Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርሙስና እያስፋፋው ያለው የጥገኝነት መንፈስ

ሙስና እያስፋፋው ያለው የጥገኝነት መንፈስ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ሰሞኑን ዓለም አቀፍም ሆነ አገራዊ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ቀን በተለያዩ ዓውደ ጥናቶችና በተለመዱ ስብሰባዎች ሲከበር፣ በቴሌቪዥን መስኮት የተመለከትኩ መሰለኝ፡፡ አስገራሚው ነገር ሙስናና ብልሹ አሠራር በከፍተኛ ደረጃ አገራዊ ፈተና እየሆነ፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚውን በማናጋት ወደ እርስ በርስ ሽኩቻ የገባ አገራዊ ፖለቲካ አንዲንሰራፋ እያበረታታ፣ አሁንም የሕዝብ ምሬታና ቅሬታ እንዲባባስ አስተወጽኦ እያደረገ ሙስና እንደ የሴቶች ቀን፣ የሕፃናት ቀን፣ የአባቶች ቀንና የፍቅረኞች ቀን በዓመት አንድ ጊዘ እየተወሳ መቀጠሉ ነው፡፡ በስሙ የተሰየሙት ማታገያ መሥሪያ ቤቶችስ ምን እየሠሩ ይሆን የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

በመሠረቱ የብልፅግና መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ እንደ አገር እያስቸገረ ያለውን ሙስናና የአቋራጭ ብልፅግና መንገድ ለመግታትና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለመዘርጋት ያለመው በቀዳሚነት ነበር፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ረገድ ይታዩ የነበሩ ሳንካዎችን ለማስተካከልም ቢሆን ቅድሚያ መልካም አስተዳደርና ግልጽነት የተላበሰ ሥርዓት መዳበር አለበት፡፡ ይሁንና ባለፉት ስድስት ዓመታት ትልሙ በታሰበው ልክ ስለመከናወኑ መረጃ መጥቀስ አይቻልም፡፡

- Advertisement -

እንዲያውም በአገር ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች በሚቀሰቀስ ግጭትና አለመግባባት አጀንዳው በቂ ትኩረት ሳያገኝ፣ አጋጣሚውን ለግል ጥቅም ማጋበሻነት ማዋል ለሚፈልጉ አካላትም ተስማሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አደጋው ቀስ በቀስ ከብሔር፣ ከፖለቲካና የእምነት ሽኩቻ በመውጣት  ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ለዚህም ነው ‹‹ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬት ሬቲንግና ዴሞክራሲ ኢንዴክስ›› የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ የሙስናና የዴሞክራሲ ደረጃ አውጭ ድርጅቶች፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ዘገባ ይፋ ሲያደርጉ የተባባሰ እንጂ የተሻሻለ ደረጃ ሊሰጡን ያልቻሉት፡፡ በእነዚህ አካላት ዕይታ ከሰባት ዓመታት በፊት የወጣ አንድ መረጃም አለ፡፡  የ150 አገሮች ጥናትን መሠረት አድርጎ በቀረበው መረጃ በሙሰኝነት ለአፍሪካ አገሮች ከተሰጣቸው ደረጃ ናሚቢያና ሩዋንዳ 41ኛ እና 40ኛ ደረጃ ሲያገኙ፣ ደቡብ አፍሪካ 52ኛ ሴኔጋል 54ኛ አግኝተዋል፡፡

በዚህ ጥናት መሠረት ከ150 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ 86ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል (ምናልባት ይህ ደረጃ ኢሕአዴግ በተሃድሶ መድረኩ የደረሰበትንም ሆነ፣ ሕዝቡ ክፉኛ እያዘነበት የነበረውንና በኋላም መንግሥት ጉሮሮውን የተያዘበትን የለውጥ ፍላጎትና ተያያዡን መረጃ እንዳላካተተ ግልጽ ነው)፡፡ በወቅቱ በከፍተኛ ሙስናና በሥርዓታዊ ዘረፋ የሚታሙት የአፍሪካ አገሮች የቅርቦቹ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ነበሩ፡፡ አሁን መረጃው (እ.ኤ.አ. 2023) ሲወጣ አገራችንን በግጭትና በፀረ ዴሞክራሲያዊ ዕሳቤ ወደኋላ የተመለሰች ሲላት፣ በሙስናና በብልሹ አሠራርም ከእነ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳና ቦትስዋና ይቅርና ከእነ አንጎላ፣ ናይጄሪያና ናሚቢያ በታች አስቀምጧታል፡፡ ይህም እንደ አገር የሚጠብቀንን ከፍተኛ ሥራና ትኩረት አመላካች ነው፡፡

እንዲያውም አደጋው አስከፊ እየሆነ ያለው በማንነት ተኮሩ ፌዴራሊዝም አንዱ ሌላውን የመቆጣጠርና የመጠያየቅ ሥሪቱ እየላላ፣ ሰዎች ከብቃትና ከተወዳዳሪነት ይልቅ በማንነትና ቤተሰብነት በመሰባሰብ እየተፈጸመ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ሙስናው  በመድበስበስና በመተሻሸት ከግለሰቦች አልፎ ወደ ቡድንና ኔትወርክ ብሎም ወደ ሥርዓት አድጎ፣ ‹‹ሙስናን የምትዋጋ ከሆንክ ሙስናው ራሱ ባለ በሌለ ኃይሉ መልሶ ይወጋሃል›› (IF you fight corruption, corruption will fight you back with everything it has got!›› ወደ ማለት አስፈሪ ሁኔታ አገር እንዳትገባ ያሠጋል፡፡ ምልክቱ ከወዲሁ በእንጭጩ መቀጨት ይኖርበታል መባሉም ለዚህ ነው፡፡

እንደ ብዙዎች ችግሮች እየገጠመን ካለው አገራዊ የሙስናና ብልሹ አሠራር ለመላቀቅ፣ ብሎም አገራችን የልማትና የብልፅግና ብቻ ሳይሆን የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍልና ተመጣጣኝ የኑሮ ገጽታ ተምሳሌት እንድትሆን ከምሁራን፣ ከሕዝቡና ከራሱ ከመንግሥት ምን ይጠበቃል በማለት የተወሰኑ የመዲናችን ነዋሪዎችን ለማናገር ሞክሬያለሁ፡፡

ቀዳሚው አስቻለው ታሪኩ (ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀይሯል) የተባሉ በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ ባለሙያነት የሚሠሩ የመዲናዋ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት፣ በከተማ ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል የመንግሥትን ቁርጠኝነት ያዝ ለቀቅ የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰው፣ አደጋው የተባባሰ ቸልታ እንዳይመጣና ሕዝቡም ተስፋ ቆርጦ መታገሉን በመተው ጥቅሙን አሳልፎ እንዳይሰጥ፣ አዲስና የተቀጣጠለ ትግል እስከ ታች ድረስ ማውረድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የፀረ ሙስና ትግል የአገርን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ከቀውስ ለማዳን ወሳኝ በመሆኑ ከላይ ጀምሮ በቁርጠኝነት መታገልና ለመርህ መቆምን ይፈልጋል ብለው ሙስና በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በጥቅም፣ በኔትወርክ ትስስርና በዝምድናም ስለሚፈጸም የፍትሕና የእኩልነት ፀረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከአስፈሪው ድባብ መውጣት አለባቸው በማለት ጭምር፡፡

እንደ አቶ አስቻለው ገለጻ ሙስና በዋናነት የሚፈጸመው በመንግሥት አካላት ነው፡፡ ስለሆነም ገዥው ፓርቲና መንግሥት በመጀመሪያ ራሳቸውን ማጥራት አለባቸው፡፡ በመቀጠል ዜጎችም በየፊናቸው እየታገሉ ሌቦችና ደፋር ቀማኞችን በማጋለጥና መንግሥትንም በመጎትጎት ትውልድ ሊታደጉ ይገባል ይላሉ፡፡

የሙስና ትግሉ በመንግሥት ጥረት ብቻ ሊቀረፍ ስለማይችልም ኅብረተሰቡ፣ ምሁራንና ፖለቲከኞችም ያላሰለሰ ጥረት መድረግ አለባቸው ብለው፣ በተለይ ምሁራን ኅብረተሰቡን በማስተማር የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራር እንዲዳብር በመርዳት፣ ብሎም የሕግ ተዓማኒነት እንዲጠነክር ማድረግ ይችላሉ ባይ ናቸው (እውነት ለመናገር የእኛ አገር ልሂቃን በፖለቲካ ዓላማ ልዩነት መፋተግ እንጂ፣ መሠረታዊ ችግሮቻችን እንዲቀረፉ ተባብሮ በመታገል አለመታወቃቸው ክፉኛ የሚያሳዝን ችግራችን ነው)፡፡

የሙስናን አፀያፊነትና ነውርነት ትውልዱ ግንዛቤ እየያዘ እንዲያድግ ተማሪዎች በመገናኛ ብዝኃን የሚተላለፉ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች እንዲከታተሉ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ እንደ እምነት ተቋማት፣ ማኅበራዊ ድርጅቶችና የኅብረተሰቡ ትስስር መገላጫዎችም ሙስናን የሚያወግዝ ተግባር እንዲያከናውኑ ማነሳሳት የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ እንደ ምርመራ ጋዜጠኝነት የመሳሰሉ የግልጽነትና የተጠያቂነት ምሰሶዎች ሊቆሙ የግድ ነው፡፡

መጋቢ አዲስ ቀሲስ መንበሩ ዮሐንስ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ ሙስና ጠፋ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ መሆኑንና ትርጓሜውም መጥፋት፣ ማጥፋት፣ ማባከን እንደሆነ ገልጸው ተግባሩም የአገርን ኢኮኖሚ መጉዳት፣ የደሃውን ማኅበረሰብ ሕይወት ማበላሸትና እጅግ አፀያፊ ወደ ሆነ ደረጃ መውረድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አሁን አሁን ከመንግሥታዊ አገልግሎት ባሻገር በእምነት ተቋማትና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ጭምር እየታየ መምጣቱ የአደጋውን መባባስ እንደሚያሳይ በመጠቆም፡፡

ይህ ክፉ አካሄድ ታሪክን፣ ባህልን፣ ሃይማኖትንና አገርን የሚያሳጣ ስለሆነ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በከፍተኛ ደረጃ መንቀሳቀስ አለበት ነው ያሉት፡፡ ሥራው ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ተግባር መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

እውነት ለመናገር የፀጥታና የደኅንነት ሥራው ያሳደረው ጫና ግምት ውስጥ እየገባ እንጂ፣ አገሪቱን በፍትሐዊነት እንዲያስተዳድር በምርጫ ካርድ ድምፅ የሰጠነው መንግሥት መልካም አስተዳደርን ከማስፈን በላይ ሥራ ሊኖረው ባልተገባ ነበር፡፡ እንደ አገር ሥር የሰደደና የከፋ የሙስና ችግር ሲፈጸም በአጭር አለመቅጨቱ ትክክል ነው ሊባልም አይችልም፡፡ ያውም ወጥ ባልሆነ የክልልና የፌዴራል የቁርጠኝነት አያያዝ ሰዎች በሚማረሩበት ሁኔታ፣ እንዲህ ያለ ዕዳ የሚሸከም የሕዝብ ጫንቃ ሊኖር አይችልም፡፡ እስካሁንም በመላ አገሪቱ ሥር የሰደደ ሙስናና ብልሹ አሠራር መኖሩ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ግፍ እንዲፈጸም አድርጓል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ እንደ አገር ከሥርዓት ለውጥና መንግሥት ከመቀያየር በላይ ወጥነት ያለው የመልካም አስተዳደር ሥሪትና ብልኃት እንዲኖር መሠራት አለበት ነው የሚሉት፡፡

ለአብነትም በአገራችን ዋናው ተዓማኒነት በፍርድ ቤትና በፍትሕ አካላት ላይ መሆን ሲገባው፣ ሙስና ግን በፍትሕና በፀጥታ ተቋማት ጎልቶ ይታያል ያሉት ቀሲስ፣ ፖሊስም ሆነ ሌሎች የፍትሕ አካላት ራሳቸውንና አሠራራቸውን  በማጥራት ቀስ በቀስ እየተንሰራፋ ያለውን ሙስና እንዲታገሉ ታሪክ አደራ ጥሎባቸዋል ብለዋል፡፡

ከ60 ዓመት በላይ በከተማዋ መኖራቸውንና ሦስት መንግሥታትን እንዳሳለፉ ያስታወሱት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጥበቡ ተኮላ በበኩላቸው፣ ኢኮኖሚው ያን ያህል ያደገ ባይሆንም በተለይ በደርግ ሥርዓት ሙስናና የኢኮኖሚ አሻጥር ክፉኛ እንደሚያስቀጣና ኅብረተሰቡም ሰጥለጥ ብሎ በላቡ ለመኖር ጥረት ያደርግ እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡

በሙስና ረገድ ኢሕአዴግም ሊታገል ቢሞክርም በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕልፈት በኋላ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የፓርቲ አባላት ሕዝብ ሲያስለቅሱ ኖረው፣ ፈራጅ የነበሩት ተፈርዶባቸው አይሆኑ ሆነው ሲወድቁ መመልከታችን አንድ ማስተማሪያ ትዕይንት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ አሁንም ድረስ አንዳንድ የሕዝብ አደራ የተሸከሙ ሰዎች ካለፈው ከመማር ይልቅ፣ ሕዝብን ማስለቀስና የአገር ሀብት መዝረፍ መደበኛ ሥራ ማድረጋቸው ለማንም እንደማይጠቅም ገልጸዋል፡፡

ይህን አገር የሚበላ ጥገኛ ኃይል በነቃ አስተሳሰብና ተግባር ለመታገል መንግሥት የጀመረው ንቅናቄ ተስፋ ሰጪና መበረታታት ያለበት ቢሆንም፣ ቅድሚያ ሰላምና ደኅንነት ብሎም የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥነ ምኅዳር መፈጠር አለበት የሚሉም አሉ፡፡ ያም ሆኖ የሰላም አለመረጋገጡን ማስቀጠል የሚፈልገው ራሱ ሙሰኛው እንዳይሆንም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በተለይ ምሁራንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትግሉ እንዳይቀዘቅዝ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡

በመንግሥት ተቋማት ያለው አብዛኛው አመራርና ባለሙያ የተማረ እንደመሆኑ ድርጊቱን መፀየፍ ያለበትም፣ ተገልጋይን ከመማረር በማውጣት ሊሆን ይገባል፡፡ በውስጥ  የሚደረገው ትግል እንዳለ ሆኖ ኅብረተሰቡ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም ወሳኝ ድርሻ እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት፡፡

ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለማዳከም በተለይ በኅብረተሰቡ የሚደረገው ትግል እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በአካባቢው የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራትና ሙስናን እግር በእግር በመከታተል ማጋለጥ ይኖርበታል፣ ይችላልም፡፡ ቅሬታ ተቀባይና ለማረም የተሰናዳ ፀረ ሙስና ተቋምና መንግሥት ግን ሊኖር የግድ ነው፡፡

ሙስና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በኢኮኖሚው ላይም ከፍተኛ ጫና ከመፍጠሩም ሌላ፣ በአገሪቱ ሞራል የሌለውና በሕግ የማይመራ ትውልድ እንዲስፋፋ ያደርጋል የሚሉ የባለሙያ ምክሮች መደመጥ አለባቸው፡፡ በተለይ እኛን ጨምሮ ከቀውስ ለመውጣት እየተቸገሩ ባሉ አገሮች ሥልጣንን ለግልና ለቡድን መጠቀሚያ የማድረግ አካሄድ ካልታረመ መገዳደልና መጠፋፋት ሊወገድ አይችልም፡፡

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሱራፌል ጌታቸው የተባሉ አስተያየት ሰጪ ለመገናኛ ብዝኃን እንደተናገሩት፣ እንደ አገር የተንሰራፋውን ሙስናና ሌብነት ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች ቢኖሩም በፍጥነትና በጥራት ዳብረው፣ በመረጃና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተሻሽለው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ መንግሥትም ተግባሩን የህልውና ትግል አድርጎ መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡

እንደ አገር የጎላ ብልሹ አሠራር ከሚታይባቸው የመንግሥት ተቋማት መሬትና የመሬት ነክ ጉዳዮች የሚመለከቱ ሥራዎችን የሚሠሩ ተጠቃሽ መሆናቸውን አስታውሰው በተለይ በአዲስ አበባ መሬት፣ ገቢ፣ ብቃት ምዘናና ትልልቅ አገልግሎቶች ላይ ሰፊ የሆነ ሙስናና የሌብነት ተግባር እንደሚፈጸም በተለያዩ ወቅቶች የወጡ መረጃዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሳቸው መዋቅሩ ውስጥ የቆዩ ሰዎች ኑሮ አመላካች እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በማንነትና በቡድን እየተሰባሰቡ ሕገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ፣ የመሬት ይዞታ ካርታ በሕገወጥ መንገድ መስጠትን ጨምሮ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት እንደሚፈጸሙ ጠቁመው፣ በሌሎች ተቋማትም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ነው ያመለከቱት፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ግለሰቦች ሀብት የሚያካብቱበት ሳይሆን ማኅበረሰቡን በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል፣ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙ መሆን አለባቸው ብለው በአመራር ደረጃ የሚቀመጡ ሰዎችም የተሻለ ሰብዕና የተላበሱ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም በከተማው ችግሩ ትግል እየተደረገበት ቢሆንም፣ አሁንም ሥጋት መሆኑን በቅርቡ በችግር ላይ በተከፈተ መድረክ አውስተው፣ ሙስና አገርና ትውልድ የሚገድል ነቀርሳ መሆኑን ተገንዝቦ የጋራ ርብርብ ከማድረግ መናጠብ እንደማይገባ ነበር የጠቆሙት፡፡

ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሙስናን ለመከላከል ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋማቸው የተጀመረውን ጥረት የሚያጠናክር እንደሆነም ገልጸው፣ ትግሉን ማቀጣጠል ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋምን አስመልክተው የተናገሩት ንግግር ይህንኑ የሚያጠናክር ነበር፡፡  ‹‹ሙስና አገርን የሚበላ ነቀዝ ነው፡፡ የአገርን አንጡራ ሀብት እየቦረቦረ ጥሪቷን ባዶ ለማስቀረት ሌት ተቀን የሚማስን ተባይ ነው። ዋልጌ ባለሥልጣናት፣ በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎችና ባለሀብቶች አንድ ላይ ሲገጥሙ፣ ከእነዚህ የሌብነት ፊታውራሪዎች ጀርባ ብዛት ያላቸው ዜጎች መሠለፍ ሲጀምሩ ሙስና የተባለው ነቀዝ አገርን እንደ ወረርሽኝ ያጠቃታል፤›› ነበር ያሉት፡፡

ሙስና በየትኛውም ቦታና በየትኛውም ዘመን ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን የአገርን ልማት አጥንቱ ድረስ እስከመጋጥ ከደረሰ ሙስና አደገኛ ወረርሽኝ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ሙስና አገርን ሊያፈርስ የሚችል የደኅንነት ሥጋት መሆኑን ያስመሰከሩ አገሮችን በዘመናችን አይተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአደንዛዥ ዕፅ፣ የኮንትሮባንድ፣ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የሕገወጥ የጦር መሣሪያ ንግድና የንግድ ማጭበርበር ሙስናን ለዓላማቸው ማስፈጸሚያነት እንደሚፈልጉትም ነበር ያስረዱት፡፡

በዓለማችን የተጀመሩ ጦርነቶች እንዳይጠናቀቁ፣ ግጭቶች እንዳይበርዱ፣ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲጋጩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ ሙሰኞች ከዚህ ዓይነት ቀውሶች ስለሚያተርፉ መሆኑንም አስታውሰው፣ ሙስና ዛሬ የአገራችን የደኅንነት ሥጋት ሆኗል፣ ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ጉዞ እጅ ተወርች አስሮ ለመያዝ ከጠላቶቻችን እኩል ሙሰኛው እየታገለን ነው፣ የተስተካከለ ቢሮክራሲ፣ የተቀናጀ መዋቅርና ዘመናዊ አሠራር ለሙስና ተጋላጭነትን ስለሚቀንሱ፣ እነዚህን ለማጥፋት ወይም ለማሰናከል ሙሰኛው ቀን ከሌት እየሠራ ስለሆነ ይህንኑ የሚመጥን ብርቱ ትግል ይጠብቀናል በማለት ነበር ያስረዱት፡፡

መንግሥት በየደረጃው የሚገኘውን መዋቅር በመፈተሽ፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን እያሳለጠ ሥራዎችን ከእጅ ንክኪ ነፃ በማድረግ፣ በሙስና ወንጀል የሚሳተፉ አመራሮችንና ሌሎች ተዋንያንን ለሕግ በማቅረብ፣ ሙስና ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠርለት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን አገራችን ያጋጠማትን ጦርነትና ኮሮናን የመሳሰሉ ወረርሽኞች የመንግሥትን ትኩረት ወስደዋል ብለው ያሰቡ ሙሰኞች፣ በየቦታው ተሰግስገውና ኔትወርክ ዘርግተው ኢትዮጵያን ለማዳከም መንቀሳቀሳቸው አይካድም ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴና በየደረጃው የሚገኙ የፀረ መስና አተገባበር ሥልቶችና አመራሮች ድርሻ ከፍ ባለ ደረጃ ውጤት የሚጠበቅበትም ከአደጋው መክፋት አንፃር ነው፡፡

በአጠቃላይ እንኳንስ በበርካታ ፈተናዎች በታጠረው የአገራችን ሁኔታ ውስጥ ይቅርና ለማንኛውም አገር ቢሆን ሙስና አደገኛ የዕድገት እንቅፋት ነው፡፡ የፀረ ሙስና ሥራ ማለትም ከአደገኛ የባህር አውሬዎች (ሻርኮች) ጋር በቁምህ ሳይበሉህ አብረህ የመዋኘት ትግል እንደ ማለት ነው የሚሉ በርካታ ናቸው (Swim with the sharks without being eaten alive.) መፍትሔው ግን ጥቂቶች ራሳችንንም አገራችንንም በልተው ሜዳ ላይ ሳይጥሉን በርትቶ መተናነቅ ብቻ ነው፡፡ ይህም መሪዎች በግላቸው ከ“ሌብነት ነፃ ነን” ብለው ከመታበይ ወጥተው በአጠቃላይ ሥርዓቱን ነፃ ስለማውጣትና ሕዝቡንም ስለማታገል እንዲያስቡ ከማድረግ መጀመር አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...