኢንዱስትሪው ከሚጠቀማቸው የጥሬ ዕቃ መካከል በአገር ውስጥ የሚመረት ከሆነ ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ከአገር ውስጥ መጠቀም የሚኖርበት መሆኑን በመመሪያው ተመልክቷል፡፡ 

ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚሸጋገሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ መሥፈርቶች ምን በተመለከተ መመሪያው እንደሚሠሩበት ከተቀመጡት ውስጥ  የአምራች ኢንዱትሪው ባለቤትነትን፣ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሠራተኞችን ጨምሮ ከ101 ሰዎች በላይ ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆን አለበት ይላል፡፡ ጠቅላላ የሀብት መጠኑ ከ90 ሚሊዮን ብር መሆን ያለበት ሲሆን፣ ከጠቅላላ ሀብቱ ውስጥ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ለቋሚ ንብረት የሚያውል፣ ዓመታዊ የግብይት ሽያጭ መጠኑም ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ መሆን እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለሚሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎች ሌሎች መሥፈርቶች የተቀመጡላቸው ሲሆን፣ ምርትና አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ ቢያንስ አምስት (ኢ ኮሜርስ በብሮድካስቲንግ ሚዲያ፣ በምርት ሌቭሊንግ፣ በኅትመት ሚዲያ) ዓይነት የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል የሚለው ተካቷል፡፡ በየደረጃው በተዘጋጀ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የተሳተፉ መሆን የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ለገቢ ወይም ለወጪ ምርቶች የሚውሉ ግብዓቶችን ወይም ገቢ ምርቶችን የሚተካ ምርት ማምረት አለበት፡፡ ከአምራች ኢንዱስትሪው አባላት ወይም ቋሚ ሠራተኞች መካከል ቢያንስ 25 በመቶ የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያገኙ መሆን እንዳለባቸውም ያመለክታል፡፡ ይህ መመሪያ ከዚህ ቀደም ሥራ ላይ የነበረውን መመሪያ ተክቶ የሚሠራበት ሲሆን፣ በቀደመው መመሪያ ነበሩ የተባሉ ክፍተቶችን የደፈነ ስለመሆኑ የሚገልጹ አሉ፡፡

መመሪያው ለአምራች ኢንደስትሪዎች የሚሰጠውን የደረጃ ምደባም ግልጽ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ግን በከተማ ውስጥ በአንዳንዱ ክፍለ ከተሞች ለአምራች ተብለው የተሰጡ ቦታዎች መፍረስና አንዳንድ ተደራጅተው ሲሠሩ የነበሩ ወጣቶች ያለአግባብ ተፈናቅለዋል የሚል ትችት እየቀረበ መሆኑን በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች